=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅ የተወለዱት በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሸዋ (መርሃ ቤቴ) ነው:: ወላጆቻቸው ዘካርያስና ሶፍያ እግዚአብሔርን የሚፈሩ: እመ ብርሃንን የሚወዱና ለነዳያን የሚራሩ ነ...በሩ::
+ደጉ ዘካርያስ መስፍን ሲሆን እርሱ በሌለበት የሸዋ ገዢ ሊያገባት በመሞከሩ ቅዱስ ገብርኤል ቀስፎታል:: ሕዝቡ ገዢነቱን ለዘካርያስ ሰጥተውታል:: ከቆይታ በሁዋላም ድንግል ማርያም የተባረከ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን "ዮሐንስ" አሉት:: በሒደት ግን ዘዮሐንስ (የዮሐንስ) ተብሏል::
+ቅዱሱ ዘዮሐንስ እስከ 7 ዓመቱ ድረስ በእናቱ እቅፍ ቆይቶ ወደ ትምሕርት ገብቷል:: ጸጋ እግዚአብሔር ጠርቶታልና በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አደን ይወድ ነበርና ሊያድን ሲወጣ 'ብርሕት ደመና' ድንገት ነጥቃ ከኢትዮዽያ (ሽዋ) ወደ ኢየሩሳሌም (ጐልጐታ) አደረሰችው::
+ደስ ብሎት ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ደመናዋ ወደ ሃገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በሁዋላም ከሰማይ ነቢዩ ኤልያስና መጥምቁ ወርደው ባረኩትና "ክፍልህ ከእኛ ጋር እንዲሆን መንን" አሉት::
+ዘዮሐንስ ወላቹንና ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ (ዲቁና ነበረውና) 25 ዓመት ሞላው:: ያን ጊዜ ወላጆቹ "እንዳርህ" ቢሉት "የለም! አይሆንም" አላቸው:: አርጅተው ነበርናስ ለእነርሱ ዕረፍት ጸለየ:: ፈጣሪም ሰምቶታልና 2ቱም በክብር ተከታትለው ዐረፉ::
+ሕዝቡ በወላጆቹ ፈንታ "እንሹምሕ" ቢሉት "እንቢ" ብሎ ወርቁን: ብሩን: ርስቱን: ቤቱን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ:: ጊዜው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባረፉ በ50 ዓመት አካባቢ ሲሆን አባ ሕዝቅያስ አበ ምኔት ነበሩ:: (ከዚህ በሁዋላ አንቱ እያልን እንቀጥል)
+አባ ዘዮሐንስ ለ7 ዓመታት ገዳሙን ረድተው መነኮሱ:: እንደ ልማዱ ደመና ነጥቆ ወስዷቸው ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ዻዻሳት ቅስና ተቀብለዋልና በደብረ ሊባኖስ ለ25 ዓመታት አገለገሉ:: ቤተ መቅደሱን በመዓልት 7 ጊዜ በሌሊት 7 ጊዜ ያጥኑ: እልፍ እልፍ ይሰግዱ: ተግተው ይጸልዩ: ይታዘዙም ነበር::
+ከዚያም በፈጣሪ ትዕዛዝ በትግራይና በሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ወንጌልን ሰብከዋል:: እድሜአቸው 70 በሆነ ጊዜ ወደ ጌታ መቃብር (ጐልጐታ) ሔደው ተሳልመው በእርሱ (በጌታ) ትዕዛዝ ወደ ደራ (ጣና ዳር) ተመለሱ::
+በአካባቢውም ገብርኤልና መስቀል ክብራ የሚባሉ ደጋግ ባለ ትዳሮች ነበሩና በእንግድነት ከቤታቸው አደሩ:: ቤቱ በቅጽበት በበረከት ሞላ:: እነርሱም የጻድቁን አምላክ አመሰገኑ::
+ቀጥሎም በመስቀል ክብራ መሪነት ጻድቁ ዘዮሐንስ ወደ ክብራን ገብርኤል ደሴት ገቡ:: (በነገራችን ላይ ደሴቱ ክብራን የተባለ መስቀል ክብራ በምትሰኘው ደግ ሴት ስም ነው:: እርሷና ባሏ ገብርኤል የተቀደሱ ሰዎች ነበሩና)
+ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ ወደ ደሴቶቹ (ክብራንና እንጦንስ ኢየሱስ) እንደ ገቡ ደሴቶቹ በግማሹ የስውራን ቤት: እኩሉ ደግሞ የጣዖት (ዘንዶ) አምላኪዎች መኖሪያ ነበር:: ጻድቁ ክብራን ገብርኤልንና እንጦንስ ኢየሱስን የመሠረቱት በ1315 ዓ/ም አካባቢ በዐፄ ዓምደ ፅዮን ዘመን ነው:: በአካባቢው ዘንዶ ይመለክ ነበርና ያንን በጸሎታቸው አጥፍተው ሕዝቡን አጥምቀዋል::
+በዚያም ገዳሙን የወንድና የሴት ብለው ከፈሉ:: የወንዶች ክብራን ሲሆን ሴት አይገባበትም:: አበ ምኔቱም ራሳቸው ጻድቁ ነበሩ:: የሴቶች እንጦንስ ኢየሱስ ከካህናት በቀር ወንድ አይገባበትም:: እመ ምኔቷም እናታችን ቅድስት ክብራ (መስቀል ክብራ) ሆነች::
+ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ በክብራን ለ35 ዓመታት ተጋድለዋል:: ለጸሎት ከመቆማቸው ብዛት እግራቸው አብጦ: ቆሳስሎ ነበር:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ይገለጽላቸው: ያነጋግራቸውም
+እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርተው: ለወንጌል እንደሚገባ ኑረው: በተወለዱ በ105 ዓመታቸው ዐርፈዋል:: ጌታችንም በስማቸው ለተማጸነና ገዳማቸውን ለሳመ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ልደታቸው ደግሞ ሕዳር 13 ቀን ይከበራል:: ገዳማቸው (ክብራን ገብርኤልና እንጦንስ ኢየሱስ) ድንቅ ነውና እንድታዩት ተጋብዛቹሃል::