Wednesday, January 30, 2013

አባታችን አቡነ ዘርአብሩክ


    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: 

 “ከቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”) መዝ.፻፲፭/፻፲፮፡፲፭ (115/116፡15)

 የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።
መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።
መዝ ፴፫፡፲፭-፲፯ (መዝ.33፡15¬-17)

  የጻድቁ አባታችን የአቡነ ዘርዓ ብሩክ አባት እና እናት የተባረኩ ከቅዱሳን ወገን የሚሆኑ ነበሩ። የአባታቸው ስምም ቅዱስ ደመ ክርስቶስ ሲባል እናታቸው ደግሞ ቅድስት ማርያም ሞገሳ ትባላለች። ጻድቁ አባታችን ገና በእናታቸው ማህጸን እያሉ ነበር ብዙ ተአምራት የሚያደርጉት እግዚአብሔር መርጧቸዋልና። በኋላም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ8ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በነሐሴ 27 ጻድቁ አባታችን ተወለዱ። በ40ኛ ቀናቸውም ተጠምቀው በካህናት አፍ "ጸጋ ክርስቶስ" ተባሉ ከዛም ቤተሰቦቻቸው በጥሩ እድገት አሳደጉአቸው። 7 አመትም በሞላቸው ግዜ "በልጅነቴ የዚን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ" ብለው ቢጸልዩ ዓይናቸው ታውሯል።
  ቤተሰቦቻቸውም ጠቢቡ ሰሎሞን "የእግዚአብሔር ቃል ነውርን ይሸፍናል" እዳለው ትምህርት ሊያስተምሩአቸው አስተማሪ ጋር ቢወስዱአቸው ታመው ተመልሰዋል የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለምና። ነገር ግን የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ፈጣሪ አምላክ ራሱ ገልጾላቸዋል:: ክህነትን እስከ ጵጵስና እራሱ መድሃኔ ዓለም ክርስቶስ ሰጥቷቸዋል። 12 አመትም በሞላቸው ግዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ አይናቸው በርቶላቸው ታላላቅ ተጋድሎን ማድረግ ጀመሩ።
በእግዚአብሔር ዘንድ ጵጵስና እንደተሾሙ የሃጥያት ማሰርያን ያስሩና ይፈቱ ዘንድ ጵጵስናን በሾማቸው ግዜ እግዚአብሔር ያወጣላቸው ሁለተኛ ስም "ዘርዓ ብሩክ" ይባል ነበር። 3ኛውም ስማቸው ደግሞ "ጸጋ እየሱስ" ይባላል:: ጻድቁ አባታችን በዚህ አለም በህይወተ ሥጋ ሳሉ አቡቀለምሲስ እንደሚባል እንደ ዮሃንስ ወልደነጎድጉአድ እግዚአብሔር እሱ ወዳለበት ወደ ሰማይ አውጥቶ በገነት መካከል ያኖራቸው ነበር:: እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጁ ለብጹዕ አባታችን ዘርዓ ብሩክ በጎ ነገር እንዳደረገለትና ያለ ድምጽ የሰማይ ደጆችን አልፎ የእሳት ባህርን ተሻግሮ ፈራሽ በስባሽ ሲሆን እንደ ህያዋን መላእክት በፍጥነት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ከአድማስ እስከ አድማስ ይደርስ ዘንድ 12 ክንፍን ሰጣቸው። መላእክትም ለሌሎች ቅዱሳን ያልተሰጠ ይህንን ስልጣን አይተው ለምድራዊ ሰው ይህ ነገር እንዴት ይቻላል? እያሉ አደነቁ።ከዛም በኋላ ጻድቁ አባታችን ከፈጣሪ ዘንድ የመላእክትን አስኬማ፣ የሾህ አክሊል አምሳያ የሆነውን መንፈሳዊ ቆብን,ሰማያዊ ቅናትን እና የደረት ልብስን(ስጋ ማርያም) ተቀብሎ በጾም እና በጸሎት በልመና እና በስግደት እግዚአብሄርን ሲያገለግል ኖረ። ከዛም በላይ ወንጌልን እጅግ ብዙ በማስተማር ደከመ።


   ከኢትዮጵያም አልፎ ግብጽ ድረስ ገባ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሐንስን አገኘውና እርስ በርስ ሰላምታን ተለዋውጠው እጅ ተነሳሱ ከዛም ተመልሶ ወደ ሃገሩ መጣ ከዛም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመላለሰ ወንጌልን አስተማረ እጅግ ስጋን በሚያስጨንቅ ትጋትም የኢትዮጵያን ህዝብ ማርልኝ እያለ እያለቀሰ ይጸልይ ነበር።


  አቡነ ዘርዓ ብሩክ "ዓባይ" እና "ግሽ ዓባይ" የሚሉ ስሞች እንዳወጡ አንድ ቀን አባታችን የንጉስ ጭፍሮች ሲያሳድዷቸው ግዮን ደረሱ። እንደደረሱባቸው ሲያውቁ ዳዊታቸውንና ለወንጌል ስብከት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 7 መጻሕፍት ሁሉ ለግዮን ወንዝ አደራ ሰጡዋት። ከ5 አመት በኋላ ሲመለሱ" ኦ ግዮን ግሥኢ መፃሕፍትየ -- ግዮን ሆይ መጻሕፍቴን ግሺ መልሺልኝ " (ግሽ ዓባይ -- የሚባልም ከዚህ የተነሳ ነው።) ቢሉአት አንድም የውሃ ጠብታ ሳይኖርባት ዳዊታቸውን ብትመልስላቸው ለደቀ መዝሙራቸው ዘሩፋኤል አሳዩት ሁለቱም የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ። ከዛም በኋላ ግዮንን ባረክዋትና "ይኩን ፈውስ ዓብይ በውስቴትኪ -- በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ" አሉ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ መካኖች ይወልዱ፣ ድዉዮች ይድኑ ጀመር "ወእም አሜሃ ተሰምየት ዓባይ ይእቲ ፈለግ -- ከዛ ጊዜ ጀምሮ ይህች ዓባይ ተብላ ተጠራች።" እስካሁንም በዚሁ ስም የሚጠራው ከዚ በመነሳት ነው:: ከዚህም ሌላ ጻድቁ አባታችን በዚሁ ወንዝ አካባቢ ለ 30 አመት ሲጸልዩ ፈጣሪ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ እጅግ ልዩ የሆነ ቃል ኪዳን ሰቶአቸዋል።

በስተመጨረሻም የሚያርፉበት እለት በደረሰ ሰአት መልአከ ሞት መቶ እስኪደነግጥ እና ወደ ኋላው እስኪያፈገፍግ ድረስ ነው ነው እግዚአብሔር ጸጋውንና ክብሩን ያበዛላቸው: በስተመጨረሻም ጥር በገባ በ13 ቀን በ482 አመታቸው ስጋቸው ከነፍሳቸው ተለይታ ገነትን ወርሰዋል::
ዋቢ መጽሐፍት /ምንጭ:/  ገድለ አቡነ ዘርዓ ብሩክ
የጻድቁ አባታችን ገድለ ዜና እንኳን በዚች በምታህል ጽሁፍ አይደለም የገድላቸውም መጽሃፍም አልበቃውም እንደው እግዚአብሔር አምላክ ከበረከታቸው እንዲያሳትፈን ነው እንጂ።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Monday, January 21, 2013

አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ

አባ ሙሴ ጸሊም  ኢትዮጵያዊ
   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
አባ ሙሴ ጸሊም በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አስቀድሞ በውንብድና ኑሮ ሕይወቱን ይገፋ ነበር፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል፡፡እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ ፤ በሥራውም ኃይለኛ ነበር፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ፤ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ
አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ፡፡ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር ፡፡

በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ፤ ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው፡፡  ያንጊዜም ተነሳ ሰይፉንም ታጥቆ ወደአስቄጥስ ገዳም ሄደ ፤ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው ፤ አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው ፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደአባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው፡፡ እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሰህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ
የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኮሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙ እና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ፡፡፡፡በኋላም በገዳመ አስቄጥስ የገዳሙ አበምኔት የነበረው የአባ ኤስድሮስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በአባ መቃርዮስ ምክር ወደ ጴጥራ ሂዶ በተባሕትዎ መኖር ቀጠለ፡፡ ከገድሉ ብዛት የተነሳ አረጋውያን መነኮሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውሃ መቅጃዎቹን ወስዶ ውሃ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር፡፡ ውሃው ከእነርሱ ሩቅ ነበርና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም በበአቱ እያለ የፈቲው ፆር ያሠቃየው ነበር፡፡ ፈተናውን ተቋቁሞ በበአቱ መቀመጥ ስላልቻለ ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ኤስድሮስ ዘንድ ሄደና ‹በበኣቴ መቀመጥ አልቻልኩም› አለው፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደ በኣቱ ተመልሶ በዚያው እንዲጸና መከረው፡፡ ሙሴ ግን ‹ፈጽሞ አልችልም› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ሙሴን ይዞት ከገዳሙ ቅጥር ውጭ አወጣው ከዚያም ወደ ምዕራብ አዞረውና ‹ተመልከት› አለው፡፡ በዚያ አቅጣጫ የአጋንንት መንጋ ለወረራ ሲዘጋጁና ሲንጫጩ አሳየው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ምሥራቅ እንዲመለከት አደረገውና እልፍ አእላፍ መላእክት ብርሃን ተጐናጽፈው አሳየው፡፡ ከዚያም ‹እነዚህ የብርሃን መላእክት ቅዱሳንን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ ናቸው እነዚህ ርኩሳን አጋንንት ደግሞ ቅዱሳንን ለመፈተን የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የብርሃን መላእክት ኃይል ከአጋንንት ኃይል ይበልጣሉና ጸንተህ ተጋደል› ሲል መከረው አባ ሙሴም ወደ በኣቱ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በገዳመ አስቄጥስ እያለ ከገዳማውያን አንዱ ጥፋት ሠራና ማኅበሩ ለፍርድ  ተሰበሰበ፡፡ አባ ሙሴ ግን በጉባኤው ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ካህኑ ተልኰ ‹ና. ሁላችንም አንተን እየጠበቅን ነው› አለው፡፡ አባ ሙሴም በሚያፈስስ ከረጢት አሸዋ ሞልቶ ያንንም በጀርባው ተሸክሞ ከኋላው እያፈሰሰ ወደ ጉባኤው አመራ፡፡ ጉባኤተኞቹ ተገርመው ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹የእኔ ኃጢአቶች በኋላየ እንደዚህ አሸዋ በዝተው ይፈሳሉ፤ ነገር ግን ላያቸው አልቻልኩም ዛሬ ግን በሌላው ላይ ለመፍረድ መጥቻለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ዝም አሉ፡፡ ያን ወንድምም በይቅርታ አለፉት፡፡
በሌላ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ያሉ መነኰሳት ተሰበሰቡና የአባ ሙሴን ትዕግሥት ለመፈተን ሲሉ “ይህ ጥቁር መነኩሴ ለምን እዚህ መጣ “ ብለው ተናገሩት፡፡ እርሱም ዝም አለ፡፡ ጉባኤው ሲበተን “አባ ክፉ ስንናገርህ ምንም ሐዘን አልተሰማህም ነበርን ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ተሰምቶኛል፣ ነገር ግን እንዳልናገረው አንደበቴን ተቆጣጠርኩት” አላቸው፡፡
በአንድ ወቅት በገዳመ አስቄጥስ ጾም ታወጀ፡፡ በዚያ ሳምንት አባ ሙሴን ለማየት ከግብጽ ወንድሞች መጡ፡፡ አባ ሙሴም በእንግድነት ተቀበላቸውና ምግብ ያበስልላቸው ጀመር፡፡ የእሳቱን ጢስ የተመለከቱ ጐረቤቶቹ “አባ ሙሴ ትእዛዝ አፍርሶ ምግብ ያበስላል” ብለው ለገዳሙ ሓላፊዎች ተናገሩ፡፡ ሓላፊዎቹም ‹አሁን ተውት ሲመጣ እኛው ራሳችን እናናግረዋለን› አሏቸው፡፡ ሓላፊዎቹም አባ ሙሴን ጠርተው ለምን ምግብን እንዳበሰለ ተረዱ፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ማኅበሩ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በአደባባይ ‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡
አንድ ጊዜ የአካባቢው ገዥ ስለ አባ ሙሴ ዝና ሰምቶ ያየው ዘንድ ወደ ገዳመ አስቄጥስ መጣ፡፡ ይህን የሰማው አባ ሙሴ ሸሽቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡ በመንገድም ላይ የገዥው መልእክተኞች አገኙትና ‹እባክህ አባ ሙሴ የት እንዳለ በኣቱን አሳየን› አሉት፡፡ ‹ከርሱ ምን ትሻላችሁ፤ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው› አላቸው፡፡ ይህን የሰማው የአካባቢው ገዥ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጣና የሆነውን ሁሉ ለአገልጋዮች ነገራቸው፡፡ ‹ብዙ ሰዎች ስለ አባ ሙሴ ሲያወሩ ሰምቼ ለማግኘት መጥቼ ነበር፤ በመንገድ ላይ ያገኘነው አንድ አረጋዊ ሰው ግን የአባ ሙሴ በኣት የት እንደሆነ ስንጠይቀው ከርሱ ምን ትሻላችሁ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው አለን› ብሎ ነገራቸው፡፡ አገልጋዮቹም በጣም ተናደዱና ‹ምን ዓይነት አረጋዊ ሰው ነው ስለ ቅዱሱ ይህን የሚናገር› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ትልቅ፣ ጠቆር ያለ፣ አሮጌ ልብስ የለበሰ ነው› አላቸው፡፡ አገልጋዮቹም ተገርመው ‹ይህማ ራሱ አባ ሙሴ ነው፤ ይህን ያለህ ሊያገኝህ ስላልፈለገ ነው› አሉት፡፡ የአካባቢው ገዥም ከአባ ሙሴ ሁኔታ ከንቱ ውዳሴን ስለ መሸሽ ትልቅ ትምህርት ተምሮ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በኣት ሠርቶ ወደ ጴጥራ ሲሄድ በአካባቢው ውኃ ስላልነበረ ተጨንቆ ነበር፡፡ አንድ ድምፅ ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› አለው፡፡ ስለዚህም በዚያ መኖር ጀመረ፡፡ አንድ ቀን በጴጥራ እያለ አበው ሊጐበኙት መጡ፡፡ የነበረችው ውኃ ጥቂት ነበረችና በርሷ ምግባቸውን አበሰለ፡፡ የሚያጠጣቸው ግን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ እየወጣ ውኃ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር፡፡ በመጨረሻ ዝናብ ዘነበና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ሁሉ ሞላቸው፡፡ እነዚያ አባቶችም ‹ትወጣና ትገባ የነበረው ለምን እንደሆነ እባክህ ንገረን› አሉት፡፡ ‹እናንተ በእንግድነት ስትመጡ ውኃ አልነበረኝም፣ ስለዚህ ያንተን አገልጋዮች ወደ እኔ ልከሃቸዋል፣ ነገር ግን ውኃ የለኝም፣ ስለዚህ እባክህ ውኃ ስጠኝ እያልኩ እግዚአብሔርን ለመለመን ነበር› አላቸው፡፡
 አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ሙሴም ‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት፡፡› አለው፡፡ ‹ሌላ አይጠበቅበትምን?› ሲል ያ ወንድም ጠየቀው፡፡ ‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ሓላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብጽን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም› አለና መለሰለት፡፡ ያም ወንድም ‹ምን ማለት ነው?› አለው፡፡ ‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ‹ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡› በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሓሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው፡፡
አንድ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ወንድሞች አብረውት እያሉ አባ ሙሴ ‹ተመልከቱ በርበሮች ገዳማችንን ሊያጠፉ እየመጡ ነው፡፡ ተነሡና ሽሹ› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ‹አባ አንተስ አትሸሽምን?› ሲሉ ጠየቁት፡፡ አባ ሙሴም ‹እኔማ ይህችን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ፡፡ ጌታ በወንጌል ‹ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ› ያለው ቃል (ማቴ. 25.52) ይፈጸማል፡፡› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹እኛም አንሸሽም፣ አብረን እንሞታለን እንጂ› አሉት፡፡ አባ ሙሴም ‹ያ ለእኔ ረብ የለውም፤ ሁሉም ሰው ለየራሱ ይወስን› ብሉ መለሰላቸው፡፡ በዚያ ለነበሩት ሰባት ወንድሞች ‹በርበሮች ወደ ገዳሙ ደጅ እየደረሱ ነው› ብሎ ነገራቸው፡፡ ወዲያውም በርበሮቹ ደርሰው ገዳማውያኑን በሰይፍ መቷቸው፡፡ ከሰባቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሸሸና በተቆለለው ሰሌን ውስጥ ተደበቀ፤ ወዲያውም ሰባት አክሊላት ሲወርዱላቸው ተመለከተ፡፡ 
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Thursday, January 10, 2013

አቡነ ሐራ ድንግል ገድል

        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን::
  ከሁሉ አስቀድመን የአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንልጆች የሆን እኛ የክርስቶስ ወገኖች ሰዎች ነገርን ከማብዛት በማሳነስ ነገርን ከማስረዘም በማሳጠር ክቡርና ልኡል ትሩፋቱ ፍፁም ገድሉም ብዙ የሆነ ምስራቃዊ የክብር ኮከብ አርያማዊ የፅድቅ ጸሀይ የኦርቶዶክሳዊ ሀይማኖት ዓምድ የመንፈሳዊ ምግባርማደሪያ የሆነየአባታችን ሐራ ድንግልን ገድሉንና ትሩፋቱን የፅድቁንም ስራ እንጽፍ ዘንድ ህይወትን ሰጪ በሚሆን በባታዊ አድሮ በሚኖር ገዳማዊውን በሚጎበኝ የአለማዊውንም ሰው በደል በመለኮታዊ ስልጣኑ በሚያስተሰርይ በአምላክ ፈቃድ ለመጀመር ተግተን ተመኘን::
 ለሁላችንም የጥምቀት ልጆች ከኦሪታዊው ከሙሴና ከወንጌላዊው ከዮሀንስ ጋር አሸናፊ እግዚአብሄርን በቀናች ሀይማኖትና በመልካም ምግባር ካገለገሉት ከጻድቃንና ከመነኮሳትም ጋር ሰማያዊ የነፍስ ደስታ እድልን ያድለን ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን ለዘላለሙ አሜን::
አቡነ ሐራ ድንግል
  አስቀድመን በመጻፋችን የጠራነው የዚህ ጻድቅ አባቱና እናቱ በላጉና ምድር ይኖሩ ነበር :: እርስዋም ከደራ ምድር አንድ ክፍል ናት::
አባቱም ዮሐንስ የሚባል የሬማ ቄስ ነበር:: እናቱም ወለተ ጊዮርጊስ ትባል ነበር ሁለቱምበወገን ከከበሩ ቤተሰቦች ነበሩ እነርሱም ጻድቃንና ደጋግ ሰዎች እግዚአብሄርን የሚፈሩ ነበሩ ከክፋትም ስራም ሁሉ የራቁ ነበሩ በበጎ ምግባርም ሁሉ የጸኑ ነበሩ ሶስት ወንዶች ልጆች ነበሯቸው ከእነርሱም አንዱ የአለም መብራት የኢትዮጵያ ብርሀን ሐራ ድንግል ነበር ይህንም ገድለኛ ልጃቸውን ከመውለዳቸው አስቀድሞ ገንዘባቸውን ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች ለባልቴቶችና ለሙት ልጆች ለካህናትና ለምእመናን ለህዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ይሰጡ ነበር :;ይህንም ያደርጉ ነበር ስጡ ይሰጣችኋል ዳግመኛም ለሌለው ይስጥ የሚለውን የወንጌል ቃልና ሌላውም መጽሀፍ ካለህ ስጥ ከሌለህም እዘን የሚለውን ቃል አስበው ነው::
 በዚህም ነገር ላይ እንዲህ እያሉ ይጸልዩ ነበር አንተን ደስ የሚያሰኝ ፈቃድህንም ሁሉ የሚያደርግ በደግነቱም ለፍጥረትህም ሁሉ የሚጠቅም ሰሎሞን:-ብልህልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ያሳዝናል ብሎ እንደተናገረ የእኛንም ልብ ደስ የሚያሰኝ ጠቃሚ ልጅ ስጠን ጸሎትም እንደሚጠቅም ከቅዱሳት መጻህፍት ምሳሌ አግኝተው ይህን ሁሉ ጸሎት ጸለዩ::
 ሀና በአንደኛ መጽሀፈ ነገስት ለሚጸልይ የጸሎትን መልስ ይሰጠዋል የጻድቃኑንም እድሜ ያረዝማል ብላለች
 ዳዊትም:-66 መዝሙር መንገድህን ለእግዚአብሄር ግለጥ በእርሱ ታመን እርሱም ያደርግልሀል ብሏል::
ከዚህም በኋላ እግዚአብሄር ጽሎታቸውን ልመናቸውንና እንደ ጣፋጭ ዕጣንና እንደ ንጹህ መሥዋዕት በተቀበላቸው ጊዜ በዚያች ዕለት በጋብቻ ስርአት ተገናኙ ሁለቱም በንጽህና ሐብል የታሰሩ ነበሩና ዝሙትንና ሀጢያትንም አያውቁም ነበርና ነገር ግን :-ወንድ ሁሉ በሚስቱ ጸንቶይኑር ሚስትም በባልዋ ጸንታ ትኑር በሚለው የመጽሀፍ ስርዓት እርስ በርሳቸው ይጠባበቁ ነበር:: በዚያችም በተገናኙባት እለትም ወለተ ጊዮርጊስ መልካም ስራው እንደጸሀይ አወጣጥ የሚያበራ የኢትዮጵያ ብርሀን ሐራ ድንግልን ጸነሰችው ከጸነሰችውም በኋላ በዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በንጉስ አጽናፍ ሰገድ ወለደችው:እርሱንም በወለደች ጊዜ እጅግ ደስ አላት አባቱና ዘመዶቹም እጅግ ደስ አላቸው ሀሴትም አደረጉ ሃጥአንን በእግዚአብሄር ዘንድ በጸሎቱ የሚያስምራቸውና ዳዊት በ111ኛው መዝሙሩ :-መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያፈራል ክፉ ዛፍ ግን ክፉ ፍሬን ያፈራል ዛፍ ከፍሬው ይታወቃልና ብሎ እንደ ተናገረ ወላጆቹን በምእመናን ሁሉ አንደበት የሚያመሰግናቸው የተባረክ ልጅ ተወልዶላቸዋልና በአርባኛው ቀንም ይህን ልጃቸውን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም አንድ ሆነ እንደ አዘዙትሥርዓት የዚያች ቤተክርስቲያን ወሰዱት ያንጊዜም በጥምቀት ፀጋ የወለደው ስሙን ሐራ ድንግል ብሎ ሰየመው::
 ከዝያም በኋላ አባቱና እናቱ ተቅብለው ወደ ቤታቸው ወሰዱት በህግና በሥርዓትም አሳደጉት የሰሎሞንን ቃል አውቀው ቅዱሳት መጽሀፍትን ብሉይ እስክ ሀዲስ የዳዊትንም መዝሙር ለሚያስተምር መምህር ሰጡት ያም ህፃን ቅዱሳት መጽሀፍትን ይሚሉትን አውቆ ስላስተዋለ እስኪያድግና አቅመ አዳም እስኪደርስ ድረስ ለትምህርት የተጋ ሆነ በመምህሩ ፈቃድ  የድቁና ሹመት ከጳጳሱ ይቀበል ዘንድ በዚያ ወራት ሄደ የድቁና ሹመትም ተቀብሎ በደስታና በሀሴት በሰላምና በህይወት ወደ መንደሩ ተመልሶ ገባ
 የጥበባት ባህርና የቋንቋ ባለቤት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የትምህርት ምንጭ ለሆነው ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ:-የዲያቆናት ንጹሓን ይሁኑ ለጸሎትም የነቁና የተጉ ይሁኑ ብሎ እንደተናገረ በንጽህናና በቅድስና በጸሎትና በጭምተኝነት በፍቅርና በትህትና እግዚአብሄርን ያገለገለው ጀመር::
  አባታችን ሐራ ድንግልም በእነዚህ የብሉይና የሐዲስ መጽሀፍት ቃላት ጸንቶ ሲኖር ክቡር ዳዊት 88 መዝሙር ሞትን ሳያይ በህይወት የሚኖር ማነው? ዳግመኛም 143 መዝሙር ሰውስ ከንቱ ይመስላል ዘመኑም እንደ ጥላ ያልፋል ብሎ እንደተናገረ:: በአቤልና በሴት ከተጀመረው ከዚህ ሞት የሚድን ስለሌለ አባቱና እናቱ ከዚህ ዓለም ድካም ዓረፉ ወደ ዘላለም ህይወትም ሄዱ አባታችን ሐራ ድንግልም በወላጆቹ ሞት የመረረ ልቅሶን አለቀሰ አዘነም :;
