Saturday, December 8, 2012

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ( የገሊላ ባሕር ፫ ስያሜዎች አሉት፡- (፩) የገሊላ ባሕር (በገሊላ አውራጃ ስለሚገኝ)፣ በዙሪያው ባሉ ጌንሴሬጥና ጥብርያዶስ በሚባሉ ከተሞች ስም ደግሞ (፪) ባሕረ ጌንሴሬጥ እና (፫) ባሕረ ጥብርያዶስ ይባላል) ባለች ቤተሳይዳ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው የአባቱ ስም ዮና ሲሆን ትውልዱም ከነገደ ሮቤል ነው። እናቱ ደግሞ ከነገደ ስምዖን ወገን የሆነች ነበረች። በመሆኑም እንደ ኦሪት ሥርዐት ስም ሲያወጡለት በእናቱ ነገድ ስም ስምዖን ብለውታል። አባቱ ዮና የያዕቆብና የዮሐንስ አባት ከሆነው ከዘብ
ዴዎስ ጋር የሥራ ባልንጀራ ሲሆን የሁለቱም ሥራቸው ዓሣ እያጠመዱ መሸጥ ነበር። እድሜው ፭ ዓመት ሲሆን ኦሪትን እየተማረ እንዲያድግ በአቅራቢያቸው ወዳለ ወደ ቅፍርናሆም ምኩራብ ሰደዱት። ቅዱስ ጴጥሮስ በቅፍርናሆም እየተማረ ካደገ በኋላ በዚያው ቤት ሠርቶ ኮንኮርድያ (ጴርጴቱዋ) የምትባል ሚስት አግብቶ እንደ አባቱ ዓሣ እያጠመደ በመሸጥ መኖር ጀመረ።

ለቅዱስ ጴጥሮስ እንድርያስ የተባለ ወንድም ነበረው። ሥራውም ልክ እንደ ወንድሙ ዓሣ ማጥመድ ነበር። ነገር ግን ይህ እንድርያስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም፤ እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እያለ ስለ ክርስቶስ ሲመሰክር ሰምተው ክርስቶስን ከተከተሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሐዋርያት አንዱ ነው (፪ኛው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ነው) /ዮሐ. ፩: ፴፭ - ፵/።

