Saturday, December 8, 2012

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ


        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
     ስለ እመቤታችን፣ ስለሐዋርያት፣ ስለነገስታት፣ ስለጻድቃን፣ ስለሰማዕታት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት በአጠቃላይ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እንወቅ፣ እንመርምር፣ እንጠይቅ፣እንማማር ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ እዝነ ልቦናችንን ይክፈትልን፤ ያዲስ ኪዳን ኪሩብ የጸጋ መፍሰሻ ምልዕተ ክብር ምልዕተ ውዳሴ የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጢር ትግለጥልን አሜን!!!
 ቅዱሳን ጻድቃን መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለምና ከተድላ ዓለም ተለይቶ ቤት ልስራ ዘር ልዝራ ሳይሉ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ ጸንተው የኖሩ ናቸው።
  አኗኗራቸው ድምጸ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ግርማ ሌሊቱን ሳይሳቀቁ ደዋ ጥሰው፣ ደንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው ነው። ይህን ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።” በማለት በዕብ.11፡37-38 የገለጸው።

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ (፩ሺ፪፻፩ ዓ.ም/1201 ዓ.ም/
 ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የቅዱስ ላሊበላ ወንድም ልጅ ሲሆን አባቱ ሐርቤይ እናቱ መርኬዛ ይባላሉ። በግብረ መንፈስ ቅዱስ ታህሳስ ፫ ማክሰኞ ዕለት ተወለዱ። “ቅዱስ ነዓኩቶ ለአብ ሲወለድ እናቱ ምጥ ይኋት ካህናት ቅዳሴውን ገብተው ሳለ ዲያቆኑ ነአኩቶ ሲል ስለተወለደ ስሙ ነዓኩቶ ለአብ ተባለ።” እንደ ዮሐንስ በድንግልና የኖረ የመንፈስ ቅዱስ መንኮራኩር ሠረገላ ተሰጥቶት እንደፈለገ እየሄደ የሚንቀሳቀስ የበቃ ጻድቅ ነበር።
ቅድስ ነአኩቶ ለአብ የጌታን መከራ እያሰበ በቁመቱ ልክ ጉድጓድ አስቆፍሮ በዙርያው ጦር አስበጅቶ ጦሩ እንዲወጋው አርብ አርብ ዕለት ደሙ እየፈሰሰ እልፈ እልፍ እየሰገደ ፵ (40) ዓመት ኖረ።
በአንድ ቀን ጌታችን በአካል በቤተ መቅደስ ተገልጾለት ወዳጄ ልጄ ነዓኩቶ ለአብ ሆይ የዚህች የቅጣት ዓለም ጊዜ በቃህ እኔ ለሰው ልጆች ስል ደሜን ያፈሰስኩት መከራውን የተቀበልኩት አንድ ቀን ነው። አንተ ግን ፵ (40) ዓመት ሙሉ ደምህን እንባህን እያፈሰስክ አትዘን ባንተ ቤተ መቅደስ ተገኝተው በአንተ አማላጅነት አምነው የተማጸኑትን፣ ቦታህን ሳይረግጥ፣ ዝክርህን ሳይዘክር ዝናህን ሰምቶ ያሰበህን እንኳ እምርልሃለሁ። አንተም እስከ ዐለተ ምጽአት ተሰውረህ ስለ ሰው ልጅ ሃጢአት ኑር ብሎታል። በተጨማሪም እስከ እለተ ምጽአት በዚህ ቦታ ለሚመጡ ሕሙማን ስትፈውስ ቆይ ብሎታል። ዛሬም ከጣራው ፀበሉ ይንጠባጠባል፤ በጋ ከክረምት አይደርቅም። እንደውውም ክረምት ይቀንሳል በጋ ይጨምራል። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ያሳነጻት አሸተን ማርያም የተባለች ቤተ መቅደስ አለች። አሸተን የተባለችበት ምክንያትም ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አንጿት ሲያበቃ ማዕጠንት ሲያጥን ብዙ ቅዱሳን ቤተ መቅደስ ገብተው ጥቅጥቅ ብለው ቁመው ሲመለከት እናንተ ደግሞ እንዴት መጣችሁ ብሎ ቢጠይቃቸው ማዕጠንቱን አሽተን መጣን ስላሉ ዛሬም ስሟ አሽተን ማርያም ትባላለች። ይህችን ቤተ ክርስቲያን በ ፩ሺ፪፻፲፩ /1211 ዓ.ም አነፃት።
የላሊበላምን ልጅ ይትባረክን አሳድጎ መንግስቱን ለእርሱ አውርሶ በሞት ፈንታ ከሥጋው ታህሳስ ፫ /3/ ቀን እንደ ሄኖክ ተሰውሯል።ወደ ፊት በሕይወት ይመጣል፤ የተሰወረውም በተወለደ በ፸ /70/ ዓመቱ ነው። በስሙ 3 ቤተክርስቲያን ተሰርቶአል። በዚህ ጻድቅ ገድል ለ፳፩ / ለ21/ ቀናት የታሸ በአማላጅነቱ ያመነ እድሜው እንደሚረዝም ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።
“ጻድቅ በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ እውነት እላችኋለሁ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።" ማቴ. ፲፡፵¬-፵፪ (10፥40¬-42)
 ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

No comments:

Post a Comment