Monday, November 19, 2012

መላእኩ ቅዱስ ዑራኤል



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
በፍጹም መጠበቅን ጠብቆ ለዚህ ያደረሰን አምላካችን ክብርና ምስጋን አምልኮትና ውዳሴ ይድረሰውና ይህን ታላቅ መልአክ በችሎታችን መጠን እንድናመሰግን እግዚአብሔር ይርዳን፤ አምላክ ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ ምስጢሩን ይግለጥልን አሜን፡፡

“ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡” መ/ዕዝ. ሱቱ. 2፡1
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።
በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ ::
  በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውለሁ። ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። መዝ. 90/91/፡11-16


አፈቅሮ ፈድፋደ፡- ዑራኤል ሆይ፣ ከመልኮች ሁሉ ይልቅ ያንተን መልክአ ጸሎት እወዳለሁ፡፡ የመልክህ ስነ ጸዳል በደመ ወልድ እግዚአብሔር የታተመ ነውና፡፡
ዑራኤል ሆይ፣ እግዚአብሔር ሀይሉን የሚገልጽብን መልአከ ብርሃናት አንተ ነህ፡፡ በዐለተ ሥቅለት በደመ ወልድ ዓለምን ለመቀደስ ከሁሉ ይልቅ አንተ ተሰይመሃልና፡፡ ስለክብርህ የሰማይ መላእክት አደነቁ፡፡

ለተፈጥሮትከ፡-
ዑራኤል ሆይ፡- ያለ መናገር በጥንት አርምሞ ከነፋስና ከእሳት ለተፈጠረ ተፈጥሮህ ሰላም እላለሁ፡፡ ዑራኤል ሆይ የተፈጥሮና የይቅርታና የቸርነት ክቡር መልአክ ነህና ስለኛ ስለሰው ልጆች ወደ ልዑል እግዚአብሔር ማልድ አማላጅነትህ ዘወትር ከጥፋት ያድናልና፡፡

ለዝክረ ስምከ፡-

ዑራኤል ሆይ፡- ከማርና ከወተት ይልቅ ለሚጥመው ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፡፡

ዑራኤል ሆይ፡- ክፍልህ /ክንፍህ/ በደመ ወልድ እግዚአብሔር የተከበረ /የታለለ/ ነውና፡፡ ለዓለሙ ሁሉ መድሃኒት ትሆን ዘንድ ግሩም የሚሆን የእግዚአብሔር ሥልጣን በክብር ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ (መልክአ ዑራኤል)

“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” መዝ.33/34/፡7 የሊቀ መልአኩ የክዱስ ዑራኤል ረድኤቱ በረከቱ ፍጹም አማላጅነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡

በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡ ሌሊትና ቀን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና ሳይሰለቹ የሚጠብቁን ሊቀነ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሩፋኤል ቅዱስ ዑራኤል ቅዱስ ራጉኤል ቅዱስ ፋኑኤል እልፍ አእላፋት የሆኑ ጠባቂ መላእክት ሳመሰግን በደስታ ነው፡፡
በጸሎታቸው ያልተለዩኝን ጻድቃን አባቶቼን አቡነ ተክለሃይማኖትን አቡነ ገብረምንፈስ ቅዱስን አቡነ ሀብተማርያምን አቡነ አረጋዊን አቡነ ኪሮስንና ሌሎች ቅዱሳን አባቶቼን እንዲሁም እናቶቼን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራን ቅድስት አርሴማን ብዙ ያልጠቀስኳቸው ቅዱሳንን ለማመስገን ቃላት የለኝም፡፡
በሰማኝትነታቸው የጥንካሬ ምሳሌ የሆኑልኝ በጸሎታቸው የረዱኝን ቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቅዱስ እስጢፋኖን መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስንና ሌሎችን ቅዱሳን ሰማዕታትን ሁሉ በእጅጉ አመሰግናለሁ ለዘላለሙ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

No comments:

Post a Comment