Tuesday, December 8, 2015

የቅድስት አርሴማ ተአምር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

እነሆ ተአምር ከሰማእቷ ቅድስት አርሴማ
ገዳም።
ለሌሌች አድርሱ ይህን መስክሩ.!
እናት ማዬት ስለተሳናት ልጃቸው ብለው ሱባኤ
ለመያዝ ጎንደር ጭልጋ ወረዳ ቅድስት አርሴ ማ
ገዳም ተገኝተዋል። በገዳሙ ስርአት መሰረት ሱባኤ ይዘው ለሁለት ሳምንት ገብተዋል፣
በፀሎት እና በልመና ሳያቋርጡ የዘውትር
ናፍቆታቸውን በልመና ወደ ፈጣሪ ያሳስባሉ
ሰማእቷን እርጅኝ ይህችን አንድ
ፍሬ ህፃን ብርሃን ስጫት ለኔም ረድኤትሽ ይድረሰኝ
እያሉ ሳያቋርጡ ይፀልያሉ። በዚህ ሁኔታ ሁለት ሳምንት ተቆጠረ
በስተመጨረሻም ቀነ ቀጠሮው ደረሰ እና አንድ ቀን
እማማ በሱባኤ እያሉ ሚጡዬ ከተኛችበት ባንና
ተነሳች እና በድንጋጤ
ሁሉን አተኩራ አዬቻቸው በማደሪያው ያሉትን
አብረዋት ያሉትንም ከእንቅልፏ ተነስታ አፍጥጣ አስተዋለቻቸው ሰዎቹም
ሁለት ልብ ሆኑ ማየት አትችልም ነበርና አሁን ግን
ሁሉንም እያዬች በልጅነት ግራ መጋባት እንዲህ ብላ
አሳገራሚ ነገር ነገረቻቸው።
>> አንዲት ሴት ተነሽ ተነሽ ብላ ቀሰቀሰችኝ
ሴትዬዋ ደግሞ እንደዚህች ትመስላለች ብላ በማደሪያው ቤት ያለውን የቅድስት
አርሴማ ስዕለ አድህኖ ጠቁማ አሳዬቻቸው። ማዬት
የተሳናት ህፃን ልጅ በሰማእቷ እርዳታ ማዬት
ቻለች። ይህም ብቻ አይደለም! ህፃኗ እንዲህ ብላም
ነግራቸዋለች የቀሰቀሰቻት ይች
ሴት ብዙ ጊዜ እየታዬቻት ታናግራት እንደነበርም ነግራቸዋለች!
እማማ በሱባኤ በነበሩበት ቀናት አይኗ ለማያዬው
ህፃን
ሰማእቷ በአይነ ልቦናዋ ትገለጥላት እና ትታያት
ነበር።
አይደንቃችሁም ወዳጆቼ? የእናት ልመና ቀላል አይደለም!!!
እምነታቸው የፀና ነውና ለዛውም ፊደል ሳይቆጥሩ
በልቦናቸው
ብርሃን እየተመሩ ፈቃዱን እየፈፀሙ ይኖራሉና
እግዚአብሔር
ም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈፅምላቸዋል! የእናቶች ፀሎት እና
ልመና ጠብ የምትል አይደለችም!! ያደለው
ቅዱሳንን ተማፅኖ
እንዲህ ቤቱ በተአምራት ይሞላል! ይባረካል
ይፈወሳል!
እኛስ??? … … እስካሁን ዶክተርን ልመና ካገር አገር
የምንባዝን ስንቶቻችን ነን? እኔ የሚገርመኝ ማን
ወደ ማን
ነበር መምጣት የሚገባው? ባለፀጋስ ማነው?
መድሀኒት
ያለውስ የት ነው? እግዚአብሔር ሁላችንም ወደ ልቦናችን
ይልሰን እና በእጃችን የያዝነውን እንቁ
እንድናስተውል ይርዳን።
እግዚአብሔር ይህንን የቅዱሳኑን ድንቅ እና በረከት
እንድናይ
የበቃን የተዘጋጀን እንድንሆን ይርዳን አሜን። የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን!
~Like
~Comment
~Share 

Thursday, August 27, 2015

መንፈሳዊ ተጋድሎ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: 
1.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ምን ማለት ነው?


መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት - አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ÷ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነፃ ፈቃዱ ወስኖ፥ በሙሉ ልቡናው፥ በሙሉ ኃይሉ የሚያደርገው የውስጥና የውጭ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፥ ጥረትና ትግል ነው፡፡
ሀ. ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው፡፡
ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም›› ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማያቋርጥ ጦርነት ነው፡፡ (ገላ 5፥12) ታላቁ አባት ኢዮብም ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ?›› በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿአል፡፡ ይህም ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው፡፡ ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል፡፡
ይህ ሲባል ግን ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ሥጋ በራሱ ርኵስ አይደለምና፤ ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰውን (ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው) ከፈጠረ በኋላ ‹‹ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡›› ተብሏል፡፡ (ዘፍ1፥31) ሥጋ ርኵስ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ወልድ (ቃል) ‹‹ሥጋ ሆነ›› ባልተባለ ነበር፡፡ (ዮሐ 1፥14) አዳምና ሔዋን ከኃጢአት በንጽሕና ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፣ አይተፋፈሩም ነበር›› እንዲል (ዘፍ 2፥25)  ህፃናት፣ ልጆች  ሰውነት አላቸው ነገር ግን የኃጢአት ምኞት የላቸውም፡፡
ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ ተፈጥሮአዊና ንጹህ የሆነ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣  በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም/መግራት ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን በመጠቀም ይሠራል÷ ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ ‹‹ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ፡፡ (ዘዳ 32፥15)
ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ‹‹ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ›› እንዳለ፡፡ በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ (1ኛ ቆሮ 9፥27) በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ›› እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባናል፡፡
ለ. ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር እንጂ›› እንዳለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ሰው ከሰው ጋር በመጣላት የሚያደርገው ትግል ሳይሆን ጥንተ ጠላታችን ከተባለው በእባብ ወይም በዘንዶ ከተመሰለው ዲያብሎስና ከእርሱ ጋር ካሉት ሠራዊቱና መልእክተኞቹ ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ (ኤፌ 6፥12)
ከአዳምና ከሔዋን ከልጃቸውም ከቃየን ጀምሮ ሰይጣን የሰው ልጆችን ዘወትር ይዋጋል፤ ከዘላለም የሞት ፍርድ ሥር ሊጥል ይሠራል፡፡ በዚህም ውጊያው ከነቢያት ፤ከሐዋርያት ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ብዙዎችን ጥሏል፡፡
ዛሬም በገዛ ባሕርያችን የሚገኘውን ፈቃደ ሥጋ በመጠቀም፣ የራሱን በመጨመርና የተለያዩ ፈተናዎችን በማቀናበር ይዋጋናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፡፡›› እንዳለ ጠላት ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በኃጢአትና ሞት ሊውጥ ዘወትር ይተጋል፡፡ ማንም ሰው ደግሞ ከዚህ ፈተናና ውጊያ ሊያመልጥ አይችልም፤ ስለዚህ ሐዋርያት ‹‹በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት››፣ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡›› እንዳሉን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ለብሰን ልንዋጋው ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ 5፥8-9፣ኤፌ 6፥11)
ሐ. የሚመጣውን ዓለም ደስታ ተስፋ እያደረጉ ብቻ በዚህ ዓለም ሕይወት ከደስታ ውጪ መሆን ማለት አይደለም፡፡
ደስታ በራሷ የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆነች፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጠች፤ ንጹሕ ፈርጥ ነች፡፡ (ገላ 5፥22)
እውነት ነው፤ በዚህ ዓለም ስንኖር መከራ አለብን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ እስካለ ድረስ ከጨለማው ዓለም ገዢ ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ የሚመጣ ልዩ ልዩ ፈተናና ከሥጋችንም ባሕርይ ከሚገኘው ክፉ ምኞትና ርኵሰት ሥራ እንዲሁም ከሌሎቹ የኃጢአትና የፈተና ዓይነቶች ጋር በማያቋርጥ እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል ውስጥ መኖሩ የግድ ነው፡፡ መከራና ስቃይ፣ ትግልና ጦርነት የሌለበት በዘለዓለማዊ ደስታ ብቻ የሚኖርበት ሕይወት በሚመጣው ዓለም የሚገኝ ነው፡፡
በዚህ ምድር በጉዞ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን ጨርሳ ድል ከነሱት አባላቷ ጋር አንድ እስክትሆን ድረስ መከራው፣ እንቅፋቱ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ የግድ ነው፡፡ ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፡፡›› እንዲል (ሐዋ 14፥22)
ይህ ሲባል ግን በዚህ ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከደስታ የተራቆቱ ዘወትር በኅዘንና በስቃይ ብቻ የሚኖሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሚለዩትና ዘወትር ለመለየት ጥረት የሚያደርጉት የውሸት ከሆነው ኃጢአት (ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል) ከሚገኘው ደስታ እንጂ ከእውነተኛውና ከሰማያዊው ደስታ አይደለም፡፡
መንፈሳዊ ተጋድሎ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና ረድኤት መንፈስ ቅዱስ መሪና አስተማሪ፣ የሚያነቃቃና የሚያጽናና፣ የሚያርምና የሚገሥጽ፣ የሚረዳና የሚያጸና፣ በመሆን ስለ ክርስቶስ በክርስቶስ ጸጋ የሚከናወን በመሆኑ መከራንና ስቃይን በሚያስረሳ እውነተኛ ደስታና ሰላም የተሞላ ሕይወት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ስለ ክርስቶስ በማስተማራቸው ምክንያት ገዢዎች ልብሳቸውን ገፈው በበትር እንዲመቱ አዘዙ በበትር ከመቷቸውም በኋላ በወኅኒ ቤት ጣሏቸው እነርሱ ግን ከጀርባቸው ደም እየፈሰሰ በመንፈቀ ሌሊት እንኳን እግዚአብሔርን በመዝሙር ያመሰግኑ ነበር፡፡ እውነተኛውና ሰማያዊው ደስታ በልቡናቸው ሞልቶ ነበርና፡፡ (ሐዋ 16፥22-25)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐዋርያት እንዲህ ይለናል ‹‹ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው  በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቷቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፡፡››(ሐዋ 5፥40-41)
ቅዱስ ዮሐንስ ካሲያን የተባለው አባት በተጋድሎ በግብጽ በረሃ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩት መነኰሳት ሲናገር ‹‹ እነዚህ ምድራዊ መላእክት ናቸው፤ የግብጽን በረሀዎች በደስታ ወደ ተሞላ መዝሙርና እግዚአብሔርን የማመስገኛ ገነትነት ለውጠዋልና››  ብሏል፡፡
በአጠቃላይ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ከተድላ ሥጋ፣ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ በመሸሽ ሰማያዊና እውነተኘ በሆነ ሰላምና ደስታ ውስጥ መኖር ይህንንም ለማግኘት መጋደል ማለት ነው፡፡

