Monday, November 24, 2014

አባ ሕርያቆስ

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አባ ሕርያቆስ በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይመልሳልና ብለው ግብረ ገብም ከሆነ ይሾም ብለዋል፡ በጸሎቱ ይጠብቃል..

''ሕርያቆስ ማለት'' :- ህሩይ ማለት ነው ፡ ለሹመት መርጠውታልና: አንድም ረቂቅ ማለት ነው ምሥጢረ ሥላሴን ይናገራልና ፡ ከሊቃውንትስ ምሥጢረ ሥላሴን የማይናገር የለም ብሎ ከሁሉ ይልቅ እሱ አምልቶ አስፍቶ አጉልቶ ይናገራልና አንድም ፀሐይ ማለት ነው፡ አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ ብሎ ጽፏልና : አንድም ብርሃን ማለት ነው፡ የምዕመናንን ልቦና በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና ፡ ዘአብርሃ መንበረ ማርቆስ በብርሃን እንዲል ፡አንድም ንብ ማለት ነው፡ ንብ የማይቀምሰው አበባ የለም እሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለም፡ይህም እንደምን ነው ቢሉ፡ ሐዋርያት የተማረ ግብረ ገብ ይሾም ብለው ሥራት ሰርተዋል፡ይህስ አይደለም ሁለቱን አስተባብሮ የያዘ አይገኝም ብሎ የተማረ ከሆነ ይሾም ብለዋል::በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይመልሳልና
ብለው ግብረ ገብም ከሆነ ይሾም ብለዋል፡በጸሎቱ ይጠብቃል: በትሩፋቱ ያጸድቃል:ትምህርቱን ውሎ አድሮ ያደርገዋልና ብለው ሾሙት ፡ይህም አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ግብረ ገብ ነው ፡ ቢማርም ለጸሎት ለቅዳሴ ያህል ነበር፡በብህንሳ በ10000  መነኮሳት በ10000 መነኮሳይያት ተሹሟል በብዙም መሾም ልማድ ነው፡፡

አባ ሆርና አባ ኤስድሮስ በ1000 አባ አሞን በ3000 አባ ጳኩሚስ በ6000 አባ ሰራብዮን በ10000 ተሾሙ:ይህችም ብህንሳ ቅድመ ትሰይም አርጋድያ ወድህረ መኑፍ ይላል: ብዙ ግዜ ስመ ተፋልሶ አግኝቷታል :በፊት አርጋድያ ኋላም መኑፍ ተብላለች ዛሬም ብህንሳ ትባላለች:ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ናት:እንደ ዘጌ እንደ ቆራጣ እንደ ቀንጠፋሜእርሱም ግብረ ገብ ነውና ሥራት ቢያጸናባቸው ይጣሉታል:ያልተማረ ነውና ይንቁታል:ከመጠምጠም መማር ይቅደም እንዲሉ ከመሾም መማር አይቀድምምን እያሉ; እሱ ግን ወእቀውም ዮም በትህትና ወበፍቅር ብሎ እንዲያመጣው: እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር እና በትህትና ጸንቶ ያስተምራቸው ነበር::


ከዕለታት ባንዳቸው በምን ምክንያት እንሻረው አሉ:ቀድሰህ አቁርበን ብለን በዚህ ምክንያት እንሻረው ብለው መክረው ቀድሰህ አቁርበን አሉት: የሱ ግን ተምኔቱ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤቴ ምስጋና እንደ ባህር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግበው እንደመጠጥ ጠጥቼው እንደ ልብስ ለብሼው እያለ ይመኝ ነበር፡ ቅዳሴ ገብቶ ሥርዓቱን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግር የማንን እናውጣለት እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ የለመኗትን የማትነሳ የነገሯትን የማትረሳ እመቤታችን ገልጻለት ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ብሎ ወይእዜኒ ንሰብሐ እስኪል ድረስ ሰተት አድርጎ ተናግሮታል:የሚንቁት የሚጠሉት ይህ የነገሩትን ቀለም እንኳን አከናውኖ መናገር የማይችል ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እደርሳለው ብሎ አገኝ አጣውን የቆጥ የባጡን ይቀባጥራል: ብለው አደነቁበት የሚወዱት የሚያከብሩት ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲ ያለ ምሥጢር ከእሩቅ ብዕሲ ይገኛልን ብለው አደነቁለት፡ ወዲያው የሚወዱት የሚያከብሩት ጽፈን ደጉሰን አንይዘውምን አሉ፡ የሚንቁት የሚጠሉት ደግሞ ማን ተናገረው ብለን እንይዘዋለን አሉ እንደ ልማዱ አድርገን አንይዘውም አሉ:: ለሃገራቸው እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደሆነ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል: ከእሳት ደህና የወጣ እንደሆነ ከውሃ ይጥሉታል ከውሃ የወጣ እንደሆነ ከህሙም ላይ ይጥሉታል ድውይ የፈወሰ እንደሆነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል፡፡


ይህንንም ቅዳሴ ማርያም ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ላይ ጣሉት ከእሳት ደህና ወጣ፡ ከውሃ ጣሉት ከውሃ ደህና ወጣ፡፡ ከህሙምላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ: ይልቁንም ሙት አስነስቷል፡፡ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ጽፈው ደጉሰው ይዘውታል:በጥራዝም 14ኛአድርገው ጠርዘውታል: ከ14ቱ ቅዳሴም ተአምራት ያልተደረገበት የለም፡ የቀደሰበት ምን ቀን ነው ቢሉ፡ ከእመቤታችን ከ 33ቱ በዓላት ባንዱ ቀን ነው፡ አንድ ባህታዊ ከባለሟልነት የተነሳ ከ33ቱ በዓላት ማንን ትወጃለሽ ብሎ እመቤታችንን ጠየቃት:ኪዳነምህረትን ልደታን አስተርአዮን ፍልሰታን አለችው፡ ከሊህ ከ4ቱስ ማንን ትወጃለሽ ቢላት ከጠባብ ወደ ሰፊ: ከጨለማ ወደ ብርሃን: የወጣውበት ነውና ልደቴን እወዳለው አለችው፡ ቀድሞ እነ ሳልወለድ እናትና አባቴን መባችሁን አንቀበልም ብለው አዝነው ተክዘው ነበር፡ የነሱ ሃዘን ሃዘኔ ነውና እኔን ከወለዱ በኋላ መባቸውን ተቀብለዋቸው ደስ ብሎዋቸዋል: የነሱ ደስታ ደስታዬ ነውና እንዳለችው የልደታ እለት ነው የቀደሰው::እሱስ ማንን ሊቀድስ ኖሯል ቢሉ ከቅዳሴ ሐዋርያት ሌላ አያቅም ነበርና ቅዳሴ ሐዋርያትን፡ ይህስ አይደለም ለእመቤታችን ቅዳሴ ሐዋርያት ምኗ ነው: ምን ቢቸግር ተበድሮ ጋሬዳ እንዲሉ ቅዳሴ እግዚእን ሊቀድስ ነበር ስሟን ባያነሳ እምድንግል ተወሊዶ ከመ ፈቃድከ ይፈጽም ብሎ በምሥጢር ያነሳታል::


ከባህር ወዲህስ ማን አምጥቶልናል ቢሉ ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ መደባይ ታብር በሚባል ቦታ ይኖር ነበር እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን ከሶርያ አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ በደመና ጠቅሳ ያሬድ ካለበት አድርሳ አንተ ውዳሴዬን አንተ ቅዳሴዬ ንነግራችሁት በዜማ ያድርስ ብላቸው እነሱም ነግረውት በዜማ አድርሶታል፡፡ ከዚሁ አያይዞ 13ቱንም ቅዳሴ በዜማ ደርሷል: ይህም ሊታወቅ ሥረይ በቅዳሴ ማርያም ይበዛል::ከተከዜስ ወዲህ ማን አምጥቶልናል ቢሉ ሳሙኤል ትውልደ ጌዴዎን ዘገበዘ አክሱም ይለዋል እሱ አምጥቶልናል እሱም ይሄን እየደገመ ሲሄድ ክንድ ከስንዝር ከመሬት መጥቆ ይሄድ ነበር: ከዕለታትም በአንዳቸው ውሃውን ቢባርከው ህብስት ሆኖለት ተመግቦ ምዕመናንን መግቧቸዋል፡፡ እመቤታችንም የፍቅር ምልክት ሁለት ንዋያት ሰታዋለች ነጭ እጣን እና እንቁ ነው፡፡ ከዛም አያይዛ ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ ጋራ አንድ አድርጎ የሚደግመውን ሰው አንተ ከገባህበት ውሳጤ መንጦላዕት አገባዋለው:ብላ ተስፋውን ነግራዋለች:: ይህውም ሊታወቅ ዛሬ በዋልድባ ያጠና በቃሉ: ያላጠና በመጽሃፍ ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል የለም:ይህም ተስፋ ውዳሴዋን ከቅዳሴዋ ጋር አንድ አድርጎ ለምደግም ሰው ሁሉ ነው:እንጂለሱ ብቻ አይደለም:አንድ ባህታዊ ከምስጋናሽ ሁሉ ማንን ትወጃለሽ ብሎ ቢጠይቃት ልጄ ዳዊትን አቡነ ዘበሰማያትን ቢደግሙለት እንዲወድ እኔም ውዳሴዬን ቅዳሴዬን ቢደግሙልኝ ወዳለሁ ብላዋለች ::
አባ ሕርያቆስ ተሹሞ ሳለ ብዙ ድርሳንን ደርሷል ብዙ ተግሳጽ ጽፏል ከብዙውም አንዱ ይህ ቅዳሴ ማርያም ነው እረፍቱ በጥቅምት 2 ነው::
አኮቴተ ቁርባን ዘእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደርሰ በመንፈስ ቅዱስ አባሕርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሃገረ ብህንሳ ጸሎታ ወበረከታ የሃሉ ምስለ ኩሎሙ ህዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም አሜን፡፡
ኃጥያታችንን ከሚያስተሰርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን አሜን !!!!!: ምንጭ ፡- ቅዳሴ ማርያም አንድምታ

Monday, November 3, 2014

አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)


            በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
*እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል!
*ቅዱሱ አባታችን:- "ቡላ-የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን::
*ዳግመኛም "አቢብ-የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን::
+እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን::
*አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
*ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ!
*ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ!
*የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን::
+" ልደት "+
=>አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ::
+በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ: ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"
+" ጥምቀት "+
=>ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በሁዋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኩዋን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ 'አጥምቀው' አለችው::
+ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ: እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::
+" ሰማዕትነት "+
=>የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገውት ድንገት ሕዳር 7 ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ::
+በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ 18 ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል::
+" ገዳማዊ ሕይወት "+
=>ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በሁዋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ::
+ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው::
+" ተጋድሎ "+
=>አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል: ፊቱን በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል: ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል::
+በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር::
+የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነሕና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን" አለው::
"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ:
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ:
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል::
+" ዕረፍት "+
=>አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ10 ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::
+ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ 'አምላከ አቢብ ማረኝ' ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::
+" ታላቁ አባ ዕብሎይ "+
=>ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው:: ብዙ መጻሕፍት 'ርዕሰ ገዳማውያን' ይሉታል:: የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ በመሆኑ በዕለተ ዕረፍቱ (የካቲት 3 ቀን) እንመለከተዋለንና የዚያ ሰው ይበለን::
+" ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት "+
=>ከሁሉ አስቀደሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ (አድናቆት): ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::
+ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘ) ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ እንኩዋን የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ-የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: (መዝ. 78:3)
+እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና 300 አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::
+በወቅቱ የክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር::
በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::
+ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር::
+እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::
+ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ ወደ ሃገረ ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ::
+በፍጻሜውም መኮንኑ ቅዱስ ዮልዮስን ከቤተሰቡና ከ1,500 ያህል ተከታዮቹ ጋር: 2ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል::
=>አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን::
=>ጥቅምት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
2.አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
4.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
5.ቅዱሳን አሞኒና ሙስያ (የታላቁ ዕብሎ ወላጆች)
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
6.ታላቁ አባ ቢጻርዮን
=>+"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ:: መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል:: +"+ (ማቴ. 16:24)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
  
writing by dn yordanos abay