Saturday, April 27, 2013

ሆሣዕና


የዓብይ ጾም  ስምንተኛ ሳምንት ሆሣዕና
በዚህ ዕለት አይሁድ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ በሰሙ ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጥተዋል፡፡ /ዮሐ.12÷12/ ዘንባባ የድል ማብሠሪያ ምልክት ነው፡፡ ጌታ የጨለማውን ኃይል በሞቱ ድል የሚነሣ ነው፡፡ የድል አድራጊነት ዘንባባ የተገባው ለዚህ ነው፡፡ የደስታችን ምንጩ ደስታን ለሚሰጥ ለእርሱ የደስታ መግለጫ ዘንባባ ቀረበለት፡፡ ሰላምን ደስታን ለዓለም ሁሉ የሚያድል ሰማያዊ ንጉሥ ክርስቶስ ነው፡፡ ከሞትና ከመበስበስ ጠብቆ ዘለዓለማዊውን ደስታ ያደለ ክርስቶስ፡፡

በዚህ የነበሩትም /መዝ.117÷25/ ያለውን የትንቢት ቃል እየዘመሩ ጮሁ፡፡ ይህም ይመጣል የተባለውን መሲህ እንዴት በጉጉት እየጠበቁት እንደነበር የሚያስረግጥ ነው፡፡ ክብር እንደሚሻ ደሀ ና የተዋረደ ሆኖ ቢመጣም እንደ ንጉሥ እና የእስራኤል አዳኝ ተቀበሉት፡፡ እንደ የጽድቅ ንጉሥ ተቀበሉት፡፡ ሆሣዕና አያሉም ጮኹ፡፡ ክርስቶስ መድኃኒት የሆነ ንጉሥ ነው፡፡ የጎሰቆለውን የሰውን ሰውነት የሚያድን የአርያም መድኃኒት፡፡ በዚህም በመዝሙራቸው ከዳዊት ጋር ተባበሩ፡፡ /መዝ.23÷7/

“በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” ጌታ ነውና በራሱ ስም መጣ፡፡ /ዮሐ.1÷1/ እስራኤል የንጉሣቸውን መምጣት በተንሸዋረረ መንገድ ይጠብቁት ስለነበር መምህራነ አይሁድ አልወደዱትም፡፡

ክርስቶስ የእስራኤል ንጉሥ መሆን ምን የሚረባው ሆኖ ነው? ክርስቶስ የእስራኤል ንጉሥ በመሆን ግብር የሚሰበስብ ወታደር በማደራጀት ጠላቶቹ ላይ ጦርነት የሚያውጅ አይደለም፡፡ ቢያምኑበት ቢታዘዙት የልቦናቸው ንጉሥ ሊሆን መጥቷል፡፡ እምነት ተስፋ ፍቅርን ገንዘብ ቢያደርጉ የሰማያዊ መንግሥቱ ዜጎች ሊያደርጋቸው የጽድቅ ንጉሥ ሆኖ መጣ፡፡ ሐሰትን በመናገር ሳይሆን ጽድቅን /እውነትን/ በመስበክ የነገሠ ንጉሥ ነው፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ዓለም በእርሱ ቃልነት የተፈጠረ የዓለም ሁሉ ንጉሥ በፈቃዱ የእስራኤል ንጉሥ ተባለ፡፡ በምድር የእስራአል ንጉሥ የተባለ ክርስቶስ በሰማያትም የመላአክት ንጉሥ ነው፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ÷ አትፍሪ፤ እነሆ÷ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል” /ዮሐ.12÷15/ ጌታ ብዙ ጊዜ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር የተጓዘው በእግሩ ነው፡፡ አሁን ግን አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ትሑት ንጉሥ ኢየሱሱ ክርስቶስ፡፡ ንጉሥ ተብሎ ወደሚከብርበት ቦታ ሲያመራ አምሮ÷ ተውቦ በአማረ ልብስ÷ በአማረ መጓጓዣ የማይሄድ ትሑት ንጉሥ ክርስቶስ በአህያ መቀመጡ ብቻ ሳይሆን አህያይቱ እንደ ሰሎሞን አህያ በተዋቡ ቁሳቁስ ያጌጠች አልነበረችም፡፡ /መኃ.መኃ.3÷9/ የክርስቶስ ክብር በቁሳዊ ነገር የሚገለጥ አይደለም፡፡ መንግሥቱ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አይደለምና በምድራዊያን ነገሥታት የንግሥና ወግ ልብስና ጌጥ አልመጣም፡፡ እጅግ ትሑት ንጉሥ አምላካችን ክርስቶስ ነው፡፡ ነቢዩ የጽዮን ልጅ እንድትነሣ ልቦናዋን በድል አድራጊነት ደስታ የሚሞላትን ንጉሥ እንድትቀበል ያዛታል ስለዚህ ፈፅማ እንድትደሰት ጠየቃት፡፡ ፍርሃቷንና ሀዘኗን የሚያጠፋ ንጉሥ መጥቷልና፡፡ የነቢዩ ዘካርያስ ትንቢት በዚህ ፍፃሜውን አገኘ፡፡ /ዘካ.9÷9/ ክርስቶስ ከሮማውያን ወይም አይሁዳውያን ጠላት የሆኑትን ሊበቀል የመጣ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ሰላምና ክብር ሊያጎናፅፋቸው እንጂ፡፡ ይህንን ቅዱስ ሉቃስ “በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር” በማለት የገለጠው ነው፡፡ /ሉቃ.19÷38/ ጠላቶቹን እስከ መስቀል ሞት የወደደ የፍቅር ንጉሥ በመግደል ሳይሆን በመሞት በልቦናችን የነገሠ የፍቅር ንጉሥ ክርስቶስ ነው፡፡ “አትፈሪ” የሚመጣው የሚያከብራት ነውና ፍርሃትን እንድታስወግድ ተበሰረች፡፡ እርሱ መከራዋን ለመቀበል ደሙን በማፍሰስ ኃጢአትን ሊደመስስ ሕይወትን ሊሰጣት መጥቷልና አትፍሪ ተባለች ቤተ አይሁድ፡፡ ውርንጫይቱ ቀድሞ ምንም ጭነት የማያውቃቸው ሕግን ያልተቀበሉ በሕግ ያልኖሩ አሕዛብ ምሳሌ፤ አህያይቱ ጭነት የለመደች ሕግና ሥርዓት ተሰርቶላቸው የነበሩ የእስራአል ምሳሌ ናቸው፡፡ /ቅዱስ አውግስጢኖስ/“ የጽዮን ልጅ ሆይ አትፍሪ” አለ፡፡ ቀድመው አይሁድ ላይ ነግሠው የነበሩ ጨካኞች እና ኢፍትሐዊያን ስለ ነበሩ፡፡ ለጠላቶቻቸው አሳልፈው የሰጧቸው ነገሥታት ስለነበሩ፡፡ ክርስቶስ ግን የፍትሕ እና የርሕራሔ ንጉሥ ሆኖ መጥቷል፡፡ /ቅድስ ዮሐንስ አፈወርቅ/ “ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህ ሁሉ ሲሆን አላስተዋሉም ነበር እስከ ጌታ ትንሣኤም በዚሁ ያለመረዳት ጉዞ ገፈተውበታል” /ዮሐ.12÷16/ ሐዋርያት በወቅቱ የተፈፀሙትን ተግባራት እውነተኛ ምሥጢራቸውን ለማስተዋል አለመብቃታቸውን ወንጌላዊ ነገረን፡፡ በወቅቱ ሐዋርያት በዙሪያቸው የሚፈጸሙ ተግባራት እውነተኛ ምንነታቸው እንደማይረዱ ሕፃናት ነበሩ፡፡ በኋላ በጌታ ስቅለት÷ ትንሣኤና እርገት በእውቀት እና በመንፈስ ቅዱስ በጎለመሱ ጊዜ በዕለተ ሆሣዕና የሆነውን ሁሉ ተረዱ፡፡ “ነገር ግን ጌታችን ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ሁሉ ስለ እርሱ እንደተፃፈ ይኸንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው” ዮሐ.12÷17/ የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለመረዳት ትንሣኤ ልቡና ያስፈልጋል፡፡ በዓለ ሆሣዕና ክርስቶስ የጽድቅ የትሕትና እና የድኅነት ንጉሥ እንደሆነ በአደባባይ የተገለጠበት ነው፡፡ ሕዝብና አሕዛብን አንድ ለማድረግ እንደመጣ በምሥጢር የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ ሐዋርያት በጌታ ትንሣኤና እርገት ምሥጢር እንደተረዱ የፍቅር የትሕትና እና ድኅነት የሆነ የክርስቶስን ነገር በትንሣኤ ልቡና ተረድተን የሰማያዊ መንግሥቱ ዜጎች ለመሆን ያብቃን አሜን!

Thursday, April 18, 2013

ስለ ጸሎት

                                                                                   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

“አንትሙሰ ሶበት ጸልዩ ስመ ዝበሉ፡፡” ማቴ.6፥
እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በላችሁ ጸልዩ “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን….
በዚህ የጸሎት ክፍል ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ81 መጻሕፍት የተገኙ አምስት ቁም ነገሮችን አስተምሯል፡፡
  1. ሃይማኖት
  2. ተስፋ
  3. ፍቅር
  4. ትሕትና
  5. ጸሎት
1.   ሃይማኖት፡- ሃይማኖት ማለት በዐይናችን ያላየነውን አምላክ አባታችን ሆይ ሲሉ መኖር ነው ቀደም ሲል የነበሩ አበው ነቢያት ሲጸልዩ እግዚእነ አምላክነ ንጉሥነ እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ ይህም ከግብርናተ ዲያብሎስ /ለዲያብሎስ ከመገዛት/ እንዳልዳኑ ለማጠየቅ ነው፡፡ እኛን ግን ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ አውጥቻችኋለሁ ሲል አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ አስተማረን፡፡ “ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ” /ገላ.4፥6፣ ሮሜ.8፥15/፡፡ አባትነቱንም በሁለት ነገር ከምድራዊ አባት ለይቶታል፡፡
በመውለድና በመግቦት ከምድራዊ አባት ይለያል፡፡ ምድራዊ አባት በዘር በሩካቤ ይወልዳል፡፡ በማር፣ በወተት፣ በፍትፍት ያሳድጋል፤ ኋላም በሞት ሲያልፍ የምታልፍ ርስትን ያወርሳል፡፡ እርሱ ግን ሲወልደን በርቀት ሲያሳድገንም በሥጋውና በደሙ ነው፡፡ “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው ዮሐ. 3፥6፡፡ ኋላም የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን “በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን” ኤፌ.1፥11፣ 1ኛጴጥ.3፥5፡፡ በአበው ነቢያት ሐዋርያትን፣ በሐዋርያትም እኛን አቅርቦ አባታችን ሆይ ብለን እንድናመሰግነው አዞናል፡፡
ምድራዊ አባት የሚመግበው እግዚአብሔር ስለሚሰጠው ለልጁ በመስጠት ተቀብሎ በማቀበል ነው፡፡ እርሱ ግን መመገብ የባሕርዩ ስለሆነ ከሌላው ነስቶ አይደለም፡፡ ምድራዊ አባት ሲያጣ አጣሁ ይላል እርሱ ግን አያጣም፡፡ ምድራዊ አባት ሰጥቶ ሲያልቅ አለቀ ይላል፡፡ የእርሱ ግን ስጦታው አያልቅም፡፡ “በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የሚያረጁትን ኮረዶች ለራሳችሁ አድርጉ” ሉቃ.12፥33፡፡ ምድራዊ አባት ከትልቁ ልጁ ይልቅ ለትንሹ የደላል እርሱ ግን ዓለምን በእኩል ምግብና ይመግባል፡፡ ምድራዊ አባት ትዕዛዙን ካልተጠበቀለት ልጁን ከቤት ያስወጣል፣ ያባርረዋል እርሱ ግን ሁል ጊዜ በትዕግስት ይመለከተናልና፡፡ “በጻድቃንና ለኀጥአንም ዝናምን ያዘንማልና” ማቴ.5፥45፡፡  እኛ አባትነቱን አምነን አባታችን ሆይ ብንለው እኛ ልጆቹ መሆናችን የልጅነት ሥልጣን እንዳገኘን እንመሰክራለን፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” እንዲል ዮሐ.1፥12፡፡ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ 1ዮሐ.3፥1፡፡
ከላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስረዱን የእግዚአብሔር ፍቅር ከምድራዊ አባት የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ምድራዊ አባት ልጁን ቢወደውም ሥልጣን አይሰጠውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለልጆቹ አጋንንትን እንዲያወጡ ድውያንን እንዲፈውሱ ለምጽ እንዲያነጹ ሙታን እንዲያስነሡ ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ “አሥራ ሁለቱን ደቀመዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው” እንዲል ማቴ.10፥1፡፡
በመኖሪያው /በሰማያት/ በመኖሩ ከምድራዊ አባት ይለያል፡፡ በሰማያት የምትኖር ብሎ በመኖሪያው ከምድራዊ አባት ለይቶታል፡፡ አሁን እግዚአብሔር በምድር የሌለ በሰማይ ብቻ የተወሰነ ሆኖ አይደለም በሰማይም በምድርም የመላ አምላክ ነው፡፡ “ከመንፈስ ወዴት እሔዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ ወደጥልቅም ብወርድ በዚያ አለህ፡፡ እንደንስር ክንፍን ብወስድ /ቢኖረኝ/ እስከባሕር መጨረሻም ብበርር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፡፡” መዝ.139፥7 በማለት ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ እንደሌለ ገልጿል፡፡
በሰማያት የምትኖር በሉኝ ያለን ብዙ ጊዜ መገለጫው፣ መቀመጫው፣ ለቅዱሳን እርሱ በወደደ እነርሱ በሚችሉት መጠን የተገለጠና የታየ በሰማይ ስለሆነ ነው፡፡
“ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀመጦ አየሁት የልብሱን ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር” ኢሳ.6፥1-6፡፡
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መርገጫ ናት” ኢሳ.66፥1፡፡
ኢሳይያስ ምልአቱን፣ ክብሩን፣ ልዕልናውን በአየው መጠን ነገረን፡፡ ይህን የአገልጋዩ የኢሳይያስን ምስክርነት ሳይለውጥ ነቢያት የተናገሩልኝ የስተማሩልኝ፣ የሰበኩልኝ እኔ ነኝ በማለት እነ “ኢሳይያስ ሰማይ ዙፋኔ ነው” ያለውን እንደአስተማሩ እርሱም በሰማያት የምትኖር ብላችሁ አመስግኑኝ አለን፡፡ ስለ ልዕልናው ስለ ክብሩ በሰማይ አለ ይባላል፡፡ “በእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት” እና ትርጓሜ ወንጌል “ስለ ልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ” ከዚህም የተነሣ ጌትችን ሲያስተምር “በሰማያ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና በምድርም አትማሉ የእግሩ መረገጫ ናትና” ማቴ.5፥32 ብሏል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌቶችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአየው ጊዜ እንዲህ መስክሯል “ወደሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና እነሆ ሰማያት ተከፍታው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ” ሐዋ.7፥55፡፡
ስለዚህ ብዙ ጊዜ በሰማይ ለወዳጆቹ ከመገለጡ የተነሣ አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ብላችሁ አመስግኑኝ አለን፡፡
2.    ተስፋ፡- ተስፋ ማለት የወደፊት አለኝታ እናገኘዋለን ብለን የምንጠብቀው መከራ የምንቀበልለት፣ በዚህ ዓለም ባይመቸን መከራ ቢጸናብን፣ ብንገፋ ብንከፋ ብናዝን ብንጨነቅ ያልፋል ብለን የምንጽናናበት ነው፡፡ ይህን ተስፋ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡ “በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም” ሮሜ.5፥2-5 ተስፋ ከላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ሰማዕታት ከነደደ እሳት ገብተው፤ የተሳለ ስዕለትን ታግሰው፤ የዓላውያን ነገሥታትን ግርማ አይተው ሳይደነግጡ፣ ሃይማኖታቸውን ሳይለውጡ፣ ሹመቱን ሽልማቱን ወርቁን ብሩን ምድራዊ ክብራቸውን ትተው መከራ የተቀበሉት ለተስፋ መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ጻድቃንም ድምጸ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ፍትወታት እኩያትን ታግሰው፣ በምናኔ በተባሕትዎ ከዘመድ ባዳ ከሀገር ምድረ በዳ ይሻለናል ብለው የኖሩት ለዚሁ ተስፋ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጴጥሮስ በሃይማኖት ምክንየት ተበትነው ለነበሩ ምዕመናን ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል፡፡ “እስመ በእንተ ዝንቱ ተጸዋእክሙ ከመ በረከተ ትረሱ በእንተ ዛቲ ተስፋክሙ” ለዚች ተስፋችሁ መከራን ትቀበሉ ዘንድ ተጠርታችኋልና 1ጴጥ.2፥22 የህ ተስፋ መጻሕፍት የተባበሩበት ነው” በተስፋ ያጽናናልና ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን” ሮሜ. 8፥24፡፡ ስለዚህ ተስፋ የምንለው የማናየውን መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ይህን ተስፋ በጸሎታችን ውስጥ መንግሥትህ ትምጣ ብለን እንድንለምን ጌታችን አስተማረን፡፡ አሁን መንግሥትህ ትምጣ ስንል መንግሥተ ሰማያት ክንፍ ኖሯት በራ፣ እግር ኖሯት ተሽከርክራ የምትመጣ ሆኖ አይደለም ትሰጠን በሉኝ ሲል ተስፋ የምናደርጋት መንግሥትን እንዲያወርሰን ለምኑ አለን፡፡
3.    ፍቅር ፡- ፍቅር ማለት አንዱ ለሌላው መጸለይ ነው፡፡ ይኸውም “የዕለት ምግባችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው ነው፡፡ ሰው ሁሉ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ሲጸልይ የዕለት እንጀራዬን ሰጠኝ ብሎ”  አይጸለይም ለጠላቶቹም ለወዳጆቹም ጠቅላላ ሰው ሆኖ የተፈጠረ የተፈጥሪሮ ወንድምና እኅት ሁሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእገሌ የሚል አደለም፡፡ ጠቅል አድርጎ የዕለት ምግባችንን ስጠን የሚል ነውና፡፡ ይህ ፍቅር ነው ሊቃውንት በትርጓሜያቸው ይህን ሲተረጉሙት ዕለት ዕለት እንድንማር፣ ሥጋውን ደሙን እንድንቀበል፣ ንሰሓ እንድገባ አድርግ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ከምግበ ሥጋ ያለፈ ጸሎት ነው፡፡ ይህም ጸሎት ለሕዝቡ ለአሕዛቡ ለጠላት ለወዳጅ ለዘመድ ለባዕድ ሳይባል ለሁሉም የሚጸለይ ጸሎት ሲሆን እግዚአብሔር እኛን እንደወደደን እርስ በእርሳችንም እንዋደድ ዘንድ ተዋደዱ “ጠላቶቻችሁንም ውደዱ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ” ብሎ አስተምሮኗል፡፡  ለሁሉም የሚሆን የጸሎት ፍቅርን የሚገልጽ ጸሎት “የዕለት ምግባችንን ስጠን” በሉኝ አለን፡፡
4.    ትሕትና፡- ትሕትና ማለት ራስን ዝቅ ማድረግ ማዋረድ ከሁሉ በታች ማድረግ ትዕቢትን ኩራትን ትዝህረትን ማስወገድ ነው፡፡ “ትዕቢትን ግን አታስቡ ራሲን የሚያዋርደውን ሰው ምሰሉ ሮሜ.12፥16፡፡ ይህም “ኀጢአታችንን ይቅርበለን” የሚለው ነው ይህን ጸሎት የበቃውም ያልበቃውም ይጸልየዋል፡፡ የበቃው የነጻው ከኃጢአት አልፎ ከአስረኛው መዓርግ የደረሰው ሁሉ ይጸልየዋል፡፡ ይህንን ሲጸልይ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ከእኛ መደብ ውስጥ አስገብቶ ኀጢአታችንን ይቅር በለን ይላል፡፡ እርሱ ግን ከኀጢአት አልፎአል ስለትሕትና እኛን መስሎ እንደኛ ሆኖ ይጸልየዋል፡፡ ጌታችን ብዙ ጊዜ ስለትሕትና አስተምሯል፣ “እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው” ማቴ 18፥4 “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ማቴ 20፥26-28፡፡
“ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” ማቴ 23፣11 እነዚህና ጌታችን ያስተማራቸውን በተግባር የሚያውሉ ቅዱሳን በቅተው ሳለ እንዳልበቁ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ይጸልያል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደተማረው የትሕትና ጥቅምን ጽፎአል “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኀይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” 1ጴጥ 5፥6፡፡ በዚህ ጸሎት ውስጥ ይህ ጠቃሚ የሆነ ጸሎት ተአምኖ ኀጣውእ (ኀጢአትን ማመን) ያለበት በደላችንን ይቅር በለን የሚለው ትሕትና ነው፡፡
5.    ጸሎት ፡- ጸሎት አባታችን ሆይ ብሎ እስከ መጨረሻው ያለው ነው አባችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥት ትምጣ ፈቃድ ይሁንልን ይደረግልን የዕለት እንጀራችንን ስጠን በደላችንን ይቅር በለን ጸሎት ነው ታዲያ ይህን በንባብ አጭር በምሥጢር ጌታ መጻሕፍት ያጠቃለለ ታላቅ ጸሎት አፍ ንባብ ይነዳ ልብ ጓዝ ያስናዳ እንዲሉ አበው ኅሊናን በማባከን ሳይሆን በንቃት፣ በትጋት ሆነን ብንጸልይ እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ነው ክብር ምሥጋና ይግባውና አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ ያለን፡፡
 “ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐና እስከ ዛቲ ሰዓት”
ወስብሔት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን::