 አባታችን ሐራ ድንግልም ከአባቱና እናቱ ሞት በኋላ ሬማ በምትባል ደሴት እየተመለለሰ በቤታቸው ውስጥ ለጥቂት ወራት ተቀመጠ ከሬማም ወደ ዘጌ ይሄድ ነበር ከዘጌም ወደዚያው ወደ ሬማ ይመለስ ነበር እንደዚህ አለም ሰዎችም ሚስት ሊያገባ አልወደደም ነገር ግን በድንግልና ኖረ::ልብሰ ምንኩስናም ሳይለብስ አርባ ዓመት ሆነው ከዚህም በኋላ በጽኑዕ ደዌ ታመመ የንዳድ በሽታም ያዛው ክደዌው ጽናት የተነሳም በስጋውና በነፍሱ ከእግዚአብሄር ፈውስን ያገኝ ዘንድ ልብሰ ምንኩስናን ለመልበስ ወደደ መዓዛ ድንግል የተባለውን የሬማ መምህር ልብሰ ምንኩስናን ይሰጠው ዘንድ ለምኖ ነገረው እርሱም ልብሰ ምንኩስናን አለበሰው ለወጣንያን ለማእከላውያንና ለፍፁማንም መነክኮሳት የሚገባቸውን የምንኩስናን ህግ ሁሉ ሰጠው ከዚህም በኋላ እግዚአብሄርን ከሞት ስላዳነው ከደዌው ተፈወሰ::ከዚህም በኋላ የቅስና ማረግን ከዚያ ጳጳስ ከተቀበለ በኋላ በዚሁ ደስ እያለውናሀሴት እያደረገ ከመንገዱ ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ እግዚአብሄር እርሱ የተመኘውንና የፈለገውን አድርጎለታልና በዚህ ሁኔታ እያለ ወደ አለም መመልስ አልፈለገም ተመልሶ ከዘመዶቹና ከሀገሩ ሰዎች ተሰውሮ ወደ ሸዋ ሊሄድ ወደደ ወደ አሰበበት ለምድረስ በመንገድ ላ ሲሄ ዘመዶቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ያገኙትና ከ እነርሱም አንዱ የወንድሙ ልጅና የልቡ ወዳጅ ስለንበር ሁሉንም ያነሳሳቸው አርከ መርዓዊ ይባላል እነርሱም ግራርያ በተባለ ሀገር ያዙትና ወዴት ትሄዳለህ አሉት እባክህ ወደ ሀገርህ ተመለስ ለሀገርና ለዘመዶችህ የሚቀርብ ገዳም እንፈልግልሃለን አንተም እንዳዘዝከን እንደርጋለን እንጂ ከፈቃድህ አንወጣም አንተ አባታችን ጽድቀህ እኛንም በጽድቅህ እንድታጸድቀን ትሉ ከማያንቀላፋ እሳቱም ከማይጠፋ ከገሀነም እሳት እንድታድነንም እንወዳለንና እንደማንሸነግልህ ም በአምላካችን በ እግዚአብሄር ስም እንምልልሀለን ይሄን ቃላቸውን ከሰማ በኋላ እሺ አላቸው::
  እንሱም 7 ምሳሮች ይዘው ከቁስቋም ጀምረው ገዳም እስካደረገው ድረስ መንገዱን ይጠርጉ ዛፎችንም ይቆርጡ ጀመሩ ወደ ገዳሙ በደረሱ ጊዜ ማረፊያዬ ይህች ናት በድካሜም ጊዜ የማርፍበት ትንሽ ቤት ስሩልኝ እንጂ ከዚህ ወደ ሌላ አትሂዱ እስከሞቴ ድረስ በ እርሷ እንድኖር እግዚአብሄር አዞኛልናየስጋዬንም በድን እስከ ሙታን ትንሳኤ ድረስ በውስጧ ይኖራል አላቸው በዚያችም ቀን ዕንጨቱን ቆርጠው መሬቱን ቆፍረው አጥር አጠሩለት እርሱንም በገዳሙ ትተውት ወደ ቤታቸው ሄዱ አባታችን ሐራ ድንግልም በተራበ ጊዜ እንጀራ አይበላ ነበር ጥቂት ምስር አተርና አደንጓሬ ይበላ ነበር ብትንሽ ጽዋ መክደኛ ጽዋ ሰፍሮ በትንሽ ድስት ይቀቅለው ነበር ያም በጽዋው መክደኛ ሰባት መስፈሪያ ነበር በሶስት አንድ ቀን ይመገበው ነበር ከምድርም ፍራፍሬም በበላ ጊዜ እሼ የሚባል ፍሬ ይመገብ ነበር ከምናኔው በኋላ ግን ከውሃ በቀር ሌሎች መጠጦችን አልጠጣም ነበር::
 ያንጊዜም ብዙዎች አራዊት አንበሶች ነብሮች ዝሆኖች ተኩላዎችና ጅቦች የዱር እንስሳዎች ያስፈራሩት ዘን ወደ እርሱ መጡ እርሱ ግን እግዚአብሄር ከእርሱ ጋር ስለነበር ከፊቱ እንዲሸሹ አስፈራርቶ አስደነገጣቸው እንጂ አልፈራቸውም ይህም ነገር ከሆነም በኋላ የቅል ዓይነት ተክልና ወይን ሎሚና ኮክ ተከለ እነዚህንም ተክሎች ከሩቅ ወንዝ ውሃ በእጁ ቀድቶ በትከሻው ተሸክሞ ያጠጣቸው ነበር መንገዱም ሩቅ ስለነበር አባታችን ሐራ ድንግል እንዲህ ብሎ ጸለየ ከ እናቴ ማህጸን ያወጣሀኝ እስከ እዚች ሰአት ያደረስከኝ ፈጣሪዬ እግዚአብሄር ሆይ እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሙሴ ከዓለት ውሃን እንዳወጣ ከዚህ ምድር ውሃን አውጣ ዘንድ ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ይህን ብሎ በሁለት ረድፎች ምድሩን ቆፈረ በመስቀልም ምልክት ባረካቸው ወዲያውኑ ከሁለቱም ረድፎች ውሃዎች ፈሰሱ በፈለቁት ውሃዎች በየጊዜው እንዲያፈሩና ሊያዩት ወደ እርሱ ለሚመጡት ሰዎች ምግብ እንዲሆኑ እንዚህን ተክሎች አጠጣቸው ለሚልውምኑትም ድሆችም ቅጠሉ ፍሬ ያፈራውን አይነት በገበያ አሽጦምጽዋት ይሰጣቸው ነበር::
በዚያ ጊዜም የበጎ ነገር ጠላት ሰይጣን በሴት አምሳል በንጭ ሀር በወርቅበብር በጉትቻዎችና በቀለበቶች አጊጦ መጣና እንዲህ አለው ለምን ብቻህን ትኖራለህ ? ሁለት ሆነው መኖር ሰዎች ልማዳቸው ነውና ከ እኔ ጋር ብትኖር አይሻልህምን? አባታችንም ትቆጣ የ እግዚአብሄርን ቃል በሚጸልይበት በጠበል እቃ የነበረውን ውሃ በሰይጣ ረጨበት ሰይጣንም ድንግጦ ሸሸ በባህርም ስጠመ አባታችን እስኪሰማ ድረስ ባህሩን አወከው አባታችንን ለማሳት ሰባት ጊዜ መጣ ነገር ግን በ እግዚአብሄር ሀይል ድል ተደረገ::
  አንዲት ሚዳቆ ነብር እያባረራት መጣች ወደ አባታችን ሐራ ድንግል ቤትም ገብታ በእርሱ ተመአጥና ከ እግሩ በታች ተጋደመች አባታችንም ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሄር እየጸለየና እየለመነ ተቀምጦ ነበር ያቺን ሚዳቆ የሚያባርራት ነብርም መጣ አባታችን ወዳለበት ደርሶ በደጁ ቆመ አባታችንንም ባየው ጊዜ ጊዜው ቀን ስለ ነበረ ፈርቶ ወደ ውስጥ አልገባም ያም ነብር ተቆጥቶ በዚያው ቦታ ተፍገመገመ አባታችን ነብሩን ገድለህ ትበላት ዘንድ እግዚአብሄር አልሰጠህም ነብሩም ይህን ነገር ከአባታችን ቃል ሰምቶ ሳይገድላት ሄደ በዚያች ሌሊት በእርሱ ዘንድ አደረች በማግስቱም ከቤቱ ወጥታ በደጅ ስትመላለስ አባታችን ባያት ጊዜ እንዲህ ብሎ አሰናበታት ከቦታሽ አባርሮ ያሳደደሽ ወደ እኔም ያደረሰሽ ያ ነብር ትናንት ስለሄደ ወደ ቦታሽ ሂጂ ይህንም ሰምታ ወደ ቦታዋ ተመለሰች:;
  አባታችንም ሁለት ደቀመዝሙሮች ነበሩት ወንዱ እሱን ያዘዘውን የሚፈጽም ነበር ተስፋዬ እና  አመተ እግዚእ አለምን ንቃወደ ገዳብ የገባች ነበረች እርሳውም ከአባታችን ቤት ትንሽ በሚርቀው ቤት ተቀምጣ ከምናኔዋ ጀሮ በሞት እስከ ተለየች ድረስ ረዳትና አገልጋይ ሆና ራሷን ለአባታችን ሰጠች እርስዋም በስጋ ዝምድና ከሚቀርቡት አንድዋ ነበረች እርሷም በአገልግሎቷና በታዛዥነቷ እንደዚህ ይሁን የሚለውን ፈቃዱን በመፈጸም እጅግ ደስ አሰኘችው በምግባርዋ ደግ በነገሯም እውነተኛ በልቡናዋም ብልህ ነበረች::
ከዚህም በሃላየአንዲት ታቅ ሴት አሽከሮች ወደ አባታችን መጡ ሊጣሉትም ወደቤቱ ገቡ አንተ ከንጉሱ ፈቃድ ወጥተህ በአመጽ የምትኖር የንጉስ ከዳተኛ አይደለህምን እያልይ ፈጽመው ሰደቡት ከገቡበትም ወጥተው የ አባታችን የወይን ዘለላም ምንም ሳያስቀሩለት ቆረጠው ወሰዱ አባታችንም ምንም አልተናገራቸውም የወሰዱትንም ወይን ለእመቤታቸው የወይኑ ዘለላ ሰጡ እመቤታቸውም ይሀ ወይን ከማን አመጣችሁ ሐራ ድንግል ከሚባለው መንኮስ ነው አላት አንዱንም የሆድ በሽታ ይዞ አንጀቱን ቆረጠው እመቤታቸውም እነዚህን አንተን ያስቀየሙ የበደሉና ማርልኝ ብላ አሽከሮችን ላከች እግዚአብሄር ይቅር የሚላቸውና በደላቸውና የሚተውላቸው ከሆነ ይቅር እላቸዋለሁ አሽከርም በተመለሰ ጊዜ ሆዱን የቆረጠው ሞተ ጻድቁ አባታችንን ስለተሳደበ እግዚአብሄር ትቆጥቶታልና ይህ የሰሙትን የተደረገውን ባዩ ጊዜ አደነቁ::
ይህ ድንቅ ነገር ከሆነ ረዥም ወራት በሃላ አመተ ወልድ የተባለች አንዲት ሴት ታመመች እርስዋም በዚሁ በሽታ ሞተች መላእክተም  ሞትም ነፍስ ወሰዱ ያችንም ነፍስ እያጣደፉና እያዳፉ ወደ ፈጣሪዋ አደረሳት በዚች ሰአትም አባታችን ሐራ ድንግል ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሄር እንዲህ እያለ ጸለየ አለቀሰም ይህችን ዛሬ የሞተችውን ሥጋዋም በመሬት ተጥሎ በነፍስዋ ወደ አንተ የመጣችውን ማርልኝና አንሳልኝ ነፍሴንና ስጋዬን በአንተ ላይ ጥያለሁ ብላ በእኔ ላይ  እንደ ተማጠነች አቤቱ አንተ ራስህ ታውቃለህና በህይወት ሳለችም እንዳገለገችኝ አንተ ራስህ ታውቃለህ አባታችንም ይህን ጸሎት ጸልዮ ዝም አለ እግዚአብሄርም ይህችን ነፍስ ለምን ወደ እኔ አመጣችሃት የሕራ ድንግል አደለች የ እርሱ ስለሆነች ወደ እርሱ መልሳት እርሳም በስማይ ሳለች ከፈጣሪዋ አንደበት ከሰማች በኋላ የመላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ለወዳጄ ሐራ ድንግል ሶስት ጊዜ እንዲህ ብለህ አዋጅ ንገር ሲለ ከዚያ ከፈጣሪ አንደበት ሰማች::
  ሐራ ድንግል ሆይ በ እጅህ የተባረከውንና በቃልህ የተጽናናውን ስምህን የጠራውንና መታሰቢያህን ያደረገውን ለተራቡትም ለተጠሙትም እህልና ውሃ በመስጠት በዓልህን ያከበረውን ሀጢአተኛና በደለኛ ሳለም በጸሎትህና በቃል ኪዳንህ የታመነውን የገድልህንም መጽሀፍ ያጻፈውን ያነበበውንና የተረጎመውን የሰማውንና ለሰዎች ያሰማውን አጽምህንም እየጠበቀ  በገዳምህ የተቀመጠውን አንተን ወድዶ ከሩቅ ወይም ከቅርብ ሀገር በመምጣት ገዳምህን የጎበኘውን ወንድ ልጁንና ሴት ልጁንም በስምህ የጠራውን እነዚህ ሁሉ በየወገናቸው ከስጋና ከነፍስ ባርነት ነጻ የወጡ ይሆኑ ዘንድ እስከ ሰባት ትውልድ ምሬልሃለሁ አንተ አገልግለሃልና ከህፃንነትህም ጀምረህ እስከዚች ሰአት ፈቃዴን ፈጽመሃልና::
 በሞት ከሥጋዋ የተለየች ያች ነፍስም ይህን ነገር በሰማች በኋላ ከሰማይ ተመለሰች ከሥጋዋ ጋር ተዋህዳ በአባታችን ጸሎት ተነሳች ለወዳጄ ሐራ ድንግል ሂድና አዋጅ ንገር ብሎ መላኩ ገብርኤልን ሲያዝዘውከ እግዚአብሄር የሰማችውን ቃል ኪዳን ለሰዋች ተናገርች አባታችን ሐራ ድንግልም በጸጋ አወቀ የእግዚአብሄር ምስጢር ባየችው በዚች ሴት መነሳት ደስ አለው::እግዚአብሄርም ለአባታችን ሁለት ቃል ኪዳን ሰጠው አንደኛው ያቺ ሴት ናት ሁለተኛውም ከዚህ አለም በሞት ተለይቶ ወደ ዘላአለም ህይወት በሄደ ጊዜ እግዚአብሄር የሰጠው ነው::
  የአባታችን ሐራ ድንግልም የእረፍቱ ቀን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሄር የምህረትና የይቅርታ ቃል ኪዳንን ይሰጠው ዘንድ ከሰማይወደ እርሱ መጥቶ  ወዳጄ ሐራ ድንግል ሆይ ስለ እኔ ብዙ አመታትን ደክመሃል እኔም እንዲህ ብዬ ቃልኪዳ እስትሃለሁ::
   ሐራ ድንግል ሆይ በ እጅህ የተባረከውንና በቃልህ የተጽናናውን ስምህን የጠራውንና መታሰቢያህን ያደረገውን ለተራቡትም ለተጠሙትም እህልና ውሃ በመስጠት በዓልህን ያከበረውን ሀጢአተኛና በደለኛ ሳለም በጸሎትህና በቃል ኪዳንህ የታመነውን የገድልህንም መጽሀፍ ያጻፈውን ያነበበውንና የተረጎመውን የሰማውንና ለሰዎች ያሰማውን አጽምህንም እየጠበቀ  በገዳምህ የተቀመጠውን አንተን ወድዶ ከሩቅ ወይም ከቅርብ ሀገር በመምጣት ገዳምህን የጎበኘውን ወንድ ልጁንና ሴት ልጁንም በስምህ የጠራውን እነዚህ ሁሉ በየወገናቸው ከስጋና ከነፍስ ባርነት ነጻ የወጡ ይሆኑ ዘንድ እስከ ሰባት ትውልድ ምሬልሃለሁ አንተ አገልግለሃልና ከህፃንነትህም ጀምረህ እስከዚች ሰአት ፈቃዴን ፈጽመሃልና::
 አባታችን ሀራ ድንግል ይህን ቃል በሰማ ጊዜ እግዚአብሄርን ሲያመሰግን እንዲህ አለ አምላኬ ሆይ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ቅዱስ ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ ሁልጊዜ አመሰግንሃለሁ ስምህንም ለዘላለም ዓለም አከብራለሁ ደግ ወይም ክፉ ቢሆን በእኔ የተማጠነ ሰው ሁይድን ዘንድ ይህን ቃል ኪዳን ሰጥተሀኛል እግዚአብሄርም ይህን ምስጋና ከእርሱ ከተቀበለ በኋላ ከእርሱ ዘንድ ሄደ:: 
 ገዳሙንም እንዲህ እያለ ባረካት የአብና የወልድ የመንፈስ ቅዱስም በረከት በገዳሜና ስሜን በሚተሩ ሁሉ ላይ ይደር አምላክን በወለደች የ እመቤታችን የማርያም በረከትም በገዳሜና እኔን በሚወድዱ ሁሉ ላይ ይደር
  የሚካኤልና የገብርኤል በረከት የማያንቀላፉ ትጉሃን ዝም የማይሉና አመስጋኞች የሆኑ የሱራፍኤልና የኪሩቤል በረከት በገዳሜና በእኔ በሚማጸኑ ሁሉ ላይ ይደር
  የ እስጢፋኖስ የጊዮርጊስ የመርቆርዮስ የፋሲለደስ የቴዎድሮስና የገላውዴዎስ የድል አድራጊዎች ሰማእታት ሁሉ በረከት በገዳሜና ፈቃዴን በሚፈጽሙት ሁሉ ላይ ይደር
 የ አባታችን አቡነ ትክለሀይማኖትና የ አባታችን አዎስጣቴዎስ የ አባታችን የገብረ መንፈስ ቅዱስና በኢትዮጵያ ውስጥ በገዳማትና በአድባራት በደሴቶችም የሚኖሩት ሁሉ በረከት በገዳሜና በውስጥዋ ሆነው አስከሬኔን በሚጠብቋት ሁሉ ላይ ይደር
 የሀይማኖት አምድና የቸርነት መዝገብ የሆነው እንደ መላእክትም በንጽህና የተሸለመው አባታችን ሐራ ድንግል ይህን ቃለ ቡራኬ ከተናገረ በኋላ በኢያቄምና በሐና በፋሲለደስና በገላውዴዎስ በፊቅጦርም በዓል ጥር አስራ አንድ ቀን ከዚህ ከሀላፊው ዓለም ድካም አረፈ:: በአሉም ጥር 11 ቀን በታላቅ ድምቀት በባህርዳር ይከበራል::
ምንጭ ገድለ አቡነ ሐራ ድንግል
 ጽሎቱና በረከቱ ከሁላችን ከህዝበ ክርስቲያን ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን:;