2.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማው ምንድነው?
ሀ. የድል አክሊል (የዘለዓለም ሕይወት) ለመቀበል
እግዚአብሔር አምላካችን ሰዎች ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ከአምላካቸው ጋር መኖር ከመረጡ ሊሰጣቸው ያዘጋጀው ከመነገርና ከመታሰብ በላይ የሆነ የዘለዓለም  ሕይወት አለ፡፡ የሰው ልጅ ሕሊናዊ ነፃ ፈቃዱ ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ በየጊዜው እየደከመና ወደ ኃጢአት እያዘነበለ መጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ከብሮ ባየ ጊዜ ከአባቶቻችን ጀምሮ ዘወትር የሚቀና ክፉ ጠላትም (ዲያብሎስ) አለን፤ ባገኘው አጋጣሚ ስንፍናችንንና ድካማችንን እየተከተለ እነዚህንም በመጠቀም ዘወትር ከአምላካችን ሊለየን እንደሚተጋም ከላይ ተመልክተናል፡፡

ሽልማት፣ አክሊል የሚሰጠው ደግሞ ማሸነፍ ለሚችል ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ሰነፍና ቸልተኛ ሰው ግን ሊሸለም አይገባውም አንድ ሰው ጎበዝ ወይም ሰነፍ መሆኑ የሚታወቀው ደግሞ በፊቱ ያጋጠመውን ውድድር ወይም ፈተናና መከራ ማሸነፍና ማለፍ ሲችል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማ በገዛ ባሕርያችን ያለን መጥፎ የኃጢአት ዝንባሌና ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያመጣብንን ፈተናና ሽንገላ ከእግዚአብሔር ርዳታና ቸርነት ጋር ሕሊናን በማንቃት፣ ራስን በመግዛትና ጠንክሮ በመጋደል አምላካችን ያዘጋጀልንን የድል አክሊል የዘላለም ሕይወትን መቀበል ነው፡፡ ‹‹ የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል›› አንዲል (1ኛ ጢሞ 6፥12) ሐዋርያቅ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ መከራዎችን አልፎ ገድሉን በድል አድራጊነት ሲፈጽም ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል ( 2ኛ ጢሞ 4፥7-8)
ለ. ለመንፈሳዊ እድገት
ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለፍሬ የሚበቃው የድል አክሊልን መቀዳጀት የምንችለው የማያቋርጥ (የማይቆም) መንፈሳዊ ዕድገት ሲኖረን ነው፡፡ በጥምቀት ያገኘነው አዲሱ ሕይወታችን ዘወትር ማደግ ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በዛፍ ተክል ይመሰላል፡፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ፍሬ እስከሚያፈራለት ጊዜ ድረስ ያለው ድካም ቀላል አይደለም፡፡ የዛፉ ችግኝ እንዲያበቅል፣ እንዲለመልም፣ አንዲያብብና እንዲያፈራ አትክልተኛው ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ በየጊዜው ውሃ ማጠጣት፣ ማረምና መኰትኰት፣ ፀረ ዕፅዋትና ፀረ ሕይወት የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን አድጎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ዕለተ ዕለት ጠንክረን በትዕግሥት መሥራት በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናት ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ተጋድሎም ዓላማው መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያቀጭጩ  ከጸጋ እግዚአብሔርም የሚያራቁቱ ኃጢአትና የዲያብሎስ ፈተናን በመቃወም መንፈሳዊ ምግቦችንም በመመገብ አዲሱ ሕይወታችንን ማሳደግ ነው፡፡
                                                                                                 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቅዱስ ሰራባሞን የኒቅዩስ ሊቀ ጳጳስ - ሕይወቱና ተጋድሎው

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 
ቤተ ክርስቲያን በዓላውያን ነገሥታት አሰቃቂ ስደት በደረሰባት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕት ዓመታት ውስጥ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አንዱ የሆነውና ለዛሬው የተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የምንመለከተው ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞን ዘኒቅዩስ ነው። አባቱ አብርሃም ይባላል፤ አያቱ የቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ አጎት ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። ሲወለድ ወላጆቹ “ስምዖን” ብለው ስም አወጡለት፤ “ሰራባሞን” የጵጵስና ስሙ ነው። የዐረብኛ እና የግዕዝ መጻሕፍት “ሰራባሞን” ሲሉት፣ የቅብጥና እንግሊዝኛ ምንጮች ደግሞ “ሰራፓሞን” ብለው ይጠሩታል።

በተወለደበት በኢየሩሳሌም ሳለ ክርስቲያን መሆን አጥብቆ ይፈልግ ነበር። እመቤታችን በራእይ ተገልጻ ወገኖቹ አይሁድ እንዳይገድሉት ወደ ግብፅ ሄዶ እንዲጠመቅና አገልግሎቱንም በዚያ እንዲፈጽም ስለነገረችው ቤተሰቦቹን ጥሎ መነነ። ግብፅ ሲደርስ እመቤታችን የእስክንድርያ 16ኛ ፓትርያርክ የነበረውን አቡነ ቴዎናስን (282-300) ባዘዘችው መሠረት አስተምሮ አጠመቀው። የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜያት፣ የነቢያትንና ሐዋርያትን መጻሕፍት ተማረ፣ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳን እና የበልኪሮስን ድርሳናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠና።

ከዚያም ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ በሆነ እልሐብጡን በተባለ በአባ ሳዊሮስ ገዳም ውስጥ መነኮሰ። ከዘመናት በኋላ በተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ዘመን (300-311) የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፍ በእርሱ ምትክ የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መራ፤ ከገድሉ እንደምናነበው ወደ ተመደበበት ሀገረ ስብከት ሲገባ የተደረገለት አቀባበል የደመቀ ከመሆኑ የተነሣ ጌታ በሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ታጅቦ ሲገባ እንደተደረገለት የሚመስል ነበረ። በቅዱስ ሰራባሞን አገልግሎት በኒቅዮስና በአጎራባች ከተሞች የነበሩ ጣዖታት ተሰባብረው ወድቀዋል፤ በእጁ በርካታ ገቢረ ተአምራት ተደርገዋል፤ በመስቀሉ አጋንንትን አባሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ስለ ወንጌል ብዙ መከራን ተቀብሏል፤ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ብዙ ዘለፋ ደርሶበታል። አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና ሚሊጦስ በእርሱ ዘመን የነበሩ መናፍቃን ናቸው። የአርዮስ ዋና ክህደት “ወልድ (ክርስቶስ) ፍጡር ነው” የሚል ሲሆን ሚሊጦስ ደግሞ “ከማርያም የተወለደው ክርስቶስ በምትሐት ነው እንጂ በእውነት አይደለም” የሚል ነበር። ሰባልዮስ “እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው” ብሎ የሚያስተምር ሲሆን፤ ሰራባሞን ሁሉንም ተከራክሮ ረቷቸዋል።

በዚህ የተነሣ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። አርዮስና ሚሊጦስ የሚያስተምረውን ባለመቀበላቸው በክፋታቸው ጸንተው ብዙዎችን እያሳቱ፣ በትዕቢታቸውም ልባቸውን እያኮሩ ቢያገኛቸው በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ የአርዮስና ሚሊጦስን አንገታቸውን በመሐረብ ይዞ “እናንተ አባታችሁን ዲያብሎስን በክህደት የምትመስሉ እስከ መቼ ድረስ ነው በዚህ ክህደታችሁ ሰውን የምታጠፉ?” ብሎ ገስጿቸዋል (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 130-137)። አርዮስ ከክሕደቱ የማይመለስ ከሆነ አንጀቱ ተበጣጥሶ እንደሚሞት፣ ሚሊጦስም ካልተመለሰ ሥጋውን በቁሙ ዕፄያት እንደሚበሉት ትንቢት ተናግሮባቸዋል። እምቢ በማለታቸው በሁለቱም ላይ ይኸው ተፈጽሞባቸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅልጥያኖስ (284-305) የሚያፈርሳትን ቤተ ክርስቲያን ሰረባሞን ሲሰራ፣ ጣዖት የሚያመልኩትንም ሰዎች በክርስቶስ ስም ሲያሳምናቸው ንጉሡ እና መኳንንቱ ስጋት ጨመረባቸው። ሰራባሞን እንዲታሰር እና ስለ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳያስተምር በእስክንድርያው ገዢ አውጣኪያኖስ፡ ኮሞስ፡ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ሰራባሞን ግን ከአቋሙ አልተናወጸም። ስለዚህ እስር ቤቱን አንዴ በታሕታይ ግብጽ አንዴ ደግሞ በላዕላይ ግብጽ በበረሃው ሁሉ በማፈራረቅ አሰቃዩት። እርሱ ግን ስቃዩንና ዛቻውን ከምንም ሳይቆጥር በእስር ቤት ውስጥም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳምኗል። የላዕላይ ግብፅ ገዢ የነበረው አርያኖስ (ከከሐዲው አርዮስ የተለየ እና የሀገረ እንጽና ገዢ የነበረ) ብዙ ካሠቃየው በኋላ በኒቅዩስ ከተማ ወደብ አቅራቢያ አንገቱን እንዲቆርጡት ትዕዛዝ ሰጠ። የሚጓዙበት መርከብ ግን አልንቀሳቀስም አለ። ቅዱስ ሰራባሞንን ከመርከቡ ሲያወርዱት በሰላም ሄዱ። በዚህ ሁኔታ እያለ እንኳን ወንጌልን መስበክና ትንቢት መናገርን አልተወም።

ይህ በእርሱ ላይ የሞት ውሳኔ የሰጠበት አርያኖስ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስን ክዶ ክርስቲያን እንደሚሆን በመጨረሻም ሰማዕትነትን ተቀብሎ እንደሚሞት፣ እንዲሁም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት እንደሚሞትና “ተፍጻሜተ ሰማዕት” እንደሚሆን እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፥ “ወበከመ፡ ጴጥሮስ፡ ቀዳማየ፡ እምሐዋርያት፡ ከማሁ፡ አንተኒ፡ ትከውን፡ ተፍጻሜተ፡ ሰማዕት። ናሁ፡ አቅደምኩ፡ ነጊሮተከ፡ ዘይከውን፡ በጊዜሁ።” (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 158)። እንደ ትንቢቱም ሁሉም ተፈጽሟል። በመጨረሻም ከሀገረ ስብከቱ ኒቅዩስ በስተደቡብ በምትገኘው ቦታ ወስደው ኅዳር 28 ቀን (በቅብጥ አቆጣጠር ሐቱር 28 ቀን) አንገቱን በሰይፍ ቀሉት።