Saturday, April 13, 2013

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ተአምር

     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ይህ የእመቤታችንን ድንቅ ተአምር የተነገረው ነሃሴ 19/2003 በግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የማታ ጉባኤ ሲሆን ነገሩም እንዲህ ነው ፦ ተአምሩን የመሰከሩት አንዲት እናት ሲሆኑ “የእመቤቴን ስም እየጠራሁ ያለአባት ያሳደግኩት ልጅ ነበርኝ ፡ እኔም ልጄም እመቤታችንን በጣም እንወድ ነበረ ፡ ያለአባት በእመቤቴ ስም ያሳደኩት ልጄ ተምሮልኝ ጥሩ ስራ ያዘልኝ ፡ በዚህ ደስ ብሎኝ ሳለ ልጄ በስራ ቦታ ካልሆኑ ልጆች ጋር ገጥሞ አዲስ ነገርን ተማረብኝ ፡ አንድ ቀን ማታ ሲመጣ “ እናቴ ሆይ ጌታን ተቀበይ” አለኝ ይህን ሲለኝ ደነገጥኩ “እመቤታችንስ” ስለው “ዙሪያ ጥምጥም መሄዱ ይበቃናል አንቺም እኔም ጌታን መቀበል አለብን” አለኝ ፡ እኔም ጧት ማታ አለቅስ ጀመር ፡ ለልጄም ይህ የነፍስ በሽታ ለስጋውም ተርፎ ሁለቱ ጆሮወቹ አልሰማም አሉት፡፡ በዚህም የተነሳ ጴንጤወች እንፀልይልህ ብለው በአዳራሻቸው ወሰዱት ፡ ጆሮወቼ ይድኑ ይሆን ብሎ ተስፋ ያደረገው ልጄም ይባስ ብሎ ሁለቱም አይኖቹ ጠፉ ፡ ከዚህ በኅላ እቤት ተኛ ፡ እኔም እያለቀስኩ እኖር ነበር፡፡ አስቡት ጆሮውንኳ ባይሰማ አይን ቢኖረው በምልክት እንግባባ ነበር ፡ ወይንም አይኑ ባይኖርና ጆሮው ቢሰማ በድምፅ እንግባባ ነበር አሁን ግን እጅግ ችግር ሆነብኝ፡፡ ከሁሉ የሚያስጨንቀኝ ግን እመቤቴን መክዳቱ ነበር፡፡ አንድ ቀን ቤተክርስቲያን ምስክርነት ሲሰጥ ሰምቼ እኔም በሃይላንድ ፀበል ይዜ ወደቤት ሄድኩኝ፡፡ በሁለቱ ጆሮወቹ ፀበሉን አፈሰስኩበት፡፡ የእመቤቴ ስእል ፊትም ተንበርክኬ “እመቤቴ ሆይ ጆሮውም አይስማ ፡ አይኑም አይይ ፡ ነገር ግን ልቡን መልሺልኝ” እያልኩ አልቅሼ ፀልየ ወደ መኝታየ ሄድኩኝ ሌሊት 10፡00 ላይ ልጄ “እማየ” ብሎ ጠራኝ እኔም “አቤት” አልኩት “ጆሮወቼ ሰሙልኝ” አለኝ፡፡ እኔም “ልብህ ቢሰማ ነውንጅ የሚሻለው” አልኩት፡፡ አሁንም ትንሽ ቆይቶ 11፡00 ላይ “ እማየ የእመቤታችንን ስእሏን ስጭኝ” አለኝ ፡ እኔም ሰጠሁት እሱም ስእሏን አቅፎ ለአንድ ሰአት ያክል አለቀሰ፡፡ ትንሽ ቆይቶም “እማየ” አለኝ ፡ እኔም “አቤት ልጄ” አልኩት ፡ እርሱም ”ሁለቱም አይኖቼ በሩልኝ” አለኝ፡፡ ደስታየን እንዴት እንደምገልፀው አላውቅም ፡ የኔ እመቤት የልጄን የነፍሱንም የስጋውንም ህመም ፈወሰችልኝ፡፡ አሁንም ልጄ እዚሁ ቤተክርስቲያን ከእመቤቴ ስእል ፊት ተንበርክኮ እየፀለየ ነው፡፡ እኔን የሰማች እናንተንም ትስማልኝ” ይህ ታአምር እንዴት ደስ ይላል፡፡ እመቤታችን ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ፡ ከፍ ከፍ እናደርግሻለን ፡ በልጅሽ አምነው በአማላጅነሽ ተማምነው ስምሽን የሚጠሩትን እንደማትተያቸው እናውቃለን፡፡ ድንግል ሆይ ስለዚህ ክብር ምስጋና ይገባሻል፡፡ አንቺን ለእናትነትና ለአማላጅነት የሰጠን ጌታችን አምላካችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅሩ ነገር ምን ይረቅ?
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Friday, April 12, 2013

መነኮስ አባ እንጦንዮስ




  • ምንጭ፡- የበረሃው ኮከብ ቅዱስ እንጦንዮስ መጽሐፍ

kiduse entonseጨለማ በዋጠው በግብፅ በረሃ ውስጥ ለብዙዎች አርዓያ በሆነ የእምነት ገድል የቅድስናን ብርሃን በማብራቱ የበረሃው ኮከብ ብለው ብዙዎች ይጠሩታል፡፡

ብፁዐዊ ቅዱስ እንጦንስ በምንኩስና ሕይወት ለመኖር ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተማረው አብነታዊ ትምህርት (ማቴ.4፥1-10) ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ ከሰዎች ሁሉ ተለይቶ  ፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎን በመጋደል በተወለደ በ106 ዓመቱ ጥር 22 ቀን በ356 ዓ.ም. ከዚች ዓለም በሥጋ ተለይቷል፡፡ “ክቡር ሞቱ ለፃድቅ በቅድመ እግዚአብሔር” “የፃድቅ ሰው ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” በማለት ክቡር ዳዊት እንደተናገረው፣ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን የልደታቸውን ጊዜ፣ የተጋድሏቸውን ሁናቴ፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉባቸውንና ያረፉባቸውን ዕለታት በክብር ታስባለች፡፡ ይህም በቅዱስ መጽሐፋችን “የፃድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው”(ምሳ.10÷7)፡፡ በመሆኑም “ስለ ፅድቅ የሚሰደዱ ብጹአን ናቸው ÷ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ.5÷8) በሚለው በጌታችን ትምህርት የዚችን ዓለም ጣዕም ንቆ በምናኔ በመኖር ለመነኮሳት አብነት የሚሆናቸውን የቅዱስ እንጦንስን ዜና ሕይወት አቅርበናል፡፡ለመሆኑ ቅዱስ እንጦንስ ማን ነው? አስተዳደጉና የፈጸማቸው አገልግሎቶቹ ምን ይመስላሉ?

