Saturday, December 8, 2012

አባ ሊቃኖስ


             በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
  ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ አባ ሊቃኖስ ዘእምተሰዓቱ ቅዱሳን /በዚህ ዕለት ከ9 ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ሊቃኖስ አረፉ።
  “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (“የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
“እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” ሐዋ.፬፡፳ (4፡20)
የቅዱሳን ሕይወት ተርታ ታሪክ ወይም ተረት አይደለም ይልቁንስ እግዚአብሔርን የሚከተሉና በሥራቸው ሁሉም የእርሱ ጥበቃ ያልተለያቸው ሰዎች ታሪክ ነው። (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)
  ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አክሱም ከቆዩ በኋላ ለስብከት በዮሓ ክፍላቸው ሲሰማሩ አቡነ ጰንጠሌዎንና አቡነ ሊቃኖስ ርቀው እንዳይሄዱ ሕዝቡ ስለተማጸናቸው ከከተማ ሳይርቁ አምስት ምዕራፍ ርቀት ገዳማቸውን መሠረቱ። አቡነ ሊቃኖስ ከአክሱም በስተ ሰሜን ከሚገኙ ደብረ ቆናጽል ከሚባለው ኮረብታ መቀመጫውን አድርገው የከተማውን ሕዝብ እያስተማሩ ለ፳፩ ዓመታት ቆይተዋል።
የአባታችን ገዳም ደብረ ቆናጽል በመባል ይታወቃል። “ደብረ ቆናጽል” ማለት “የቀበሮ ታራራ” ማለት ነው። ደብረ ቆናጽል በተፈጥሮ ልምላሜ የማይለየው ቦታ ሶሆን ተራራማ ሆኖ ዙርያው ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነው። የአክሱም አከባቢው ክርስቲያኖች ንዋያተ ቅዱሳቱን የሚጠብቅላቸና ጽላተ ሙሴን የሚያጥንላቸው መነኩሴ የሚመርጡት ከዚህ ከአባ ሊቃኖስ ደብረ ቆናጽል ገዳም ነው። የአክሱም ሕዝብ ይህን የተመረጠውን መነኩሴ ንዋያተ ቅዱሳት ጠባቂ፣ አጣኝ ብቻ ሳይሆን ከጳጳስ በበለጠ አባትነቱን ይቀበሉታል።
በዚህ አኳኋን እስከ ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም ድረስ ተጠብቆ የኖረውን ገዳም ፋሽስት ኢጣልያን ሀገራችንን በግፍ ሲወር ይህን ገዳም እጅግ አጎሳቆለው። ቤተ ክርስቲያኑን ማደርያቸውና የጦር መሣርያ ተሸካሜዎች የአጋሰሶች ማጎሪያ አደረጉት። ገዳሙ ከፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ ጀምሮ ጠፍ ወይም ምድረ በዳ ሆኖ ሲኖር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥቂት መነኮሳት በቦታው መቀመጥ ጀምረዋል።
ይህን ገዳም የመሠረቱት ከተሰዐቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ሊቃኖስ ለአክሱም ሲታይ ቅርብ በሆነ ቦታ ስለተቀመጠ ከአጼ ካሌብና ከአጼ ገ/መስቀል ጋር ለማገናኘት ዕድል ስለነበራቸው ለሐዋርያዊ ተግባራች እገዛ አድርጎላቸዋል። በዚህ መሠረት ደግሞ ከፅርዕ፣ ከሱርስ ቋንቋዎች መጽሐፈ ሐዲሳትን በከፊል ወደ ግእዝ እንደተረጎሙ ይነገራል። ይህን ሁሉ ተጋድሎ ካደረጉ በኋላ በክብር  ኅዳር ፳፰ አርፈዋል። የአባታችን ረድኤትና በረከት አይለየን።
የጻድቃን መሥዋዕታቸው የዐይናቸው እንባ ነው። (ማር ይስሐቅ) የቅዱሳን ሁሉ በረከታቸው ልመናቸው ሁላችንንም ታበርታን አሜን።

ዋቢ መጽሐፍት

ነገረ ቅዱሳን ፪ በማኀበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል፣ መዝገበ ታሪክ ፩፣፪፣ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ በአቡነ ጎርጎርዮስ

የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment