Monday, June 10, 2013

ጰራቅሊጦስ

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡ ይህ በዓል ጌታችን በሚያርግበት ጊዜ ደቀመዛሙርቱን አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እሰከ ትለብሱ ኃይለ እም አርያም ሉቃ 2449 ብሏቸው አርጎ ነበር፡፡ተናግሮ የማያስቀር ነውና ባረገ በ10ኛው በተነሣ በ50ኛው ቀን ጰራቅሊጦስን ሰዶላቸዋል ፡፡
ጰራቅሊጦስ ማለት ፡-
1/ናዛዚ (አፅናኝ) ማለት ነው ከመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች አንዱ ያዘኑትን የተጨነቁትን በተለያየ ነገር ውስጥ ገብተው ግራ የተጋቡትን ሁለ ሰለሚያጽናና ናዛዚ ይባላል ፡፡
2/ከሣቲ (ምስጢር ገላጭ) ማለት ነው የተደበቀውን የሚገልጥ የረቀቀውን የሚያገዝፍ የተሰወረውን የሚያሳይ በመሆኑ ከሣቲ ( ምስጢር ገላጭ) ይባላል ፡፡
3/መጽንኢ (የሚያጻና) በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ገብተው የሚባዝኑት ለመውደቅ የተፍገመገሙትን እንዳይወድቁ የሚደግፍና የሚያጸና በመሆኑ መጽንኢ (የሚያጸና) ይባላል ፡፡

4/ መንፅሂ (የሚያነፃ) ማለት ነው በኃጢአት የወደቁትን ከኃጢአታቸው የሚያነጻቸው ነውና መንጽሂ (የሚያነጻ) ይባላል ፡፡
5/ መሠተሰርየ (ይቅር ባይ )ማለት ነው በኃጢአት የወደቁትን የበደሉትን ተጸጽተው ንሰሃ ሲገቡ ይቅር የሚል በመሆኑ መሠተሰርይ ይቅር ባይ ይባላል ፡፡
6/መስተፈስሔ (ደስታን የሚሠጥ) ማለት ነው የተጨነቁት፤ ያዘኑትን፤ያለቀሱትን እንባቸውን የሚያብስና ደስታን የሚሰጥ በመሆኑ መስተፈሥሔ (ደስታን የሚሰጥ) ይባላል  ፡፡
በአጠቃላይ ጰራቅሊጦስ ማለት መንፈሰ ጽድቅ ፤መንፈሰ ሕይወት ፤ባሕርያዊ እስትንፋስ ፤ አካላዊ ሕይወት ፤አካላዊ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡
ለምንድን ነው  ቆይቶ በአረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን የላከላቸው ቢሉ ፡-
Ø    10ኛ መዓረግ የተቀመጥን እኛ ነበርንና ወደ ክብራችን ወደ መዓረጋችን እንደመለሰን ለማጠየቅ ነው
Ø    ዳግመኛም 10ሩን ቃሊት ቢጠብቁ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጥ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡
ሐዋርያት ድንግል ማርያምን ይዘው  በሚጸልዩበት  በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ወአስተረአይዎሙ ልሳናተ እሳት ከፋሊት ከመ እሳትዘይትከፈል በእሳት አምሳል የተከፋፈለ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው የሚያውቁት ጸንቶላቸው የማያውቁት ተገልጾሊቸው ሁሉም ከሚያውቁት ቋንቋ በተጨማሪ የማውቁት ቋንቋ ተገልጾላቸዋል ፡፡
በአጠቃላይ ሐዋርያት የሰባ ሁለት  ቋንቋ ባለቤት ሆነው በአደባባይ ስለአምላካቸው በድፍረት መስክረዋል ፤ ስለ እውነት ሲሉ በአደባባይ መከራን ተቀብለዋል ፤ ፈሪዎች የነበሩት ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታጠቃቸው እሳቱን ፤ግርፋቱን፤ስደቡን የሰይፍ ስለቱን ባለመፍራት እራሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ የላይኛው ቤታቸውን አሳምረዎል ፤ ዛሬም በክብር የወርቅ መዝገብ ላይ ሰማቸውን አጽፈዋል ፤ ክብራቸው ይህ ብቻ ሳይሆን አምላካችን በሚመጣበት ወቅት በ12 ነገደ እስራኤል ላይ ለመፍረድ ይመጣሉ፡፡

እንግዲህ በዓለ ጰራቅሊጦስ እኛ ክርስቲያኖች የምናከብረው እንደ ሐዋርያት ምስጢር እንዲገለጥልን ፤እንዲያረጋጋን ፤ይቅር እንዲለን ፤እንዲያጽናናን ፤ደሰታን እንዲሰጠን ነውና ሁላችንም ከዚህ በረከት የታደልን እንድንሆን በዓሉን በንጽሕና በቅድስና ሆነን፤ነጭ ልብስ ለብሰን፤በሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ቅዳሴ በማስቀደስ ፤በዕለቱ በጎ ስራ በመሰራት ልናከብረው ይገባል፡፡

አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን -  አሜን፡፡

አባ ኖብ

     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
  የጻድቅ ሰው ጸሎት በስራዋ እጅግ ሐይል ታደርጋለች:: ያዕቆብ 5 : 16 
  ልብ ሰባሪው ክስተት  ንግስ. . . .እና. . .አንጋሽ
አባኖብ ኤል ነሐስይ(ABANOUB EL NAHEESY) በግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስናቸው ከፍተኛ ማዕረግ ካላቸው ቅዱሳን አንዱ ነው:: አባ ኖብ በደቡባዊ ግብጽ ልዩ ስሙ ንሒስ በተሰኘ ስፍራ የተወለደ ጻድቅ አባት ሲሆን አባቱ መቁራሬ እናቱ ማርያም ይሰኛሉ፡፡ በጥር 24 ቀን የተወለደው ኖብ እጅግ በጣም መንፈሳዊ ነበርና በተወለደ በአምስተኛ ቀኑ መልአክ ሲያነጋግረው ወላጆቹ ዓይተው በአንክሮ ይጠብቁት ነበር፡፡ ገና በ12 አመቱ ወላጆቹ በሞት በመለየታቸው በ14 ዓመቱ መነኮሰ፡፡
በዘመኑ የክርስቲያን ደም እንደ ውሃ የሚያፈስ ዲዮቅልጥያኖስ የተባለ ንጉስ ነግሶ ስለነበር ክርስቲያኖች ላይ መከራና እንግልት ያበዛ ነበር፡፡ አባ ኖብም የገፈቱ ግንባር ቀደም ተቋዳሽ ነበር፡፡ አባ ኖብ ወላጆቹ በሃብት የከበሩ ስለነበሩ የወላጆቹን ሀብት ለድሆች መጽውቶ ወደ ሞትና መከራ ተሰደደ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ በአንድ ጊዜ በመጋቢት 9 ቀን ከቀኑ 3 ሰዓት አምስት ሺህ ክርስቲያኖችን አንገታቸውን ሲቆርጥ አባ ኖብ ያጽናና ነበር፡፡ በኋላም የብረት ጋን ጥደው ዘይት፣ ሰም፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል አፍልተው ከዚያ ጨመሩት፡፡ አባ ኖብም ከፍላቱ ውስጥ ሆኖ ይፀልይ ነበር፡፡ ግን እንደ አናኒያ፣ አዛሪያና ሚሳኤል /ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብድናጐም/ ምንም አልነካውም መልአኩ አዳነው እንጂ፡፡ የዚህ ጻድቅ እረፍት በ89 ዓመቱ በሐምሌ 24 ቀን ነው፡፡ ከሞተም በኋላ በሰኔ 6 ቀን ተአምራትን ሰርቶ በግንቦት 10 ቀን ማህበረ ኖብ ከተባሉት ከ350 ጋር ተሰውተዋል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአባ ኖብ ስም የተሰራ ቤተ-ክርስቲያን ብዛት 5 ነው፡፡
ስንቶቻችን ግን አባ ኖብን እናውቃቸዋለን?
በሰሜን ሸዋ በሰላሌ ሀገረ ስብከት በአሌልቱ ወረዳ በጎመን አገር እና በአብሮ አገር የሚገኘው የምዕራፈ ቅዱሳን አባ ኖብ ገዳም የተመሰረተው በ1735 ዓ.ም በዓፄ ሣህለ ስላሴ ሲሆን የሁለት መቶ ሰባ /270/ ዓመት ዕድሜ ያለው ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ይህ ቤትክርስቲያን ዕዳሜ ጠገብ ቢሆንም የጠንታዊነቱን ያህል ግን ነገሮች የተመቻቹለት አይደለም፡፡ በግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ.ም በንግስ በዓላቸው ላይ ተገኝቼ የታዘብኩትን እነሆ፡-