ቅዱስ ጴጥሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር የተዋወቀው በወንድሙ በእንድርያስ ግብዣ ነው። እንድርያስ ከመምህሩ ከመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ሰምቶ ክርስቶስን ከተከተለ በኋላ ወዲያውኑ ለወንድሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ “በትርጓሜው ክርስቶስ የሚሉት መሲሕን አገኘነው” በማለት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወስዶታል። ጌታም ቅዱስ ጴጥሮስን ባየው ጊዜ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ (ጴጥሮስ) ትባላለህ” አለው /ዮሐ. ፩ : ፵፪ - ፵፫/። ይህም ወደ ፊት እርሱን እንደሚከተለውና “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ ሲመሰክር ስሙን ቀይሮ “አንተ ዐለት (ጴጥሮስ) ነህ …” እንሚለው ትንቢት ሲነግረው ነው /ማቴ. ፲፮ : ፲፫ - ፳/።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ እየተዘዋወረ ሲያስተምር አንድ ቀን ጠዋት በጌንሴሬጥ ባሕር ወደብ ብዙ ሰዎች ቃሉን ለመስማት ተሰበሰቡ። ጌታችን በወደቡ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ሲደክሙ ያደሩ ዓሣ አጥማጆችን አገኘ። ከነዚህም መካከል ቅዱስ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ እንዲሁም ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ። ጌታችንም ቃሉን ለመስማት የተሰበሰበውን ሕዝብ ብዛት አይቶ ከሕዝቡ ጋር ፊት ለፊት እየተያየ ለማስተማር እንዲመቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ታንኳ ገብቶ በታንኳው ላይ ሆኖ ማስተማር ጀመረ። ትምህርቱን ሲጨርስ ቅዱስ ጴጥሮስን “መረብህን ጣልና ዓሣ ያዝ” አለው። ሌሊቱን ሙሉ ሲደክሙ አድረው ምንም አይነት ዓሣ አላገኙም ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ “መምህር ሆይ! ሌሊቱን ሁሉ ስንደክም አድረን ምንም አላገኘንም፤ ነገር ግን እንደቃልህ መረቡን ወደ ባሕር እንጥላለን” በማለት ሳይጠራጠር መረቡን ወደ ባሕር ጣለ። በዚህ ጊዜ መጎተት እስኪያቅታቸውና እስኪደነቁ ድረስ ጌታችን ብዙ ዓሦች ወደ መረቡ እንዲገቡ አደረገ። ቅዱስ ጴጥሮስ የተደረገውን ተአምር አይቶ ከጌታችን እግር ሥር ሰገደና እንዲህ አለ፡- “እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና አቤቱ ከኔ ፈቀቅ በል” /ሉቃ. ፭ : ፰/። አባቶች ይህንን ሲተረጉሙ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን የተናገረው “ባሕርንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት የሚያውቅ የእኔንማ ኀጠአት እንዴት መርምሮ ይፈርድብኝ ይሆን?!” ብሎ በመፍራትና ስለራሱ ኀጢአት በማሰብ “ካንተ ጋር መኖር የማይገባኝ ኀጥእ ነኝ” በማለት ስለፍጹም ትሕትና ነው ይላሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ጴጥሮስን ፍርሃትና ድንጋጤ አይቶ፡- “ስምዖን ሆይ አትፍራ! ከእንግዲህ ወዲህ ዓሣ ሳይሆን ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” ብሎ ሁለቱንም “ተከተሉኝ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ሁሉን ትተው ተከተሉት /ሉቃ. ፭ : ፩ - ፲፩/። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቱን፣ ትዳሩን፣ ሥራውን፣ ዘመዶቹን በአጠቃላይ የዚህን ዓለም ኮተት በሙሉ እርግፍ አድርጎ ትቶ ሙሉ ጊዜውን ከጌታ ጋር በማድረግ መደበኛ ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ለዚህም ማስረጃው በሌላ ቦታ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን “ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” ሲል መጠየቁና ጌታም “የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት በ፲፪ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በ፲፪ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስትን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” ብሎ መመለሱ ነው /ማቴ. ፲፱ : ፳፯ - ፳፱/።

ጌታችን እንደ ልማዱ በገሊላ ባሕር ዳር ባሉ መንደሮችና ከተሞች እየገባ ሲያስተምር አንድ ቀን በቤተ ሳይዳ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን ከበሽታዋ ፈወሰለት። ይህንንም ሲያደግለት የቅዱስ ጴጥሮስ እምነት ይበልጥ ጸና፤ ልቡንም ደስ አሰኘው።

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ከተከተለ ጊዜ ጀምሮ ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ የጌታችንን ትምህርት በሚገባ ተከታትሏል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ጌታ በሚያስተምራቸው ወቅት በጥያቄና መልስ ፈጣንና ንቁ ተሳትፎም ነበረው። ጌታችን ሐዋርያትን ጥያቄ ሲጠይቃቸው ብዙ ጊዜ ፈጥኖ ይመልሳል፤ እርሱም ያልገባውን ነገር ለመረዳትና የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ በተደጋጋሚ ለጌታችን ጥያቄ ያቀርብ ነበር። ጌታም በበኩሉ የተለያዩ ትዕዛዛትን ሲያዘው እንመለከታለን። ለአብነትም የተወሰኑትን ብንመለከት፡-