ደቀመዛሙርቱ አስከሬኑን በመንገድ ላይ እንዳልባሌ ነገር ተጥሎ ሲያዩት በመረረ ሐዘን ተውጠው እያለቀሱ “እረኛችን ሆይ ለማን ታስጠብቀናለህ? አባታችን ሆይ እንግዲህ ማን ይሰበስበናል? አውሬ ከቦናል፣ በወንጌል ኮትኩተህ ያሳደግከው ተክልህን ከእንግዲህ ማን ይንከባከበው?” እያሉ መሪር እንባን ያነቡ ነበር። ከብዙ ለቅሶ በኋላ አስከሬኑን ወስደው በኒቅዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር አሳረፉት (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል166)።

ከገድሉ እንደምናነበው ሰራባሞን ባደረገው ተጋድሎና በጽንአቱ በርካታ የክብር ስሞችና ቅጽሎች ተሠጥተውታል። ዋና ዋናዎቹም፥ “ብፁዕ ወቅዱስ ሰማዕት”፣ “ለባሴ መንፈስ”፣ “ለባሴ፡ አምላክ”፣ “ዓምደ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ሐረገ ወይን”፣ “ሐዲስ ዳንኤል”፣ “ላዕከ መንፈስ ቅዱስ”፣ “ሙሴ ሐዲስ”፣ “ጳውሎስ ዳግመ”፣ “ዮሐንስ ሐዲስ”፣ “መስተጋድል ዐቢይ” የሚሉት ናቸው።

በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በስሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ታንጸዋል፣ ገድል ተጽፎለታል፣ በስንክሳርም ይዘከራል። ገድሉ እና የሰማዕትነቱ ዜና በቅብጥ እና ዐረብኛ ቋንቋ የተጻፈና የተተረጎመ ሲሆን ሁሉም ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አልተገኘም። የቅብጡ ቅጂ በHyvernat, (ገጽ. 304-31) የታተመ ሲሆን የዐረብኛው ደግሞ (Kairo 27 በሚል ዝርዝር) በKraf (1934:12) ካታሎግ ተሠርቶለታል። በቅርቡ ደግሞ Youssef (2013: 263-280) የሚባል ተመራማሪ “ሰራባሞንን የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን ምንባባት” ብሎ ጥናታዊ ጽሑፍ አውጥቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያነ የቅዱስ ሰራባሞን ዜና ሕይወት እና ተጋድሎ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን እምብዛም ጎልቶ የሚታወቅ ባይሆንም በሕዳር 28 ስንክሳር ይታወሳል። ከዚህም በላይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገድሉ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1408-1497) ተተርጉሞ ይገኛል። ይህም ገድል አሁን ከሚገኙት የቅብጥና ዐረብኛ ቅጂዎች ይልቅ የተሟላ እና ይዘቱም ሰፊ ነው። ይህ ገድል በ1970ዎቹ ውስጥ (EMML 6533) በሚል መለያ ማይክሮ ፊልም ተነስቷል።

ብራናው አጠቃላይ 168 ቅጠል ያለው ሲሆን ከመጀመሪያ እስከ 118 ድረስ የሐዋርያው ጳውሎስ ገድል፣ ከቅጠል 119-167 ድረስ ደግሞ የሰማዕቱ ሰራባሞንን ገድል ይዟል። የሰራባሞን ገድሉ አራት ክፍሎችን ይዟል፤ እነዚህም፥ 1) ድርሳን (ከቅጠል 119-131)፣ 2) ገድል (ከቅጠል135-142)፣ 3) ተአምር (ከቅጠል 132-149)፣ 4) ስምዕ (ከቅጠል 150-167) የሚሉ ናቸው። ይህም ስለ ሰራባሞን የሚጠናውን ጥናት ይበልጥ የተሟላ የሚያደርግና በተለይ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ለዜና አበው እና ለነገረ ቅዱሳን የጥናት መስክ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ከስንክሳሩና ከገድሉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሰራባሞን የተዘጋጁ ልዩ ልዩ አርኬዎች (Chaîne ቁ. 48 እና Wein፣ Athiop. 19 [በN.Rhodokanakis አማካይነት ካታሎግ የተሠራላቸው])፣ እንዲሁም ሁለት የተለያዩ መልክአት (Chaîne ቁ. 158 እና 325) ተዘጋጅተዋል። በኢትዮጵያው የገድል ቅጅ ላይ እስካሁን የተደረገ ጥናት የለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ መነሻ ጥናት አድርጎ ገድሉንም እየተረጎመ ይገኛል።

ይህን ጽሑፍ የምንደመድመው በቪየና የሚገኘው ብራና (Vienna ms f.62v-63r) ስለ ቅዱስ ሰራባሞን ከሚያመሰግነው አርኬ ውስጥ አንዱን በማንበብ ይሆናል፤
ለከ፡ ስነ፡ ሰረባሞን፡ ዘኤፍራታ፤
ነጺሮሙ፡ ጥቀ፡ ለሕሊናሁ፡ ጥብዓታ፤
ከመ፡ ይከውን፡ ሰማዕት፡ ውስተ፡ ዓውደ፡ ግሩም፡ ሐተታ፤
ገደፈ፡ አብ፡ እጓሎ፡ ወእም፡ ወለታ፤
ወሐማትኒ፡ ሐደገት፡ መርዓታ።
የሰማዕቱ ሰራባሞን በረከት ይድረሰን!!!
ስምዓት
  • መጽሐፈ ስንክሳር - በግዕዝና በአማርኛ (ከመስከረም እስከ የካቲት)፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1994 ዓ.ም.
  • ገድለ ጳውሎስ ወሰራባሞን - (EMML 6533)- ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝ፣ በ15ኛው መ/ክ/ዘ/ የተጻፈ ብራና (እስካሁን አልታተመም)።
  • Amsalu Tefera, 2013, “Gädlä Särabamon: the case of the Ethiopic version”, a paper read on a workshop titled “EMML@40: The Life and Legacy of the Ethiopian manuscript microfilm Library” organized by Hill Museum & Manuscript Library, Saint John’s University, Collegeville, MN, USA, July 25-26, 2013.
  • Budge, Wallis, 1928, The Book of the Saints of the Ethiopian Church: a translation of the Ethiopic Synaxarium መጽሐፈ፡ ስንክሳር፡ made from the manuscripts Oriental 660 and 661 in the British Museum, vol. I, Cambridge at the University Press.
  • Chaîne, M., 1912, “Catalogue des manuscrits Ethiopiens de la collection Antoine d’Abbadie”, Paris.
  • Chaîne, M., 1913, “Répertoire de salam et Melke’e contenus dans les manuscrits éthiopiens des bibliotheques d’Europe” in Revue de L’Orient Chrétien, , deuxieme Serie, Tome viii, no. 2
  • Colin, G. 1988, “Le Synaxaire Éthiopien mois de Ḫedār” in Patrologia Orientalis, Tome 44, fascicule3, no. 99)
  • Coptic Synaxarium, reading on Hatour 28, – retrieved online -http://popekirillos.net/EN/books/COPTSYNX.pdf, accessed on May 14, 2012.
  • Hayvernat, Henry, Les Actes des martyrs del’Égypte, retrieved online from http://www.archive.org.detailes/lesactesdesmarty01hyve - accessed on November 6, 2012.
  • Kraf, George, 1934, Catalogue de manuscrits Arabes Chrétiens conserves au Caire, studi e testi 63, Città del Vaticano Biblioteca Apostolica Vaticana
  • Rhodokanakis, N. 1906, Die Äthiopischen Handscriften der K. K. Hofbibliothek zu Wein, Wein Athiop. 19.
  • Youssef, 2013, “Liturgical Texts Relating to Sarapamon of Nikiu”, Peeters Online Journal, pp. 263-280.
  • ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
    የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ

Tuesday, May 26, 2015

አቡነ ዓብየ እግዚእ

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
  ዕረፍቱ ለአቡነ ዓብየ እግዚእ
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ከአባታቸው ያፈቅረነ እግዚእ እና ከእናታቸው ከጽርሐ ቅዱሳን በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት በትግራይ ሀገረ ስብከት: በሀገረ ሰላም ወረዳ ልዩ ስሙ መረታ አሪያ በሚባል ቦታ ተወለዱ። ዕድሚያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ገና በ7 ዓመታቸው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ ምናኔ ገብተው አባ ዘርዓሚካኤል ከተባሉ አባት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎችንም መንፈሳዊ ትምህርቶች ተማሩ።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ለመጀመሪያ ጊዜ ሱባኤ የያዙት አገፋት በሚባል ቦታ ነው። ጸሎታቸውን (ሱባኤያቸውን) ከጨረሱ በኋላ ከዚህ አገፋት ከሚባል ቦታ ወደ ደብረ ዓባይ ገዳም በዝሆን ተጭነው ሄደዋል። እዛም ከቅዱሳን በረከት ተቀብለው እንደገና ወደ ዋልድባ ገዳም በመሄድ በምናኔና በጸሎት ቅዱሳንን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ቦታቸው ዋልድባ እንዳልሆነ ጌታ በራእይ ገለጸላቸው። እሳቸው ግን ቦታውን በጣም ስለወደዱ ከዚህ አልሄድም አሉ። እግዚአብሔር አምላክ ቅዱሳኑንን እንዳያዝኑበት ይጠነቀቃልና ዮናስን ቀስ አድርጎ እንዳስረዳው አባታችንን ደግሞ በተኙበት ጊዜ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ለበረከትም እንዲሆን የተኙባት ቦታ ቀርድደው ከነ አፈሩ አንስተው አሁን ገዳማቸው ባለበት ቦታ በመረታ አኖሩዋቸው።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ወደ ኢየሩሳሌም በደመና ሰረገላ ተጭነው፣ በመሄድ የጌታን መቃብርና ጎልጎታን በመሳለም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ከአቡነ እንጦንስና ከአቡነ መቃርስ መቃብር አፈራቸውን ለበረከት ይዘው በመምጣት በገዳሙ በትነውታል።
ንዕማን ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር ወደ አገሩ እንደወሰደ፣ እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ከተቀበሩበት መቃብር ከሮም፣ ከደብረ ምጥማቅ ከእመቤታችን ገዳም፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ መቃብር፣ ከአክሱም ጽዮንና ከሌሎችም ቅዱሳን መካናት፣ አፈራቸውን ያዙ።
መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል "ገዳምህ ይዘኸው ብትሄድ ለሰውና ለእንስሳ መድኃኒት ይሆንልሃል። ገዳምህ ልዩ ስሙ ተንስሐ በተባለ ቦታ ነው" ብሎ በራእይ ስለነገራቸው ህዳር 20 ቀን በብርሃን ሰረገላ ተጭነው የተቀደሰውን አፈር በትነውታል።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ልዩ ልዩ ተአምራት በእግዚአብሔር ኃይል አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል
   1- የጻድቁ አባታችንን የተቀደሰው አፈር ይዘው ሲመጡ መምጣጣታቸውን ያወቁ ተንስሐ በሚባል ገዳም የተቀበሩ ቅዱሳን አባቶች፣ ልክ እንደ አልዓዛር ከመቃብራቸው በመነሳት ጻድቁ አባታችንን ተቀብለዋቸዋል። ጻድቁ አባታችን ዓብየ እግዚእም በብርሃን ሰረገላ ወርደው ባርከዋቸዋል።
    2- አጼ ገብረመስቀልና የመንፈስ ቅዱስ ጓደኛቸው አቡነ ብእሴ እግዚእ የተባሉት አብረው እያሉ ሁለት ሰዎች ሞተው ወደ ቀብር ሲወስዷቸው በስውር በእግዚአብሔር ስም ጸልየው ከሞት አስነስተዋቸዋል። ይህ ተአምር የተደረገው በአክሱም ጽዮን ውስጥ ነው። ይህንን የአቡነ ዓብየ እግዚእ ቅድስና የገለጹት አቡነ ብእሴ እግዚእ ናቸው።
    3- በተጨማሪም ኤልያስ በመጎናጸፊያው ዮርዳኖስን ወንዝ መትቶ ከኤልሳዕ ጋር በደረቅ እንደተሻገሩ እና ሙሴ የኤርትራን ባህር ከፍሎ እስራኤላውያንን እንዳሳለፋቸው ሁሉ ጻድቁ በነበሩበት ወቅት የተከዜን ወንዝ ሞልቶ ብዙ ነጋድያንና አረማውያን ተጨንቀው እያሉ የተከዜን ወንዝ በመባረክ ውሃዉን አቁመው እንዲሻገሩ አድርገዋል።
(ነገ ካልዕ 1:7-10፣ ዘዳ 14:10-30)
ይህንን ድንቅ ተአምር የተመለከቱ ከ 900 በላይ የሚሆኑ እስላሞች: የእግዚአብሔርን ቸርነትና የጻድቁን ድንቅ ሥራ በማድነቅ ወደ አባታችን ዓብየ እግዚእ በመቅረብ ተጠምቀው ወደ ክርስትና እምነት ተመልሰዋል።
ጻድቁ አባታችን አቡነ ዓብየ እግዚእ ኢልክን በተባለ ከመቀሌ 10 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ሱባኤ ይዘው ይጸልዩ ነበር። በዚህ ስፍራም በስማቸው በፈለቀው ጠበል ብዙ የካንሰር (የነቀርሳ) በሽታ ታማሚዎች እየዳኑ ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ መድኃኒት ታጥቶለት በዚህ ደዌ ለሚማቅቁት በሽተኞች የዚህ ቅዱስ ጻድቅ ጠበል በእምነት መጥተው ለሚጠመቁት ሁሉ ፍቱን መድኃኒት ስለሆነ ወጥተው በመጠመቅ ከበሽታቸው እንዲፈወሱ እግረ መንገዳችንን ሳንጠቁም አናልፍም።
ጻድቁ አባታችን አቡነ ዓብየ እግዚእ ከማረፋቸው በፊት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ የተገለጹበት ቦታ ከምርፋቁ በላይ ባለው ተራራ ላይ ይገኛል።
ቅድስት ሥላሴ የገቡላቸው ቃል ኪዳንም -- በስምህ የዘከረ፣ የመጸወተ፣ ገድልህን የሰማ፣ ቤተ ክርስቲያንህን ያሳነጸ፣ በዚህ ቦታ መጥቶ የጸለየውንና የቆረበውን እስከ 30 ትውልድ እምርልሃለሁ ብሏቸዋል። የተሰቀልኩባት፣ የተቀበርኩባት የቀራንዮ፣ የእናቴ የማርያም እንዲሁም የቅዱሳኑን መቃብር አፈር በዚህ ቦታ ስለበተንከው ቦታው እንደ ኢየሩሳሌም ይሁንልህ ብሎአቸዋል።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ በጾምና በጸሎት፣ በትምህርት እንዲሁም የክርስቶስን ወንጌል በማስፋፋት፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽ ሃይማኖታዊ ገድላቸውንና ሩጫቸውን ከፈጸሙ በኋላ በ 190 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም መንግሥተ ሰማያት ተሸጋግረዋል።
የጻድቁ መቃብር ያለው በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ ውስጥ ነው። ግንቦት 19 ቀን በገዳሙና በስማቸው በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በታላቅ መንፈሳዊ አከባበር ይከበራል።
    የጻድቁ በረከት በጸሎትና ረድኤት ካንዣበበው መከራ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን አሜን !!!

Friday, March 13, 2015

አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2





    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን
  1. አርባ መአልትና አርባ ሌሊት
  2. ጾም የሚሉት ናቸው፡፡

በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/

“ወላምድኅረ ተፈጸመ ለአዳም ፵ መዋዕል በምድር ኀበ ተፈጥረ አባዕናሁ ውስተ ገነተ ኤዶም ኩፋ.9፥12 ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደገነት አስገባነው፡፡ ሔዋንንም በሁለት አርባ ማለትም በሰማኒያ ቀኑዋ ወደገነት አስገቧት ኩፋ.4፥12

በተጨማሪም አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔር ካፈረሰ በኋላ ዲያብሎስ በአቋራጭ መጥቶ አስወጣው እንጂ ሱባኤ የገባው ለአርባ ቀናት ነበር፡፡ ይህን አርባ ቀን የሰው ልጆች ከስህተት በኋላ በቀንም ሆነ በዓመት ለጾም፣ ለሱባኤ፣ ከዚያ አልፎ ለመቅጫነት አግልሏል፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው የሰው ልጅ በንፍር ውኃ የተቀጣው አርባ መአልትና ሌሊት ነበር፡፡ “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናም አዘንማለሁና የፈጠርሁትንም ፍጥረት በምድር ላይ አጠፋለሁና ዘፍ.7፥12 “የሰማይ መስኮቶች ተከፈቱ ዝናቡም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ” ዘፍ.7፥12

በዚህ ዐይነት አርባ ቀን እግዚአብሔር ሰውን እንደቀጣበት እናያለን፡፡ መቅጣት ብቻ ሳይሆን በዚህ የአርባ መአልትና የአርባ ሌሊት ዝናም ምድርን ከበዛባት ርኲሰት አጥቧታል፡፡ ምክንያቱም የጥምቀት ምሳሌ ነውና፡፡ ማየ አይህ /የጥፋት ውኃ/ የጥምቀት ምሳሌ ለመሆኑ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡” 2ጴጥ.3፥20ና21

አሁንም ከዚሁ ሳንርቅ የመርከቧ መስኮቶች የተከፈቱት በአርባ ቀን መሆኑን ይገልጻል፡፡ “ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ” ዘፍ.8፥6 መርከቧ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት ያደረጉት ጉዞ አርባ ዓመት እንደፈጀ ተጽፏል፡፡ ይህም መንገድ ደግሞ የአርባ ቀን መንገድ ነበር በእግዚአብሔር ቁጣ ወደ አርባ ዓመታት ተለወጠ እንጂ፡፡ “በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ ዓመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ” ዕብ.3፥7-19 ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎታል፡፡

እስራኤል አርባ ዘመን መና ከደመና እየወረደላቸው ተመግበዋል፣ ውኃ ከአለት እየፈለቀላቸው ጠጥተዋል፡፡ ሲያምጹም ተቀጥተዋል፡፡ ሙሴ ወንድሞቹን እስራኤልን ለመጎብኘት የመጣው በአርባ ዓመት ነበር “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ የሥራቸውን መከራ ተመለከተ” ዘፀ.3፥11 ሐዋ.7፥23 የተሰደደውም በዚሁ እድሜው ነው፡፡ በምድያም በግ በመጠበቅ አርባ ዘመን ኖሯል እንደገና እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዲያወጣ እግዚአብሔር የላከው በአርባ ዘመን ነበር፡፡ “አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ ታየው፡፡ ዘፀ.3፥30

ይህም ብቻ አይደለም ሙሴ ለዚህ አገልግሎት በተመረጠበት ጊዜ በሲና ተራራ አርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል “ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ቆየ” ዘፀ.24፥19 ዝም ብሎ ሥራ ፈትቶ አይደለም የቆየው እየሠራ ነው ሥራውም ጾም ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው በዚያም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበር አልበላም አልጠጣም” ዘፀ.34፥27 እየጾመ ነበር ማለት ነው በዚህ ጾሙ ሙሴ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች ተቀብሎበታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከንቱ ሳይሆን ዋጋ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ የኤልያስ ጉዞ አርባ ቀን አርባ ሌሊት እንደነበረ ተጽፏል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና የምትሔድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው ተነሥቶም በላ ጠጣ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሔደ” 1ነገ.19፥4-8

ሕዝቅኤል አርባ ቀን ጾሞ 600 ሙታን አስነሥቷል፡፡ እዝራ ሱቱኤል አርባ ቀን ጾሞ የጠፋ መጻሕፍትን መልሷል አብረው የነበሩ አምስት ሰዎች ቀን ቀን ይጽፋሉ ማታ ማታ ጥቂት እህል ውኃ ይቀምሱ ነበር እዝ.ሱቱ.13፥23-25 ጌታችን በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል ሉቃ.2፥22 ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2 በተነሣ በአርባኛው ቀን ወደሰማይ አረገ ሐዋ.11፥10 ሰው በተጸነሰ በአርባ ቀኑ ተስዕሎተ መልክዕ ይፈጸምለታል፡፡ “በአርባ ቀን ትሾመዋለህ” እንዲል ቅዱስ አትናቴዎስ ወንድ በተወለደ በአርባ ቀኑ ሴትም በ80 ሁለት አርባ ክርስትና ይነሣል፡፡ ሰው በአረፈ በአርባ ቀኑ ጸሎተ ፍትሐት ይደርስለታል፡፡ ሰው በአርባ ቀን ጸሎት ተክሊል ይደርስለታል ፍት.ነገ. እን.24 ገጽ 322