Wednesday, January 9, 2013

ተዋሕዶ ያለ ጥርጥር ታላቅ ምስጢር /1ኛጢሞ 3፥16/


በዲ/ን ኅሩይ ባየ



  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሁለት ዓመት የዕሥር ጊዜውን ጨርሶ ከሮም ከተማ ከወጣ በኋላ ጥቂት የአገልግሎት ጊዜ ሲያገኝ በ66 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የጢሞቴዎስ መልእክት ጽፏል፡፡

“እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል” እንደሚባለው  በግብር በቃል በሐሳብ ሥነ ፍጥረትን ከፈጠረበት አምላካዊ ጥበቡ ይልቅ ሰው በወደቀ ጊዜ ከወደቀበት የተነሣበት የአምላክ ሰው መሆን ምስጢር ታላቅ በመሆኑ ይኸ ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ተብሎ ተጽፏል፡፡ “በሥጋ የተገለጠ በመንፈስ የጸደቀ ለመላእክት የታየ በአሕዛብ የተሰበከ በዓለም የታመነ በክብር ያረገ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወሰኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ታላቅ ነው፡፡

አዳም የ30 ዘመን ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በገነት 7 ዓመት ከኖረ በኋላ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ልጅነቱን ቢያጣም ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃደ ሥጋን በጾም ድል ነሥቶ ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር አስተምሮ ስስትን ድል አደረገ፡፡ የአዳም እግሮች ወደ ዕፀ በለስ ተጉዘው በእጁ ቆርጦ ቢበላ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ተጉዞ እጆቹና እግሮቹን ተቸንክሮ ተሰቅሎ አዳነው፡፡ አዳም ከጸጋ ልብሱ ቢራቆት ኢየሱስ ክርስቶስም የብርሃን ልብሱ እንዲመለስለት እርቃኑን ሆኖ ተሰቀለ፡፡ ይህ ሁሉ የማዳን ሥራው በሥጋ በመገለጡ የተደረገ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ የአዳምን ሞት ወሰዶ የእሱን ሕይወት ሰጥቶ የመቃብርን ኀይል ሽሮ ሞትን ድል አድርጎ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ያለጥርጥር ታላቅ ነው፡፡


የእግዚአብሔር ምስጢሩ ታላቅ መሆኑን ቅዱስ አትናቴዎስ ሲያስረዳ “ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት መረዳት /ማወቅ/ የልብሱን ጠርዝ ብቻ እንደማወቅ ነው፡፡ ስለ ምስጢረ መለኮት የበለጠ በመረመርኩ ቁጥር የበለጠ ምስጢር ይሆንብኛል” ይላል፡፡ እውነትም የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት መመርመር የአምላክ ሰው የመሆንን ምስጢር መረዳት ለሰው አእምሮ የረቀቀ ነው፡፡

አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ አዳምን እና ልጆቹን ያዳነበት ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ በመሆኑ በቸርነቱ ያዳነንን አምላክ ከማመስገን በቀር ምን ልንል እንችላለን?

በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ትምህርታችን አምላክ ሰው ሆኖ አዳምንና ልጆቹን አዳናቸው ብለን እናስተምራለን አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ ስንል በምስጢረ ተዋሕዶ ነው፡፡ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ ንስጥሮስን ከክህደቱ ለመመለስ 200 የሚሆኑ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ የሊቃውንቱ አፈ ጉባኤ የነበረው ቅዱስ ቄርሎስ ተዋሕዶ የሚለውን ቃል አጉልቶ ተጠቅሞበታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኦርቶዶክስ ከሚለው ቃል ጋር ተዋሕዶ የሚለው ቃል የበለጠ መታወቅ ጀምሯል፡፡

አምላክ ሰው ሆነ ስንል መለኮት ወደ ሥጋነት ሥጋም ወደ መለኮትነት ተለወጠ ማለታችን አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ /ሐውልት/ ሆናለች /ዘፍ.19፥26/፡፡ በቃና ዘገሊላም በገቢረ ተአምር ውኃው ወደ ወይን ጠጅ ተለውጧል /ዮሐ.2፥1/፡፡ የሎጥ ሚስት የጨው ሐውልት እንደሆነችው፤ ማየ ቃናም ፍጹም የወይን ጠጅ እንደሆነው አምላክ ሰው ሆነ ስንል አምላክነቱን ለውጦ ፍጹም ሰው ብቻ ሆነ ማለታችን አይደለም፡፡ እንዲሁም አምላክ ተለውጦ ሰው ቢሆንማ ኖሮ የእሩቅ ብእሲ ደም ድኅነትን ሊያሰጥ ስለማይችል በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ፍጹም ድኅነት ከንቱ ያደርግብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ እንደማይለወጥ በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል /ሚል.3፥6/፡፡ በመሆኑም አምላካችን ሰው የሆነበት ምስጢር ቃል /መለኮት/ በሥጋ ሥጋም በቃል ሳይለወጥ ሳይጠፋፉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡

“ቃል ሥጋ ሆነ…. በእኛም ላይ አደረ” /ዮሐ.1፥1-14/ የሚለው ገጸንባብ መጽሐፍ በማኅደር ውኃ በማድጋ እንዲያድር መለኮት በሥጋ ላይ አደረበት ማለት አይደለም፡፡ “የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ማርያም በተወለደው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አደረበትና የጸጋ አምላክ አደረገው እንጂ ሥጋን አልተዋሐደም” ብሎ ንስጥሮስ ያስተማረው  የኅድረት /ማደር/ ትምህርት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተወገዘ ክህደት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” /ማቴ.3፥17/ አለ እንጂ “የልጄ ማደሪያ የሆነውን እርሱን ስሙት አላለም”፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ነቢዩ ሲያስረዳ “…ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ…” /ኢሳ. 9፥6/ ብሏል፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው እያለች ታስተምራለች፡፡

አምላክ ሰው የሆነው መለኮትና ሥጋ ተቀላቅለው ነው አንልም፡፡ መቀላቀል /ቱሳሔ/ መደባለቅንና ከሁለቱም የተለየ ማእከላዊ ነገር መፍጠርን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ውኃና ወተት ሲቀላቀሉ ስም ማእከላዊ መልክ ማእከላዊና ጣእም ማእከላዊን ያመጣሉ፡፡ ስም ማእከላዊ ውኃ ከወተት ጋር ቢቀላቀል ፈጽሞ ውኃ ፈጽሞም ወተት ባለመሆኑ አንጀራሮ የተባለ ሌላ ስም ይሰጠዋል፡፡ መልክ ማእከላዊ ስንልም ውኃው እንደወተቱ ባለመንጣቱ እንደ ውኃውም ባለመጥቆሩ መካከለኛ የሆነ መልክ ይይዛል፡፡ ጣእም ማእከላዊ ውኃውም ወተቱም የቀደመ ጣእማቸውን ለቀው እንደ ውኃ ባለመገረም/ባለመክበድ/ እንደ ወተቱ ባለመጣም ማእከላዊ የሆነ ጣእም ያመጣል፡፡ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢር ግን ሥጋ የሥጋን ባሕርይ ሳይለቅ መለኮትም የመለኮትነትን ባሕርይ ሳይለቅ በተአቅቦ /በመጠባበቅ/ ባለመጠፋፋት ነው፡፡ መለኮትና ሥጋ ሳይቀላቀሉ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ የራሱ አድርጎ መለኮትም የሥጋን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ በተዋሕዶ ሰው ሆነ፡፡

አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ስንል ልብስ በልብስ ላይ እንደሚደረብ መለኮትና ሥጋ እንደዚሁ በትድምርት /በመደራረብ/ ሰው ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በቆሎና ስንዴ ቢቀላቀሉ ይህ በቆሎ ነው ይህ ስንዴ ነው ብለን እንደምንለያቸው የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ በመለያየት /በቡአዴ/ ከቶ አልሆነም፡፡

ማኅተመ አበው ቅዱስ ቄርሎስ ምስጢረ ተዋሕዶን ባስተማረበት ትምህርቱ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ስንል በተዋሕዶ እንደሆነ በምሳሌ ገልጦ አስተምሯል፡፡ ተዋሕዶውም ነቢዩ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በጎቹን ሲጠብቅ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥል ሐመልማሉም በነበልባሉ ሳይጠፋ እንዳልተጠፋፉት መለኮት ሥጋን ሳያቀልጠው መለኮትም በሥጋ ሳይጠፋ በተዋሕዶ አንድ ሆነ እንላለን፡፡ በእሳት ውስጥ የገባ ብረትም የባሕርዩ ያልነበረውን ብሩህነት በእሳቱ ያገኛል፤ ቀድሞ አይፋጅ የነበረው ብረት ይፋጃል፡፡ አካል ያልነበረው እሳትም በብረቱ ሆኖ ቅርጽ ይኖረዋል፡፡ አይጨበጥ የነበረው እሳት ይጨበጣል፤ አይዳሰስ የነበረው እሳት ይዳሰሳል፡፡ አንጥረኛው በጉጠት ብረቱን ይዞ ፍህም የሆነውን ብረት ይቀጠቅጠዋል፡፡ ብረቱ ሲደበደብ የተመታው እሳቱ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ብረቱ ነው አይባልም፡፡ እሳትና ብረት በተዋሕዶ አንድ ስለሆኑ ብረቱ ሲመታ እሳቱ አለ፤ እሳቱ ሲመታም ብረቱ አለ፡፡ እሳቱ ሲፋጅም /ቢያቃጥልም/ ብረቱ አለ፡፡የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም በዚህ መልክ ስለሆነ መለኮት ሥጋን በመዋሐዱ መከራን ተቀብሎ ሞቶ አዳነን ብለን እናምናለን፡፡

በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ዐይነ ስውሩን ሰው አምላካችን ሊያድነው በፈቀደ ጊዜ ምራቁን ወደመሬት እንትፍ ብሎ በጭቃ ዐይኑን ቀብቶ አድኖታል /ዮሐ.9፥1/ ምራቅ ብቻውን ዐይንን በማብራት ተአምር መሥራት የማይችል የሥጋ ገንዘብ ነበረ፡፡ መለኮት ብቻውንም ምራቅ ማውጣት አፈር ማራስ አይስማማውም ሥጋ ከመለኮት ጋር ተዋሕዷልና በምራቁ ዕውርን አበርቷል፡፡ ገቢረ ተአምራቱም የተከናወነው በሥጋ ብቻ ነው ወይም በመለኮት ብቻ ነው አይባልም፡፡

ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ሰው በመሆኑ በባሕርዩ ተዋራጅነት የለውም በላይ በሰማያት ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እየተመሰገነ በምድር ዞሮ አስተምሮ መከራን ተቀብሎ ፍጹም ድኅነትን ሰጥቶናል፡፡ በሥጋ ተርቧል፣ ተጠምቷል አንቀላፍቷል፡፡ አምላክ ነውና ሙት አንሥቷል ድውይ ፈውሷል፡፡ በመሆኑም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆነ የምንለው በተዋሕዶ ነው፡፡ በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ በመሆኑ የሥጋንም የመለኮትንም ሥራ ባለመለያየት ባለመነጣጠል ሠራ በቅዱስ መጽሐፍ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ፡፡” /ሐዋ.26፥28/ ተብሎ መጻፉ መለኮት በባሕርዩ ሥጋ ደም ኖሮት አይደለም፡፡ ይህ የሐዋርያው ቃል መለኮት የሥጋን ባሕርይ ባሕርዩ አደረገ ደሙን አፈሰሰ ሥጋውን ቆረሰ ብለን ለምናስተምረው የተዋሕዶ ትምህርት የታመነ ምስክር ነው፡፡ እግዚአብሔር “በገዛ ደሙ” ቤተ ክርስቲያንን የዋጃት በተዋሕዶ ሰው በመሆን ነውና በእውነት ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስለምስጢረ ሥጋዌ እንዲህ ይላል” ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ስለልጁ የተናገረ በሰብአዊ ሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደ በአብና በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን ዐሳየ ዳግመኛም ነቢዩ እንባቆም እንዲህ አለ፤ እግዚአብሔር ከቴማን ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል፡፡ ፋራን በጣዕዋ /በጥጃ/ ይተረጎማል ጣዕዋ በንጽሕት ድንግል ይተረጎማል፡፡ ክብሩ ሰማያትን  ከድኗል፡፡ ይህም በመለኮት ኀይል ከአባቱ ጋር እኩል ትክክል በመባል ይተረጎማል፡፡ ምስጋናውም ምድርን ሞልቷል ይህም በአጽናፈ ዓለም በተሰበከው ገቢረ ተአምራት ይተረጎማል በምድር ሁሉ ነገራቸው ወጣ፡፡ እስከ አጽናፈ ዓለም ንግግራቸው ደረሰ፤ ተብሎ በነቢዩ እንደተነገረ፤ ዳግመኛ በነቢይ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው ተብሎ እንደተነገረ፤ ዳግመኛም ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ፤ ጌታ እግዚአብሐር ተገለጠልን፤ እንደገና በኪሩቤል የሚቀመጥ ተገለጠ፤ ተብሎ እንደተነገረ ያለሥጋዌ እግዚአብሔርን ያየ ማነው? ሙሴን “ፊቴን ዐየቶ በሕይወት የሚቆይ የለም” እንዳለው ነው” ይላል፡፡ /ሮሜ.1፥33፣ ዕብ.1፥1፣ ዕን.3፥3፣ መዝ.18፥4፣ መዝ.117፥26-27፣ መዝ.79፥1፣ ዘፀ.33፥1/ (መጽሐፈ ምስጢር 2000፥82 በአማኑኤል ማተሚያ ቤት ኀይለ ማርያም ላቀው /መ/ር/ እንደተረጎመው)

ተዋሕዶ ከሚጠት /ከመመለስ/፣ ከውላጤ /ከመለወጥ/፣ ከቱሳሔ /ከመቀላቀል/፣ ከትድምርት /ከመደረብ/ ከቡዐዴ /ከመቀራረብ/ በራቀና በተለየ ሁኔታ አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር ነው፡፡ መለኮትና ሥጋ አንዱ አንዱን ሳያጠፋው፣ ሳይለውጠው፣ ያለ መለያየት፣ ያለመከፋፈል ያለ መጠፋፋት ያለ መቀላቀል በተዐቅቦ /በመጠባበቅ/ የተዋሐዱበት አምላክ ሰው የሆነበት ይህ ምስጢር ድንቅ ነው፡፡

ቅዱስ ቄርሎስ የተዋሕዶን ምስጢር በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል “የሚረዳህስ ከሆነ የትስብእትና /የሥጋ/ የመለኮትን ተዋሕዶ በእኛ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ መስለን እንነግርሀለን፤ እኛ በነፍስና በሥጋ የተፈጠርን ነንና፤ አንዱን የሥጋ አንዱን የነፍስ ብለን ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አናደርገውም፤ ሰው ከሁለት አንድ በመሆኑ አንድ ነው እንጂ፡፡ ከሁለቱም ባሕርያት አንድ በመሆኑ ሁለት ሰው አይባልም፡፡ በነፍስ በሥጋ የተፈጠረው ሰው አንድ ነው እንጂ፡፡ ይህንንስ ካወቅን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶ በፊት እርስ በርሳቸው አንድ ካልነበሩ ከተዋሕዶ በኋላም ከማይለያዩ ከሁለት ባሕርያት አንድ እንደሆነ እናውቃለን” /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ.78፥19/

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ በምድር ላይ በመገለጡ ከባሕርዩ የጎደለበት ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በላይ በሰማያት በመላእክት እየተመሰገነ በምድር ዞሮ አስተማረ፤ መከራ ተቀበለ ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ አስተምህሮ ምስክር የሚሆነን የቅዱሳን መላእክትና የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ቃል ነው፡፡መላእክቱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” አሉ /ሉቃ.2፥14/፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ /በክንድሽ/ ተቀምጦ እንደ ሕፃን ጡትሽን ሲጠባ መላእክት ባዩት ጊዜ በአርያም ፈለጉትና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት” ብሎ አመስጥሮታል፡፡ ፀሐይ ባለችበት ሆና ምድርን እንደምታሞቅ እርሱም በዙፋኑ ተቀምጦ   /ዓለምን እየገዛ/ በምድር በሥጋ ማርያም ተገለጠ፡፡ ሥጋን ተዋሕዶ ዞሮ አስተማረ” /አንቀጸ ብርሃን ዘቅዱስ ያሬድ/

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ በልባችን ስናስበው በአንደበታችን ስንናገረው ምስጢሩ ድንቅ በመሆኑ ሐዋርያው ይህ ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ይላል፡፡ ነቢዩ ሙሴም የእግዚአብሔር ሥራ ግሩም በመሆኑ አምነን ከመቀበል ውጭ መርምረን መድረስ ስለማንችል “ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው” ዘዳ.29፥29 እንድንል ያስታውሰናል፡፡

ሎቱ ስብሐት ለዘበስብሐተ አቡሁ ይሴባሕ ወሎቱ ቅድሳት ለዘበቅድሳተ መንፈሱ ይትቄደስ ለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን፡፡በአባቱ ምስጋና ለሚመሰገን ለእርሱ ምስጋና ይገባል፡፡ በመንፈሱ ቅድስና ለሚቀደስ ለእርሱ ምስጋና ይገባል ለዘለዓለሙ አሜን፡፡