ልጅነት
እንጦንዮስ/እንጦንስ/ ትውልዱ ግብጻዊ ሲሆን ቤተሰቦቹም መልካሞችና ባለጸጎች ነበሩ፡፡ እነርሱም በሕፃንነት ኑሮው ከቤቱና ከወላጆቹ በስተቀር ምንም አላወቀም፡፡ እያደገና ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ትምህርት ቤት አልገባም ነበር፡፡ ይህም ከሌሎች ልጆች ጋር ጓደኝነት ባለመፈለጉ ነበር፡፡ የእርሱ ፍላጎት በቅዱስ መጽሐፍ ተጠቅሶ እንደሚገኘው እንደ ያዕቆብ በብቸኝነትና በጭምትነት በቤቱ በመቀመጥ ቀላል ሕይወትን መምራት ነበር፡፡ ዘፍ.25፥27 በእርግጥ ከወላጆቹ ጋር ቤተ ክርስቲያን እየሄደ ያስቀድስ ነበር፡፡ በዚህም ከአንድ ልጅ ወይም ከአንድ ወጣት የሚታየው የመሰልቸትና የጥላቻ መንፈስ በጭራሽ አልታየበትም፡፡ ለወላጆቹ በመታዘዝ የሚሰጡትን ትምህርቶችና የሚነበቡትን ቅዱሳት መጻሕፍት በጥሞና ይከታተል ነበር፡፡ ከነዚህም የሚቀስመውን ጥቅም በልቡ በማስተዋል አኖረ፡፡ በሌላም በኩል በልጅነቱ ወራት ምንም እንኳ ያለ አንዳች ችግር ቢኖርም ወላጆቹን ለቅንጦትና ለድሎት ለምግብም ሲል አያስጨንቃቸውም ነበር፡፡ ይህን በመሰሉት ሁሉ አይደሰትም ነበር፡፡ በፊቱ በሚቀርብለት ብቻ ይረካ ነበር፡፡ ተጨማሪም አይጠይቅም፡፡

መጠራት
ወላጆቹ ከሞቱ በኂላ እንጦንዮስ ገና ልጅ ከነበረች አንዲት እኅቱ ጋር ብቻኛ ሆነ፡፡ በዚህ ወቅት ዕድሜው ከ18 እስከ 20 ዓመት ገደማ ነበር፡፡ ቤቱንና እኅቱንም ይጠብቅ ጀመር፡፡ እነርሱን ካጣ ከስድስት ወር በኋላ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ በመንገድ በኅሊናው ያስብ ጀመር፡፡

ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታን እንደተከተሉት (ማቴ.10፣ 20፣19፣ 27)፤ በግብረ ሐዋርያት ሕዝቡ ያላችውን ሁሉ ሸጠው ለድሆች ይከፋፈል ዘንድ በሐዋርያት እግር ሥር ስለማኖራቸው (ሐዋ.4፡35)፤ ይህን ለመሳሰሉ ሥራዎች በሰማያት እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ እንዳላቸው (ኤፌ.1፡18 ቆላ.1፡15) እኒህን አሳቦች በኅሊናው እያወጣና እያወረደ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡ በዚያም ወቅት ወንጌል ይነበብ ነበር፤ ሲያዳምጥ ጌታ በሀብታሙ ሰው የተናገረውን የሚጠቅሰው ምዕራፍ ተነበበ፡፡

“ልትጸድቅ ብትወድድ ሂደህ ያለህን ሁሉ ሽጥና ለድሆች ስጥ፡፡ መጥተህም ተከተለኝ፡፡ በሰማያት መዝገብ ታከማቻለህ፡፡” ማቴ.19፡21 ፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞ ስለ ቅዱሳን እንዲያስብ እንዳደረገውና እዚህም የተነበበው በቀጥታ ለእርሱ እንደተነገረ ስለተሰማው እንጦንዮስ በቀጥታ ከቤተ ክርስቲያኑ በመውጣት ከዘመዶቹ የወረሰውን 300 ሄክታር ወይም 12 ጋሻ መሬት ለድሆች አከፋፈለ፡፡ መሬቱ ለምና ለዐይንም ያማረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለእርሱም ሆነ ለእኅቱ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አልፈለገም፡፡ የተረፈውን ሁሉን ተንቀሳቃሽ ሀብቱን ሸጠ፡፡ አብዛኛውን ለድሃ ሰጥቶ ጥቂቱን ለእኅቱ አስቀመጠው፡፡

እንጦንዮስ በሌላ ቀን እንደገና ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሳለ ጌታ በወንጌል የተናገረውን ሲነበብ አደመጠ፡፡ “ለነገ አትጨነቁ” ይል ነበር ጥቅሱ ማቴ.6፡34፡፡ ይህንንም ሰምቶ ሳይዘገይ ወደ ቤቱ በመመለስ የተረፈውን ሁሉ ለድሆች ያከፋፍል ጀመር፡፡ እኅቱን ግን የታወቁና የታመኑ ወደሆኑ ደናግል ማኅበር ወሰዳት፡፡ በዚያም ታድግ ዘንድ ለደናግል ትቷት ተመለሰ፡፡ ከዚያ በኋላ ብቻውን በመሆኑ ንቁ ሆኖ ራሱን በመካድ በመኖሪያ ቤቱ አጠገብ ጊዜውን ለብሕትውና ሕይወት ሰጠው፡፡

ትሕትና
እንጦንዮስ ራሱን ዝቅ በማድረግና በነፍስ ትሕትና የጸና ነበር፡፡ ምንም እንኳ ታላቅና ዝነኛ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያንን ልዑካንና ጸሐፍትን ከእርሱ ይልቅ እንዲከበሩ ይሻ ነበር፡፡ በጳጳሳትና በካህናት ፊት እራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ ሲነሣ አሳፋሪ አያደርገውም፡፡ ዲያቆን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ጠቃሚ ነጥብን ካገኘም ላገኘው ዕውቀት ሳያመሰግን አያልፍም፡፡

በገጽታው ሊገለጽ የማይቻልና ታላቅ የሆነ ብሩህ ገጽ ይነበብበታል፡፡ በመነኮሳት ጉባኤ ተቀምጦ ሳለ ቀድሞ የማይተዋወቀውን ሰው ሊያነጋግረው ከፈለገ ማንም ሳያመለክተው በዓይኖቹ እንደተሳበ ሁሉ ሌሎቹን አልፎ በቀጥታ ወደ እንጦንዮስ ይሄዳል፡፡ ከሌሎቹ ልዩ አድርጎ የሚያሳውቀው ቁመናው ምስሉ ሳይሆን የረጋ ባሕርይውና የነፍሱ ንጽሕና ነበር፡፡ ነፍሱ የማትነዋወጽ በመሆንዋ አፍአዊ ገጽታውም የረጋ ነበር፡፡ በመጽሐፍ  “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፡፡ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች፡፡”ተብሎ እንደተነገረው (ምሳ.15፥13)፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብ አጎቱ ደባ ተንኮል እንዳሰበበት ባወቀ ጊዜ ለሚስቶቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፡፡ ዘፍ.31፥5፡፡ ነቢዩ ሳሙኤል ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ ይቀባው ዘንድ በተላከ ጊዜ ደስታን የሚያንጸባርቁ ዓይኖቹንና እንደ ወተት የነጡ ጥርሶቹን አይቶ አወቀው፡፡ 1ሳሙ.16፥10፡፡ እንጦንዮስም እንዲሁ ይታወቅ ነበር፡፡ አይነዋወጽም፡፡ ነፍሱ እርጋታ ነበራትና፡፡ አያዝንም፡፡ አዕምሮው ደስታን የተሞላ ነበር፡፡

ቅዱስ እንጦንዮስ ፍቅረ ነዋይ ላለቀቀው መነኩሴ ያስተማረው ትምህርት
ዓለመን ንቆ ገንዘብ ስለመውደድ ከመነኮሰ በኋላ ለድሆች ካከፋፈለ በኋላ ለራሱ ጥቂት ያስቀረ አንድ ወንድም ወደ ባሕታዊው ወደ እንጦንዮስ መጣ፡፡ እንጦንዮስም ይህን ካወቀ በኋላ እንዲህ አለው፡፡ “ መነኩሴ ለመሆን ከፈለግህ ወደ መንደር ሂድና ጥቂት ሥጋ ገዝተህ ራቁትህን በሰውነትህ ላይ ተሸክመህ ተመለስና ወደእኔ ና” አለው፡፡ያም ወንድም ይህን ባደረገ ጊዜ ወፎችና ውሾች በሰውነቱ እያንዣበቡ ይታገሉት ጀመር፡፡ በደረሰም ጊዜ እንጦንዮስ እንዳዘዘው ማድረጉን ጠየቀው፡፡ እርሱም የቆሰለውን ሰውነቱን ባሳየው ጊዜ እንጦንዮስ እንዲህ አለው፡-“ዓለምን ከናቁ በኋላ ገንዘብ የሚመኙትም እንደዚሁ በአጋንንት ይገደላሉ፡፡” አለው፡፡

ቅዱስ እንጦንስ ስለ ዕረፍቱ በቀደ መዛሙርቱ ፊት የተናገረው የመጨረሻ ንግግር
የአባቶቼን መንገድ እሄዳለሁ
እንደልማዱ መነኮሳትን ይጎበኝ ዘንድ በተራራው ውጭ ሳለ በጌታ ቸርነት አስቀድሞ ስለ ሞቱ ስላወቀ ለወንድሞች እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡፡ “ይህ ከናንተ ጋር የማደርገው የመጨረሻው ግንኙነት ነው፡፡ በዚህም ሕይወት ዳግመኛ እንተያይ እንደሆነ እንጃ እጠራጠራለሁ፡፡ ዕድሜዬ አንድ መቶ አምስት ዓመት ገደማ ሆኗልና አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ነው፡፡” ይህን በሰሙ ጊዜ ሽማግሌውን ሰው አቅፈው እየሳሙ ያለቅሱ ጀመር፡፡ እርሱ ግን ከውጭ ከተማ እንደሚለይ ሁሉ በደስታ ያወጋቸው ነበር፡፡ በጥብቅም መከራቸው፡፡ “ከጥረታችሁ ግዴለሽ አትሁኑ፡፡ በብሕትውና ሕይወት ፍጹም ተስፋ አትቁረጡ፡፡ ዕለት ዕለት እንደምትሞቱ ሆናችሁ ኑሩ፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኩት ነፍስን ከርኩስ አሳቦች ለመጠበቅ በሥራ ትጉ፡፡ ቅዱሳንን ምሰሉ፡፡ ቅድስና የሌለውን የስንፍና ትምህርታቸውን ታውቃላችሁና ወደ መለጣውያን (መናፍቃን) አትቅረቡ ኑፋቄያቸው ለማንም ግልጽ ነውና፡፡

