በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
=>ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኄኖክ ከአባታችን አዳም 7ኛው ደግ ሰው ሲሆን አባቱ ያሬድ ይባላል:: በእርግጥ ቅዱሱ ሚስት አግብቶ ማቱሳላና ሌሎች ልጆችን ወልዷል:: አካሔዱ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ነበርና ሞትን አላየም::
+ነቢዩ ኄኖክ በ1486 ዓ/ዓ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (መጽሐፈ ኄኖክን) ጽፏል:: የዚሕ መጽሐፍ ባለቤት ደግሞ ሃገራችን ናት:: ቅዱሱ ብዙ ሰማያዊ ምሥጢሮችን ተመልክቷል::
+የእርሱ ሞትን አለመቅመስ በአቤል ሞት የፈሩትን ውሉደ አዳም በተስፋ አነቃቅቷቸዋል::
"በአቤል አፍርሆሙ:
ወበኄኖክ አንቅሆሙ" እንዳለው ሊቁ:: (ዘፍ. 5:24, ኄኖክ. 4:1)
+" ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ "+
=>ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ በቀድሞዋ ሮሜ ግዛት ውስጥ የጦር አለቃ: የከተማዋ መኮንን እና እጅግ ባለጸጋ የነበረ ሰው ነው:: ግን በእምነቱ አረማዊ: በስሙም 'ቂዶስ' ተብሎ የሚጠራ ነበር:: ምክንያቱ ባይገባውም እጅግ ቅን: ደግና ለምጽዋት የሚፋጠን ነበር::
+እግዚአብሔር ታዲያ ይህን ሰው ወደ ቀናው ጐዳና (ወደ ክርስትና) ሊመራው ወደደና ተገለጠለት:: ቂዶስ ለአደን ወጥቶ ዋሊያ ሲያድን (ያኔ ዋሊያ ከዓለም አልጠፋም ነበር:: ዛሬ ግን ያለ ኢትዮዽያ ውስጥ ብቻ ነው) መድኃኒታችን በዋሊያው ራስ ላይ የብርሃን መስቀልን ገልጦ ተነጋገረው::
+ክርስቲያን እንዲሆንና መከራንም እንዲታገሥ አዘዘው:: ቂዶስም ወደ ቤቱ ተመልሶ ለሚስቱና ለ2 ልጆቹ የሆነውን ነገራቸው:: ክርስትናን ተምረው ሲጠመቁ አበው ቂዶስን 'ኤዎስጣቴዎስ' አሉት::
+ከዚህ በሁዋላ ክርስቶስን እያመለኩ ቆይተው ረሃብ በሃገሪቱ መጣ:: ቅዱሱ ምንም መኮንንና ሃብታም ቢሆንም ገንዘቡ በምጽዋት በማለቁ ባሮቹ ተበትነው ደሃ ሆነ:: የሚበላውንም አጣ:: ከሥጋዊ ሥልጣኑም ተሻረ:: እርሱ ግን ይህንን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ታገሠ::
+ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ረሃቡ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ሚስቱንና 2 ልጆቹን ይዞ ስደት ተነሳ:: ለጉዞ በተሳፈረበት መርከብ የሚከፍለው ገንዘብ ስላልነበረው ሚስቱን ቀሙት:: ልጆቹን ይዞ እያለቀሰ ከሌላ ወንዝ ደረሰ::
+እንዳይሳፈር መርከበኞቹ ልጆቹን ሊቀሙት ስለሆነ ለመዋኘት ወሰነ:: አንዱን ልጁን ተሸክሞ አሻግሮት ሲመለስ ትቶት የሔደውን ልጁን አንበሳ ወስዶት አገኘው:: እያለቀሰና እየቸኮለ ወደ 2ኛው ቢመለስ ደግሞ ይህኛውንም ተኩላ ወስዶት ነበር::
+ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ አንጀቱ በሃዘን ተቃጠለ:: በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ መራራ ለቅሶን አለቀሰ:: ነገር ግን ኢዮባዊ ሰው ነውና "እግዚአብሔር ሰጠ: እርሱም ነሣ" ብሎ በእንባ ተጉዋዘ:: በአንዲት ሃገርም ባርነት ተቀጥሮ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ኖረ::
+ከብዙ ዓመታት በሁዋላ የረሃቡ ዘመን አልፎ የቅዱሱ ወዳጅ የነበረ ሰው በሮም ላይ በመንገሱ ወታደሮችን "ወዳጄን ኤዎስጣቴዎስን ፈልጋችሁ አምጡ" ብሎ ላካቸው:: ከአድካሚ ፍለጋ በሁዋላ ያ ደግ ጌታቸው በባርነት ተቀጥሮ: ተጐሳቁሎ አገኙት::
+ፈጥነው ወደ ሮም ከተማ ወስደው በቀደመ ክብሩ ላይ አኖሩት:: እርሱ ግን ሃዘንተኛ ነበር:: ከቀናት በሁዋላም አዳዲስ ወታደሮችን ከተለያየ ቦታ መለመለ:: ከእነዚያም መካከል መልካም የሆኑትን 2ቱን አለቆች አደረጋቸው:: ሁለቱ ደግ ወጣቶችም በጣም ይዋደዱ ነበር::
+አንድ ቀን እኒህ 2 ወጣቶች ወይን ሊገዙ ሔደው ጠባቂዋን 'ስጭን' አሏት:: ሰጥታቸው እዚያው ያወራሉ:: አንደኛው "ታሪኬን ልንገርህ" ይለዋል:: "እሺ" ሲለው "እኔ ወላጆች የሉኝም:: ሕጻን እያለሁ በሃገራችን ረሃብ መጥቶ: ሃብታችን አልቆ ስንሰደድ እናታችን መርከበኛ ወሰዳት:: አባቴ ወንድሜን ሲያሻግረው እኔን አንበሳ ወስዶ ከአንድ መንደር ጣለኝ" አለው::
+ባልንጀራው ገርሞት "ታሪካችን ተመሳሳይ ነው:: እኔም እንዳንተ ሆኜ: አባቴ ሲያሻግረኝ ተኩላ ወስዶ አንድ መንደር ውስጥ ጣለኝ" አለው:: ይህንን ትሰማ የነበረችው ወይን ጠባቂ "ልጆቼ!" ብላ ጮሃ አለቀሰችና ደነገጡ:: እርሷም ቀርባ አቅፋቸው እያለቀሰች ነገሩን ሁሉ አስታወሰቻቸው::
+ይህን ጊዜ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰምቶ ደረሰ:: ከረጅም ዓመታት በሁዋላ ሚስቱ አትክልት ጠባቂ ሁና ማንም ሳይነካት: 2 ልጆቹንም አገኘ:: እያለቀሱ ተቃቀፉ:: እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመሰገኑት:: የሰማ ሁሉ "ዕጹብ! ዕጹብ!" አለ::
(እኛ የምናመልከው ጌታ እንዲህ ነው:: ክብር ለእርሱ: ለድንግል እናቱና ለወዳጆቹ)
+ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ በቀሪ ዘመናቸው ቤተ ክርስቲያን አንጸው በምጽዋት ኑረዋል:: በመጨረሻም ዘመነ ሰማዕታት መጥቶ "ክርስቶስን አንክድም" በማለታቸው ብዙ ተሰቃይተው 4ቱም ሰማዕት ሆነዋል::
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
No comments:
Post a Comment