አርባ ቀን ይህን ያህል ምስጢር ያለው ቀኑ ነው ጌታችን ለምን? አርባ ቀን ጾመ ስንል ከላይ ያየናቸው አበው ነቢያት ብዙውን ጊዜ የጾሙት አርባ ቀን ነው፡፡ ቢቀንስ አጎደለ ከፍ ቢያደርግ አበዛ ብለው አይሁድ የነቢያትን ሕግ አፈረሰ በማለት ትምህርቱ አንቀበልም ባሉ ነበርና ይህን ምክንያት ለመንሳት አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ፡፡ እስራአል 40 ዓመት ተጉዘው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ እናንተም 40 ቀን ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የጥፋት ውኃ በምድር አርባ ቀንና ሌሊት ዘነመ ምድር ነጻች ሰው አርባ ቀንና ሌሊት ቢጾም ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል ሲለን ነው፡፡ ጾም ለርስት ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃ ከኀጢአት የሚያነጻ እንደሆነ ሊያስተምረን በኦሪት በተጾመው ቁጥር ጾሞ ሥርዓትን ሰጠቶናል፡፡

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17

መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡

መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስፈጽመን
                                                                                                          በመ/ር ምሥጢረሥላሴ ማናየ

ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል


   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
 ቀውስጦስ ዘመሐግል ፥ ኢትዮጵያዊ አባቱ ገላውዲዎስ(ዘርዓ ኢየሱስ)
እናቱ እብነ ጽዮን ይባላሉ። በግንቦት 1 ቀን ተወለደ ሲወለደም ይኩኖ አምላክ ተባለ
ሀገሩ ሽዋ መሐግል ይባላል። ሲጠራም ቀውስጦስ ዘመሐግል ተብሎ ይጠራል።
ይህ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት እግዚእ አርያና እብነ ጽዮን ታላቅና ታናሸ ናችው።
ይህ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሙአቸው ከ12 ንብረ ዕድ ወስጥ አንዱ ሲሆን ደብረ ሊባኖስንም የሚያጥንበትም ወር በመጋቢት ወር ነበር።
ቁጥሩም ሲሾምኛ12 ነው ሕዝቡ አጥብቆ የሚወደውና የሚያከበረው አባት ነበር።
ይህንን ጻድቅ አመደ ጽዮን የተባለው ሰው በ11አሽከሮች አስይዞ አብዮ ከተባለው ቦታ ወደ አንሳሮ
አሰወሰደወና ከዚያም ወደ አርሲ ፈነታሌ ተራራ ጫካ ሄዶ 47 ሺህ 300አጋንነትን ከሰማይ እሳታ አውርዶ አቃጥሎአቸዋል በጸሎቱ።ይህ ጻድቅ ልደቱ ከእመቤታችን  ልደት እረፍቱ  ከእመቤታችን እረፍት ጋር ሲሆን እረፍቱም በጥር 21 ቀን ነው።    የጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ በረከት ይደርብን!!!!!

Thursday, February 12, 2015

ታላቁ አባት ቅዱስ ዻውሊ

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
=>አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ:: "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ::
+"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል::
*በእርግጥም ከአንተ 20 ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ
*በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ
*ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኩዋ የማትመጥነው
*በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት
*ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው" ብሎት ተሠወረው::
+ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ:: እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ:: በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)::
*በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው:: ለ80 ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል:: ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ: ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ (ማለትም ሽቻለሁና ላግኝ: ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ)" ሲል አሰምቶ ተናገረ::
+ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው:: መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ:: ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት::
+ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ዻውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር: ይመስገን" ሲል ፈጣሪውን ባረከ:: ቅዱስ ዻውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኩዋን ደህና መጣህ" አለው:: 2ቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ::
+" ቅዱስ ዻውሊ ማን ነው? "+
=>ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት:: ለምሳሌ:-
*የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ
*የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
*የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን እና
*የመጀመሪያውን ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ዻውሊን ማንሳት እንችላለን::
+ቅዱስ ዻውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ: በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው:: ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ:: ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ዼጥሮስን ወልደዋል:: 2ቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው:: ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም::
+ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ዼጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለዻውሎስ (ዻውሊ) መስጠቱ ነበር:: ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ::
+ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ዻውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው:: በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ:: በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል" ሲል ነገረው::
+በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ዻውሊ ሐሳብ ተለወጠ:: ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ:: በመቃብር ሥፍራ ለ3 ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው::
+በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት:: እየጾመ ይጸልይ: ይሰግድ ገባ:: ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት: ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለ80 ዓመታት ኖረ:: (አንዳንድ ምንጮች ግን ለ90 ዓመታት ይላሉ) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በሁዋላ ነው::
+ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የ2 ቀናት ቆይታም ቅዱስ ዻውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል:: በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል::
+ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል:: 80 ዓመት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች::
<< ጻድቅ: ቡሩክ: ቀዳሚው ገዳማዊ: መላእትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ዻውሊ ክብር ይገባል >>
+"+ ገዳማዊ ሕይወት +"+
=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::
+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::
+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::
+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::
+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::
+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::
+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::
=>አምላክ በበረከታቸው ይባርከን::
=>የካቲት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ኁሉ አባት)
2.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ-ግብፅ)
3.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት ጠበቃ)
4.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
5.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ
=>+"+ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: +"+ (ዕብ. 11:35-38)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
writing by dn yordanos abay

ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር)


    
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
=>ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው::

+ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት ካልዕ / ሁለተኛው ሊቀ ሰማዕታት ሲሉ ይገልጹታል:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር 'አሮስ' የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት: እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር::

+አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል: 'እንስሳ ተያዘልን' ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: 2 ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር::

+እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ: ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ: ወገባቸው እንደ ሰው: ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስል::

+እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና:- አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው::

+"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት" አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ 2ቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት::

+ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ-የአብ ወዳጅ" ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን ልጁንና 2ቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ::

+አበው ካህናት እሱን 'ኖኅ': ሚስቱን 'ታቦት': ልጁን ደግሞ 'መርቆሬዎስ' ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ-የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው::

+ከዚያም ደስ እያላቸው: ክርስቶስን እያመለኩ: ነዳያንን እያሰቡ: ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ 'ካላመጣሃቸው' አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ::

+ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን 2ቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::

+በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን 'ላግባሽ' ስላላት የ5 ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው::

+እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በሁዋላ ግን በሕጻኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ::

+በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ: ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::

+በጦርነትም እጅግ ኃያል: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ: የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸ ውዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ::

+ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው::

+በማግስቱም 'ምን ይሻላል?' ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቁዋቁዋማቸዋለሁ" ቢል ሳቁበት::

+እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ: በሰላም ሒዱ" ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ ::

+ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ 'ድሉ የጣዖቶቼ የነ አዽሎን ነው' በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ::

+በ3ኛው ቀንም 'ለጣዖት ሠዋ' የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው::

+"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ (ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ)" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ: የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው::

+ያም አልበቃ: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት:-
"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም:
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም:
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም" ያሉት::

+ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ: በግርፋት: በእሳት: በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር 25 ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::

+እርሱ ካረፈ በሁዋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ200 ዓ/ም እንደ ተወለደ: በ220 ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ225 ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::

=>ሰማዕቱ በዚህች ዕለት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል::
<<የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው>>

=>አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን:: ከርስቱም አያናውጠን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ቅዱስ ኄኖክ ነቢይ



    
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
=>ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኄኖክ ከአባታችን አዳም 7ኛው ደግ ሰው ሲሆን አባቱ ያሬድ ይባላል:: በእርግጥ ቅዱሱ ሚስት አግብቶ ማቱሳላና ሌሎች ልጆችን ወልዷል:: አካሔዱ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ነበርና ሞትን አላየም::

+ነቢዩ ኄኖክ በ1486 ዓ/ዓ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (መጽሐፈ ኄኖክን) ጽፏል:: የዚሕ መጽሐፍ ባለቤት ደግሞ ሃገራችን ናት:: ቅዱሱ ብዙ ሰማያዊ ምሥጢሮችን ተመልክቷል::

+የእርሱ ሞትን አለመቅመስ በአቤል ሞት የፈሩትን ውሉደ አዳም በተስፋ አነቃቅቷቸዋል::
"በአቤል አፍርሆሙ:
ወበኄኖክ አንቅሆሙ" እንዳለው ሊቁ:: (ዘፍ. 5:24, ኄኖክ. 4:1)

+" ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ "+

=>ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ በቀድሞዋ ሮሜ ግዛት ውስጥ የጦር አለቃ: የከተማዋ መኮንን እና እጅግ ባለጸጋ የነበረ ሰው ነው:: ግን በእምነቱ አረማዊ: በስሙም 'ቂዶስ' ተብሎ የሚጠራ ነበር:: ምክንያቱ ባይገባውም እጅግ ቅን: ደግና ለምጽዋት የሚፋጠን ነበር::

+እግዚአብሔር ታዲያ ይህን ሰው ወደ ቀናው ጐዳና (ወደ ክርስትና) ሊመራው ወደደና ተገለጠለት:: ቂዶስ ለአደን ወጥቶ ዋሊያ ሲያድን (ያኔ ዋሊያ ከዓለም አልጠፋም ነበር:: ዛሬ ግን ያለ ኢትዮዽያ ውስጥ ብቻ ነው) መድኃኒታችን በዋሊያው ራስ ላይ የብርሃን መስቀልን ገልጦ ተነጋገረው::

+ክርስቲያን እንዲሆንና መከራንም እንዲታገሥ አዘዘው:: ቂዶስም ወደ ቤቱ ተመልሶ ለሚስቱና ለ2 ልጆቹ የሆነውን ነገራቸው:: ክርስትናን ተምረው ሲጠመቁ አበው ቂዶስን 'ኤዎስጣቴዎስ' አሉት::

+ከዚህ በሁዋላ ክርስቶስን እያመለኩ ቆይተው ረሃብ በሃገሪቱ መጣ:: ቅዱሱ ምንም መኮንንና ሃብታም ቢሆንም ገንዘቡ በምጽዋት በማለቁ ባሮቹ ተበትነው ደሃ ሆነ:: የሚበላውንም አጣ:: ከሥጋዊ ሥልጣኑም ተሻረ:: እርሱ ግን ይህንን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ታገሠ::

+ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ረሃቡ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ሚስቱንና 2 ልጆቹን ይዞ ስደት ተነሳ:: ለጉዞ በተሳፈረበት መርከብ የሚከፍለው ገንዘብ ስላልነበረው ሚስቱን ቀሙት:: ልጆቹን ይዞ እያለቀሰ ከሌላ ወንዝ ደረሰ::

