ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሁለት ዓመት የዕሥር ጊዜውን ጨርሶ ከሮም ከተማ ከወጣ በኋላ ጥቂት የአገልግሎት ጊዜ ሲያገኝ በ66 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የጢሞቴዎስ መልእክት ጽፏል፡፡
“እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል” እንደሚባለው በግብር በቃል
በሐሳብ ሥነ ፍጥረትን ከፈጠረበት አምላካዊ ጥበቡ ይልቅ ሰው በወደቀ ጊዜ ከወደቀበት የተነሣበት የአምላክ ሰው መሆን
ምስጢር ታላቅ በመሆኑ ይኸ ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ተብሎ ተጽፏል፡፡ “በሥጋ የተገለጠ በመንፈስ የጸደቀ
ለመላእክት የታየ በአሕዛብ የተሰበከ በዓለም የታመነ በክብር ያረገ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠባብ ደረት በአጭር
ቁመት ተወሰኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ታላቅ ነው፡፡
አዳም የ30 ዘመን ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በገነት 7 ዓመት ከኖረ በኋላ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ልጅነቱን ቢያጣም
ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃደ ሥጋን በጾም ድል ነሥቶ ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር አስተምሮ ስስትን ድል አደረገ፡፡
የአዳም እግሮች ወደ ዕፀ በለስ ተጉዘው በእጁ ቆርጦ ቢበላ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ተጉዞ እጆቹና
እግሮቹን ተቸንክሮ ተሰቅሎ አዳነው፡፡ አዳም ከጸጋ ልብሱ ቢራቆት ኢየሱስ ክርስቶስም የብርሃን ልብሱ እንዲመለስለት
እርቃኑን ሆኖ ተሰቀለ፡፡ ይህ ሁሉ የማዳን ሥራው በሥጋ በመገለጡ የተደረገ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ የአዳምን
ሞት ወሰዶ የእሱን ሕይወት ሰጥቶ የመቃብርን ኀይል ሽሮ ሞትን ድል አድርጎ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ያለጥርጥር ታላቅ
ነው፡፡
የእግዚአብሔር ምስጢሩ ታላቅ መሆኑን ቅዱስ አትናቴዎስ ሲያስረዳ “ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት
መረዳት /ማወቅ/ የልብሱን ጠርዝ ብቻ እንደማወቅ ነው፡፡ ስለ ምስጢረ መለኮት የበለጠ በመረመርኩ ቁጥር የበለጠ
ምስጢር ይሆንብኛል” ይላል፡፡ እውነትም የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት መመርመር የአምላክ ሰው የመሆንን
ምስጢር መረዳት ለሰው አእምሮ የረቀቀ ነው፡፡
አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ አዳምን እና ልጆቹን ያዳነበት ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ በመሆኑ በቸርነቱ ያዳነንን አምላክ ከማመስገን በቀር ምን ልንል እንችላለን?
በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ትምህርታችን አምላክ ሰው ሆኖ አዳምንና ልጆቹን አዳናቸው ብለን እናስተምራለን አምላክ
ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ ስንል በምስጢረ ተዋሕዶ ነው፡፡ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ ንስጥሮስን ከክህደቱ
ለመመለስ 200 የሚሆኑ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ የሊቃውንቱ አፈ ጉባኤ የነበረው ቅዱስ ቄርሎስ ተዋሕዶ የሚለውን ቃል
አጉልቶ ተጠቅሞበታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኦርቶዶክስ ከሚለው ቃል ጋር ተዋሕዶ የሚለው ቃል የበለጠ መታወቅ
ጀምሯል፡፡
አምላክ ሰው ሆነ ስንል መለኮት ወደ ሥጋነት ሥጋም ወደ መለኮትነት ተለወጠ ማለታችን አይደለም፡፡ በመጽሐፍ
ቅዱስ የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ /ሐውልት/ ሆናለች /ዘፍ.19፥26/፡፡ በቃና ዘገሊላም በገቢረ ተአምር ውኃው ወደ
ወይን ጠጅ ተለውጧል /ዮሐ.2፥1/፡፡ የሎጥ ሚስት የጨው ሐውልት እንደሆነችው፤ ማየ ቃናም ፍጹም የወይን ጠጅ
እንደሆነው አምላክ ሰው ሆነ ስንል አምላክነቱን ለውጦ ፍጹም ሰው ብቻ ሆነ ማለታችን አይደለም፡፡ እንዲሁም አምላክ
ተለውጦ ሰው ቢሆንማ ኖሮ የእሩቅ ብእሲ ደም ድኅነትን ሊያሰጥ ስለማይችል በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ፍጹም
ድኅነት ከንቱ ያደርግብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ እንደማይለወጥ በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ “እኔ
እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል /ሚል.3፥6/፡፡ በመሆኑም አምላካችን ሰው የሆነበት ምስጢር ቃል /መለኮት/ በሥጋ
ሥጋም በቃል ሳይለወጥ ሳይጠፋፉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡
“ቃል ሥጋ ሆነ…. በእኛም ላይ አደረ” /ዮሐ.1፥1-14/ የሚለው ገጸንባብ መጽሐፍ በማኅደር ውኃ በማድጋ
እንዲያድር መለኮት በሥጋ ላይ አደረበት ማለት አይደለም፡፡ “የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ማርያም በተወለደው
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አደረበትና የጸጋ አምላክ አደረገው እንጂ ሥጋን አልተዋሐደም” ብሎ ንስጥሮስ ያስተማረው
የኅድረት /ማደር/ ትምህርት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተወገዘ ክህደት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ
ዮሐንስ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” /ማቴ.3፥17/
አለ እንጂ “የልጄ ማደሪያ የሆነውን እርሱን ስሙት አላለም”፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው
ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ነቢዩ ሲያስረዳ “…ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ…” /ኢሳ. 9፥6/ ብሏል፡፡
ለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው እያለች ታስተምራለች፡፡
አምላክ ሰው የሆነው መለኮትና ሥጋ ተቀላቅለው ነው አንልም፡፡ መቀላቀል /ቱሳሔ/ መደባለቅንና ከሁለቱም
የተለየ ማእከላዊ ነገር መፍጠርን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ውኃና ወተት ሲቀላቀሉ ስም ማእከላዊ መልክ ማእከላዊና
ጣእም ማእከላዊን ያመጣሉ፡፡ ስም ማእከላዊ ውኃ ከወተት ጋር ቢቀላቀል ፈጽሞ ውኃ ፈጽሞም ወተት ባለመሆኑ አንጀራሮ
የተባለ ሌላ ስም ይሰጠዋል፡፡ መልክ ማእከላዊ ስንልም ውኃው እንደወተቱ ባለመንጣቱ እንደ ውኃውም ባለመጥቆሩ
መካከለኛ የሆነ መልክ ይይዛል፡፡ ጣእም ማእከላዊ ውኃውም ወተቱም የቀደመ ጣእማቸውን ለቀው እንደ ውኃ
ባለመገረም/ባለመክበድ/ እንደ ወተቱ ባለመጣም ማእከላዊ የሆነ ጣእም ያመጣል፡፡ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢር ግን
ሥጋ የሥጋን ባሕርይ ሳይለቅ መለኮትም የመለኮትነትን ባሕርይ ሳይለቅ በተአቅቦ /በመጠባበቅ/ ባለመጠፋፋት ነው፡፡
መለኮትና ሥጋ ሳይቀላቀሉ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ የራሱ አድርጎ መለኮትም የሥጋን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ በተዋሕዶ
ሰው ሆነ፡፡
አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ስንል ልብስ በልብስ ላይ እንደሚደረብ መለኮትና ሥጋ እንደዚሁ በትድምርት
/በመደራረብ/ ሰው ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በቆሎና ስንዴ ቢቀላቀሉ ይህ በቆሎ ነው ይህ ስንዴ ነው ብለን
እንደምንለያቸው የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ በመለያየት /በቡአዴ/ ከቶ አልሆነም፡፡
ማኅተመ አበው ቅዱስ ቄርሎስ ምስጢረ ተዋሕዶን ባስተማረበት ትምህርቱ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ
ስንል በተዋሕዶ እንደሆነ በምሳሌ ገልጦ አስተምሯል፡፡ ተዋሕዶውም ነቢዩ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በጎቹን ሲጠብቅ ነበልባሉ
ሐመልማሉን ሳያቃጥል ሐመልማሉም በነበልባሉ ሳይጠፋ እንዳልተጠፋፉት መለኮት ሥጋን ሳያቀልጠው መለኮትም በሥጋ
ሳይጠፋ በተዋሕዶ አንድ ሆነ እንላለን፡፡ በእሳት ውስጥ የገባ ብረትም የባሕርዩ ያልነበረውን ብሩህነት በእሳቱ
ያገኛል፤ ቀድሞ አይፋጅ የነበረው ብረት ይፋጃል፡፡ አካል ያልነበረው እሳትም በብረቱ ሆኖ ቅርጽ ይኖረዋል፡፡
አይጨበጥ የነበረው እሳት ይጨበጣል፤ አይዳሰስ የነበረው እሳት ይዳሰሳል፡፡ አንጥረኛው በጉጠት ብረቱን ይዞ ፍህም
የሆነውን ብረት ይቀጠቅጠዋል፡፡ ብረቱ ሲደበደብ የተመታው እሳቱ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ብረቱ ነው አይባልም፡፡ እሳትና
ብረት በተዋሕዶ አንድ ስለሆኑ ብረቱ ሲመታ እሳቱ አለ፤ እሳቱ ሲመታም ብረቱ አለ፡፡ እሳቱ ሲፋጅም /ቢያቃጥልም/
ብረቱ አለ፡፡የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም በዚህ መልክ ስለሆነ መለኮት ሥጋን በመዋሐዱ መከራን ተቀብሎ ሞቶ አዳነን
ብለን እናምናለን፡፡
በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ዐይነ ስውሩን ሰው አምላካችን ሊያድነው በፈቀደ ጊዜ ምራቁን ወደመሬት እንትፍ
ብሎ በጭቃ ዐይኑን ቀብቶ አድኖታል /ዮሐ.9፥1/ ምራቅ ብቻውን ዐይንን በማብራት ተአምር መሥራት የማይችል የሥጋ
ገንዘብ ነበረ፡፡ መለኮት ብቻውንም ምራቅ ማውጣት አፈር ማራስ አይስማማውም ሥጋ ከመለኮት ጋር ተዋሕዷልና በምራቁ
ዕውርን አበርቷል፡፡ ገቢረ ተአምራቱም የተከናወነው በሥጋ ብቻ ነው ወይም በመለኮት ብቻ ነው አይባልም፡፡
ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ሰው በመሆኑ በባሕርዩ ተዋራጅነት የለውም በላይ በሰማያት ከባሕርይ አባቱ ከአብ
ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እየተመሰገነ በምድር ዞሮ አስተምሮ መከራን ተቀብሎ ፍጹም ድኅነትን
ሰጥቶናል፡፡ በሥጋ ተርቧል፣ ተጠምቷል አንቀላፍቷል፡፡ አምላክ ነውና ሙት አንሥቷል ድውይ ፈውሷል፡፡ በመሆኑም
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆነ የምንለው በተዋሕዶ ነው፡፡ በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ
በመሆኑ የሥጋንም የመለኮትንም ሥራ ባለመለያየት ባለመነጣጠል ሠራ በቅዱስ መጽሐፍ “በገዛ ደሙ የዋጃትን
የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ፡፡” /ሐዋ.26፥28/ ተብሎ መጻፉ መለኮት በባሕርዩ ሥጋ ደም ኖሮት
አይደለም፡፡ ይህ የሐዋርያው ቃል መለኮት የሥጋን ባሕርይ ባሕርዩ አደረገ ደሙን አፈሰሰ ሥጋውን ቆረሰ ብለን
ለምናስተምረው የተዋሕዶ ትምህርት የታመነ ምስክር ነው፡፡ እግዚአብሔር “በገዛ ደሙ” ቤተ ክርስቲያንን የዋጃት
በተዋሕዶ ሰው በመሆን ነውና በእውነት ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስለምስጢረ ሥጋዌ እንዲህ ይላል” ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ
ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ስለልጁ የተናገረ በሰብአዊ ሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደ በአብና
በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን ዐሳየ ዳግመኛም ነቢዩ እንባቆም እንዲህ አለ፤ እግዚአብሔር ከቴማን
ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል፡፡ ፋራን በጣዕዋ /በጥጃ/ ይተረጎማል ጣዕዋ በንጽሕት ድንግል ይተረጎማል፡፡ ክብሩ
ሰማያትን ከድኗል፡፡ ይህም በመለኮት ኀይል ከአባቱ ጋር እኩል ትክክል በመባል ይተረጎማል፡፡ ምስጋናውም ምድርን
ሞልቷል ይህም በአጽናፈ ዓለም በተሰበከው ገቢረ ተአምራት ይተረጎማል በምድር ሁሉ ነገራቸው ወጣ፡፡ እስከ አጽናፈ
ዓለም ንግግራቸው ደረሰ፤ ተብሎ በነቢዩ እንደተነገረ፤ ዳግመኛ በነቢይ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው ተብሎ
እንደተነገረ፤ ዳግመኛም ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ፤ ጌታ እግዚአብሐር ተገለጠልን፤ እንደገና በኪሩቤል የሚቀመጥ
ተገለጠ፤ ተብሎ እንደተነገረ ያለሥጋዌ እግዚአብሔርን ያየ ማነው? ሙሴን “ፊቴን ዐየቶ በሕይወት የሚቆይ የለም”
እንዳለው ነው” ይላል፡፡ /ሮሜ.1፥33፣ ዕብ.1፥1፣ ዕን.3፥3፣ መዝ.18፥4፣ መዝ.117፥26-27፣
መዝ.79፥1፣ ዘፀ.33፥1/ (መጽሐፈ ምስጢር 2000፥82 በአማኑኤል ማተሚያ ቤት ኀይለ ማርያም ላቀው /መ/ር/
እንደተረጎመው)
ተዋሕዶ ከሚጠት /ከመመለስ/፣ ከውላጤ /ከመለወጥ/፣ ከቱሳሔ /ከመቀላቀል/፣ ከትድምርት /ከመደረብ/ ከቡዐዴ
/ከመቀራረብ/ በራቀና በተለየ ሁኔታ አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር ነው፡፡ መለኮትና ሥጋ አንዱ አንዱን ሳያጠፋው፣
ሳይለውጠው፣ ያለ መለያየት፣ ያለመከፋፈል ያለ መጠፋፋት ያለ መቀላቀል በተዐቅቦ /በመጠባበቅ/ የተዋሐዱበት አምላክ
ሰው የሆነበት ይህ ምስጢር ድንቅ ነው፡፡
ቅዱስ ቄርሎስ የተዋሕዶን ምስጢር በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል “የሚረዳህስ ከሆነ የትስብእትና /የሥጋ/
የመለኮትን ተዋሕዶ በእኛ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ መስለን እንነግርሀለን፤ እኛ በነፍስና በሥጋ የተፈጠርን ነንና፤
አንዱን የሥጋ አንዱን የነፍስ ብለን ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አናደርገውም፤ ሰው ከሁለት አንድ በመሆኑ አንድ ነው
እንጂ፡፡ ከሁለቱም ባሕርያት አንድ በመሆኑ ሁለት ሰው አይባልም፡፡ በነፍስ በሥጋ የተፈጠረው ሰው አንድ ነው
እንጂ፡፡ ይህንንስ ካወቅን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶ በፊት እርስ በርሳቸው አንድ ካልነበሩ ከተዋሕዶ
በኋላም ከማይለያዩ ከሁለት ባሕርያት አንድ እንደሆነ እናውቃለን” /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ.78፥19/
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ በምድር ላይ
በመገለጡ ከባሕርዩ የጎደለበት ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ
ቅዱስ ጋር በላይ በሰማያት በመላእክት እየተመሰገነ በምድር ዞሮ አስተማረ፤ መከራ ተቀበለ ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ
አስተምህሮ ምስክር የሚሆነን የቅዱሳን መላእክትና የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ቃል ነው፡፡መላእክቱ “ክብር
ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” አሉ /ሉቃ.2፥14/፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ፍጥረትን
ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ /በክንድሽ/ ተቀምጦ እንደ ሕፃን ጡትሽን ሲጠባ መላእክት ባዩት ጊዜ በአርያም
ፈለጉትና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት” ብሎ አመስጥሮታል፡፡ ፀሐይ ባለችበት
ሆና ምድርን እንደምታሞቅ እርሱም በዙፋኑ ተቀምጦ /ዓለምን እየገዛ/ በምድር በሥጋ ማርያም ተገለጠ፡፡ ሥጋን ተዋሕዶ
ዞሮ አስተማረ” /አንቀጸ ብርሃን ዘቅዱስ ያሬድ/
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ በልባችን ስናስበው በአንደበታችን ስንናገረው
ምስጢሩ ድንቅ በመሆኑ ሐዋርያው ይህ ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ይላል፡፡ ነቢዩ ሙሴም የእግዚአብሔር ሥራ ግሩም
በመሆኑ አምነን ከመቀበል ውጭ መርምረን መድረስ ስለማንችል “ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው” ዘዳ.29፥29
እንድንል ያስታውሰናል፡፡
ሎቱ ስብሐት ለዘበስብሐተ አቡሁ ይሴባሕ ወሎቱ ቅድሳት ለዘበቅድሳተ መንፈሱ ይትቄደስ ለዓለመ ዓለም አሜን
ወአሜን፡፡በአባቱ ምስጋና ለሚመሰገን ለእርሱ ምስጋና ይገባል፡፡ በመንፈሱ ቅድስና ለሚቀደስ ለእርሱ ምስጋና ይገባል
ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
|
No comments:
Post a Comment