በመጽሐፈ መነኮሳት (ፊልክስዮስ) መቅድም ላይ ስለ ቅዱስ እንጦንስ ከተፃፈው የሚከተለው ይገኛል፡-እንጦንዮስ (እንጦንስ) አባቱ ባለጸጋ ነበር፡፡ አገሩም ጽኢድ ዘአምፈለገ አቅብጣ ናት፡፡ …በሕጻንነቱ ከትምህርት ቤት ሄደ፡፡ ተምሮ ሲመለስ አባቱ “ሕግ ግባ” አለው፡፡ እርሱ ግን “አይሆንም” አለ፡፡ምነው ቢሉ ፈቃዱ እንደ ቀደሙ ሰዎች እንደ ኤልያስ፤ እንደ ኋላ ሰዎች እንደ ዮሐንስ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት ርቆ በድንግልና መኖር ነውና፤ ግድ አለው፡፡ “ግድማ ካልከኝ …ፍቀድልኝና ለእግዚአብሔር አመልክቼ ልምጣ እንጂ” አለ፡፡ “ደግ አመልክተህ ና” አለው፡፡ሄዶ ባቅራቢያው ካለ ዋሻ ገባ፡፡ ወዲያው አባትህ ታመመ አሉት፡፡ ቢሄድ አርፎ አገኘው፡፡ ገንዘቡን ሦስት ነገር አስቦ አስቀድሞ ይመጸውታል፡፡ መጀመሪያ ያባቴ በድኑ ከመቃብር ሳይከተት መብሉ በከርሰ ርሁባን፤ መጠጡ በጉርኤ ጽሙአን፤ ልብሱ በዘባነ ዕሩቃን ይከተት ብሎ፡፡ ሁለተኛው ወኢይወርድ ምስሌሁ ኩሉ ክብረ ቤቱ /ሀብቱ ንብረቱም ሁሉ አብሮ መቃብር አይወርድም/ ያለውን የነቢዩን ቃል ያውቃልና፤ ሦስተኛ የሚመንን ነውና ልብ እንዳይቀረው፡፡ ሲመጸውትም አየቴ ኀይልከ፤ አይቴ አእምሮትከ አይቴ ፍጥነትከ /ኀይልህ የት አለ እውቀትህስ የት አለ ፍጥነትህስ የት አለ/ እያለ መጽውቶታል፡፡ መጽውቶ አባቱን አስቀብሮ ሲያበቃ ቅዳሴ ለመስማት ከቤተክርስቲያን ገብቶ ቆመ፡፡ ቄሱ ወንጌል ብሎ ወጥቶ ሲያነብ እመሰ ፈቀድከ ትኩን ፍጹመ ሲጥ ኩሉ ንዋይከ ወሀብ ለነዳያነ ወነዓ ትልወኒ ያለውን ቃል ሰማ፡፡ ይህ አዋጅ የተነገረ ለኔ አይደለምን? ብሎ እኅት ነበረችው ከደብረ ደናግል አስጠግቶ ሂዶ ፊት ከነበረባት ዋሻ ገብቶ ተቀመጠ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ወለተ አረሚ ሠናይተ ላህይ ይላታል ከደንገጡሮቿ ጋር በቀትር ጊዜ መጥታ ከዛፉ እግር ከውኃው ዳር አረፈች፡፡ ፊት እሷን አስጠጓት፤ ኋላ እርስበሳቸው ይተጣጠቡ ጀመር፡፡ እሱም እርቃናቸውን እንዳያይ ዓይነ ሥጋውን ወደ ምድር ዓይነ ነፍሱን ወደ ሰማይ አድርጎ ሲጸልይ ቆየ፡፡ ያበቃሉ ቢል የማያበቁለት ሆነ፡፡ ኋላ ደግሞ ቆይተው ነገረ ኀፊር እያነሱ ይጨዋወቱ ጀመር፡፡ ምነው እንግዲህማ አይበቃችሁም? አትሄዱም? አላቸው፡፡ ኦ እንጦኒ! ኦ እንጦኒ!፤ ለእመ ኮንከ መነኮሰ ሑር ኀበ ገዳም እንጦኒ ሆይ መነኩሴ እንደሆንክ ከዚህ ምን አስቀመጠህ ከበረሃ አትሄድም ነበርን?/ አለችው፡፡ ከዚያ አስቀድሞ መነኩሴ አልነበረ መነኮስ ማለት ከምን አምጥታ ተናገረች? ቢሉ ጌት ለአበው ትምህርት የሚሆነውን ነገር በማናቸውም ባልበቃ ሰው አድሮ መናገር ልማዱ ነው፡፡ አንድም እሱ ከመነኩሴ ፊት እንዲህ ያለ ኀፊር ትናገሪያለችን? አላት፡፡ ከሱ ሰምታ ኦ እንጦኒ ኦ እንጦኑ እመሰ ኮንከ መነኮሰ ሑር ሐበ ገዳም አለችው፡፡

እንጦኒ ኦ እንጦኒ እመሰ ኮንከ መነኮሰ ሑር ሐበ ገዳም እያለ ራሱን እየገሰጸ ፊቱን እየሰፋ ጽሕሙን እየነጨ ከዚያ ተነሥቶ አናብስት፤ አናምርት፤ አካይስት፤ አቃርብት ካሉበት ነቅዐ ማይ፤ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት ድሩክ ለተአቅቦ ይላል ዘር ተክል ከማይገኝበት ገዳመ አትፊር ሄደ፡፡ የዚህ መንገዱ ፍለጋ የለውም፡፡ አሸዋ ላሸዋ ነው፡፡ ነጋድያን ሲጓዙ የወደቀውን ያህያና የግመል ፋንድያ እያዩ በዚያ ምልክት ይሄዳሉ፡፡ በረሃነቱም ጽኑ ነው፡፡ ከሐሩሩ ጽናት የተነሣ በቀትር ጊዜ ከደንጊያ ላይ ተልባ ቢያሰጡ ይቆላል፡፡ እሱም ከዚያ ሄዶ ሲጋደል አጋንንት ጾር አነሱበት፡፡ ኦ ሕጹጸ መዋዕል እፎ ደፈርከ ዝየ፡፡ /በእድሜ ሕፃን የሆንክ ከዚህ እንደምን ደፍረህ መጣህ?/ አዳም ከወጣበት ገነት እንጂ እገባ ብሎ ነው፡፡ ብለው ዘበቱበት፤ እሱም በትሕትና ይዋጋቸዋል፡፡ መሆንማ ይሆን ብላችሁ ነውን? እናንተ ብዙ አኔ አንድ ብቻዬን፤ እናንተ ረቂቃን እኔ ግዙፍ፡፡ እናንተ ኀያላን እኔ ደካማ በኀይለ ክርስቶስ ብችላችሁ ነው እንጂ ያለዚያስ አልችላችሁም እያለ በትሕትና ሲዋጋቸው ኖረ፡፡

ከዕለታት ባንድ ቀን ይኸን ፆር አልቻልሁትም ልሂድ እንጂ ብሎ ሲያስብ አደረ፡፡ ማለዳ በትረ ሆሣዕና ነበረችው ያችን ይዞ ከደጃፉ ላይ ቆመ፡፡ እንዳይቀርም ፆሩ ትዝ እያለው እንዳይሄድም በዓቱ እየናፈቀው አንድ እግሩን ከውስጥ፤ አንድ እግሩን ከአፍአ አድርጎ ሲያወጣ ሲያወርድ መልአኩ የሰሌን ቆብ ደፍቶ፤ የሰሌን መቋረፊያ ለብሶ፤ የሰሌን መታጠቂያ ታጥቆ ብትን ሰሌን ይዞ መጣ፡፡ ምን ሊያደርግ ይሆን? ሲል ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ፡፡ ወዲያው ጸሎተ ወንጌልን፤ ነአኩቶን፤ ተሠሀለኒን፤ ደግሞ መጀመሪያ ለሥላሴ እጅ ነሳ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ሠላሳ ስድስት ሰጊድ አድርሶ በመጨረሻ አንድ ጊዜ እጅ ነሥቶ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ያን ብትን ሰሌን አቅርቦ ይታታ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም እንግዲህማ የዚህን ፍጻሜ ሳላይ እሄዳለሁን? ብሎ ተቀምጦ ይመለከተው ጀመር፡፡ ሠለስት ሲሆን ደግሞ ተነሥቶ አቡነ ዘበሰማያቱንም ሰጊዱንም ያንኑ ያህል አደረሰው፡፡ የቀሩትንም የሰዓቱንም የሠርኩንም እንደዚሁ አድርጎ አሳየው፡፡ በሠርክ ኦ እንጦኒ ከመ ከመዝ ግበር ወለእመገበርከ ዘንቱ ትድኀን እምጸብአ አጋንንት አለው /እንጦኒ ሆይ እንደዚህ እንደዚህ ሥራ፤ ይህንን ከሠራህ ከአጋንንት ጠብ ትድናለህ/፡፡ ማለት ነው፡፡ የንዋሙን የመንፈቀ ሌሊቱን ግን እርሱ ጨምሮታል፡፡ ንዋም ጌታ የጸለየበት፤ ቀትር የተሰቀለበት፤ ሰዓት ነፍሱን ከሥጋው የለየበት፤ ሰርክ መቃብር የወረደበት ነውና ይህን ሁሉ አንድ አድርጎ ዳዊት ሰብአ ለዕለትየ እሴብሐከ ብሏል፡፡ /መዝ.118፥164/

ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ጌታ በዕለተ ዓርብ የለበሰውን ልብስ አልብሶታል፡፡ ማየት ከመልአክ፤ መቀበል ከአምላክ እንዲሉ ይህም ምሳሌ ነው፡፡ ቆብ የአክሊለ ሦክ፤ ቀሚሱ የከለሜዳ፤ ቅናቱ የሀብል፤ ሥጋ ማርያም የሥጋ ማርያም፤ አስኬማ የሰውነት ወተመሰለነ በአስኬማሁ እንዲል፤እርሱም ይህን ተቀብሎ በዚህ ዓለም እኔ ብቻ ነኝን ሌላም አለ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ ጌታም አለ እንጂ አንድ ጊዜ ተራምዶ ሁለተኛውን ሳይደግም የሚሠራውን ሥራ ዓለሙ ሁሉ ቢሰበሰብ የማይሠራው፡፡ በጸሎቱ ዝናም የሚያዘንም ፀሐይ የሚያወጣ፤ እንደዚህ ያለ ወዳጅ አለኝ አለው፡፡ ይኸን ሰው ለማየት ልሂድን ልቅር? ቢለው ሂድ አለው፡፡ መልአኩ እየመራ አደረሰው፡፡ ጳውሎስ /ጳውሊ/ ከበዓቱ ወጥቶ ፀሐይ ሲሞቅ ነበር፡፡ ሲመጣ አይቶ ከበዓቱ ገብቶ ወወደየ ማእጾ ውስተ አፈ በዓቱ /ከበዓቱ አፍ ውስጥ መዝጊያ ጨመረ/ ይላል ዘጋበት፡፡ ከደጃፉ ቆሞ አውሎግሶን አውሎግሶን አለ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ክፈትልኝ ማለት ነው፡፡ ሰው እንደሆንክ ግባ ብሎ ከፈተለት፡፡ ገብቶ ማን ይሉሃል? አለው ስሜን ሳታውቅ እንደምንም መጣህ? አለው፡፡ እንጦንዮስም ፍጹም ነውና ቢጸልይ ወዲያው ተገልጾለት፤ ጎድጎድኩ ወተርህወ ሊተ ሀሰስኩ ወረከብኩ ጳውሎስ ገዳማዊ አለው፡፡

ጳውሎስ/ጳውሊ/ ትባላለህ ቢለው አደነቀ፡፡ ተጨዋውተው ሲያበቁ ባጠገቡ ለብቻው በዓት ሰጠው፡፡ እንጦንዮስም ከዚያ ሆኖ ጸሎቱን ሲያደርግ ዋለ፡፡ ወትሮ ለጳውሊ መንፈቀ /ግማሽ/ ኅብስት ይወርድለት የነበረ ማታ ምሉዕ ኅብስት ወረደለት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር መምጣቱን ያን ጊዜ አወቀው፡፡ ወዲያው ያን ኅብስት ከሁለት ገምሶ እኩሌተውን ለራሱ አስቀርቶ እኩሌታውን ሰጠው፡፡ ያን ተመግበው ሌት ሁሉም በየሥራቸው ክብራቸው ተገልጾ ሲተያዩ አድረዋል፡፡ ጳውሎስ አሥር ጣቶቹን እንደ ፋና ሆነው እያበሩለት አራቱን ወንጌል ሲያደርስ እንጦንዮስም እንደ አምደ ብርሃን ተተክሎ ሲያበራ ተያይተዋል፡፡

በዚያች ሌሊት ከዚያ ቦታ ጨለማ ጠፍቶ አድሯል፡፡ በነጋው ሠለስት እላፊ ሲሆን ጸሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ ተገናኝተው ሲጨዋወቱ፤ እንጦንዮስ ያረገውን ቆብ አይቶ፤ ይህማ ከማን አገኘኸው? አለው፡፡ እርሱ ባለቤቱ ስጠኝ አለ፡፡ እርሱም የጌታን ቸርነት ያደንቅ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም እስኪ በኔ ብቻ የሚቀር እንደሆነ ለሌላም የሚያልፍ እንደሆነ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ፡፡ ወዲያው ተገለጸለት፡፡ ወአክሞሰሰ ይላል፡፡ ደስ አለው፡፡ ምን አየህ? ቢለው ጽዕድዋን አርጋብ /ነጫጭ ርግቦች/ በጠፈር መልተው አንተ እየመራሀቸው ተከትለውህ ሲሄዱ አየሁ አለው፡፡ ምንኑው ቢለው? እሊህማ በዚህ በቆቡ የምትወልዳቸው ንጹሐን ጻድቃን ልጆችህ ናቸው አለው፡፡  ሁለተኛ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ ወደመነገጹ ይላል፡፡ አዘነ ምነው ቢሉ በክንፋቸው ጥቁር ተቀላቅሎባቸው አየሁ አለው፡፡ ምንድንናቸው ቢለው ጽድቅና ኀጢአት እየቀላቀሉ የሚሠሩ ልጆችህ ናቸው አለው፡፡ ሦስተኛ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ ገአረ ወበከየ ይላል፡፡ ቃሉን ከፍ አድርጎ ጮኸ፡፡ ምነው አለው አርጋብስ አርጋብ ናቸው አለው፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ዘመን የሚነሡቱ እንደ ቁራ ጠቁረው አየሁዋቸው አለ፡፡ ምንድናቸው? ቢለው ሀሳሲያነ ሢመት /ሹመት ፈላጊዎች/፤ መፍቀሪያነ ንዋይ /ገንዘብ የሚወዱ/ እለ ይሠርኡ በነግህ ማዕደ ምስለ መኳንንት /ከመኳንንት ጋር በጥዋት ማዕድ የሚቀመጡ/ ይላቸዋል፡፡ በፍጻሜ ዘመን የሚነሡ ኀጥአን ልጆችህ ናቸው፡፡ አለው፡፡ ያለ ንስሓ ባይጠራቸው እስኪ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ፡፡ የዚህ ምላሽ አልመጣለትም ይላሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ጳውሊ እንግዲህ ይህን ከራስህ ያደረግኸውን ለኔ ስጠኝ ላንተ ሌላ ሠርተህ አድርግ አለው፡፡ ይህንንስ እንዳልሰጥህ ከባለቤቱ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራውን ለምጄዋለሁ ሌላ ሠርቼ ላምጣልህ አለው፡፡ እንዲያስ አትዘግይ ቶሎ ሠርተህ አምጣልኝ አለው፡፡ ጊዜው እንደደረሰ አውቆታልና ይላሉ፡፡ እንጦንስም ሠርቶ ይዞ ሲመጣ ጳውሊ አርፎ ነፍሱን መላእክተ ብርሃን ይዘዋት ሲያርጉ አየ፡፡ ማነው ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ያ ሰው አርፏልና ሂደህ ቅበረው አሉት ይህንሳ የያዝኩትን ቆብ ልተወውን? አላቸው፡፡ አትተው አድርግለት ብለውታል፡፡ ከምንኩስና አስቀድሞ የሠሩትን ሥራ ከንቱ እንዳይደለ ለማጠየቅ ነው፡፡

ቢሄድ መጽሐፉን ታቅፎ፤ አጽፉን ተጎናጽፎ፤ ከበዓቱ አርፎ፤ አገኘው፡፡ ከራስጌው ቆሞ ሲያለቅስ ሁለት አናብስት መጡ፡፡ የመቃብሩን ነገር እንደምን ላድርግ ነኝ አያለ ሲጨነቅ በእጃቸው እንደመጥቀስ አድርገው አሳዩት፡፡ ልኩን ለክቶ ሰጣቸው፡፡ ቆፈሩለት እሱን ቀብሮ እንግዲህ ከዚህ እኖራለሁ ብሎ አሰበ፡፡ ጌታ ግን ዛሬ በሱ ቦታ ላይ ሌላ ሰው አላየበትምና አይሆንልህም ሂድ አለው፡፡ አጽፉንና መጽሐፉን ይዞ ሂዶ እስክንደርያ ሲደርስ ሊቀ ጳጳሱ አትናቴዎስ ወዴት ሄደህ ነበር? አለው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ልጠይቅ ሄጄ ነበር፡፡ አርፎ አግኝቼ ቀብሬው መጣሁ፡፡ አለ፡፡ ልሄድና ከዚያ ልኑር? አለው አይሆንልህም አትሂድ እኔም አስቤ ነበር፡፡ የማይሆንልኝ ሆኖ መጣሁ እንጂ አለው፡፡ ባይሆን ለበረከት ያህል አጽፊቱን ጥለህልኝ ሂድ ብሎ ትቶለት ሄደ፡፡ መዓርግ ሲሰጥ ሥጋውን ደሙን ሲለውጥ በውስጥ ያቺን ይለብስ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ በዚህ ቆብ እንጦንዮስ መቃርስን፤ መቃርስ ጳኩሚስን፤ ጳኩሚስ ጳላሞንን፤ ጳላሞን ቴዎድሮስ ሮማዊውን ቴዎድሮስ ሮማዊ አቡነ አረጋዊንና አባ ዳንኤልን ይወልዳል፡፡ አባ ዳንኤል አቡነ አውስጣቴዎስ፤ አቡነ አረጋዊ እስከ አቡነ ተክለሃይማኖት ያሉትን ወልደዋል፡፡ ከዚህ በኋላ መነኮሳቱ እንደ ሳር እንደ ቅጠል በዝተው ተነሥተዋል፡፡ ይሩማሊስ፤ ጳላድዮስ የሚባሉ ሁለት ሊቃውንት መነኮሳት ከግብፅ ተነሥተው አገር ላገር እየዞሩ የአበውን ዜና በሕይወት ያሉትን ከቃላቸው የሞቱትን ከአርድአቶቻቸው እየጠየቁ ቃለ አበው፣ ዜና አበው እያሉ ጽፈዋል፡፡
         ምንጭ፡- የበረሃው ኮከብ ቅዱስ እንጦንዮስ መጽሐፍ
 