+እንዳይሳፈር መርከበኞቹ ልጆቹን ሊቀሙት ስለሆነ ለመዋኘት ወሰነ:: አንዱን ልጁን ተሸክሞ አሻግሮት ሲመለስ ትቶት የሔደውን ልጁን አንበሳ ወስዶት አገኘው:: እያለቀሰና እየቸኮለ ወደ 2ኛው ቢመለስ ደግሞ ይህኛውንም ተኩላ ወስዶት ነበር::

+ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ አንጀቱ በሃዘን ተቃጠለ:: በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ መራራ ለቅሶን አለቀሰ:: ነገር ግን ኢዮባዊ ሰው ነውና "እግዚአብሔር ሰጠ: እርሱም ነሣ" ብሎ በእንባ ተጉዋዘ:: በአንዲት ሃገርም ባርነት ተቀጥሮ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ኖረ::

+ከብዙ ዓመታት በሁዋላ የረሃቡ ዘመን አልፎ የቅዱሱ ወዳጅ የነበረ ሰው በሮም ላይ በመንገሱ ወታደሮችን "ወዳጄን ኤዎስጣቴዎስን ፈልጋችሁ አምጡ" ብሎ ላካቸው:: ከአድካሚ ፍለጋ በሁዋላ ያ ደግ ጌታቸው በባርነት ተቀጥሮ: ተጐሳቁሎ አገኙት::

+ፈጥነው ወደ ሮም ከተማ ወስደው በቀደመ ክብሩ ላይ አኖሩት:: እርሱ ግን ሃዘንተኛ ነበር:: ከቀናት በሁዋላም አዳዲስ ወታደሮችን ከተለያየ ቦታ መለመለ:: ከእነዚያም መካከል መልካም የሆኑትን 2ቱን አለቆች አደረጋቸው:: ሁለቱ ደግ ወጣቶችም በጣም ይዋደዱ ነበር::

+አንድ ቀን እኒህ 2 ወጣቶች ወይን ሊገዙ ሔደው ጠባቂዋን 'ስጭን' አሏት:: ሰጥታቸው እዚያው ያወራሉ:: አንደኛው "ታሪኬን ልንገርህ" ይለዋል:: "እሺ" ሲለው "እኔ ወላጆች የሉኝም:: ሕጻን እያለሁ በሃገራችን ረሃብ መጥቶ: ሃብታችን አልቆ ስንሰደድ እናታችን መርከበኛ ወሰዳት:: አባቴ ወንድሜን ሲያሻግረው እኔን አንበሳ ወስዶ ከአንድ መንደር ጣለኝ" አለው::

+ባልንጀራው ገርሞት "ታሪካችን ተመሳሳይ ነው:: እኔም እንዳንተ ሆኜ: አባቴ ሲያሻግረኝ ተኩላ ወስዶ አንድ መንደር ውስጥ ጣለኝ" አለው:: ይህንን ትሰማ የነበረችው ወይን ጠባቂ "ልጆቼ!" ብላ ጮሃ አለቀሰችና ደነገጡ:: እርሷም ቀርባ አቅፋቸው እያለቀሰች ነገሩን ሁሉ አስታወሰቻቸው::

+ይህን ጊዜ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰምቶ ደረሰ:: ከረጅም ዓመታት በሁዋላ ሚስቱ አትክልት ጠባቂ ሁና ማንም ሳይነካት: 2 ልጆቹንም አገኘ:: እያለቀሱ ተቃቀፉ:: እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመሰገኑት:: የሰማ ሁሉ "ዕጹብ! ዕጹብ!" አለ::

(እኛ የምናመልከው ጌታ እንዲህ ነው:: ክብር ለእርሱ: ለድንግል እናቱና ለወዳጆቹ)

+ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ በቀሪ ዘመናቸው ቤተ ክርስቲያን አንጸው በምጽዋት ኑረዋል:: በመጨረሻም ዘመነ ሰማዕታት መጥቶ "ክርስቶስን አንክድም" በማለታቸው ብዙ ተሰቃይተው 4ቱም ሰማዕት ሆነዋል::

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ቅዱስ ዮናስ ነቢይ


          

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አማላክ አሜን::
=>ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (ነገ) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

+ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በሁዋላ: ቅ.ል.ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

+"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ ተርሴስ ኮበለለ::

+ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኩዋን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሸት እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

+ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው:: "ወበከመ ነበረ ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12:39)

+ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

+እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

+ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

+የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቁዋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በሁዋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

=>አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

=>በጾመ ነነዌ ስለ ሃገርና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት መጸለይ ይገባል::

=>+"+ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:39)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Ephrem the Syrian




Our Righteous Father Ephrem the Syrian was a prolific Syriac language hymn writer and theologian of the 4th century. He is venerated by Christians throughout the world, but especially among Syriac Christians, as a saint. His feast day in the Orthodox Church is January 28.

St. Ephrem the Syrian

Ephrem was born around the year 306, in the city of Nisibis (the modern Turkish town of Nusaybin, on the border with Syria). Internal evidence from Ephrem's hymnody suggests that both his parents were part of the growing Christian community in the city, although later hagiographers wrote that his father was a pagan priest. Numerous languages were spoken in the Nisibis of Ephrem's day, mostly dialects of Aramaic. The Christian community used the Syriac dialect. Various pagan religions, Judaism and early Christian sects vied with one another for the hearts and minds of the populace. It was a time of great religious and political tension. The Roman Emperor Diocletian had signed a treaty with his Persian counterpart, Nerses in 298 that transferred Nisibis into Roman hands. The savage persecution and martyrdom of Christians under Diocletian were an important part of Nisibene church heritage as Ephrem grew up.

St. James (Mar Jacob), the first bishop of Nisibis, was appointed in 308, and Ephrem grew up under his leadership of the community. St. James is recorded as a signatory at the First Ecumenical Council in 325. Ephrem was baptized as a youth, and James appointed him as a teacher (Syriac malpânâ, a title that still carries great respect for Syriac Christians). He was ordained as a deacon either at this time or later. He began to compose hymns and write biblical commentaries as part of his educational office. In his hymns, he sometimes refers to himself as a "herdsman" (`allânâ), to his bishop as the "shepherd" (râ`yâ) and his community as a "fold" (dayrâ). Ephrem is popularly credited as the founder of the School of Nisibis, which in later centuries was the centre of learning of the Assyrian Church of the East (i.e., the Nestorians).

In 337, emperor Constantine I, who had established Christianity as the state religion of the Roman Empire, died. Seizing on this opportunity, Shapur II of Persia began a series of attacks into Roman North Mesopotamia. Nisibis was besieged in 338, 346 and 350. During the first siege, Ephrem credits Bishop James as defending the city with his prayers. Ephrem's beloved bishop died soon after the event, and Babu led the church through the turbulent times of border skirmishes. In the third siege, of 350, Shapur rerouted the River Mygdonius to undermine the walls of Nisibis. The Nisibenes quickly repaired the walls while the Persian elephant cavalry became bogged down in the wet ground. Ephrem celebrated the miraculous salvation of the city in a hymn as being like Noah's Ark floating to safety on the flood.

One important physical link to Ephrem's lifetime is the baptistry of Nisibis. The inscription tells that it was constructed under Bishop Vologeses in 359. That was the year that Shapur began to harry the region once again. The cities around Nisibis were destroyed one by one, and their citizens killed or deported. The Roman Empire was preoccupied in the west, and Constantius and Julian the Apostate struggled for overall control. Eventually, with Constantius dead, Julian began his march into Mesopotamia. He brought with him his increasingly stringent persecutions on Christians. Julian began a foolhardy march against the Persian capital Ctesiphon, where, overstretched and outnumbered, he began an immediate retreat back along the same road. Julian was killed defending his retreat, and the army elected Jovian as the new emperor. Unlike his predecessor, Jovian was a Nicene Christian. He was forced by circumstances to ask for terms from Shapur, and conceded Nisibis to Persia, with the rule that the city's Christian community would leave. Bishop Abraham, the successor to Vologeses, led his people into exile.

Ephrem found himself among a large group of refugees that fled west, first to Amida (Diyarbakir), and eventually settling in Edessa (modern Sanli Urfa) in 363. Ephrem, in his late fifties, applied himself to ministry in his new church, and seems to have continued his work as a teacher (perhaps in the School of Edessa). Edessa had always been at the heart of the Syriac-speaking world, and the city was full of rival philosophies and religions. Ephrem comments that Orthodox Nicene Christians were simply called "Palutians" in Edessa, after a former bishop. Arians, Marcionites, Manichees, Bardaisanites and various Gnostic sects proclaimed themselves as the true Church. In this confusion, Ephrem wrote a great number of hymns defending Orthodoxy. A later Syriac writer, Jacob of Serugh, wrote that Ephrem rehearsed all female choirs to sing his hymns set to Syriac folk tunes in the forum of Edessa.

After a ten-year residency in Edessa, in his sixties, Ephrem reposed in peace, according to some in the year 373, according to others, 379.

