Thursday, July 4, 2013

አቡነ ተክለ ሐዋርያት ዘደብረ ጽሞና ካልዕ


  
        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
  አቡነ ተክለ ሐዋርያት ዘጽሞና ካልዕ ዘያበርህ አዕፋሩ የተባሉት ደገኛ አባት ትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ደብረ ጽሞና የሆኑት በአጼ ዘርዓያዕቆብ የነበሩ በአባ አትናቴዎስ መቃብር ላይ ሄደው አጥብቀው የጸለዩ ፯ አክሊል የወረደላቸው ጌታ ተገልጾ ከጊዮርጊስና፤ ከዮሐንስ መጥምቁ ጋር ነው ክፍልህ ያላቸው ጻድቅ ናቸው። በዚህም ሙታን የተነሱላችሁ ብዙ ተዓምር ያደረጉ ብርሃን የወረደላቸው ታላቅ ጻድቅ ናቸው። ሲጸልዩ ነፍሴ ፫ (ሦስት) ነገርን ትፈልጋለች ይሉ ነበር። 1 ከዚህ ዓለም ሀሜት መራቅን 2 ክፉ ነገር ከማየት መራቅን 3 ከንቱ ነገር ከመስማት መራቅነ እያሉ ይማጸኑ ነበር። እንዲህ እያሉ በሚጸልዩበትም ወቅት መልአኩ መጣና ወደ በረሃ ምንም ሰው ወዳሌለበት ሂድ አላቸው። እንዳላቸው ወደ ምድረ ሐጋይ በዝዋይ አድርገው አልፈው ከባሕር ውስጥ ባለ ዋሻ ገቡ። ከዚያ ገብተው ይጸልዩ ጀመር። በዚያም ብርሃን ወርዶላቸው ነፍሴ ሰውነቴን ተጸየፈች እያሉ ይጸልዩ ጀመር። በዚያን ጊዜ ጌታ ተገልጾላቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ለኢትዮጵያ መኩሪያ ነህ ሲል ታሪካቸውን በብጹህ አቡነ ባስልዮስ ትዕዛዝ በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በ1945 እና 1946 ዓ.ም በወጣ ታሪካቸው በስፋት ተመዝግቦአል። በመጨረሻም አባታችን አቡነ ተክለ ሐዋርያት ሕዳር 27 ቀን በክብር አርፈዋል። መላዕክትም 5 ሆነው ወርደው ቀብረዋቸዋል። መጀመሪያ በደብረ ብርሃን ተቀብረው ከ13 ዓመት በኋላ በምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ስር በምትገኘው ወደ ደብረ ፅሙና አፅማቸው መጥተዋል።

አባታችን አቡነ ተክለሐዋርያት ከሌሎች ፃድቃን ለየት የሚያደርጋቸዉ አንድ ዓመት የታመመ ህመምተኛ ሥጋወደሙ ወስዶ (ተቀብሎ ) ከህመሙ የተነሳ አስመለሰዉ ዲያቆኑ ያስመለሰዉን በእቃ ተቀበለዉ ። ደምና መግል የተቀላቀለበት ነበር አባታቺን አቡነ ተክለሐዋርያት ሰለ ስጋወ ደሙ ክብር በእለተ አርብ ሃሞትና ሆምጣጥዉን እንደ አጠጡት የወልድን የመስቀሉን መከራ አስበዉ ፈጣሪአቸዉን ከመዉደዳቸዉ የተነሳ ያንን ያስመለሰውን ግጥም አደርገዉ ጠጡት በዘያን ጊዜ ጌታችን ወደሳቸዉ መጥቶ ወዳጄ ተክለሐዋርያት ሆይ በሰዉ ፊት እዳከበርከኝ በሰማያዊ መላአክትና በምድራወዊ ፃድቃን ሰማእታት ፊት አከብርሃለሁ ብሎ ጣቱን አንስቶ በጣቱ ፊታቸዉን በባረከዉ ግዜ ፊታቸዉ እንደ ፀሐይ አበራ በፊቱም ላይ ያለዉ የፀሐይ ብረሃን በምድር ላይ ሁሉ ታየ ።
አንድ ዶሮ በሰበት ቀን ከባለቤቱ አምለጦ መጥቶ አስጥለኝ ብሎ ለመናቸዉ አሳቸዉ የዶሮዉን ባለቤት ሰንበት ነዉ አትረደዉ ቢሉት አልሰማ ሰላላቸዉ ያላቸዉን ሸማ (ልብስ ) ሰጥተዉ ከመታረድ አድነዉታል በስእሉ ላይ አንደሜታየዉ ።
ክብር ይግባዉና የኛ አምላክ የቅዱሳንን ሥራ አይተን ሰምተን አንብበን እነሱ የሰሩትን መስራት ባንችል እንኳን ተስፋ እድንቆርጥ አልተወንም ምንም እንኳን እነሱ የተጋደሉትን ተጋድሎ መጋደል ባንችል ደካሞች ብንሆን ይልቁንም እነሱን ብንቀበል በነሱ ስም አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ዉሃ ብንሰጥ የነሱን ዋጋ እደሚሰጠን ቃል ገባልን አንጂ ማቴ ፲ ፬፩ አቡነ ተክለ ሐዋሪያት መድህን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ግንባራቸው ላይ ጸሐይ ያተመባቸው ታላቁ አባት ናቸው ቅድስት ቤተክርስቲያንም ወር በገባ በ27 አስባቸው ትውላለች፡፡ የጻድቁ በረከታቸው ይደርብን አሜን
†እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።† ዕብ. ፲፪:፩-፪
  የአባታችን አቡነ ተክለ ሐዋርያት ረድኤታቸው፣ ጸሎታቸው፣ ቃል ኪዳናቸው አማላጅነታቸው ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን።
አሜን†††

 ዋቢ መጽሐፍት፡-
 የኢትዮጵያ ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ፲፱፻፪ ዓ.ም ገጽ ፶፩-፶፪ (51-52)
 ሽንቁሩ ሚካኤል ከሚል መጽሐፍ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