1. ጌታችን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አበርክቶ አምስት ሺህ ሕዝብ ሲያጠግብ አይተው ሕዝቡ ይህንንስ እናንግሠው ብንራብ ያበላናል፣ ብንታመም ይፈውሰናል፣ ብንሞት ያሥነሣናል በሚል ሥጋዊ አስተሳሰብ ሊያነግሡት ፈለጉ። ጌታችንም ይህን ሐሳባቸውን አውቆ የመጣበት ዓላማ ይህ አይደለምና ደቀ መዛሙርቱ ቀድመውት በጀልባ ተሻግረው እንዲሄዱ አድርጎ እርሱ ብቻውን ወደ ተራራ ወጥቶ መጸለይ ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱ እንደታዘዙት በመርከብ ሲሄዱ ብርቱ ነፋስ ተነሥቶ አናወጣቸው። ባራተኛው ሰዓተ ሌሊት ጌታችን በባሕሩ ላይ በእግሩ ተከተላቸውና አጠገባቸው ደረሰ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የማዕበሉ ብርታት ከጨለማው ጋር ተዳምሮ እጅግ በተጨነቁበት ጊዜ ወደ እነርሱ የሚመጣው “ምትሐት ነው” ብለው እጅግ ተረበሹ። በዚህ ጊዜ ጌታችን “አይዟችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ” ብሎ ማንነቱን ነገራቸው። ድምፁን ሰምተው ከተረጋጉ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አንተስ ከሆንህ በባሕሩ ላይ በእግሬ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ብሎ ጠየቀው። ጌታም “ና” አለው። ቅዱስ ጴጥሮስ ከመርከቡ ወረዶ መጓዝ እንደጀመረ ገና በመንፈስ ቅዱስ አልታደሰም ነበርና የማዕበሉን መበርታት እይቶ ስለፈራ መስጠም ጀመረ፤ ወደ ጌታም “አድነኝ” ሲል ጮኸ። ጌታም እጁን ዘርግቶ ወደ መርከቡ ካወጣው በኋላ “ከእኔ ጋር ሆነህ እንዴት ትጠራጠራለህ” በሚል ገሰጸው /ማቴ. ፲፬ ፥ ፳፭ - ፴፬/።

2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተማረ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ሲደርስ ሐዋርያትን በጥበብ ስለራሱ ማንነት ለማስረዳት ሲል በተዘዋዋሪ ሌሎች ሰዎች ምን እንደሚሉት ሐዋርያትን ጠየቃቸው። ሐዋርያትም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፣ አንዳንዱ ኤልያስ ነው፥ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” ሲሉ መለሱለት። ጌታችንም “ለመሆኑ እናንተስ ምን ትሉኛላችሁ” ብሎ ስለ እርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ጠየቃቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ሲል መሰከረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የእኔ ትክክለኛ ማንነት ሌሎች(አይሁድ) እንዳሉት ሳይሆን ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው (እንደተናገረው) ነው” በማለት ቅዱስ ጴጥሮስን እጅግ አድርጎ አመስግኖታል:- “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ አንተ ብፁዕ ነህ፤ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም” /ማቴ. ፲፮ ፥ ፲፫ - ፲፱/። ቅዱስ ጴጥሮስ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ከመሰከረ በኋላ ጌታችን ስሙን ቀይሮለታል። ስምዖን ይባል የነበረው “ዐለት” ተባለ (በዕብራይጥ ኬፋ፣ በጽርዕ(ግሪክ) ጴጥሮስ፣ በግዕዝ ኰኵሕ በአማርኛ ዐለት ማለት ነው)። ጌታ በዚህች ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኑን እንደሚሠራትም ተናግሯል። ይህም ማለት ቤተክርስቲያን የምትመሠረተው በቅዱስ ጴጥሮስ ሃይማኖት ማለትም በክርስቶስ ማንነት ላይ ባለ ትክክለኛ እምነት ነው ማለት ነው። እርሱም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ” መሆኑን ጠንቅቆ ማመን ነው። ሁሉም ሐዋርያት ከጌታ ጋር በነበራቸው የተማሪነት ቆይታ ከተረዷቸው ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማዎች) አንዱ ይህ ነው። ጌታም “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ የጠየቃቸውና ቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛውን መልስ ሲመልስ ማመስገኑ ይህንን ሊያስተምራቸው ስለወደደ ነው። ፫፻ (ሠለስቱ ምዕት) በኒቅያ ጉባኤ እምነታቸውን ሲመሰክሩ ካስቀመጡት ጸሎተ ሃይማኖት በፊት ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ የእምነት አገላለጽ የጥንት ክርስቲያኖች ይህን እየመሰከሩ ይጠመቁ ነበር (በመንገድ ሲሄዱም ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም መልሶ፣ እነሆ ውኃ መጠመቅን ምን ይከለክለኛል አለው። ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ይገባሃል አለው። ጃንደረባውም መልሶ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እኔ አምናለሁ” አለው . . . አጠመቀውም” እንዲል /ሐዋ. ፰፥ ፳፮ - ፍጻሜ/ )።

3. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነቱን በደብረ ታቦር ተራራ ከገለጠላቸው ሦስት ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስ አንዱ ነው። “ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ለብቻቸው ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው /ማቴ. ፲፯ ፥ ፩ - ፫/። ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችንን ጌትነት ከተመለከተ በኋላ ከደስታው ብዛት የተነሣ ጌታችንን እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር፤ “አቤቱ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ ሦስት ቤቶችን በዚህ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ” /ማቴ. ፲፯ ፥ ፩ - ፯/። ሙሴና ኤልያስ በደብረ ታቦር ከጌታችን ጋራ መታየታቸው ለቅዱስ ጴጥሮስ እምነቱን የሚያረጋግጥለትና የሚያጸናለት ነገር ነው። “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል” ብሎ በጠየቀ ጊዜ “ኤልያስ ነው ወይም ከነብያት አንዱ (ሙሴ) ነው” ብለውት ነበርና የሙሴና ኤልያስ ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ መታየት ጌታችን ሙሴ ወይም ኤልያስ አለመሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም ለቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ የመሰከረውን አብ ደግሞ በደመና ሆኖ “የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ማለቱ የቅዱስ ጴጥሮስን ምስክርነት የሚያረጋግጥ ነው።

4. ጌታችንና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ የቤተ መቅደስ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ቅዱስ ጴጥሮስን “መምህራችሁ ለቤተ መቅደስ ግብር ይገብራል ወይስ አይገብርም” የሚል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። “ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጥተው መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር አይገብርምን? አሉት። እርሱም መልሶ አዎን (ይገብራል) አለ” እንዲል /ማቴ. ፲፯ ፥ ፳፬ - ፳፭/። ቅዱስ ጴጥሮስ ግብር ተቀባዮች በጠየቁት ጊዜ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የመሰከረውንና ልጅ ደግሞ ከግብር ነጻ መሆኑን ባለማገናዘብ “አዎን ይገብራል” አላቸው። ጌታችንም “አዎን” ማለቱን አውቆ እርሱ ከግብር ነጻ መሆኑን በነገሥታት ልጆች ምሳሌ ካስረዳው በኋላ ነገር ግን እነርሱን ላለማሰናከል በተአምራት ከዓሣ ሆድ ገንዘብ አስገኝቶ ለሁለታቸውም እንዲሰጥ አዘዘው። “ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ አስቀድሞ ስምዖን ሆይ፥ ምን ትላለህ? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች? አለው። ጴጥሮስም፦ ከሌሎች ነው አለ፤ ጌታችን ኢየሱስም አለው፤ እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው። ነገር ግን እንዳያጉረመርሙ፥ ወደ ባሕር ሂድና መረብ ጣል፥ በመጀመሪያም የያዝከውን ዓሣ ወስደህ አፉን ክፈት፤ በውስጡም ሰጣጢራ ታገኛለህ፤ ይከውም አራት ድሪም ነው፤ እርሱንም ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለው” እንዲል “ማቴ. ፲፯ ፥፳፭ ፍጻሜ/። እንዳያጉረመርሙ (እንዳናሰናክላቸው) ማለቱ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ለቤተመቅደስ ግብር ሳይገብር ቀርቶ ቢሆን ኖሮ አምላክነት ብቻ እንጂ ሰውነት የለውም ባሉ ነበርና ነው።

