በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!
የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ‹‹ክብር›› የሚለውን ኃይለ ቃል ሲተረጉም ‹‹ጌትነትንና፣ ከፍተኝነትንና ብርሃንነትን፣ ዋጋንና ጥቅምን አጠቃሎ ይዟል›› ይለናል፡፡
ክብር እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክትን በተመለከተ ግን ‹‹ከፍተኛነትን፣ ብርሃንነትን፣ ዋጋና ጥቅምን አጠቃሎ ይዟል›› የሚለው ሐረግ በቀጥታ ይመለከተታቸዋል፡፡
- ክብራቸው፡- የእግዚአብሔር ሠራዊት በመሆናቸው፡፡
- ከፍታቸው፡- ሰማያውያን መሆናቸው፡፡
- ብርሃንነታቸው፡- በሥነ - ተፈጥሮአቸው፡፡
- ዋጋና ጥቅማቸው፡- በአገልግሎታቸው ይታወቃል፡፡
ክብራቸው
የክብር ምንጭ እግዚአብሔር ሲሆን መላእክቱ ደግሞ የክብሩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ መላእክቱ ሲገለጡ የእግዚአብሔር ክብር እንደሚታይ መጽሐፍ ቅዱስ ያስነብበናል፡፡
‹‹እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፣ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ›› (ሉቃ. 2÷9) እንዲል፡፡ ‹‹አክባሪ ከአከበረ፣ ንጉሥ ካስገበረ›› እንዲሉ የአክባሪው ጌታ ክብር በላያቸው ሲያርፍ ቅዱሳን መላእክትን እንደሚገባ መጠን ያላከበረ የእግዚአብሔር ክብር ያልገባው ነው፡፡
ከፍታቸው
የቅዱሳን መላእክት ከፍታቸው እግዚአብሔር፣ መኖሪያቸውም በከፍታ (በሰማይ) በመሆኑ ከፍ ከፍ ያሉ ናቸው፡፡
ብርሃንነታቸው
የመላእክት ብርሃናዊነት ብሩህ አእምሮ፣ ብሩህ ተፈጥሮ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ቅዱሳን መላእክት በተገለጡበት ሥፍራ ጨለማ፣ እነርሱ በገለጡበት ልቦና ድንቁርና የለም፡፡
ለበለዓም የቀና መንገድ፣ ለዕዝራ የዕውቀት ጽዋ፣ ለዳንኤል የጥበብ ፍቺ፣ ለቆርኖሌዎስ የመዳን ሚጥስር ጉዞ፣ ለአባታችን ለኃብተ ማርያም የመጻሕፍት ትርጉም….. የሆነላቸው በመላእክት ብርሃናዊ አጋዥነት ነው (ዘኁ. 22÷35፤ ትን. ዳን. 9÷21፤ ሐዋ. 1ዐ÷3፤ ገድለ አቡነ ኃብተማርያም)፡፡
ዋጋና ጥቅማቸው
ዋጋና ጥቅማቸው አገልግሎታቸው ነው፡፡ ዋና አገልግሎታቸው እግዚአብሔርን ማመስገን ነው (ኢሳ. 6÷1-3፤ ራዕ. 5÷11)፡፡ ምሥጋናቸው እረፍታቸው፣ እረፍታቸው ምሥጋናቸው በመሆኑ ሲያመሰግኑት ‹‹ቀንና ሌሊት አያርፉም (አያቋርጡም)›› (ራዕ. 4÷8)፡፡
ቀጥሎ ያለው አገልግሎታቸው ‹‹መዳንን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው መላክ ›› ነው (ዕብ. 1÷14)፡፡ ከአዳም ውድቀት በፊት የመላእክት አገልግሎት ምሥጋና ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የቆመውን ሲያበረቱ፣ የወደቀውን ሲያነሱ፣ ንስሐ በገባውም ሲደሰቱ ከሰው ልጆች ጋር ልዩ ፍቅር፣ ፍጹም ሕብረት አላቸው (ትን. ዳን. 1ዐ÷11፣ መዝ. 9ዐ÷12፣ ሉቃ. 15÷1ዐ)፡፡
የተሟላ መልእክተኛ አድርሶ ተመላሽ ብቻ ሳይሆን አድርሶ መላሽ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት በአገልግሎት የተሟሉ በመሆናቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመልእክት፣ ለእርዳታ የሚላኩ ብቻ ያይደሉ የእኛንም ጸሎት፣ ስእለት፣ እንደሚያሳርጉ የማኑሄ መስዋእት እና የዮሐንስ ራዕይ መስክረውታል (መሳ. 13÷2ዐ፤ ራዕ. 8÷4)፡፡
ሌላው አገልግሎታቸው ደግሞ ጸሎትና ምልጃ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ ላይ የመላእክት ጸሎት እና እርዳታ ያለውን ጉልህ ድርሻ ወለል አድርጎ ያሳየናል፡፡ ጌታ የመላእክትን የምስጋናቸውን ብቻ ሳይሆን የልመናቸውን ድምጽ ይወዳል፡፡ ይህንንም በጥልቀት ለመረዳት የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጽሑፋትን ማንበብ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ትንቢተ ዳንኤል ስለ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹በዚያ ዘመን ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል›› ይለናል (ትን. ዳን. 12÷1)፡፡ መቆም፡ - ጸሎት፣ ልመና በመሆኑ ‹‹ስለሕዝብህ ልጆች›› የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ በወንጌል እንደተጻፈ የሐዋርያት ሕይወት እንዲዝል፣ እንደ ስንዴም እንዲበጠር ሰይጣን ለክፋቱ ጌታን ከለመነ እንደመገበሪያ ስንዴ እንድንነጻ ደግሞ ለደግነታቸው መላእክት እንዴት አይለምኑም? ይለምናሉ፣ ይጸልያሉ እንጂ!
