Wednesday, February 20, 2013

ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ

          በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና …. ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው……የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።” መዝ.፴፫፡-፲፱
የእናታችን የቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ፀጋ በረከትዋ ይደርብን።

ሀገሯ ቡልጋ ጽላልሽ ቅዱስጌ ነው። አባቷ ደርበኒ እናቷ እሌኒ ይባላሉ። ለአካለ መጠን ስትደር ሠምረ ጊዮርጊስ ለሚባል ደግ ካህን ዳሯት። ፲፪ ልጆችም ወልዳለታለች። ንጉስ አጼ ገብረ መስቀል የልቧን ቅንነት የምግባሯን ደግነት የምትለብሰው የምታነጥፈው አልባሳት ወርቅ ወጥተው ወርደው የሚያገለግሏት መቶ ሰባ አራት አገልጋዮች ሠደውላታል። በኋላ ዓለምን ንቃ ልብሰ ምንኩስናን አዘጋጅታ ስትሔድ ሕጻን ልጇን ይዛ ኖሮ ልጇ ከዚህ አይገባም ቢሏት ከበር ትታው ገብታለች። ቅዱስ መካኤል ነጥቆ ሄሮድስ ካስፈጃቸው ፲፬ እልፍ ሕጻን ደምሮታል። እሷን በክንፉ ተሸክሞ ታና ሐይቅ አድርሷታል።
“ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” ዮሐ.፫፡፲፪ በዚህ ከመከራዋ ብዛት ከገድሏ ጽናት ሰውነቷ ተበሳስቶ የዓሣ መመላለሻ እስኪሆን ድረስ ከባሕሩ ገብታ ወደ ግራ ቀኝ ሳትል አሥራ ሁለት ዓመት ጸልያለች። በመጨራሻም ጌታ ምን አደርግልሽ ዘንድ ትሽያለሽ? አላት። እሷም ሰው ሆኖ የማይበድል እንጨትሆኖ የማይጨስ የለምና ውሉደ አዳም እንዳይስቱ ዲያብሎስን ማርልኝ አለችው። ከሆነልሽማ አንጪው አላት ቅዱስ ሚካኤል ወስዶ ሲዖል አደረሳት። ዲያብሎስ ና ውጣ አለችው። በምድር ፈልጌ ባጣሽ ሳዝን ነበር። አሁንማ ከቤቴ መጣሽልኝ ብሎ ጎትቶ አስገባት። ቅዱስ ሚካኤል ተከትሎ ገብቶ ነጥቆ አውጥተቷተታል። ስተወጠጣ ስለ ገድሏ ጽናት ስድስት ክንፍ ተሰጥቷት በዚያ ነፍሳትን ማርካ ወጥታለች። 

በፍጻሜ ዘመኗ በቁመቷ ልክ በዓት ሰርታ ከግራ ከቀኝ ከፊት ከኋላ ዐሥራ ሁለት ጦር ተክላ ወዲያ ወዲህ ሳትል፤ ቆማ ፲፪ አመት ኖራለች። ስትሰግድም ሥጋዋ በጦር ተወግቶና ተፈቅቶ አልቋል። ጌታም ይህን ሁሉ መከራዋን እንደመሥዋዕት ቆጥሮላት በቃል ኪዳኗ የተማጸነውን ስሟን የተራውን እስከ አሥር ትውልድ እንዲምርላት ተስፋዋን ነግሯት ክብርት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሜ መላእክት አሳርጓታል። የዕረፍቷ መታሰቢያ ነሐሴ ፳፬ ይከበራል። በረከቷ አማላጅነቷ፤ ቃል ኪዳኗ አይለየን አሜን።
“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” ወደ ዕብ.፲፪፡፩¬-፪
(12:-1-2)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን ይቆየን።

Wednesday, February 6, 2013

ዐብይ ጾም


                                             በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሕልና ትውፊት እና ሥርዓት የሚጀመረው የጾም ወራት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው፣ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡

ይህ ታላቅ የሆነው የጾማችን ወራት በተለያየ ስያሜ ይጠራል፡፡

1. ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡

ሌሎች አጽዋማት ከቅዱሳን አበው የወረስናቸው የኑሮአቸው ፍሬዎች (ዕብ.13፤7) ሲሆኑ ይኼኛው ግን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ (ታላቅ) ይባላል፡፡ የጌታ ጾም ስለሆነ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሡበት፣ ድል የሚነሡበት ጾም ስለሆነም ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡

2. ጾመ ሁዳዴ ይባላል፡፡

ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት፣ የመንግሥት ርስት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ጊዜ፣ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ ዐዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ ይህንንም የጌታ ጾም የጌታ ወይም የጌታ ሁዳድ የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታልና ጾመ ሁዳዴ ይባላል፡፡

3. የካሣ ጾም ይባላል፡፡

አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት$ ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነበር፡፡ በሆዳምነቱ የወደቀውን የሰው ልጅ በፈቃዱ በጾመው ጾም ካሠው$ እንዲሁም አዳም ከገነት ሲባረር ረሃበ ጸጋ (መንፈሳዊ ረሃብ) ደርሶበት ነበርና ረሃቡን በረሃብ ካሠለት፡፡ የኛን ረሃብ እርሱ ተራበ፡፡

4. የድል ጾም ይባላል፡፡

ጌታችን ተጠምቆ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሔድ ከሰው ተለይቶ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በመጾም አዳምና ሔዋንን በመብል የረታቸውን ዲያብሎስን እርሱ ድል አደረገላቸው፡፡ ዲያብሎስን ድል ያደርግ ዘንድ ከዚህ ዓለም ርቆ ወደ ገዳም መሄዱ አዳም ከዚህ ዓለም ርቃ በምትገኘው ገነት ድል ሆኖ ነበርና እርሱም ዲያቢሎስን በገዳም$ በዚህ ዓለም ርቆ ድል አደረገልን ለእኛም ፈቃደ ሥጋችንን የምናሸንፍበተ ኃይል ሰጠን፡፡ ይህ ጾም ጠላት ዲያቢሎስ የተሸፈነበት ነው፡፡

5. የመሸጋገሪያ ጾም ይባላል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝቡን ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኣሪት ሲያሸጋግር አርባ መዓልትና ሌሊት በደብረ ሲና እንደ ጾመው ሁሉ ጌታችንም እኛን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሲያሸጋግረን አርባ መዓልትና ሌሊት ጾመ፡፡ ስለዚህም የመሸጋገሪያ ጾም እንለዋለን፡፡

6. ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡

ሁሉን ነገር በቅጽበትና ያለ ድካም ማድረግ የሚችለው አምላክ እኛን ልጆቹን ያስተምረን ዘንድ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ መልካም መምህር ተማሪዎቹ ይገባቸው ዘንድ ዝቅ ብሎ በነርሱ ቋንቋ እየተናገረ በሚችሉት እየመሰለ እንዲያስረዳ ጌታችንም እኛን ወደርሱ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እርሱ ወደ እኛ መጣ፡፡ ረሃባችንን ተራበ ፤ ድካማችንን ደከመ ፤ ፈተናችንን ተፈተነ ለእኛም አርአያ ሆኖ ትሕትናን ፤ ትዕግሥትንና ፈተናን በጾም ማሸነፍን አስተማረን፡፡

7. የቀድሶተ ገዳም ጾም ይባላል፡፡

እነ መጥምቁ ዮሐንስ እነ ነቢዩ ኤልያስ የኖሩትን የብሕትውና ኑሮ ጌታ ባርኮ ሰጠን፡፡ ከከተማ ወጥቶ ከሰው ርቆ በበረሃ ከአራዊት ጋር እየኖረ በዲያብሎስ ተፈትኖ ድል አደረገ፡፡ ዛሬም ልጆቹ በየገዳማቱ ድምፀ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ተግሠው ዓለምን ንቀው ፤ ከሰው ርቀው በጾም በጸሎት ከአጋንንት ጋር ይታገላሉ$ ድልም ያደርጋሉ፡፡