Saturday, March 16, 2013

ሰማእት ማርታ


                                                                                        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ሞቤድ ፋርሶች ሶርያን በተቆጣጠሩበት በ4ተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የዞሮአስትራኒዚም እምነት ተከታይና ፈራጅ ዳኛ ነው፡፡ ማርታ ደግሞ እርሱ በዳኝነት በተሰየመባት ከተማ ትኖር የነበረች በጥንታዊያን የሶርያ ክርስቲያኖች ዘንድ “የቃል ኪዳን ልጆች” ተብለው ከሚጠሩት ወገን ነበረች፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለእርሱዋም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰማዕትነት የምትቀበልበት ጊዜው ደርሶ ኖሮ ይህ የከተማዋ ዳኛ ወደ እርሱ አስጠርቶ እንዲህ ብሎ አስጠቅቆ ተናገራት፡-
 “አንቺ ሴት እኔ የምልሽን ብቻ ልብ ብለሽ አድምጪ፤ ምኞትሽን ተከትለሽ እኔ የምልሽን ከመፈጸም እንዳትዘገዪ ተጠንቀቂ፡፡ በእምነትሽ ትኖሪ ዘንድ አልከለክልሽም፤ እምነትሽን በተመለከተ እንደ ፈቃድሽ ማድረግ ትችያለሽ፡፡  ነገር ግን እኔ የማዝሽን ብቻ ፈጽሚ፤ እኔ የምልሽን የፈጸምሽ እንደሆነ ከሞት ቅጣት ትድኛለሽ፡፡ ማርታ ሆይ ይህ “ቃል ኪዳን” የምትይውን የማይረባ ነገርሽን ትተሽ ገና ወጣትና መልከ መልካም ሴት ነሽና ባል ፈልገሽ አግቢ፤ ሴቶች ልጆችንና ወንዶች ልጆችን ወልደሽ ኑሪ” ብሎ አዘዛት፡፡

ጥበብን የተሞላች ማርታም እንዲህ ብላ መለሰችለት “አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ከታጨች በኋላ አንድ ሰው መጥቶ እጮኛዋን ገድሎ የታጨችይቱን ድንግል ሊነጥቅ ወይም ከእጮኛዋ ውጪ ይህቺ ሴት ሌላ ወንድ ልታገባ ሕጉ ይፈቅዳልን? ብላ ጠየቀችው፡፡ ሞቤድም  “አ…ይ በፍጹም!” ብሎ ይመልሳል፡፡ ራሱዋን ለክርስቶስ ያጨች ማርታም “እንዴት ታዲያ አንተ እጮኛዬ ያልሆነውን እንዳገባ ታዘኛለህ፤ እኔ ለአንድ ሰው የታጨው ድንግል ነኝና” አለችው፡፡ ሞቤድም በመገረም “በእርግጥ አንቺ እጮኛ አለሽን? ብሎ ይጠይቃታል፡፡ ክብርት ማርታም “እኔ ለእውነት የታጨው ድንግል ነኝ” ብላ ትመልስለታለች፡፡ እርሱም መልሶ “ለማን?” ብሎ  ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም “እርሱን ታውቀው ዘንድ አንተ የሚገባህ አይደለህም” ብላ ትመልስለታለች፤ “እሺ የት ነው ያለው?” ብሎ መልሶ ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም “ለንግድ እሩቅ ሀገር ሄዷል፤ ነገር ግን የመመለሳሻው ቀን ስለተቃረበ በቅርቡ ይመጣል፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡ ሞቤድም በመልሱዋ በመደነቅ “ስሙ ማን ይባላል? አላት፡፡ እርሱዋም “ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይባላል ብላ መለሰችለት፡፡
ይህን ሁሉ ስትናገር ግን ሞቤድ ስለክርስቶስ እየነገረችው እንደሆነ አላስተዋለም ነበር፡፡ “የት ሀገር ነው ለንግድ የሄደው የሀገሪቱ ከተማስ ማን ትባላለች? ብሎ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ እርሷም “ሀገሩ በሰማያት ነው፤ እርሱ ያለባትም ከተማ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ትባላለች” አለችው፡፡ በዚህን ጊዜ ዞሮአስትራናዊው ሞቤድ ስለጌታችን ስለመድኃኒታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ እየነገረችው እንደሆነ ተረድቶ ልቡ በቁጣ ነደደ፡፡ በቁጣም ገንፍሎ በዙሪያው ላሉት መሰሎቹ “አስቀድሜም እነዚህ ሰዎች ግትሮች ናቸው ብያችሁ ነበር ለእነዚህ ተለሳልሶ መናገር ስንፍና ነው፡፡”ብሎ ከደነፋ በኋላ ወደ እርሱዋ ተመልሶ “አንቺን ከራስሽ እስከ እግር ጥፍርሽ ድረስ በሰይፍ ቆራርጬ ከገደልኩሽ በኋላ ያኔ እጮኛሽ መጥቶ ከትቢያና ከቆሻሻ ውስጥ ፈልጎሽ በማግኘት ያገባሽ እንደሆነ እናያለን” ብሎ ዝቶ ተናገራት፡፡ ማርታም በድፍረት “በእርግጥም እርሱ በታላቅ ክብር ይመጣል፡፡ ለእርሱ የታጩትን ከትቢያ ለይቶ ያስነሣቸዋል፡፡ በሰማያዊ ጠልም ንጹሐን ያደርጋቸዋል፤ የደስታንም ዘይት ይቀባቸዋል፤ የሰርግ ቤቱ ወደሆነችው በሰው እጅ ወዳልተሠራች ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም አስገባቸዋል”ብላ መለሰችለት፡፡ እርሱም አሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ሰውነቱዋን ሁሉ በሰይፍ ቆራርጠው እንዲገድሉዋት ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡ እነርሱም እንደታዘዙት ፈጸሙባት፡፡ እርሱዋም ሰማዕትነት በዚህ ጨካኝ ዳኛ ተቀብላ በሰማያት ወደ ተሰበሰቡት በኩራት ማኅበር ገባች፡፡ እነሆ አሁን በነፍሱዋ የሚወዳትን አምላኩዋን እያመለከች ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከአእላፋት መላእክት፤ ከቅዱሳን ነፍሳት ሁሉ ጋር በፍጹም ደስታና ደኅንነት ትኖራለች፡፡”
ጥያቄው ግን እኛስ ለክርስቶስ የታጨን ደናግላን አይደለንምን? የሚለው ነው፡፡ ጥንቱን መጠመቃችን እንደ አምስቱ ደናግላን መብራታችንን ከዘይታችን ጋር ይዘን ማለትም መልካም ሥራን ከፍቅር ጋር፣ ንጽሕናን ከምጽዋት ጋር አስተባብረን በመያዝ የጌታችንን መምጣት በትጋት እንጠባበቅ ዘንድ አይደለምን?
ቅዱስ ጳውሎስ በትዳር የተሳሰሩ ባልና ሚስት በራሳቸው አካል ላይ ሥልጣን እንደሌላቸው ገልጦ ጽፎልናል፡፡(1ቆሮ.7፡4) በዚህ ምሳሌ እኛም ለክርስቶስ ታጭተናል፡፡(2ቆሮ.11፡2) ስለዚህም ይህ ሐዋርያ “ሥጋ ግን ለጌታ ነው …. ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? ብሎ ተናገረ፡፡ በመሆኑም የኃጢአት ፈቃድ ከውስጣችን መንጭቶ ሊያሳድፈን ሲነሣ ይህ አካል እኮ የኔ አይደለም፤ የብርቱው ንጉሥ የክርስቶስን አካል ነው ብለን የኀጢአትን ፈቃድ ልንቃወም ይገባናል፡፡ በዝሙት ሊያረክሰን የመጣውን ሰውንም ልክ እንደ ማርታ አካላችን የክርስቶስ እንጂ የእኛ እንዳልሆነ ገልጠን እንነገረውና እንደአመጠጡ እንመልሰው፡፡ በእግጥም በዋጋ ተገዝተናልና የእኛ አይደለንም፤ ስለዚህ በሥጋችን እግዚአብሔርን እናክብረው፡፡ (1ቆሮ.6፡13-20)ሁል ጊዜም ለአእምሮአችን ሰውነታችን የእኛ እንዳልሆነ የንጉሥ እልፍኝና የመንፈሱ ቤተ መቅደስ እንደሆነ እንገረው፡፡ ለልጆቻችንም ሰውነታችውን ከኃጢአት እንዲጠብቁ “ሰውነታችሁ የእናንተ እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ ተጠምቃችሁ በሁሉ ሥፍራ ለሚገኘው ለክርስቶስ ሆናችኋልና ጌታ በእናንተ ላይ እንዳይቆጣ ራሳችሁን ከነውር ሁሉ ንጹሐን አድርጉ” ብለን እንምከራቸው፡፡ ሰውነትን የሚያረክሱ ኃጢአቶች ምን ምን እንደሆኑ ገልጠን እናስረዳቸው፡፡
ጌታ ሆይ! ይህን ልዩ የሆነ ክብር ያጎናጸፍከን ላንተ ክብር ይሁን፤ ነገር ግን እኛ በደምህ ዋጅተህ፣ ከጎንህ በፈሰሰው ውኃ አንጽተህ የራስህ ያደረግኸውን ይህን ሥጋችንን በመተላለፋችን አሳደፍነው፡፡ ጌታ ሆይ! ለዚህ መተላለፋችን ይቅር በለን፤ በንስሐ አንጻን፣ ቀድሰንም፤ ዳግም ወደዚህ ታላቅ በደል እንዳንገባ ማስተዋልን አድለን፤ እኛም ስላንተ ያለን መረዳት ታላቅ እንዲሆንልን እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን!!! 