አቡነ ታዴዎስ_ዘጽላልሽ


        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

እንደዚሁ አንድ ሰው በቅዱሳን ምልጃ መጠቀም የሚችለው በቅዱሳኑ አማላጅነት ማመን ሲችል ብቻ ነው፡፡ነገር ግን ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆቿ እንዳይጠፉ ዜጋ ለሆነውም ላልሆነውም የቅዱሳኑን አማላጅነት ዘወትር ትሰብካለች ፡፡ቅዱሳን ከእረፍተ ሞታቸው በኋላ እንደቀደመው በአጸደ ስጋ እያሉ ሲያደርጉ እንደነበረው የመጾም ፤የመስገድ ፤ ልዬ ልዬ መከራዎችን መቀበል ባይኖርባቸውም አስቀድመው ባደረጉት ተጋድሎ በተሰጣቸውን የማማለድ ጸጋ አምነው ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች እንደሚድኑበት እንዲህ ተብሎ ነው::  ትውልድ ሀገራቸው ጽላልሽ (ዞረሬ) ነው። አባታቸው ሮማንዮስ እናታቸው ማርታ ይባላሉ። አባታቸው ሮማንዮስ ቄስ ነው። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ናቸው።
በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ በጽላልሽ ረሀብ ፀንቶ ነበር። እሳቸው ግንቦት ፳፫ ቀን በመንፈቀ ሌሊት በልብሰ ብርሃን ተጠቅልለው ተወለዱ። ቤታቸው በበረከት ተመላ። ለሀገሬው ዝናብ ዘንቦለት ህዝቡ ከፃድቁ እናትና አባት የተመፀወቱትን ከፍለው ዘሩ።
አቡነ ታዴዎስ በተወለዱ በ፵ ቀናቸው ሐምሌ ፪ ቀን ሲጠመቁ የተዘራው እህል አንድ ሳይቀር አፍርቶ ተገኝቷል።

ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ ሰጥተዋቸው ሲማሩ አደጉ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት (ወላይታ) ተሻግረው መተሎሚን አስተምረው “በእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ፀሎት መተሎሚን በሃይማኖት ወልጄዋለሁ። በምግባር አሳድጌዋለሁና እህትህን ይዘህ በቶሎ ና፤” ብለው ላኩባቸው።
እህታቸው ትቤጽዮን ትባላለች። የመተሎሚን ወንድም ዝግናን አግብታ አባ ኤልሳዕን ወልዳለች። ከባሏ ተጣልታ ነበርና እሷን ከባሏ አስታርቀው እሳቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን እያገለገሉ ፱ አመት ኖረዋል።

በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ እሳቸውም ወደ ጽላልሽ ተመልሰው ስለነበር አፄ ይኩኖ አምላክ እንድትመክረኝ እንድትገስፀኝ ከቤቴ ተቀመጥ ብለው ከቤተመንግስት አስቀመጣቸው።
ሰይጣን ለፀብ ለምቀኝነት አያርፍምና ጠላ ቤቷን ክፉ የሚገድል ሽታ አሸተታትና ሞተች። አባ ታዴዎስ ወንዝ ገብተው ሲፀልዩ ሙቷ ተነሥታለች። ከዚህ በኋላ ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል ብለው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመለሱ።

አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ጽጋጋ (ጅጅጋ) ሂድ አሏቸው። ለምን ቢሉ? አባ አኖሬዎስ ሄደው ሲያስተምሩ ያገሬው ሰዎች ደብድበው አስረዋቸው ነበርና እሳቸውን ለማሰወፈታት ነበር።
የአካባቢው ንጉስ መዩጥ ይባላል። በነፋስ ሰረገላ ተጭነው ሄደው ከፊቱ ወርደው ሲቆሙ ደንግጦ ከሰማይ መላእክት ነህ ወይስ ከሰው ወገን? ቢላቸው። እኔ ከሰው ወገን ነኝ አሉት። ክርስትናንም አስተማሩት ጋኔን ከእሳት ላይ ጥሎት ሲሰቃይ የሚኖር ልጅ ነበረው አድነውለታል።
ይህን አይቶ አምኖ ሕዝቡም እንዲያምኑና ክርስትናን እንዲቀበሉ አዋጅ ነገረ።

እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ ፳፭ ግመል በመርፌ ቀዳዳ በተአምራት አሳልፈው በማሳየታቸው አፍጃል የሚባል ያንድ ባለጠጋ ልጅ በምትሐት እንደሚያደርጉት አድርጎ በመናገሩ ከግመሎቹ አንዲቱ ረግጣው ሞተ፤ ይህን ሙሳ የሚባል ልጅም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን «አልዓዛርን ከሙታን በአስነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ና ተነስ» ብለህ ይህንን መቋሚያዬን ወስደህ ከመቃብሩ ላይ አኑር ብለው በአፍጃል ሰጥተውት እንዳሉት ቢያደርግ አፈፍ ብሎ ተነስቷል።
ይህን አይተው ህዝቡ ሁሉ አምነዋል። ከዚህ በኋላ ሙሳን ሙሴ ብለው ሊቀ ካህናት አድርገው ፲፪ አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው አኖሬዎስን ይዘው ተመልሰዋል።

አቡነ ተክለሃይማኖትም ከንጉሱ ተማክረው ሊቀካህናት ዘጽላልሽ ብለው ሾመዋቸዋል።
ንጉስ ዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አድሮበት የአባቱን ቅምጥ ቢያገባት ሄደው ገሰፁት። በዚህ የተናደደች የንጉሱ ሚስት የኋሊት አሳስራ ከጥልቅ ገደል አሰጣለቻቸው።
በዚህ ጊዜ የመቶ ሃያ አመት አረጋዊ ነበሩ።

የታዘዘ መልአክ ገብረ እግዚአብሔርና ውቢት የተባሉ ደጋግ ሰዎችን አስነስቶ ስጋቸውን ወስደው ከበዓታቸው ቀብረው የተሰጣቸውንም ቃል ኪዳን በዳግማዊ አፄ ዳዊት ዘመን በህዝቡ ፊት መስክረዋል።
ንጉስ ዳዊትም ዜና ገድላቸውን አጽፈዋል፤ ስጋቸውንም ወደ ከተማቸው በክብር አፍልሰው በተቀደሰ ስፍራ አኑረውታል።