8. የመዘጋጃ ጾም ይባላል፡፡

ለእሥራኤላውያን ስለ በዓለ ፋሲካ አከባበር ሲነገራቸው የፋሲካውን በግ ሥጋ ከመራራ ቅጠል ጋር እንዲበሉት ታዘው ነበር (ዘጸ.12፤18)፡፡ ይኽም መራራ ቅጠል በግብፅ ይኖሩት የነበረውን የመከራ ኑሮ የሚያሳስባችውና ደግም ወደ ግብፅ (ምድረ ፋይድ) እንዳይመለሱ ከኃጢአተ ይርቁ ዘንድ የሚያስተምራቸው ነበር፡፡ የፋሲካው በግ ደግሞ እግዚአብሔር በፍቅሩ የሰጣቸውን ነፃነት ያሳስባቸዋል፡፡

ዛሬም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከበዓለ ትንሣኤው በፊት የጾም ወራት ያስቀደምነው ለዚህ ነው፡፡ ከመብል ስንከለከል ለአዳምና ሔዋን የተሰጠውን ሕግ እናስባለን$ ረሃብ ሲሰማን በሰው ልጅ ላይ ደርሶ የነበረው የጸጋ ረሃብ$ የመንፈስ ረሃብ ይታወሰናል$ ስንደክም ስንጐሰቁል በአዳምና ሔዋን የደረሰው የመንፈስ ጉስቁልና$ የበደልን የዕዳ ቀንበር ተሸክመው የደረሰባቸው ድካም ይታሰበናል፡፡ እኛም በነርሱ የደረሰችው ሞት በእኛ እንዳትደርስ ዳግም ወደ ኃጢአት እንዳንመለስ ይመክረናል ያሳስበናል፡፡

በጾሙም መጨረሻ የሐዲስ ኪዳንን በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም እንቀበላለን፡፡ ያን ጊዜም ሞትን ካሸነፈው አምላክ ጋር አንድ እንሆናለን (ዮሐ.6፤55-58)፡፡ ሞታችን በሞቱ እንዳለፈ እናስባለን (1ቆሮ.11፤26)፡፡ በመሆኑም ይህ ወቅት በዓለ ትንሣኤ- የሐዲስ ኪዳን ፋሲካን ለማክበር$ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ራሳችንን የምናዘጋጅበት የምንፈትንበት ነው (1ቆሮ.11፤27)፡፡

9. የሥራ መጀመሪያ ጾም ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ሥራውን ከመጀመሩ$ የመንግሥተ ሰማያትን አንቀጽ ከማስተማሩ በፊት በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ መዓልትና ሌሊት ጾመ፡፡ ይህም ለእኛ የማንኛውም ነገር መጀመሪያው ጾም መሆኑን ሲያሰተምረን ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያት ጾምን የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉት፡፡

እንዲሁም ይህ የጾም ወቅት፡-

የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ተኩላዎች እንድንጠነቀቅ ያስተምረናል፡፡ ጠላት ዳያብሎስ ጌታችንን ሲፈትን ከመጽሐፍ ቅዱሰ እየጠቀሰ ነበር (መዝ 2ዐ፤11)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም የጠራ፣ ጥቅስ የጠቀሰ ሁሉ መንፈሳዊ ሰው ፤ እውነተኛ ክርስቲያን ሊባል አይችልም፡፡ መጥቀስማ ዲያብሎስም ይጠቅሳል ሕይወቱን አይኖረውም እንጂ፡፡

