Monday, November 3, 2014

አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)


            በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
*እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል!
*ቅዱሱ አባታችን:- "ቡላ-የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን::
*ዳግመኛም "አቢብ-የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን::
+እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን::
*አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
*ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ!
*ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ!
*የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን::
+" ልደት "+
=>አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ::
+በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ: ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"
+" ጥምቀት "+
=>ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በሁዋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኩዋን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ 'አጥምቀው' አለችው::
+ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ: እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::
+" ሰማዕትነት "+
=>የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገውት ድንገት ሕዳር 7 ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ::
+በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ 18 ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል::
+" ገዳማዊ ሕይወት "+
=>ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በሁዋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ::
+ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው::
+" ተጋድሎ "+
=>አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል: ፊቱን በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል: ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል::
+በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር::
+የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነሕና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን" አለው::
"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ:
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ:
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል::
+" ዕረፍት "+
=>አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ10 ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::
+ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ 'አምላከ አቢብ ማረኝ' ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::
+" ታላቁ አባ ዕብሎይ "+
=>ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው:: ብዙ መጻሕፍት 'ርዕሰ ገዳማውያን' ይሉታል:: የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ በመሆኑ በዕለተ ዕረፍቱ (የካቲት 3 ቀን) እንመለከተዋለንና የዚያ ሰው ይበለን::
+" ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት "+
=>ከሁሉ አስቀደሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ (አድናቆት): ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::
+ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘ) ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ እንኩዋን የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ-የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: (መዝ. 78:3)
+እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና 300 አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::
+በወቅቱ የክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር::
በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::
+ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር::
+እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::
+ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ ወደ ሃገረ ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ::
+በፍጻሜውም መኮንኑ ቅዱስ ዮልዮስን ከቤተሰቡና ከ1,500 ያህል ተከታዮቹ ጋር: 2ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል::
=>አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን::
=>ጥቅምት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
2.አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
4.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
5.ቅዱሳን አሞኒና ሙስያ (የታላቁ ዕብሎ ወላጆች)
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
6.ታላቁ አባ ቢጻርዮን
=>+"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ:: መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል:: +"+ (ማቴ. 16:24)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
  
writing by dn yordanos abay

No comments:

Post a Comment