ችግሩ ከአባኖብ ቅዱስ ፀበል ይጀምራል፡፡ ወደ አባ ኖብ ቤተክርስቲያን ሲኬድ ቀድሞ የሚኘው ይህ ቅዱስ ፀበል ከተራራ ስር የሚፈልቅ ሲሆን ዙሪያው በትናንሽ ቁጥቋጦዎች እና ዕፀዋት የተከለለ ነው፡፡ ለመጠመቂያ ተብሎ የተሰራለት ምንም ነገር በስፍራው የለም፤ በዚህም ሳቢያ የአካባቢው ነዋሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲቀጠምበት፣ ከብቶች ሲጠጡ እንዲሁም አራዊት ሲፈነጭበት ይስተዋላል፡፡ “ከጓሮ ያለ ፀበል ልጥ ይነከርበታል” እንዲሉ ፀበል እንኳን መሆኑን የማያውቅ የአካባቢው ተወላጆች አጋጥመውኛል፡፡ ይህ ከየት መነጨ ቢሉ አንድም ስፍራው የተቀደሰ መሆኑን ካለማሳወቅ በሌላ በኩል ደግሞ ቦታው ያልተከለለ በመሆኑ ነው፡፡ አስቸጋሪውንና ድንጋያማውን ቁልቁለት አልፈን ከደረስንበት የአባ ኖብ ቅዱስ ፀበል ለቀን ወደ አባ ኖብ ቤተክርስቲያን ስናመራ የጠበቀን ሌላ ድንጋያማ ቁልቁለትና መጠነኛ ዳገት ነበር፡፡ መልከአ ምድሩ ፈፁም ግሸን ማርያምን ይመስላል፡፡ ተራራማ ነው፤ እጅጉን ለዓይን ይማርካል፡፡
ከቤተክርስቲያኑ ስንደርስ ገና ታቦት አልወጣም ነበር፡፡ የአካባቢው ጥቂት ነዋሪዎች እና ከአዲስ አበባ የመጡ እጅግ በጣም ጥቂት ምዕመናን በቤተክርስቲያኑ እንደ ለቀስተኛ ተቀምጠው የታቦቱን መውጣት በትካዜና በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ ድባቡ እጅጉን ልብ ይሰብራል፡፡ በቦታው የአባ ኖብን ዓመታዊ ንግስ ለማክበርና ከበረከታቸው ለመካፈል የተገኘው ምዕመን ብዛት በጣም በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ሁለት መቶ እንኳን አይሞላም ነበር፡፡ በከተማ ባሉ አብያተክርስቲያናት ለዓመታዊ ቀርቶ በወራዊ በዓላት መንገድ የሚዘጋው፣ ቅጥርን የሚያጨናንቀው ሕዝብ እዚህ የለም፡፡ ቆሞስም ሆነ ጳጳስ እዚህ የለም ከተማው ሙሉ የሚከተላቸው ሰባኪያን የሉም፣ ዘመሪ የለም፣ መዝሙር የለም፣ የሰንበት ተማሪ አጀባ የለም፣ ነዳይ /የኔ ቢጤ/ እንኳን የለም፡፡ የኔ ቢጤውስ ምፀዋት ከማን ሊጠይቅ ይኖራል? ሁኔታዉ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ሰው የሌለው ቦታው ስለራቀ ይሆን? ብዬ እራሴን ጠየኩ፡፡ የሚገርመው ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ሰው እየጐረፈ ያለባቸው የኩክ የለሽና የጻድቃኔ ማርያም ገዳማት ከአባ ኖብ ቤተክርስቲያን አንጻር ሲታዩ እሩቅ ናቸው፡፡ የአባ ኖብ ቤተክርስቲያን አልፈን ነው ኩክ የለሽና ጻድቃኔ ማርያም የምንሄደው፡፡
አሁን ታቦቱ ወጥቷል፤ ሊያነግስ የመጣው ሁለት መቶ የማይሞላው ሕዝብ በዝማሬ፣ በእልልታና በጭብጨባ አጀባው፡፡ የአባ ኖብ አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር ድንቅ ነው፤በጥቂት ሰዎች ደማቅ በዓል ተከበረ፡፡ የአባ ኖብ ገድል አስደናቂ ነው፤ ነገር ግን ገድላቸው እንኳን ተጽፎ የምናገኘው በልሙጥ ወረቀት በእጅ ጹሑፍ ነው፣ አልታተመም መታተሙም ይቅርና በኮምፒውተር አልተተየበም፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ እንደነገሩኝ ገድሉን እንዲት ሴት አሣትመዋለው ብለው ወስደው ከጠፉ በኋላ በጾምና በፀሎት በተዓምር ሊመለስ ችሏል፡፡ የካሕናቱ ኑሮ ያሳዝናል አርሶ አደሮች ስለሆኑ ቀድስው ወደ እርሻ፣ ከእርሻ ወደ አገልግሎት ይባክናሉ፡፡ የእንግዳ አቀባበላቸው ግን ድንቅ ነው፡፡ ከማዕዳቸዋ ሳይሰስቱ አርደው አብልተውናል፡፡ በጣም የደነቀኝ ለቤተክርስቲያኑዋ መደገፊያ ገንዘብ ሲሰበሰብ ካሕናቱም ከሌለው ምዕምን እኩል ይለግሱ ነበር፡፡ በከተማ ያልተዘብኩት አርአያ የሚሆን ልዩ ክስተት ነበር ለኔ፡፡ ጥንግ ድርብ፣ ያማረ መስቀልና መቋሚያ፣ መጎናፀፊያ፣ ጥምጣም፣ መጫሚያ ወዘተ . . .ሳያምራቸው እጃቸውን ለልግስና ይዘረጋሉ፣ ሰጥተው አርአያ ይሆናሉ ድንቅ አይደል ታዲያ ይሔ?
