ቅዱስ፡- ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥ ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ ማለት ነው።
ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል።
ቅዱስ ማነው?
ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥ ማዕከለ ዓለም ፥
ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው የለም፡፡ ነቢዩ አሳይያስ « እንግዲህ
እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ። ኢሳ ፵ ፥ ፳፭
፡፡
፩ ስሙ ቅዱስ ነው
የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ « ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። «ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና»
እንዲል ይህ ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው ፥ በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው
በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት
እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነድዳቸው ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ
ፊት በቆመ ጊዜም «አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች
አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ
በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ።
በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ
ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ
አርትተውታል። የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ
ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ ፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት
ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም
ጠንቋዩን በርያሱስን በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት
ፈውሷታል። የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ።
፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤
የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ ፥ አምላክ ፥ ንጉሥ
ነው ፤ ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረ ዓለምን
አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥
ሕያው ፥ ኃያል ፥ ረቂቅ ፥ መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው ፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ
የራቀ ምሕረቱ የበዛ ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ ፥ ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና
አባት ነው።
ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር
ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ፤ » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫። እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት
ቤት የታደጋቸውን እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥
ድንቅንም የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤ » እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮።
ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ ፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ
ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ
እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ ፮፥፱-፲፩ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ
ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
No comments:
Post a Comment