Friday, December 21, 2012

ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ

           በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ዮሐንስ ማለት ፍሰሓ ወሐሴት ሠላም ርህራሄ ወሳህል ማለት ነው። ወልደ ነጎድጓድ፣ አቡቀለምሲስ፣ ነባቤ መለኮት፣ ታዖሎጎስ ይለዋል፡፡ “ቃዳሚሁ ቃል ውእቱ” ብሎ ምስጢረ ሥላሴን አምልቶ አስፍቶ ይናገራልና፡፡ ፍቁረ እግዚእ ይለዋል፡፡ “ዝኩ ካልዕ ረድዕ ዘያፈቅሮ እግዚእ ኢየሱስ” ይለዋልና፡፡ ዮሐንስ 21፡7 መውደድንስ ሁሉንም ይወዳቸው የለምን ቢሉ የርሱ የተለየ ነውና፡፡ ከቶማስም የሱ መወደድ ይበልጣል፡፡ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን ቢዳስሰው እጁ ከእሳት እንደገባ ጅማት ተኮማትሯል፡፡ እርሱን ግን በከናፍሩ ቢስመው በጭኑ ቢያስቀምጠው ምንም ምን አልሆነም ::
  ንጹህ ወድንግል ይለዋል፡፡ ጌታን ከመውደዱ የተነሳ ጌታም እናቱን እነዃት እናትህ ሲል ድንግል ማርያምን በሱ በኩል ተሰታናለች፡፡ እኛም ዛሬ ልጆቿ ነንና ደስ ይበለን ይበላችሁ የድንግል ማርያም የአስራት፣ የተስፋና የስስት ልጆች፡፡ ዮሐንስ 19፡26፡፡ ዮሐንስ ሀገሩ ገሊላ አውራጃ ሲሆን ከታላቅ ወንድሙ ከያዕቆብና ከአባቱ ከዘብድዮስ ጋር ዓሣ እያጠመደ ይኖር ነበር። እናቱ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ስትሆን ማርያም ትባላለች።

     ዮሐንስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን በሕይትም በኑሮም ጌታ ስለሚመስል (ፍቁረ እግዚእ) ይባለል። ነገረ መለኮትን በበለጠ ከሌሎች አምልቶ አስቶ በጥልቀት በማስተማሩ ነባቤ መለኮት (ታዖሎጎስ)ተሰኝቷል። ስለጌታም ባለው ቅናት ባሳየው የሀይል ሥራ በኦኔርጌስ (ወልደ ነጎድጓድም) ተብሏል። ፍጥሞ በምትባል ደሴት በራዕይ መጻእያትን በመግለጡ ባለራዕይ (በግሪክ አቡቀለምሲስ) ይባለል። በዕለተ ዓርብ በመስቀል ሥር ተገኝቶ የጌታን መከራ መስቀል በማየቱ ፊቱ በሀዘን ስለተቋጠረ ቁጽረ ገጽ (ፊቱ በሀዘነ የተቋጠረ) ስምም ተሰቶታል። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የፋሲካን እራት ያዘጋጀ አንካሳን የፈወሰ ታለቅ ሐዋርያ ነው። (ሊቃስ 22፡8) እስከ መስቀል አምላኩን ተከትሎ እመቤታችንን በአደራ የተረከበ ባለአደራ ሐዋርያ ሲሆን ከጰራቅሊጦስ በዓል በኋላ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋራ በኢየሩሳሌም በአንጾኪያ በሎዶቅያ በእስያ ከተሞች በተለይ በኤፌሶን በአሁኑ ቱርክ አስተምሯል። (ዮሐ.19፡26) በወጣትነት ዕድሜው ተጠርቶ በዕለተ ዓርብ የጌታን መከራ እያሰበ ያነባ የነበረ በፍቅር በታማኝነት እስከመጨረሻ ድረስ የጸና ከጌታ ያልተለየ ወንጌላዊ ሲሆን ወንጌልን ጨምሮ 3 መልዕክታትን የጻፈ እንዲሁም በበፍጥሞ ደሴት ራዕይ የጻፈ ታላቅ ሐዋርያ ነው።
ከወንጌላዊው፣ ከሐዋርያው፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ረድኤትና በረከት ይክፈለን አሜን። !!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን አሜን።

No comments:

Post a Comment