ሌላው የአባ ኖብ ቤተክስርቲያን ችግር መብራት ነው፡፡ በቦታው ጄኔሬተርም ሆነ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኃይል ማመንጫ የለም፡፡ ይህም አልግሎቱን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ቦታውን የሚረግጠው ጥቂት ምዕመን ለዓመት የሚበቃ ጧፍ የሚያበረክት ቢሆንም ችግሩን ግን አቃሎታል ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅዳሴ ጊዜ ወሳኝ የሆኑት እንዲሁም መገበሪያዎች እጣን፣ ዘቢብ፣ጧፍ፣ እና የመሳሰሉት በበቂ ሁኔታ ስለሌሉ ቅዳሴ እንዲታጐል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እና ከእኔ፣ ከአንቺ እና ከአንተ ምን ይጠበቃል? ኦርቶዶክስ የሆነ ምላሹ ምንድነው? የተዋህዶ ልጅ ምን ይጠብቃል? አበው “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ይላሉ፡፡ ኦርቶዶክስ የሆነ ሁሉ ልቡን ቢመልስ፣ ቢተባበር፣ ሐዘን ቢሰማው ይህን ታላቅ መንፈሳዊ ስፍራ መለወጥ ፣ ችግሩን መፍታትና ላላወቁት ማሳወቅ ይችላል፡፡
ማንም መኖሪያ ቤቱ ሲበላሽ፣ ሲራቆት፣ ሲፈርስ፣ የሃዘን ድባብ ሲያጠላበት የሚወድ የለም፡፡ ቤተክርስቲያንስ መንፈሳዊ ቤታችን አይደለችም? ጉዳቷ ያስደስተናል? በፍፁም፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዳይ የረሳችን ጉዳይ ከሆነ እንተባበር፡፡ እኔ እጅግ ኃጢያተኛው ሰው ስሆን ይህን ተናግሬያለው፡፡
ቦታውን ለቀሪው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ለማሳወቅ ይረዳ ዘንድ እንዲሁም በችግሩ ዙሪያ ለመወያየት በቅርቡ መንፈሳዊ ጉዞ ወደ አባ ኖብ ቤተክርስቲያን ለማድረግ ሐሳቡ አለ፡፡ ሐሳቡ ወደ ተግባር የሚለወጠው የእኔ፣ የአንተና የአንቺ በጐ ፍቃድ ሲታከልበት ነው፡፡ ስለዚህ አስተያየታችሁን ስጡን፣እንብዛ፣እንተባበር፣ለስጋ ያልሆነ የነፍስና የጹደቅ ስራን በጋራ እንስራ በውጭም በአገር ውስጥም ያለው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጅ በጋራ ከተነሳ የከበደው እንዲቀል፣ ተራራው እንዲናድ እናምናለን፤ መንፈሳችን ከእውነተኛው አምላክ ነውና፡፡
በአጠቃላይ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃን የምትሹ እንዲሁም በጉዞው ላይ ተሳትፋችሁ ቦታውን ማየት የምትፈልጉ በ0911-33-43-47 ልታገኙን የምትችሉ መሆኑን እያሳወኩ በቀጣይ መደረግ ያለባቸውን ተግባራት ከደብሩ አስተዳዳሪና ከሌሎች ደጋፊ አካላት ጋር በመወያየት የማሳውቃችሁ መሆኑን እገልፃለሁ፡፡
የአባ ኖብ ቤተክርስቲያን የተመረጡ ብቻ የሚያዩት እና በነብር የሚጠበቅ ነው፡፡ እኔ በኃጢያት ያደፍኩ ሲሆን የመቅደላዊት ማርያም አምላክ መረጠኝ፣ እኔ ኃጢያተኛው ይህን ብያለው የአባታችን የአባ ኖብ ረድኤት፣ በረከት፣ ምልጃ ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን!
እግዚአብሔር ኃይል ነው!
ክብር ለድንግል ማርያም!
እባካችሁ ይህን ጹሐፍ ለሌሎች በማስተላለፍ (Share በማድረግ)ክርስቲያናዊ ግዴታዎትን ይወጡ!!!
 ፀሐፊ  ደረጄ ስዩም /ሚማገኤል/