የፃድቁ አባታችን እረድሄት በረከት ይደርብን አሜን!!!
writing by sisay poul

Friday, January 16, 2015

ጻድቁ አቡነ ስነ ኢየሱስ

     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
አባታችን ጻድቁ አቡነ ስነ ኢየሱስ የትውልድ አገራቸው ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ልዩ ቦታው ልብሆ  ከአባታቸው አብርሃም ከ እናታቸው አስካለ ማርያም ይባላሉ ጻድቁ ስነ ኢየሱስ በምናኔ ገዳመ ዋፊት ገብተው ማህበሩን ሲያገለግሉ ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ከ አቡነ ዮሐንስ እጅ ምንኩስናን ተቀብለዋል:: ከዚያም በቅዱስ ገብርኤል መሪነት በእግዚአብሄር ፈቃድ ወደ ሰሜን ጎንደር አርማጭሆ በመሄድ የወርቅ ለብሆ ቅዱስ ያዕቆብ ዝግሙድ የተባለው ገዳም እንደገና አቅንተው በተጋድሎ ለብዙ ጊዜ ሲጋደሉ ኖረዋል ጻድቁ ስነ ኢየሱስ በህይወታቸው ዘመን ሁሉ በትሩፋትና በተጋድሎ ሰውነታቸውን ከአጥንታቸው ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ስጋደሉ መኖራቸው በገድላቸው ተዘግቦ ይገኛል በዚህም ክቡር ቅዱስ ዳዊት የጻድቅ ሰው ሞቱ እረፍቱ ነው እንደሚለው መስከረም አንድ ቀን መላከ ሞት ከሰማይ ወደ እሳቸው መቷል:: ጻድቁም እግዚአብሄር በሰጣቸው ፀጋ ወደ እሳቸው መምጣቱን ስለተረዱ ለምን መጣህ ብለው ሲጠይቁት ታዞ መምጣቱን ሲገልፅላቸው የወዳጄ ቅዱስ ገብርኤል የወርና የዓመት በአሉን ሳላከብር አልሄድም በማለት ገዝተው አቁመውታል:: ከቆመበት ሳይነቃነቅ ከመስከረም 1 ቀን እስከ ታህሳስ 19 ቀን እንደቆመ ሳይንቀሳቀስ ዝክራቸውን ዘክረው እንደፈጸሙ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታህሳስ 19 ቀን ካዕላፍ መላዕክት ከሐዋርያት: ከጻድቃን:ከሰማእታት:ከነእንጦስ ከነመቃርስ:ከደናግል መነኮሳት እንዲሁም  ከእናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በመሆን ከቦታው በመውረድ በአለም የደከመ ሁሉ ለዘላለም ይድናል እንዳለው ወደጄ ልጄ ስነ ኢየሱስ ሆይ ስለ ስሜ መከራ ተቀብለህ እንዳስደሰትከኝ እኔም ደስ ላሰኝህ ልታዘዝህ እነሆ አለሁኝ አላቸው:: ጻድቁም በትህትና እንደ አንተ ቸርነት እንጂ እንደ እኔ ስራ አይደለም ብለው በፍርሀትና በመጨነቅ ወደ ምድር ወደቁ አምላካችንም ጻድቁን አንስቶ የከበረውን ነፍሳቸውን በተቀደሱ እጆቹ ተቀብሎ ስምህን ለጠራ ዝክርህን ለዘከረ በእረፍትህ ቀን እጣን መብራት መባ ላመጣ አንተ ከገባህበት ዘላለማዊ ቤትህ አገባቸዋለሁ:: ቦታህን ሊሳለም የመጣውን ኢየሩሳሌም እንደሄደ እቆጥርለታለሁ:: ሐጢያቱን ለካህን ለመናገር አሳፍሮት የበዛ ሐጢያቱን አባታችን አቡነ ስነ ኢየሱስ 3 ጊዜ ይቅር በለኝ ቢል ሐጢያቱን እደመስስለታለሁ:: ለክብርህ ቀን እንጨት የለቀመውን ውሃ የቀዳውን ከንጹሃን አርድህቶችህ እደምራቸዋለሁ:: በቦታህ ከወደቀው ፍርፋሪ እንኳን በስምህ የወደቀውን ምግብ ቢመገብ ስጋ ወደሙ እንደተቀበለ አደርግለታለሁ:: የእጀ ሰብ ስራይ ተደርጎበት የመቃብርህን አፈር አዋህዶ ቢረጨው ስራዩን እፈታለታለሁ:: በሬም ላምም ቢሆን ቢታመምበት በስምህ ጻድቁ ስነ ኢየሱስ ብሎ ቢማጸን በደልና ሐጢያቱን እደመስስለታለሁ:: አንተን አምኖ ከቦታህ ላይ ቢቀበር ከሰሳ ወቀሳ ሳይኖርበት በክብሬና በመንግስቴ ለዘላለም ከእኔ ጋር ይኖራል:: ቦታህን እየረዳ ያረፈውን እንደ ሰማእቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰማእትነት እቆጥረዋለሁ:: ቦታህን ለአንዲት ቀንም ስያልፍም ቢሆን የረገጠ 12 ትውልዱን እምርለታለሁ::በጉልበቱ በገንዘቡ በእውቀቱ ወጥቶ ወርዶ የሚራዳውን በክብርህ ቀን የሚዘምረውን በእግሩ ደክሞ ቦታህን ረግጦ ያከበረህን ራሱ ድኖ ለወገኖቹ 60 ትውልድ ከሲኦል አወጣለታለሁ ብሎ እውነት እንጂ ሐሰት በማይታበለው ቃሉ ቃል ኪዳን ሰጥቶአቸው በምስጋና በእልልታ በክብር መንግስቱ ወደ ሰማይ አርጓል:: ቅዱሳን ልጆቻቸው በክብር ገንዘው ከቤተመቅደስ ውስጥ በሳጥን የጻድቁ አጽም ይገኛል ዛሬም ምንም በአካለ ስጋ ቢለዩም ከቦታቸው ላይ ለበቁ አባቶች በአካለ ነፍስ በመገለጽ ቦታቸውን አስከብረውት ይገኛሉ::
  ጻድቁ ስነ ኢየሱስ ቀን የሰሩትን  ቤተክርስቲያን ሌሊት እየመጣ ጨለማ ለብሶ ፈላሻ የተባለ ጽረ ቤተክርስቲያን እያፈራረሱባቸው ሲያዝኑና ሲተክዙ እግዚአብሄር ባወቀ በ እግዚአብሄር ፈቃድ ዋልክዳ ከሚባል ቦታ አውሬ አዳኝ ወደገዳሙ በመምጣት አጋዘኗን በጥይት መቷት ደሟን እያዘራች ጻዲቁ ቆመው ከሚጸልዩበት እግራቸው ስር ወድቃለች አዳኙም ፈለጓንና ደሟን ተከትሎ ከወደቀችበት ሲደርስ ጻዲቁ ስነ ኢየሱስ ብርሃን ተጎናጽፎ በሚያስፈራ ግርማ ሲመለከታቸው ፈጥኖ ወደ መሬት ወድቋል:: ጻዲቁም በአበው ስርአት  ሰውም ሆነ አውሬ መግደል ወንጀል ሐጢያት ነው በማለት ገስጸው መክረው አስተምረው ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ አይነት ስራ እንዳይደግምህ ተጠንቀቅ ብለው ከአሳሰቡት በኋላ ለአሁኑ የመታሃትን አጋዘን ፈቅጄልሃለሁ ባርከህ ተጠቀምባት ስሉት አዳኙም ስጋዋን አወራርዶ እንደጨረሰ ታላቅንና ታናሹን ለጻድቁ ሊሰጣቸው ስሞክር እግዛብሄር ያዘዘኝ በአርምሞና በጸሎት እንድጋደል እንጂ ሥጋ በልቼ በመንፈስ ደካማ እንድሆን አይደለም:: አንተ ግን የአንተ ልጆች ለእኔ ልጆች ግዳይ ባደረጉ ጊዜ ታላቅና ታናሽ ለገዳሙ በመስጠት በረከት እንዲቀበሉ ስርአት ይሁንላችሁ ሲሉ ተናግረውታል:: አሁን ግን አንተን የምጠይቅህናንድ ጉዳይ አለኝ ቀን የምሰራውን ማታ የሚያፈርስብኝ ሰጣን ያደረባቸው ፈላሾችን እንድታጠፋልኝ ፈቃድህ ይሁን ሲሉ ጠይቀውታል ጻድቁ ስነ ኢየሱስም ፈጣሪዬን ስባዬ ገብቼ ከጠየኩ በኋላ እኔ ስነግርህ የምገባውን ትዕዛዝ ታደርጋለህ በዚህም መሰረት ሱባዬ ገብተው ሲጨርሱ ያንን አዳኝ ለጻዲቁ ጥቃት  መወጣት የተላከ መሆኑን ስለተረዱ የ እግዚአብሄር ሃይል ታጥቀህ ድል እንደምታደርጋቸው አምላኬ ነግሮኛል አዳኙም ጻድቁ በጸሎት የሰጡትን ግዳጅ በደስታ ተቀብሎ ንቂት ከተባለው ቦታ በድንገት ደርሶዐያነቀ ድል አድርጓቸዋል:; አዳኙም ወደ ገዳሙ በማቅናት ጠላቶቹን ድል በማድረጉ እያበሰረ ከጻድቁ ፊት ደርሳል ጻድቁ ስነ ኢየሱስም እግዚአብሄር በሰጣቸው ጸጋ ድል እንዳደረጋቸው ተመልክተው መነኮሳቱን አሰልፈው በደስታና በዝማሬ ተቀብለውታል:: ጻድቁም ከዛሬ ጀምሮ ከልጆቼ መነኮሳት አንድነት ደምሬሃለሁ እንደ አንድ ሰው ምከር ብለው መካሪያን ተብላል::
     የወርቅ ለብሆ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ ገዳም አመሰራረት
በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በታች አርማጭሆ በሣንጃ ወረዳ በደብረ ሲና ቀበሌ የሚገኝ ገዳም ሲሆን በኢትዮጵያ ከርዕሰ ገዳማት አንዱ ነው በዚህ መሠረት በዮዲት ጉዲት ዘመን ቤተክርስቲያኑ ተቃጥሏል ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለብዙ ዘመን ጠፍ ሆኖ ስኖር ጻድቁ ስነ ኢየሱስ ከገዳመ ዋፊት በመልአኩ ቅዱስ ገብር ኤል እየተመሩ በራዕይ አምደ ብርሃን ከሰማይ ወደ ምድር ከሚያርፉበት ቦታ ተተክሎ አይተዋል:: ተጋድሎህን እግዚአብሄር በዚህ ቦታ  በስምህ ብዙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች የሚወለዱበት አጽምህ የምፈልስበት ቦታ መሆኑን ስለተረዱ በ 1210 ዓ/ም በአጼ ይስሐቅ ዘመነ መንግስት አባታችን ስነ ኢየሱስ ይህን ገዳም ገድመውታል:: ከተገደመጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 797 ዓመታትን አስቆጥራል:: ጽድቁ ስነ ኢየሱስም አቦ ገዳም እየተባለ ከሚጠራው ቦታ ቆመው ሲጸልዩ ከቆሙ ሳይቀመጡ እጃቸውን ከዘረጉ ሳያጥፉ ለ 7አመት ለድህነት ምክንያት የሆነ ፀበል ፈልቆላቸው በጸበሉ አጋንንት ያደረባቸውን የተለያዩ ደዌ ያለባቸውን ሁሉ እየተፈወሱበት ይገኛል:: የፈጣሪኢያቸውን ቸርነት  እያመሰገኑ ወደ ሰሃአራአ ገዳም በመሄድ ለ 3 አመት በሱባኤ እንደቆዩ ቦታው ለልጆቻቸው ጾር ላሳቀቃቸው ደዌ ለጸናባቸው ማረፊያ በህርመት ፆም ለቆዩ የሚገድፉበትን መሆኑን ተረድተው ለ3ኛ ጊዜ ገድመውታል:: በገዳሙ ውስጥ በግራኝ ጊዜ 320 መነኮሳት በአቦ ገዳም 83 መነኮሳት ሰሀራ ገዳም 96 መነኮሳት ተሰይፈው አልፈዋል:: ቦታውም የሰማእታት ቦታ እየተባለ ይጠራል ጻድቁ ስነ ኢየሱስ በገዳሙ ውስጥ ለ 300 አመት ከ አንዲት የምሶብ ቅርጽ ካላት ድንጋይ ላይ ቆመው ጸልየዋል ከቆሙበት ድንጋይ ስርም 2ኛ ጸበል ፈልቆቸው ብዙ ገቢረ ተዐምር ሲደረግበት እንደነበር በገድሉ ተመዝግቦ ይገኛል በጸበሉም በበሽታው አይነት እውራኖች ሲያይበት መስማት የተሳናቸው ሲሰሙበት መካን የነበሩ የማይወልዱ ሲወልዱበት የስካር በሽታ ሲዱንበት ለምጻሞች ሲነጹበት አንካሶች ሲረቱበት የነቀርሳ ኪንታሮት ሌሎችም መስል በሽታዎች በጻድቁ እምነትና ጸበል እንዲሁም መኮሬታ በመጠቀም እየተፈወሱ ይገኛሉ በእጀሰብ በስራይ የተያዙ እንዲሁም በዘመኑ በሽታ ኤድስና ካንሰር የተበከሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ድነውበት በቦታው ምስክርነት እየሰጡ ይገኛሉ:: በገዳሙ ውስጥ በርካታ አባቶች በ እጃቸው የፈለፈሉት ብዙ ዋሻ ይገኛሉ:: ዛሬም ብዙ መነኮሳቶች ከስው ተለይተው ማህበሩ ፈቅዶላቸው በጽሞናና በአርምሞ የሚኖሩ አባቶች በገዳሙ ዘግተው ይገኛሉ:: ጻድቁ ስነ ኢየሱስ በመላእክት ከሰማይ የወረደላቸው አንድ የድንግልና አንድ የተጋድሎ አክሊል  በክብር በመቅደስ ይገኛል:: የጻድቁ አጽምና በሳቸው እግር የተኩት አቡነ የማነ ክርስቶስ አጽም ብዙ ገቢረ ተአምር እያደረገ ዘወትር በጸሎት እጣን እየታጠኑ ይገኛሉ በጻድቁ ስነ ኢየሱስ እጅ የተባረከ የመልአኩ ገብርኤል ታቦትና የማህበረ በኩር ጽላት በየዓመት በአላቸው እየተቀደሰባቸው ይገኛል::
  ጻድቁ ስነ ኢየሱስ ካረፉ በምትካቸው አቡነ የማነ ክርስቶስ የተባሉ ልጃቸው ተሹመዋል አቡነ የማነ ክርስቶስም የአባታቸውን ፈለግ በመከተል በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ በመሆናቸው በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት ጊዜ ንጉሱ ሃይማኖታቸውን ከኦርቶዶክስ እምነት ውጪ በመውጣታቸው አንደበታቸው ተዘግቶ አጼ ፋሲልም የአባታቸውን ችግር በጸሎት ከእግዚአብሄር ምህረት እንዲስጣቸው ሲማጸኑ መባም የሚያስፈልገውን ለገዳሙ ቃል ገብተዋል አበው መነኮሳትም ሌሊት በሰዓታት ቀን በዳዊት በመፀለይ የእግዚአብሄር ቸርነት ተገልጾላቸው ከመሰል የመንፈስ ቅዱስ ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን ስጋ ወደሙ ቀድሰው ሲያቀብላቸው ተመዞ የነበረው ምላሳቸው ወደነበረበት ሊመለስ ችሏል:: በዚህም በመደሰት ለገዳሙ መተዳደሪያ 44 ቅፈፍ ጉልት ተቀብልው እንደነበር ገዳሙ አስራት እያስከፈለ ሣንጃ ወረዳን እራሱ እንደሚያስተዳድር ታሪካቸው ያስረዳል::
  የእግዚአብሄር ክብርና ምስጋና ይሁንና የአባታችን የጻዲቁ ስነ ኢየሱስ እና የቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ አንድነት ገዳም  ቃል ኪዳን ከብዙው ባጭሩ ከዚህ ላይ ተፈጸመ አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለቸሩ አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ለእሱ ይሁን:: writing by deme ad