እንዲሁም በዚህ የጾም ሰሞን ጠላታችን ዲያብሎስ ያዘጋጀልንን ወጥመድ አስበን ለገድል የምንዘጋጅበትም ነው፡፡ ጌታን ወደ መቅደስ ጫፍ አውጥቶ ወደ ታች ተወርወር እንዳለው ሁሉ እኛንም በትዕቢትና በከንቱ ውዳሴ ወደ ላይ አውጥቶ በኃጢአትና በውርደት በኃፍረትና ከመንፈስ በማራቆት ሊወረውረን ይሻል፡፡

ስለዚህ ትሕትናን በምታለብስ ጾም ድል እንንሣው፡፡

እንግዲህ ዐቢይ ጾም ማለት፡-

· ጌታ ስለኛ ባየው መከራ የምናዝንበት፣

· በሰጠን ኃይል ከሰይጣንና ከፈቃደ ሥጋ የምንዋጋበት፣

· በበደልነው ተገብቶ የካሠልንን እያሰብን ዳግም ወደ ኃጢአት ላንመለስ ቃል የምንገባበት ፤

· አርአያ ሆኖ ከሠራልን ሥርዓት፣ ከኖረልን ሕይወት የምንማርበት፣

· ራሳችንን ለፋሲካው በግ ለሥጋ ወደሙ የምናዘጋጅበት ሰሞን ነው፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡


  

Sunday, February 3, 2013

አቡነ መበዓ ጽዮን


         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር፣ ውሉደ ብርሃን፣ በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን የተሰኛችሁ የኀያሉ የልዑል እግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ልጆች፣ የቅዱሳን ሁሉ በለሟሎች፣ በእግዚአብሔርና እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን ስም ሰላም እያልኳችሁ  ነው::
 “እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡“ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ †♥† መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው። በአባታቸው ስም ሀብተ ጽዮንም ብሎ ይጠራቸዋል። እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው። አባታቸው ንቡረ ዕድ ሀብተ ጽዮን እናታቸው ሂሩት ይባላሉ። ደገኛ ጻድቅ ሲሆኑ ከታወቁበት ግብራቸው በሳምንት ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። ጌታ ሐሞት እንዳጠጡት ያንን እያሰቡ። አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚ፣ ቡናና ትርንጎ አፈርቷል፤ ጻድቁ ሌላ አስደናቂ ታሪክ አላቸው አርብ አርብ ሲዖል እየገቡ እልፍ እልፍ ነፍሳትን ያወጡ፤ በገበያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ካስተማሩ በኋላ ይመግቡ ነበር። በየወሩ የመድኃኔ ዓለም በዓል እየዘከሩ የወጣ የወረደውን ሁሉ የገበያውንም ሰው ሁሉ ያበሉ ይመግቡ ነበር። ዛሬም ሲዖል እየገቡ ያወጣሉ። “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?”ዮሐ.3፡12 እንዳለ ጌታ ዛሬም ይህንን የሚጠራጠሩ ብዙዎች አሉ። እኛ ግን በዚህ እናምናለን እንታመናለን። በጥቅምት 27 ብዙ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ቀንም ነው። አባታችን በጥቅምት 27 ቀንም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። አባታችንን አንድ ገበያ የሚያህል ሰው ይከተላቸው ነበር። የአባታችን አባ መባ ጽዮን በራሳቸው ገዳም ማጢቆስ በተባለ ገዳም አፅማቸው ይገኛል። በትግራይ ሽሬ አሎጊንም የሚባል ትልቅ ገዳም አላቸው። የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድኃኔ ዓለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው። እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በዓብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች። ጌታችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ክብሩ ከጻድቁ አቡነ መበዓ ጽዮንና ከአባ ጽጌ ድንግል በረከት ረድኤትን ያድለን አሜን።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያውያን ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ፣ መጽሐፈ ስ/ሳር፣ ነገረ ቅዱሳን ፪
        ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
      በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
አዘጋጅ ቤተ ማርያም