Saturday, March 9, 2013

ጦማችንና ምጽዋታችን ምን ይምሰል (በቅዱስ ኤፍሬም)


                         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ለቅዱስ ኤፍሬምና ለሌሎችም የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ጦም፣ ጸሎት እንዲሁም ምጽዋት ለነፍስ እንደ ብርሃን ናቸው፡፡ ዐይን ያለ ብርሃን ድጋፍ እንደማታይ እንዲሁ ነፍስም ያለእነዚህ ድጋፍ መንፈሳዊውን ዓለም መረዳት አትችልም፡፡ ጌታችንም “እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!”(ማቴ.6፡22)በማለት ብርሃን ያላቸው እነዚህን ነው፡፡ እነዚህን በአግባቡና ከከንቱ ውዳሴ ተጠብቀን የፈጸመናቸው ከሆነ መንፈሳዊ ማስተዋላችን እጅግ የጠለቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ከሰው ክብርን በመሻት የፈጸምናቸው ከሆነ እነዚሁ ራሳቸው መልሰው ያጠፉናል፡፡
እነዚህ በአግባቡ ካልተገለገልንባቸው በኃጢአትችን ላይ ኃጢአትን እንድንጨምር ያደርጉናል፡፡ ስለዚህ በእኛ ያለው ብርሃን (ጦም፣ጸሎት፤ እንዲሁም ምጽዋት) በከንቱ ውዳሴና በሌሎችም ኃጢአት ጨለማ ከሆነ በፊት ከፈጸምናቸው ኃጢአት ጋር ተደምረው እኛን ወደ ጥልቁ ጨለማ ይጥሉናል፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችን “ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ” ማለቱ፡፡ ይህን ድንቅ የሆነ አስተምህሮ እንድታስተውሉትና እኔ በትርጉሙ እንደተደነቅሁ በእናንተም ትደነቁ ዘንድ ቅዱስ ኤፍሬም ወንጌላትን ከተረጎመበት መጽሐፉ ያገኘሁትን ትርጓሜ እነሆ ብያችኋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መጽሐፉን ገዝቶ በመላክ የተባበረኝን ወንደሜን ሙሉጌታ ሙላቱን ከልቤ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡   
ጌታችን ጦማችን ምን መምሰል እንዳለበት ሲያስተምር “እንደ ጦመኛ እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡(ማቴ.6፡18)

የመጀመሪያውና ሁለተኛውን ትርጉም ጌታችን በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ የመጀመሪያው ስትጦሙ ከሰው ዘንድ ክብርንና ምስጋናን እናገኛለን ብላችሁ የምትጦሙ ከሆነ ከአምላክ ዘንድ አንዳች ዋጋ አታገኙም ሲለን ነው፤ ሁለተኛው ትርጉሙ ደግሞ በማይታየው እግዚአብሔር ፊት ጦምን የሚጦም ሰው በስውር የሚያየው አምላኩ በግልጥ ይከፍለዋል ሲለን ነው፡፡ ስለዚህ “አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡ 
እንዲህም ስለሆነ እግዚአብሔር ቃል ይህን ደግ ስጦታውን ትቀበል ዘንድ ጋብዞሃል፡፡ አእምሮህን በእግዚአብሔርዊ እውቀት የቀባኸውና ነፍስህን በንስሐ ውኃ ከኃጢአት ሁሉ ያጠራሃት ከሆነ እግዚአብሔር ለቅዱሳኖቹ ያዘጋጃትን ዐይን ያላያትን ጆሮም ያልሰማትን በረከት ይሰጥሃል፡፡ ስለዚህም በሰውነትህ ሕዋሳቶች ሁሉ ይህን እንደ መመሪያ ተቀበለህ ከነፍስህ ኃጢአትን አስወግድ፡፡ ራስህንም የቅድስናን ዘይት ቀባት፤ እንዲህ በማድረግህ የመሲሕው ክርስቶስ ወዳጅ ትባላለህ፡፡ አስከትሎም ጌታችን፡-
“እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል”(ማቴ.6፡22)አለን፡፡ እንዲህ ሲል ለአንተ ልክ እንደ ዐይኖችህ ብርሃን በሆኑት ጦምህና ምጽዋትህ ከበደልክ፤ በኃጢአትህ ምክንያት ያገኘህ ድንቁርናና አለማስተዋል እጥፍ ይሆንብሃል ሲለን ነው፡፡ ከሰው ምስጋናን ሽተህ የምትጦም ከሆነና የሰው ፊት አይተህ የምታደላ ከሆነ ለነፍስ ዐይን እንደ ብርሃን በሆኑት በጦምህና በምጽዋትህ በበደልከው በደል ምክንያት ከመጀመሪያው ኃጢአትህ ጋር ተደምሮ ቅጣትህን እጥፍ ድርብ ያደርግብሃል፡፡ ሴሰኝነትና እግዚአብሔርን መሳደብ ለከንቱ ውዳሴ ብለን በምንጦመው ጦምና በአድሎ በምንፈጽመው ምጽዋት ምክንያት በእኛ ላይ የሚሰለጥኑብን ኃጢአቶች ናቸው፡፡
 ጦምህና ምጽዋትህ ሁለት ዋጋ አላቸው፡፡ ከሰው ክብርን ሽተህ የምትጦም ከሆነ ኃጢአት በአንተ ላይ እንድትበረታ ደንቁርናህም እጅግ ጽኑ እንዲሆን እወቅ፡፡ ነገር ግን እጆችህን ለተቸገረ ሰው የምትዘረጋ ሕሊናህን ግን ወደ አምላክ የምታነሣ ከሆነ፣ እንዲሁም ስትጦም ጦምህን በእግዚአብሔር ፊት ያደረግህ እንደሆነ ከፈጣሪህ ዘንድ መልካምን ዋጋ ትቀበላለህ፡፡ ይህ ኃይለ ቃል “ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና፡፡”(ማቴ.6፡21) ብሎ ጌታችን ካስተማረው ትምህርት ጋር አንድ  ዓይነት ትርጉም ያለው ነው፡፡
ጦምና ምጽዋታችን በከንቱ ፈቃዳችን ምክንያት ለኃጢአት አሳልፎ እንዳይሰጠንና በደላችንንም እጥፍ ድርብ እንዳያደርግብን አምላካችን ይህን ማስተዋል ዘወትር ይሰጠን ዘንድ በዚህ የጦም ወር እንለምነው፡፡ ለወደደንና  በእኛ ጥቂት ድካም ዘለዓለማዊ ዋጋን ለሚሰጠን ለእርሱ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም  ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

Sunday, March 3, 2013

መልዐኩ ቅዱስ ሩፋኤል



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
“እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና።” ዕብ.፲፫፡፩
ሩፋኤል ማለት ፈታሄ መሕፀን ማለት ነው። ሣልሳይ ሊቀ መላእክት ነው። ለሄኖክ ወልደ ያሬድ 6 ዓመት በእግረ ገነት ወድቆ ሳለ ህበዓቱን ክሡታቱን አሳይቶታል። መ/ሄኖክ 8፡5
ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡ ቤቱንም በበረከት ሞልቶታል።
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች። ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡
የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ‹አባባ የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? ሀገሩን አላውቀውም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያን ‹አብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግ› አለው፡፡
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው ‹የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን ያህል እሰጥሃለሁ› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ‹እሺ ካንተ ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁና› አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም አዛርያስ ይባላል አለው፡፡ ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹አንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝ› ብሎ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡ እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው ፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡

ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚያገለግል ለመረዳት ‹ይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ‹ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል እነግርልሃለሁ› አለው፡፡
ጦብያም ‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ አድናን ‹ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል› አላት ከዚያም ጋር አያይዞ ‹ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነሱም ‹ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን› አሉት፡፡ ‹ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት ‹እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ› አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል ‹የወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ ‹መልአከ ከብካብ› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የ14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡
የ14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያን ‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡
ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2 ፡፡
ጦቢት ከእህሉ ከፍሎ ለተራበ የሚያበላ ከልብሱ ለተራቆተ ሰው የሚያለብስ እግዚአብሔርን ዘወትር የሚያመሰግን ለወገኖቹ የሚራራ አሥራት በኩራት የሚያወጣ ሰው ነበር፡፡ በመሆኑም በሥራው ሁሉ እንዲረዳው በችግሩ ጊዜ እንዲያጸናው ቅዱስ ሩፋኤል ተልኮለታል፡፡ እኛም በሕይወታችን የጐደለብንን ነገር እንዲሞላልን ጐዳናችንን እንዲያስተካክልልን ከክፉ ጋኔን እንዲጠብቀን አምላክ ቅዱስ ሩፋኤል ተለመነን ቅዱስ ሩፋኤልንም አማልደን ማለትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጳጉሜ የዘመን መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ዕለተ ምጽአትም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንሸጋገርባት ስለሆነች ከወዲሁ የቅዱስ ሩፋኤልን የመታሰቢያ በዓሉን ስናከብር በአማላጅነቱ ከቅዱሳን ኅብረት እንዲደምረን በንስሐ ታጥበን ደጅ ልንጠና ይገባል፡፡
የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ምልጃው፣ ጥበቃውና ቃልኪዳኑ ይደረግልን በረከቱ ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
ልመናው ከእኛ ከሀገራችንም ከኢትዮጵያ ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር።
“ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐና እስከ ዛቲ ሰዓት”
ወስብሔት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን ይቆየን።
አዘጋጅ ቤተማርያም