የእውነት መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ›› ብሏል፡፡ (ሉቃ. 1÷19)፡፡ ቅዱስ ገብርኤልን ያህል መልአክ ቆሞ ካልማለደ ዛሬ የገብርኤልን ጸሎት ማን ይተማመን ነበር? መቆም መጸለይ ነው፡፡ ጸሎትም የመላእክት ሥራ (አገልግሎት) ነው፡፡ እንኳን መልአክ ነጋዴ በአቅሙ ‹‹ያለ ሥራ መቆም ክልክል ነው›› ይላል፡፡
በዮሐንስ ራዕይ ተጽፎ እንደምናነበው ሰባቱ ታላላቅ (ሊቃነ) መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ (ይጸልያሉ) (ራዕ. 8÷1)፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መቆማቸው የአገልግሎታቸው አንዱ ክፍል ነው፡፡
ሥልጣናቸው
ሹመት ኃላፊነት ሲሆን ሥልጣን ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ኃይል ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት ‹‹አለቅነት›› ወይም ‹‹ሥልጣን›› እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡም በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም›› ይላል (2ኛ ጴጥ. 2÷11)፡፡
መላእክት የስድብን ፍርድ ቢመልሱ ዛሬ ተሳዳቢ አይኖርም ነበር፡፡ የእነርሱ ሥልጣን ግን ከቁጣ ትዕግስትን፣ ከፍርድ ምህረትን፣ ከግደል ይቅር በልን፣ ከአጥፋ መልስን ያስቀድማል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹የስድብን ፍርድ አያመጡም›› የተባለው፡፡ ደፋሮቹና ኩሩዎቹ ግን መላእክቱ ፍርድን ሳያመጡባቸው እራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስ በመቀጠል ‹‹በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፣ የአመጻቸውንም ደመወዝ ይቀበላሉ›› ብሏል (ቁ. 12)፡፡ በመላእክት ጸሎት የማይድን አመጽ፣ የማይሰበር ኩራት ምንኛ ከባድ ነው?
የቅዱስ ሚካኤል ሥልጣን
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤል ፊት ስለላከው መልአኩ ስለ ቅዱስ ሚካኤል እንዲህ መስክሯል፡፡
‹‹በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ፣ ወደ አዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፣ ቃሉንም አድምጡ ፣ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኀጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት›› (ዘጸ. 23÷2ዐ-21)፡፡ ይቅር ማለት ወይም አለማለት የእግዚአብሔር ገንዘብ ሲሆን ጌታ ራሱ‹‹በፊቱ ተጠንቀቁ፣ ቃሉን አድምጡ፣ ኃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት›› እያለ ለመልአኩ የሰጠውን ሥልጣን አከበረ፡፡ አክባሪው በአከበረው፣ ሿሚ ሥልጣን በሰጠው ይተማመናል፡፡ ለምን? የሚል ቢኖር ግን እግዚአብሔር በሥራው ስህተት የለውምና ይግባኝ አይጠየቅም!
የቅዱስ ገብርኤል ሥልጣን
ልጅ አጥቶ እድሜው የገፋው ካህኑ ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ ይነግረው ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮለት ነበር፡፡ ካህኑ ግን በመጠራጠሩ ቅዱስ ገብርኤል የሚቀጥለውን እንደተናገረ እናነባለን፣ ‹‹እንድናገርህም፣ ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር››፡፡ ይህ ቃል መልአኩ የተላከው ለብስራት ዓላማ ብቻ እንደነበር ያሳምነናል፡፡ መልአኩ ግን በመቀጠል እንዲህ አለ ‹‹እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፣ መናገርም አትችልም›› (ሉቃ. 1÷19-20)፡፡ መልአኩ የተላከው ለብሥራት ሲሆን ‹‹ቃሌን›› አላመንህም ብሎ አንደበቱን የዘጋው በሥልጣኑ አይደለምን? ነው ወይስ አንደበቱን የሚዘጋበትን ፈቃድ ለማግኘት ወደ ላከው ጌታ ይመለስ? ሥልጣን ኃይል ነው!
ቅዱሳን መላእክት በተሰጣቸው ሥልጣን በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚፈጽሟቸው አዎንታዊ ድርጊቶች ብዙዎች ናቸው፡፡
አዘጋጅ መቅረዝ ዘተዋህዶ በመምህር ቃለአብ ካሳዬ
የቅዱሳን መላእክቱ ጥበቃ፣ ጸሎትና ምልጃ አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
amen... kale hiwotin yasemalin wondimachin berta
ReplyDelete