Thursday, December 6, 2012

አቡነ ኢየሱስ ሞአ


†”በስመ ሥላሴ“†
†♥† ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ አበ መነኮሳት አቡነ ሞአ ኢየሱስ /በዚህ ዕለት የመነኮሳት አባት አባ ኢየሱስ ሞአ (ኢየሱስ አሸነፈ) አረፉ።/”†♥†
†♥† “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (“የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
አቡነ ኢየሱስ ሞአ (፲፪፻፲-፲፪፻፺፪)
አቡነ ሞአ ኢየሱስ /አሸነፈ ኢየሱስ/ ሐይቅ የተባሉት ሀገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ግንቦት ፳፮ ፩ሺ፪፻፲ ከአባታቸው ዘክርስቶስና ከእናታቸው እግዚእክብራ ተወለዱ። የአባታችን የአቡነ ኢየሱስ ሞአ ጽንሰታቸው በነሐሴ ፳፮ ነው። የተወለዱትም በቅዱስ ነአኩቶ ለአብ
ዘመነ መንግስት ነው፡፡
እኒህ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ የሐይቅን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው። ታሪክን ታሪክ ስለሚያነሳው ሐይቅን ካልዕ ሰላማና አጼ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ቆረቆሩት። ጻድቁም በሐይቅ ገዳም ሳይተኙ መቶ ዘመን የቆሙ ሲሆኑ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ እሳቸው መልአኩ ወደ ሐይቅ እንዲሄዱ ነገራቸው። ከዚያም አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በመልካም ተቀብለው አስተናግደው አመነኮሱአቸው። ኢየሰሱስ ሞአ ያለላመነኮሱት ያላስተመማሩት አባት የለም።
የመጀመሪያው መነከኩሴ አባ እንጦንስ ነው። እንጦንስ መቃርስ፣ መቃርስ ጳጉሚስ፣ ጳጉሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊን እና ፰ ቅዱሳንን አመነኮሱ። ገድለ አረጋዊ እንደሚለው አባ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው አባ ኢየሱስ ቤዛ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞአን፣ መስቀለ ሞአም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞአን፣ አባ ኢየሱም ሞአም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኮሱ። ስለዚህ ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት ናቸው። በ30 ዓመታቸው በደብረ ዳሞ ገዳም መልአኩ ወስዶ ደብረ ዳሞ ጣለቸው። በጴጥሮስና በጳውሎስ ገዳም 7 ዓመት አገለገሉና ወደ ሐይቅ ገብተው 800 መነኮሳትን ያስተማሩ ቀደምት አባት ናቸው። 45 ዓመት በአስተዳዳሪነት ኑረው በዕለተ እሁድ በዕረፍታቸው ጊዜ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ጠርተው በጸሎት ላይ እንዳሉ ብርሃን ወረደ። እረፍታቸውም በዚሁ ገዳም በዛሬው ዕለት ሕዳረ 26 ነው።
†እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።† ዕብ. ፲፪:፩-፪
†††የአባታችን የአቡነ ኢየሱስ ሞአ ሐብተ ረድኤቱ፣ ጸሎቱና አማላጅነቱ ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን።
አሜን†††
“ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር” /የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ዕብ.፲፫፡፯ (ዕብ.13፡7)
ዋቢ መጽሐፍት፡¬-
† ነገረ ቅዱሳን በማኅበረ ቅዱሳን ት/ክፍል የተዘጋጀ ገጽ ፺፫¬-፺፬ (93¬-94)
†የኢትዮጵያ ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ፲፱፻፪ ዓ.ም ገጽ ፶፩¬-፶፪ (51¬-52)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ይቆየን።
አዘጋጅ  ቤተ ማርያም

No comments:

Post a Comment