Thursday, February 6, 2014

ቅዱሳን ጻድቃን አባቶች እና የሰማእታትን ክብር


         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 ‘’ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ’’ ሮሜ 13፡7
ቅዱሳን ጻድቃን አባቶች እና የሰማእታትን ክብርመስጠት እንዳለብን አጭር መልዕክት ቃል ኪዳን ማለት በሁለት ወገኖች መካካል የሚደረግ ስምምነት፤ማሐላ፤ኑዛዜ ማለት ነው፡፡በዚህ ቃል መሰረት እግዚአብሔር ከፍቅሩ ብዛት የተነሳ በህይወት ዘመናቸው ሁሉ ራሳቸውን ለእርሱ አሳልፈው የሰጡትን መስቀሉን ተሸክመው ለኖሩ እና ካገለገሉ ቅዱሳን ጋር የማይሻር፤ የማይለወጥለ፤ የማይረሳ፤የማያረጅ ህያውና ዘለዓለማዊ የሆነ ቃል ኪዳን እንደገባላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ህሩያንየ - ከመረጥኩት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ››መዝ 88፡3 እግዚአብሔር አምላክ ከወደደው ጋር ቃል ኪዳን እንደሚያደርግ የማይለወጥ መሆኑንንም አረጋግጦ ሲናገር ‹‹ኪዳኔን አላረክስም ከከንፈሬ የወጣውን አልወጥም››በማለት በግልጽ ይነግረናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሰጠው ቃል ኪዳን ሞት ሊገድበው አይችልም፡፡ ብዙ ጊዜ ቅዱሳን በአጸደ ሥጋ ያማልዳሉ ብለን ስንናገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ሆነን አይደለም፡፡ሲጀመር አንድ ነዋሪ ወይም ዜጋ ዜግነታዊ መብቱ የሚጠበቅለት ግዴታውን መወጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡እንደዚሁ አንድ ሰው በቅዱሳን ምልጃ መጠቀም የሚችለው በቅዱሳኑ አማላጅነት ማመን ሲችል ብቻ ነው፡፡ነገር ግን ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆቿ እንዳይጠፉ ዜጋ ለሆነውም ላልሆነውም የቅዱሳኑን አማላጅነት ዘወትር ትሰብካለች ፡፡
ቅዱሳን ከእረፍተ ሞታቸው በኋላ እንደቀደመው በአጸደ ስጋ እያሉ ሲያደርጉ እንደነበረው የመጾም ፤የመስገድ ፤ ልዬ ልዬ መከራዎችን መቀበል ባይኖርባቸውም አስቀድመው ባደረጉት ተጋድሎ በተሰጣቸውን የማማለድ ጸጋ አምነው ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች እንደሚድኑበት እንዲህ ተብሎ ነው የተጻው ቆላ 2፡5 ‹‹በስጋ ምንም እንኳ ብርቅ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ ›› ሐዋሪያው በስጋ ምንም እንኳን ቢለይ በመንፈስ ከእነርሱ የማይረቀው ለምንድነው የሚለውን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ይህም የሚያስረዳን ቅዱሳን ከእረፍታቸው በኋላ ከእኛ የማይርቁ መሆኑን ነው የሚያሳየን፡፡ አንዲህም ተብሎ ተጽፏል ‹‹ኤልሳዕ ሞቶ ቀበሩትም ከሞዓብም አደጋ ጣዬች በየዓመቱ ወደ ሀገሩ ይገቡ ነበር፡፡ ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዬች አዬ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ ››2 ነገስት 13፡20 ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም እንደማይባል እርገጠኛ ነኝ፡፡እንደው ስንፍና ይዞአቸው ካልሆነ፡፡
ሌላው በቅዱሳን ስም ዝክር እያሉ መደገስ መብላት ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ይወዳሉ በምክንያት ነው የሚበሉት ይላሉ እንዲህ ተብሎ ነው በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን የጻድቃን ስም ለሚጠሩ በማይታበይና በማያልፈው ህያው ቃሉ እንዲህ ይላል ‹‹ነቢይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብዩን ዋጋ ይወስዳል ፤ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኃለው ዋጋው አይጠፋበትም›› ማቴ 10፡41-42
ታናናሾቹ የተባሉት ይኸውም በስጋዊ ኑሮአቸው የሌላውን እጅ ጠብቀው ለሚኖሩ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በስጋዊ ኑሮ በልጽገው ለሚገኙት ሁሉ የሚሰጠው ነገር ቢያጣ እንኳ በነቢያና በጻድቃን ስም ‹‹ ስለ አምላከ ጻድቃን አምላከ ነቢያት›› ብሎ የጻድቅን ወይም የነብይን ስም ከክርስቶስ ጋር አስተባብሮ ጠርቶ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ ቢሰጥ ዋጋው እንደማይጠፋበት መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው፡፡የዚህንም ዋጋ ታላቅነት ሲናገር የነብዩን የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል በማለት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ዋጋው ተገልጸል፡፡
የቅዱሳን ስም በመጥራት የሚደረገው መንፈሳዊ ስራ ጊዜያዊና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ ሳይሆን የማይቋረጥ መሆኑን ክቡር ዳዊት በመዝ 111/112፡6 የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል: በማለት ዘላለማዊ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ እንዲሁም የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ምሳ 10፡17
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምጽዋት፣ዝክር እና ሌሎችንም ስራዎች በቅዱሳን ስም የምታደርገው ክርስቶስ ለወዳጆቹ የገባውን ቃል ኪዳን ይዛና እግዚአብሔር ያዘዘውን የወደደው መሆኑን አውቃ ነው፡፡ስለ አምላከ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ ስለ አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፤ስለ አምላከ ሰማእት ቅድስት አርሴማ ….. እያለች ስማቸውን ከአምላካችን ስም ጋር አስተባብራ የምትጠራው ከባለቤቱ ተምራ ነው፡፡ ቅዱሳን ራሳቸው የእግዚአብሔርን ስም የሚጠሩት በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ስም በማንሳት ነበር፡፡ ኤልያስ ፈጣሪውን ሲጠራ የአብርሃም የይሳቅ የያዕቆብ አምላክ ሆይ እያለ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረና ፡፡ኤልሳዕ ደግሞ የኤልያስ አምላክ እያለ ይጠራ ነበር፡፡
እንዲህ እንደ ኤልያስ በዘመናቸው ከእነርሱ በፊት የነበሩ ቅዱሳንን የሚከብሩ እነርሱ ደግሞ በተተኪው ትውልድ በመልካም ስማቸው ይዘከራሉ፡፡ መታሰቢያቸውም በኢሳ 56፣4-7 “እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚለኝንም ነገር ለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና፡- በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣችኃለሁ የማይጠፋ የዘለዓለም ስም እሰጣችኃለሁ አለ “ የማይጠፋ ስም “ /ይሰመርበት/ ምልጃ የእግዚአብሔር ትዕዛዝና ፈቃድ ነውን? አዎ አንዳንድ ሰዎች ራሳችን በቀጥታ እንጸልያለን እንጂ አማላጅ መፈለግ መንገድ ማብዛት ነው ይላሉ ይህ ድፍረት ነው:: መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ዘፍ 20፡1-7 መመልከት እንችላለን አቤሜሌክን አብርሃም እንዲጸልይለት ራሱ እግዚአብሔር እንደነገረው እንመለከታለን፡፡እንዲሁም ኢዮ 42፡7-9 ባሪያዬ ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል ያለው እግዚአብሔር ነው እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ በእኛ የማታረቅን አኖረ፡፡እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን 2ኛ ቆሮ 5፡19-20 ታዲያ መናፍቃን ይህ ሁሉ ማስረጃ እያለ ለምን ይክዳሉ ከተባለ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው በመጨረሻው ዘመን እንደገዛ ምኞታቸውና አሳባቸው ለክህደት እንዲመቻቸው አድርገው መጽሐፍትን የሚያጣምሙ ክፉዎች እንደሚመጡና እንደሚያስቱ ብዙዎችም ከዚህ የተነሳ ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ እናንተ ግን ልጆቼ ሆይ አስቀድማችሁ እወቁ ተብሏል፡፡በመሆኑም ‹‹አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ ››2ኛ ዜና መዋ 13፡12 አዎ አትዋጉ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ያስተማረን እግዚአብሔር ነውና አላውቅም አስተምሩን ሌላ ነገር ነው ቅዱሳንን መስደብ መዝለፍ ግን ሐጢያት ነው፡፡ምክንያቱም በቅዱሳን አማላጅነት እንኳን ባያምኑ መጽሐፍ ቅዱስ እናትና አባትህን አክብር ይላል እናም ቅዱሳን እናቶቻችን ቅዱሳን አባቶቻችንን ልናከብር ይገባል፡፡እርግጠኛ ነኝ ማናችንም ወላጅ እናታችንን ወይም ወላጅ አባታችንን አንድ ሰው ከመሬት ተነስቶ ቢሰድብብን ወይም ቢመታብን ዝም እንል ይሆን? ቅዱሳን እናቶቻችን ቅዱሳን አባቶቻችንን ከዚህም በላይ ናቸውና አይ አላከብርም የሚል ካለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል “ እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደተወለዱ አዕምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ሆነው በማያውቁት ነገር/ባልገባቸው/ እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ የአመጻቸውን ደመወዝም ይቀበላሉ“ 2 ጴጥ 2፣12 እኛ ግን ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በ 2 ጢሞ 3፣17 ላይ እንደገለጸው ከልጅነት ጀምሮ በተማርነው ትምህርት ጸንተን ስንገኝ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ እንሆናለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የማያውቁ ይቃወማሉ ይህ ግን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጽሐፍትንና የእግዚአብሔርን ሀይል አታውቁምና ትስታላችሁ ማቴ 5፡22-29 ብሎ እናውቃለን እያሉ ይስቱ የነበሩትን ሰዶቃውያኑን ከገሰጻቸው ተግሳፅ ተካፋዮች የእነርሱን እርሾ ተቀብለው ይስታሉ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም የጌታችንን ትምህርት አስተማረች እንጂ የስድብ ቃልን አላስተማረችም፡፡ ይሁ 1፣8-10 “እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ስጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ስልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፡፡የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ስጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ “ ግን ግን አንድ ጥያቄ ላንሳ ? አለም ለበሽታዎች ቀን እየሰየመች በዓል ብላ ታከብራለች ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን አብነት አድርገው ቃን ኪዳኑን የፈጸሙ ቅዱሳን እንደምን አይከበሩ፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ይቆየን
አቅራቢ ገዛኸኝ ፋንታሁን ዘአርሴማ 

No comments:

Post a Comment