5. ቅዱስ ጴጥሮስ ትዳሩን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን፣ ዘመዶቹን በአጠቃላይ ይህን ዓለም እርግፍ አድርጎ ትቶ ጌታችንን በመከተሉ ምን እንደሚያገኝ ጌታችንን በአንድ ወቅት ጠይቆት ነበር። “ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ መልሶ፥ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን አለው” እንዲል። ጌታችንም ሐዋርያት በጠቅላላ በፍጹም ልባቸው ዓለም በቃኝ ብለው እርሱን በመከተላቸው የሚያገኙትን ዋጋ ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፡- “እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በ፲፪ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በ፲፪ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስትን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” /ማቴ. ፲፱ : ፳፯ - ፳፱/።

6. መዝገበ ትሕትና የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ትሕትናን ሊያስተምራቸው ዝቅ ብሎ እግራቸውን ማጠብ በጀመረ ጊዜ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲደርስ ለጌታው ካለው አክብሮትና ፍቅር የተነሣ እንዲሁም እርሱ አምላክ ሲሆን ዝቅ ብሎ የእነርሱን እግር በማጠቡ እጅግ ተደንቆ “በፍጹም አታጥበኝም” አለ። ጌታችን ኢየሱስም “እኔ የምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፥ ኋላ ግን ታስተውለዋለህ” ቢለውም አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ በጌታውና በአምላኩ እግሩን መታጠብ እጅግ ስለደነቀውና ስለከበደው “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም” አለው። በዚህ ጊዜ ፈጽሞ እንቢ ማለቱን ባየ ጊዜ “እውነት እውነት እልሃለሁ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም” ብሎ መለሰለት። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁሉን ትቶ የተከተለውን ጌታ ከማጣት የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ ስለሚያውቅ “አቤቱ፥ እንኪያስ የምታጥበኝ እጆቼንና ራሴንም እንጂ እግሮቼን ብቻ አይደለም አለው። ጌታችን ኢየሱስም፦ ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤ እናንተማ ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው።” /ዮሐ. ፲፫ ፥ ፩ - ፲፩/።

7. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በካህናት አለቆችና በአይሁድ ሽማግሌዎች ተላልፎ የሚሰጥበትና መከራ የሚቀበልበት ሰዓት ሲደርስ ይህንን መራራ እውነት ለደቀ መዛሙርቱ ሲነገራቸው እጅግ ተረብሸው ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ በመጨረሻው ሰዓት ሁሉም ደቀ መዛሙርት እንደሚክዱት በነገራቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “ሌሎች ቢክዱህ እንኳን እኔ በፍጹም አልክድህም” አለው። ጌታችን እርሱ ባወቀ ዶሮ ሳየጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ቢለውም እርሱ “በፍጹም” አለ። ነገር ግን አይሁድ ጌታችንን ይዘው መከራ ሲያጸኑበት አይቶ እርሱን ያገኘ ያገኘኛል ብሎ “አንተ ከእርሱ ወገን ነህ” ሲሉት “በፍጹም አይደለሁም” እያለ መማል ጀመረ። ወዲያው ዶሮ ሲጮክ ጌታ የተናገረውን ቃል አስታውሶ በዚያችው ቃል “አላበጀሁም” በማለት በፍጹም ጸጸት ማንባት ጀመረ(ንስሓ ገባ) /ማቴ. ፳፮ ፥ ፳፱ - ፍጻሜ/።

ቅዱስ ጴጥሮስ ለጌታችን ካለው ፍቅርና ቀረቤታ ታሪኩ በቅዱስ ወንጌል በስፋት ተገልጿል፤ ሁሉንም ዘርዝሮ መጥቀስ ባይቻልም። ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን በእውነት ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን መቃብሩን በማየት ያረጋገጠ፣ ጌታችን ግልገሎቼን ጠቦቶቼንና በጎቼን ጠብቅ ብሎ እንደሾመው እርሱም ልክ እንደጌታው ለበጎቹ መልካም እረኛ በመሆን የታመነ፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ታድሶ በአንድ ጊዜ ሦስት ሺህ ነፍሳትን አሳምኖ ያጠመቀ፣ ብዙ ተአምራትን በጌታችን ኃይል ያደረገ፣ የሐናንያንና የሰጲራን ድብቅ ሥራ በመንፈስ የመረመረ፣ በሰማርያ በኢዮጴና በልዳ ዞሮ ወንጌልን ያስተማረ፣ በመጨሻም በሮማ ወንጌልን ሲሰብክ በአደባባይ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ፍጹም ጌታውን የመሰለ ታላቅ ሐዋርያ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ እየተዘዋወረ ሲያስተምር በወንጌል የወለዳቸውን ክርስቲያኖች ከልዩ ልዩ ፈተናዎች ለማጽናት ሲል ሁለት መልእክታትን ጽፏል። የመጀመሪያ መልእክቱን የጻፈው አይሁድ ለሚያሳድዷቸውና መከራ ለጸኑባቸው ከእስጢፋኖስ ሰማዕትነት በኋላ በስደት ለተበተኑ ክርስቲያኖች ነው። ሁለተኛውን መልእክቱን የጻፈበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የሮማ ግዛት መሪ የነበረው ኔሮን ቄሣር ክርስቲያኖች ሁሉ እየተያዙ እንዲፈረድባቸው አዋጅ ነግሮ ነበርና በዚሁ ምክንያት ለተጨነቁ በእስያ ላሉ ክርስቲያኖች ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሐሰተኞች መምህራን ተነሥተው በሐሰተኛ ትምህርታቸው ስላስጨነቋቸው ለማጽናት ጽፎላቸዋል።

በታናሽ እስያ እየዞረ በቃልም በመጣፍም ካስተማረና አማንያንን በመከራ እንዲጸኑ ካደረገ በኋላ በስተመጨረሻ ወደ ሮሜ ገብቶ ያስተምር ጀመረ። በዚህ ጊዜ ኔሮን ቄሣር አስይዞ አሳሰረውና በስቅላት እንዲቀጣ ተፈረደበት። ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት መፈረዱን በሰማ ጊዜ ጌታችን፡- “በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል” ያለውን ቃል /ዮሐ.21፡18/ ትዝ አለውና “አላውቀውም ብዬ መካዴን ሳያስብብኝ በዚህ ፍጹም ይቅርታ ያደርግልኛል” በማለት እጅግ ደስ አለው፡፡ የሚሰቀልበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከግዞት ቤት አውጥተው ሲወስዱት፡- “ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ እኩል እንዳልሆን ራሴን ወደ ታች ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ” ብሎ ለመነ፡፡ እነርሱም እንደለመነው አድርገው ሰቅለው ገደሉት፡፡ የተሰቀለውም ሐምሌ አምስት ነው፡፡ ይህን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡


በአጠቃላይ የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት ታሪክ በአጭሩ ከላይ የቀረበው ነው፡፡ ከዚህ ቅዱስ አባት ሕይወት ብዙ የምንማረው አለ፡፡ አንድ ጊዜ ባጠፋው ጥፋት ሁል ጊዜ እየተጸጸተ የጌታውን ይቅር ባይነት ተስፋ ሳይቆርጥ በመረረ አንብዓ ንስሐው ይቅርታን ስላገኘ ለዘመኑ ተነሳሕያን (ንስሐ ለሚገቡ) ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት መተላለፉን የቀረችለት፣ ኃጢአቱ የተከደነችለት፣ በደሉን የማይቆጠርለት ሰው ምስጉን ነው እንዳለ /መዝ.31፡1-2/ እስከ ሞት ድረስ ፍቅሩን በመግለጽ ሰማዕትነትን በሮማ አደባባይ እስከተሰቀለበት ድረስ የአይሁድን ዱላ ፈርቶ በቀላሉ አላውቀውም ብሎ ለካደው አምላክ በቆራጥነትና በታማኝነት ቁልቁል እስከ መሰቀል የደረሰ ታላቅ ሐዋርያ ነው፡፡
ጸሀፊ ቤተ ማርያም
ጸሎቱና በረከቱ በእኛ በሕዝበ ክርስቲያን ላይ አድሮ ይኑር አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment