Friday, May 31, 2013

ፃዲቁ አቡነ በግዑ


          በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 የቅዱሳን ተጋድሎ ማውሳት ለመንፈሳዊነታችን ታላቅ አስተዋፅኦ አለው:: በየዕለቱ የምንሰማው የቅዱሳን ህይወትና ታሪክ እነርሱ ወደ ተጋደሉበት የቅድስና መንገድ የሚመራንና ለተሻለ የመንፈሳዊ ህይወት የምንጒዝበት ትልቅ ድልድይ ነው::

የጻድቅ ሰው ጸሎት በስራዋ እጅግ ሐይል ታደርጋለች:: ያዕቆብ 5 : 
 ጻድቁ አቡነ በግዑን ላስተዋውቆ በቤተክርስቲያናችን ታስበው ከሚውሉ ቅዱሳን መካከል ጻድቁ አቡነ በግዑ አንዱ ናቸው:: ለመሆኑ አቡነ በግዑ ማን ናቸው? ምንስ ተጋድሎ አደረጉ? ምንስ ቃል ኪዳን ተሰጣቸው? የሚለውን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንመልከት መልካም ንባብ
ፃዲቁ አባታችን አቡነ በግዑ ቀድሞ በክፉ ስራ በኋላም በመልካም ተጋድሎ ፈጣሪው እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ መጀመሪያ እንደ ሽፍታ በማታለል ከኖረ በኋላ ግን በብዙ ጾምና ፀሎት ወደ እግዚአብሔር ተመለሰ፣ ሲዘርፍና ሲቀማ ኖረ፣ ባማረ ልብሶች ሲያጌጥ ኖረ በኋላ ግን ጽድቅን እንደልብስ ለበሰ በጉልምስና ጊዜው ብርቱ ጠንካራ ስለነበረ ወደ እርሱ መቅረብ የሚችል አልነበረም፡፡ ብርቱ ጠንካራ ስለነበረ ወደ እርሱ መቅረብ የሚችል አልነበረም፡፡ የሀገሩ ሰዎች ሁሉ ይፈሩታል፡፡ በሰዎች ሁሉ ዘንድ የታወቀ ነበረ፡፡
አባታችን አቡነ በግዑ አስቀድሞ በስም ክርስቲያን ነበረ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቁርባን ሊቀበል ከህዝቡ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሄደ፡፡ ካህኑ ባየው ጊዜ ከመንገድ አስገልሎ የህይወት ዘመንህን ሁሉ በከንቱ አሳለፍክ ዛሬ ስማ ልንገርህ በዘመን ፍፃሜ እግዚአብሔር ይጎበኝሃል፣ መንፈስ ቅዱስ ያድርብሃል ፍፁም መነኩሴ ትሆናለህ ከቤተሰቦችህም ተለይተህ ከፍ ወደ አለ ቤተክርስቲያን ትደርሳለህ በጾም በፀሎት በብዙ መከራም በዚያ ትኖራለህ አለው፡፡ ይህንንም በሰማ ጊዜ በእውነት ይደረግልኝ ይሆን? እያለ አሰበ የክርስቶስን ክቡር ስጋው ቅዱስ ደሙን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
ከዚያች ዕለት ጀምሮ እስከ መቼ በስንፍናዬ እኖራለሁ እስከ መቼስ የነፍሴን መዳኛ ሳላስብ እኖራለሁ እያለ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገር ወጥቶ ሄደ ኢዮ 40፡4 ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ገባ፡፡ ከመነኮሳት ማህበር ገብቶ እያገለገለ ከአንድ አረጋዊ መነኩሴ ጋር ኖረ፡፡ በጸም በፀሎትተወስኖ እግዚአብሔርን እያገለገለ በትንሽ በዓት ብቻውን ሆነ፡፡ በጾም ወራት ይኸውም በአብይ ጾም በህብስትና በውሃ ብቻ መጾም ጀመረ፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ዕለት አርብ በህማማት ሳምንት ሁሉ ከንቱ ነው ብላሽ ነው የዚህ ዓለም አኗኗር ኃላፊ ነው የሚል የመጽሐፍ ቃል ሲነበብ ሰማ እንባው እንደውሃ እስኪወርድ ድረስ መሪር ልቅሶ አለቀሰ 1ዮሐ 2፡15 ከዚያች ቀን ጀምሮ ስጋዊ ስራን ተወ፡፡ ምግቡንም የዱር ዛፍ ፍሬና ቅጠል አድርጎ በተጋድሎ ውሃ ሳይጠጣ ኖረ፡፡
አበምኔቱና ቅዱሳን መነኮሳት ያለውሃ በመኖሩ የእግዚአብሔር ቸርነቱን አደነቁ፡፡ አባታችን አቡነ በግዑ አበምኔቱን አስጠርቶ ከበአቴ አልወጣም ብሎ በፈቃዱ ሁለት እጁንና ሁለት እግሩን በብረት ሰንሰለት አሰረ፡፡ አበምኔቱም ፈቀዱለት ባአቱንም በውስጥም በውጭም እጅ የሚያስገባ ትንሽ መስኮት በመተው በጭቃ መረጉት ይህም ለምግብ የሚሆን ቅጠል የሜዳ ጐመንና የዱር ፍሬ የሚገባበት ነው፡፡ አባታችን አቡነ በግዑ አፉን በጨርቅ አሰረ፡፡ በጾም በፀሎት ከእንባ ጋር ተጋድሎውን አደረገ፡፡ አበምኔቱ በትንሽ ልጅ የሚልኩለትን ቅጠል የኃጢአቱን ክርፋት እያሰበ ያለውሃ አብስሎ እስኪከረፋ ከአጠገቡ ያስቀምጠዋል ሽታውም ከአይነ ምድር ይከፋል፡፡ በጾመ በሶስተኛው ቀን ያን የከረፋ ቅጠል ይበላል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ቀን ከበአቱ ወጥቶ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ቁርባንም ተቀብሎ አስቀድሞ እንደነበረው ወደ በአቱ ገባ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አልዘጋውም ለበአቱ ደጃፍ መዝጊያ አሰራ ቁርባን መቀበል አላቋረጠም፡፡
የአባታችን የአቡነ በግዑ ተጋድሎው ከውሃ ተከልክሎ የተቀበለው መከራ በሀገሩ ሰዎች ዘንድ ተሰማ፡፡ የሀገሪቱ ንጉስም በፀሎት አስበኝ ብሎ በመልክተኛ ልብስ ላከ ፃዲቁ አባታችን እንዲህ አለው የእግዚአብሔር ቸርነት ከአንተ ጋር ይሁን ይሄንን ልብስ አልቀበልም ለአንተም ለእኔም ወደ እግዚአብሔር እማልድ ዘንድ በዚህ ልብስ ፈንታ እጣን ላክልኝ አለው፡፡ ንጉሱም እንደተባለው አደረገ አባታችንም ዕጣኑን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ሰጠ፡፡ ምሳ 18 ፡ 12
ፃዲቁ አባት አቡነ በግዑ ውሃ መጠጣት ከተወ አምስት ዓመት ሆነው መቀመጥና በጎኑም መሬት ላይ መተኛት ተሳነው ስጋው አልቋልና፡፡ ከንፈሮቹም ከውሃ ጥም የተነሳ ደረቁ፣ ምላሱም ተጣበቀ፣ አይኖቹም በእንባ ደፈረሱ፣ አፍንጫውም ቆሰለ መገለ፣ መሄድም ተሳነው ሲወጣና ሲገባ በሁለቱ እጆቹና እግሮቹ ይድሃል፡፡ ቁርባን ሲቀበል ሁለት መነኮሳት አድርሰው ይመልሱታል፡፡ ይህን ጽኑ መከራ ከተቀበለ በኋላ ነፍሱን እንዲወስድ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ በምሳሌ አስረዳው ከሞት ወደ ህይወት ትሻገር ዘንድ መከራውን ረኃቡንና ጥሙን ታገስ አለው፡፡ ያዕ 1 ፡ 12
አባታችን አቡነ በግዑ ይህን ሁሉ ተጋድሎ በእግዚአብሔር ኃይል አደረገ፣ ለሰባት አመት ውሃ ሳይጠጣ ኖረ፡፡ ከሰባት ዓመት በኋላ ከብዙ ረኃብና ጥም የተነሳ በጣም ታመመ፡፡ መናገርም ተሳነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ጎበኘ፡፡ የኃጥአን መኖሪያቸውን ተመለከተ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር አዕላፍ ቅዱሳንን ይዞ መጥቶ ስምህን ለጠራ፣ መታሰቢያህን ላደረገ፣ ወደ ተቀበርክበት ቦታ ሄዶ ለተሳለመ፣ በበአልህ ቀን ምጽዋት ለሰጠ እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለሁ አለው ዳግመኛ በፀሎትህ አምኖ መልካም ስራ የሰራ የገድልህን መጽሐፍ የሰማ ሁሉ የእሳትን ባህር በግልጽ ይለፍ ብሎ ቃለ ኪዳን ገባላት፡፡
የእግዚአብሔር ሰው አቡነ በግዑ በአባታችን አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እጅ ምንኩስናን ተቀበለ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዓን ዛሬ ግን ደክሜያለሁ መናገር ተስኖኛል፡፡ ነፍሴ ከስጋዬ መለያዋ ጊዜው ቀርቧል፡፡ መቃብር አስቆፍርልኝ አሁን ግን ወደ በዓትህ ተመለስ ብሎ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አሰናበተው ህመሙ ሲጠናበት አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ተመልሰው መጡ፡፡ አቡነ በግዑንም ስለ ጽድቅ ብለህ እስከ ሞት ድረስ ተጋደልክ አሁን ግን ከእጅህም ከእግርህም ይህን የብረት ሰንሰለት እንፍታ አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው አቡነ በግዑ ከሞትኩ በኋላ የታሰርኩበትን ሰንሰለት ፍቱት ፈቃድህ ከሆነ አሁን ፍታኝ ብሎ የብረት ሰንሰለቱ ተፈታ፡፡ ጥቂት ደቂቃ እንደቆየ ታህሳስ 27 ቀን አረፈ፡፡ መዝ 115/116 ፡ 6
የአባታችን የአቡነ በግዑ ረዴትና በረከት ይደርብን!!!
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡  
ፀሀፊ ገዛኸኝ ፈንታሁን       By gezahagn fantahun

Wednesday, May 22, 2013

ቅዱሳን መላእክት - ስግደት ለመላእክት


  • በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
    መስገድ የሚለው ቃል መዋረድ፣ ማጐንበስ፣ መንበርከክ፣ መደፋት፣ በግንባር መውደቅ፣ ግንባርን ምድር አስነክቶ መሬት ስሞ መመለስ ነው በማለት የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ያትታል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ስግደት የአምልኮና የጸጋ ተብሎ ይከፈላል፡፡ የአምልኮ ስግደት ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ሲሆን የጸጋ ስግደት ደግሞ እግዚአብሔር ላከበራቸው ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት የሚቀርብ ነው፡፡

    ለቅዱሳት መላእክት የምናቀርበው ስግደት ከላይ እንደተገለጸው የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ጸጋ የሚለው ቃል በቁሙ ሲተረጎም ሀብት፣ መልካም ሥጦታ፣ ዕድል ፈንታ፣ ትምህርት፣ ብዕል፣ ክብር፣ ሞገስ የቸርነት ሥራ አለዋጋ የሚሰጥና የሚደረግ ማለት ነው፡፡[1] የጸጋ ስግደት ስንል እግዚአብሔር የሰጣቸውን ክብርና ሞገስ አምኖ መንበርከክ ነው፡፡ ይህም ራስን ለእግዚአብሔር ከማስገባት የሚመነጭ ነው፡፡

    ሰዶምና ገሞራን በእሳት ለማቃጠል የተላኩት መላእክት ወደ ሎጥ ቤት በገቡ ጊዜ ሎጥ በግምባሩ ተደፍቶ ለመላእክቱ እንደሰገደ ተጽፏል (ዘፍ. 19፥1)፡፡

    ኢያሱ ወልደ ነዌ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በተገለጠለት ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ ለመልአኩ ሰግዶለታል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል የተቃውሞ አነጋገር አልተናገረም፡፡ ‹‹የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ›› ከማለት በስተቀር (መጽ ኢያሱ 5፥13)፡፡

    የእሥራአል ንጉሥ የነበረው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ከእሥራኤል ሽማግሌዎች ጋር ከመሬት ከፍ ብሎ ሰይፉን ዘርግቶ ለተገለጠላቸው ለእግዚአብሔር መልአክ ሰግደውለታል (ዜና መዋዕል ቀዳ 21፥16)፡፡

    ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአባል ወንዝ አጠገብ በተገለጠበት ጊዜ ለመልአኩ ለቅዱስ ገብርኤል ራሱን ዝቅ አድርጐ በግንባሩ ወድቆ ሰግዶለታል፡፡ በዚሁም ላይ የግርማውን አስፈሪነት እና አስደንጋጭነት ጠቅሷል (ዳን. 8፥15)፡፡

    ከላይ የተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሚያስገነዝቡን ለመላእክት ቅዱሳን ሰዎች እንዴት አክብረው እንደሰገዱላቸው ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሐርን ቃል የተናገሩአቸሁን ዋሃቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሮ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው›› (ዕብ. 13፥7) እንዳለው የቅዱሳን አባቶቻችንና ሕይወት አኗኗር ዛሬ ለእኛ መመሪያ ሊሆነን ይገባል፡፡ እነርሱ አድርገው የተጠቀሙበትን ሁሉ እኛም እናደርገዋለን፡፡ እነርሱ ለቅዱሳን መላእክት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በስግደት እንደገለጹ እኛም እግዚአብሔር ላከበራቸው ቅዱሳን መላእክት ፍቅራችንንና አክብሮታችንን በሥዕላቸው ፊት በመንበርከክ በመስገድ እንገልጻለን፡፡

    መላእክት ቢገለጡም ባይገለጡም ሕልውናቸው የተረጋገጠ ነውና ክብራቸው ያው ነው፡፡ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ሲገለጡ እንጂ ካልተገለጡ ሊሰገድላቸው አይገባም ሊሉ ይችላሉ፡፡ በዓይን ዓይቶ በእጅ ዳብሶ ከማመን ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን እንደሆኑ ጌታችን አስተምል (ዮሐ. 2ዐ፥29)፡፡

    ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በዓይናቸው ዓይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው ያደረጉትን እና ያመኑትን ለእኛ በማስተላለፋቸው እኛም የእነርሱን ዓይን ዓይን አድርገን ማእነርሱ አይተዋቸው የሰጡትን ክብር እንሰጣቸዋለን፡፡ መገለጣቸውና አለመገለጣቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ያላቸውን ክብር አይጨምረውም አይቀንሰውምና ክብራቸው አንድ ነው፡፡ ስለዚህ ይሰገድላቸው ዘንድ የሚገባ ከሆነ ሲገለጡ ሳይገለጡ የሚል ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ ለእግዚአብሔር በመንፈስ የአምልኮት ስግደት እንደምንሰግድ ሁሉ (ዮሐ. 4፥24) እግዚአብሔር ባለበት ቦታ ሁሉ አብረው ለሚገኙት ቅዱሳን መላእክትም የጸጋ ስግደት በእምነት ማቅረብ ይገባል፡፡ እነርሱም እግዚአብሐር ባለበት ቦታ ሁሉ አሉና፡፡

    ራእ. 19፥10 (‹‹አትስገድልኝ››)

    አንዳንዶች ተጠራጣሪዎች ደግሞ ለመላእክት ሲገለጡም ሆነ ሳይገለጡ ምንም ዓይነት ስግደት አይገባቸውም በማለት ራእ. 19፥10 (‹‹አትስገድልኝ››) ላይ ያለውን ይጠቅሳሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ ጥቅስ ለመላእክት የጸጋ ስግደት መስግድ እንደሚገባን እንጂ መስገድ እንደማይገባን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ለመልአኩ መስገዱ ሳያውቀው ሳይረዳው ያደረገው ድርጊት እንዳልሆነ እንድናምን ማንነቱና ሕይወቱ ያስገነዝበናል፡፡ ምክንያቱም የጥበብ፣ የማስተዋል፣ የዕውቀት ጸጋን የሚያድል መንፈስ ቅዱስ አድሮበት እያለ ሳያውቀው አደረገው ብሎ መናገርና ማመን መንፈስ ቅዱስን እንደ መጽረፍ /መስደብ/ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ሰው የሚያመልከውንና የሚሠራውን ሁሉ የሚያውቅ ነው፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ አካል ከሕልውና ተገልጾለት ምሥጢረ መለኮትን የተናገረ ታላቅ ሰው ሆኖ ሳለ ትንሿ ጉዳይ ተሰውራው ለመልአኩ ሳያውቅ ሰግዶ ተግሳጽ ደረሰበት ብሎ ማመን ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ክህደትም ጭምር ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ሰላም ማቃለል ነው፡፡ «መንፈስ ቅዱስ የሰደበ ደግሞ ኃጢአቱ አይሠረይለትም፡፡» (ማቴ. 12፥31-32)፡፡

    የመልአኩ አነጋገር ታዲያ እንዴት ይተረጎማል? መልአኩ ቅዱስ ዮሐንስን አትስገድልኝ ማለቱ ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡

    1ኛ. ስለ ትኀትና

    ዲያብሎስ ከሥልጣኑ የተሻረው ከክብሩ የተዋረደው በትዕቢቱ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት ግን ትሕትናን ገንዘብ ያደረጉ በመሆናቸው እንደ ሰይጣን ስገዱልን የሚሉ አይደሉም፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ይከበሩ ዘንድ ፈቃዱ በመሆኑ የእግዚአብሔር ሰዎች እንዲወዷቸውና እንዲያከብåቸው አድርጓል፡፡ ለዮሐንስ በሰገደለት ጊዜ «አትስገድልኝ» ማለቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ከአምልኮተ እግዚአብሔር የሚያወጣ ለጣኦት እንደመስገድ የሚያስቆጥር ሆኖ ሳይሆን መልአኩ ራሱን በዮሐንስ ፊት ዝቅ ከማድረጉ የተነሣ ስለ ትሕትና የተናገረው ነው፡፡ አንድ ሰው ሌላውን ሰው አክብሮ እጅ ቢነሣው /ከመቀመጫው ሲነሳና ሲቀበለው/ éረ አይገባም እንደሚለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ለዚሁም ማረጋገጫ የሚሆነን (ለትሕትና የተናገረ መሆኑን) በምዕራፍ 19 የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በምዕራፍ 21 ላይ መድገሙ ነው፡፡ ለትሕትና የተናገረው መሆኑን ያወቀው ዮሐንስ ለመልአኩ ክብር መስጠት እንዳለበትና መስገድ እንደሚገባው ዐውቆ ድጋሚ ሲገለጥለት በድጋሚ ሰግዶለታል፡፡

    2ኛ ስለ ሥልጣነ ክህነት ክብር ሲል

    የቤተ ክርስቲያን የአጥቢያ ኮከብ ቅዱስ ጳውሎስ የካህናትን ሥልጣን አስመልክቶ ሲያስተምር #ካህናት ሰውን ሁሉ እንደሚዳኙ አታውቁምን? እናንተ ሰውን ሁሉ የምትዳኙ ከሆናችሁ ይህን ትንሹን ነገር ልትፈርዱ አይገባችሁምን? የዚህንስ ዓለም ዳኝነት ተውትና መላእክትን ስንኳ እንድንገዛ አታውቁምን$ (1ቆሮ 6፥2-3) ብሏል፡፡

    ከዚህ ትምህርቱ የምገነዘበው ካህናት በሥልጣናቸው መላእክትን ስንኳ ሳይቀር እንደሚያዙ ነው፡፡ ይህንንም ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት እንረዳለን፡፡ በ344 ዓ.ም. በአንጾኪያ ከተማ የተወለደው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እምነትንና ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ትሕትናን፣ በአንድነት ገመድ አስሮ ሕዝቡን ለ7 ዓመት ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በ387 ዓ.ም. በአንጾኪያ ከተማ ፖትርያርክነት ተሾሞ ሳለ አንድ ጉዳይ ይገጥመዋል፡፡

    ንጉሡ አርቃድዮስና ንግሥቲቱ አውዶክያስ ልጅ እየወለዱ እየሞተባቸው አላድግ ስላላቸው የዚህን ምክንያት ቢጠይቁ ደግ ሰው ክርስትና ባያነሣላችሁ ይሆናል ስላሏቸው ከዮሐንስ አፈወርቅ የበለጠ ደግ ሰው በዘመናችን አለን? በማለት ሴት ልጅ በወለዱ ጊዜ መጥተህ ክርስትና አንሣልን ብለው ላኩበት እርሱም ጥሪውን አክብሮ ሲሆድ በመንገድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተላከ መልአክ ጋር ይገናኛል፡፡ የበቃ ነውና ረቂቁን መልአክ ሊያየው ችሏል፡፡ ዮሐንስም መልአኩን ‹‹ወዴት ትሄዳለህ?›› ብሎ ጠየቀው መልአኩም ሲመልስለት ‹‹አሁን አንተ የምትሄድባትን ብላቴና ነፍሷን ከሥጋዋ ለይተህ አምጣ ብሎኝ የታዘዝኩትን ለመፈጸም ወደዚያ መሄዴ ነው›› ይለዋል፡፡ ዮሐንስም ‹‹ቆየኝ በጥምቀት ሀብተ ውልድና፣ ስመ ክርስትና ከተሰጣት በኋላ የታዘዝከውን ትፈጽማለህ፡፡ እስከዚያው ግን ከዚሁ አትንቀሳቀስ›› ብሎት በሥልጣነ ክህነቱ ገዝቶት ሄደ፡፡ መልአኩም የዮሐንስን ግዝት ጠብቆ ባለበት ቆመ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ልጅቷን ካጠመቃት በኋላ ንግቶት በሌላ መንገድ ተመለሰ፡፡

    የካህናት ሥልጣናቸው የማይናቅ፣ ትእዛዛቸውም ክብር የሚገባው መሆኑን ስለሚያውቅ ያ መልአክ ወደ ላይም ወደታችም ሳይል አሥር ዓመት ከዚያው ሥፍራ ቆሞ ኖረ፡፡ አሥር ዓመት ሲሆናት ለባል ታጨች ያጠመቅካት ብላቴና እነሆ ለአቅመ ሔዋን፣ ባል ልታገባ ነውና መጥተህ ባርከህ ስደዳት ብለው ለዮሐንስ አፈወርቅ ላኩበት፡፡ እርሱም በጥሪው መሠረት ከዛሬ አሥር ዓመት ልጅቱን ሊያጠምቅ ሲሔድ በሄደበት መንገድ መልአኩን ቆሞ አገኘው፡፡ «ምነው ከዚህ ቆመሃል?» አለው፡፡ መልአኩም ሲመልስለት «የካህናት ማዕረጋቸው የከበረ ነውና መች ወዲያ ወዲህ ያሰኛል፡፡ ቃልህን አክብሬ አንተ ቆይ ካልከኝ ወዲያና ወዲህ ብዬ አላውቅም» አለው ቅዱስ ዮሐንስም በዝንጉዕነቱ ራሱን ወቅሶ መልአኩን የታዘዘውን ያደርግ ዘንድ አሰናብቶታል፡፡

    ከላይ በተገለጸው ታሪክ ብናይ በፍጥሞ ደሴት መልአኩ ለዮሐንስ ወንጌላዊ አትስገድልኝ ማለቱ ዮሐንስ ካህንም ነውና ሥልጣኑ ሊያከብር እንደሚገባው ለመግለጽ ሽቶ ነው፡፡ በክብር ዮሐንስ ከመልአኩ ይበልጣልና፡፡
     ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Saturday, May 18, 2013

መንፈሳዊ ተጋድሎ





                                                              መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ምን ማለት ነው?
መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት - አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ÷ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነፃ ፈቃዱ ወስኖ፥ በሙሉ ልቡናው፥ በሙሉ ኃይሉ የሚያደርገው የውስጥና የውጭ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፥ ጥረትና ትግል ነው፡፡
 
  ሀ. ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው፡፡
ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም›› ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማያቋርጥ ጦርነት ነው፡፡ (ገላ 5፥12) ታላቁ አባት ኢዮብም ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ?›› በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿአል፡፡ ይህም ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው፡፡ ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል፡፡
ይህ ሲባል ግን ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ሥጋ በራሱ ርኵስ አይደለምና፤ ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰውን (ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው) ከፈጠረ በኋላ ‹‹ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡›› ተብሏል፡፡ (ዘፍ1፥31) ሥጋ ርኵስ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ወልድ (ቃል) ‹‹ሥጋ ሆነ›› ባልተባለ ነበር፡፡ (ዮሐ 1፥14) አዳምና ሔዋን ከኃጢአት በንጽሕና ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፣ አይተፋፈሩም ነበር›› እንዲል (ዘፍ 2፥25)  ህፃናት፣ ልጆች  ሰውነት አላቸው ነገር ግን የኃጢአት ምኞት የላቸውም፡፡
ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ ተፈጥሮአዊና ንጹህ የሆነ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣  በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም/መግራት ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን በመጠቀም ይሠራል÷ ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ ‹‹ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ፡፡ (ዘዳ 32፥15)
ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ‹‹ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ›› እንዳለ፡፡ በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ (1ኛ ቆሮ 9፥27) በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ›› እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባናል፡፡
   ለ. ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር እንጂ›› እንዳለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ሰው ከሰው ጋር በመጣላት የሚያደርገው ትግል ሳይሆን ጥንተ ጠላታችን ከተባለው በእባብ ወይም በዘንዶ ከተመሰለው ዲያብሎስና ከእርሱ ጋር ካሉት ሠራዊቱና መልእክተኞቹ ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ (ኤፌ 6፥12)
ከአዳምና ከሔዋን ከልጃቸውም ከቃየን ጀምሮ ሰይጣን የሰው ልጆችን ዘወትር ይዋጋል፤ ከዘላለም የሞት ፍርድ ሥር ሊጥል ይሠራል፡፡ በዚህም ውጊያው ከነቢያት ፤ከሐዋርያት ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ብዙዎችን ጥሏል፡፡
ዛሬም በገዛ ባሕርያችን የሚገኘውን ፈቃደ ሥጋ በመጠቀም፣ የራሱን በመጨመርና የተለያዩ ፈተናዎችን በማቀናበር ይዋጋናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፡፡›› እንዳለ ጠላት ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በኃጢአትና ሞት ሊውጥ ዘወትር ይተጋል፡፡ ማንም ሰው ደግሞ ከዚህ ፈተናና ውጊያ ሊያመልጥ አይችልም፤ ስለዚህ ሐዋርያት ‹‹በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት››፣ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡›› እንዳሉን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ለብሰን ልንዋጋው ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ 5፥8-9፣ኤፌ 6፥11)
ሐ. የሚመጣውን ዓለም ደስታ ተስፋ እያደረጉ ብቻ በዚህ ዓለም ሕይወት ከደስታ ውጪ መሆን ማለት አይደለም፡፡
ደስታ በራሷ የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆነች፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጠች፤ ንጹሕ ፈርጥ ነች፡፡ (ገላ 5፥22)
እውነት ነው፤ በዚህ ዓለም ስንኖር መከራ አለብን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ እስካለ ድረስ ከጨለማው ዓለም ገዢ ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ የሚመጣ ልዩ ልዩ ፈተናና ከሥጋችንም ባሕርይ ከሚገኘው ክፉ ምኞትና ርኵሰት ሥራ እንዲሁም ከሌሎቹ የኃጢአትና የፈተና ዓይነቶች ጋር በማያቋርጥ እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል ውስጥ መኖሩ የግድ ነው፡፡ መከራና ስቃይ፣ ትግልና ጦርነት የሌለበት በዘለዓለማዊ ደስታ ብቻ የሚኖርበት ሕይወት በሚመጣው ዓለም የሚገኝ ነው፡፡
በዚህ ምድር በጉዞ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን ጨርሳ ድል ከነሱት አባላቷ ጋር አንድ እስክትሆን ድረስ መከራው፣ እንቅፋቱ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ የግድ ነው፡፡ ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፡፡›› እንዲል (ሐዋ 14፥22)
ይህ ሲባል ግን በዚህ ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከደስታ የተራቆቱ ዘወትር በኅዘንና በስቃይ ብቻ የሚኖሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሚለዩትና ዘወትር ለመለየት ጥረት የሚያደርጉት የውሸት ከሆነው ኃጢአት (ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል) ከሚገኘው ደስታ እንጂ ከእውነተኛውና ከሰማያዊው ደስታ አይደለም፡፡
መንፈሳዊ ተጋድሎ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና ረድኤት መንፈስ ቅዱስ መሪና አስተማሪ፣ የሚያነቃቃና የሚያጽናና፣ የሚያርምና የሚገሥጽ፣ የሚረዳና የሚያጸና፣ በመሆን ስለ ክርስቶስ በክርስቶስ ጸጋ የሚከናወን በመሆኑ መከራንና ስቃይን በሚያስረሳ እውነተኛ ደስታና ሰላም የተሞላ ሕይወት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ስለ ክርስቶስ በማስተማራቸው ምክንያት ገዢዎች ልብሳቸውን ገፈው በበትር እንዲመቱ አዘዙ በበትር ከመቷቸውም በኋላ በወኅኒ ቤት ጣሏቸው እነርሱ ግን ከጀርባቸው ደም እየፈሰሰ በመንፈቀ ሌሊት እንኳን እግዚአብሔርን በመዝሙር ያመሰግኑ ነበር፡፡ እውነተኛውና ሰማያዊው ደስታ በልቡናቸው ሞልቶ ነበርና፡፡ (ሐዋ 16፥22-25)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐዋርያት እንዲህ ይለናል ‹‹ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው  በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቷቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፡፡››(ሐዋ 5፥40-41)
ቅዱስ ዮሐንስ ካሲያን የተባለው አባት በተጋድሎ በግብጽ በረሃ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩት መነኰሳት ሲናገር ‹‹ እነዚህ ምድራዊ መላእክት ናቸው፤ የግብጽን በረሀዎች በደስታ ወደ ተሞላ መዝሙርና እግዚአብሔርን የማመስገኛ ገነትነት ለውጠዋልና››  ብሏል፡፡
በአጠቃላይ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ከተድላ ሥጋ፣ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ በመሸሽ ሰማያዊና እውነተኘ በሆነ ሰላምና ደስታ ውስጥ መኖር ይህንንም ለማግኘት መጋደል ማለት ነው፡፡
       መንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማው ምንድነው?
ሀ. የድል አክሊል (የዘለዓለም ሕይወት) ለመቀበል
እግዚአብሔር አምላካችን ሰዎች ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ከአምላካቸው ጋር መኖር ከመረጡ ሊሰጣቸው ያዘጋጀው ከመነገርና ከመታሰብ በላይ የሆነ የዘለዓለም  ሕይወት አለ፡፡ የሰው ልጅ ሕሊናዊ ነፃ ፈቃዱ ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ በየጊዜው እየደከመና ወደ ኃጢአት እያዘነበለ መጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ከብሮ ባየ ጊዜ ከአባቶቻችን ጀምሮ ዘወትር የሚቀና ክፉ ጠላትም (ዲያብሎስ) አለን፤ ባገኘው አጋጣሚ ስንፍናችንንና ድካማችንን እየተከተለ እነዚህንም በመጠቀም ዘወትር ከአምላካችን ሊለየን እንደሚተጋም ከላይ ተመልክተናል፡፡

ሽልማት፣ አክሊል የሚሰጠው ደግሞ ማሸነፍ ለሚችል ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ሰነፍና ቸልተኛ ሰው ግን ሊሸለም አይገባውም አንድ ሰው ጎበዝ ወይም ሰነፍ መሆኑ የሚታወቀው ደግሞ በፊቱ ያጋጠመውን ውድድር ወይም ፈተናና መከራ ማሸነፍና ማለፍ ሲችል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማ በገዛ ባሕርያችን ያለን መጥፎ የኃጢአት ዝንባሌና ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያመጣብንን ፈተናና ሽንገላ ከእግዚአብሔር ርዳታና ቸርነት ጋር ሕሊናን በማንቃት፣ ራስን በመግዛትና ጠንክሮ በመጋደል አምላካችን ያዘጋጀልንን የድል አክሊል የዘላለም ሕይወትን መቀበል ነው፡፡ ‹‹ የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል›› አንዲል (1ኛ ጢሞ 6፥12) ሐዋርያቅ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ መከራዎችን አልፎ ገድሉን በድል አድራጊነት ሲፈጽም ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል ( 2ኛ ጢሞ 4፥7-8)
ለ. ለመንፈሳዊ እድገት
ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለፍሬ የሚበቃው የድል አክሊልን መቀዳጀት የምንችለው የማያቋርጥ (የማይቆም) መንፈሳዊ ዕድገት ሲኖረን ነው፡፡ በጥምቀት ያገኘነው አዲሱ ሕይወታችን ዘወትር ማደግ ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በዛፍ ተክል ይመሰላል፡፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ፍሬ እስከሚያፈራለት ጊዜ ድረስ ያለው ድካም ቀላል አይደለም፡፡ የዛፉ ችግኝ እንዲያበቅል፣ እንዲለመልም፣ አንዲያብብና እንዲያፈራ አትክልተኛው ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ በየጊዜው ውሃ ማጠጣት፣ ማረምና መኰትኰት፣ ፀረ ዕፅዋትና ፀረ ሕይወት የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን አድጎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ዕለተ ዕለት ጠንክረን በትዕግሥት መሥራት በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናት ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ተጋድሎም ዓላማው መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያቀጭጩ  ከጸጋ እግዚአብሔርም የሚያራቁቱ ኃጢአትና የዲያብሎስ ፈተናን በመቃወም መንፈሳዊ ምግቦችንም በመመገብ አዲሱ ሕይወታችንን ማሳደግ ነው፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Thursday, May 9, 2013

አቡነ ቀውስጦስ

   
      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ::

እንኳን ታላቁ ኢትዮጵያዊው አባት አቡነ ቀውስጦስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ
በቤተክርስቲያናችን ግንቦት 1 ታስበው ከሚውሉ ታላላቅ አባቶች መካከል ኢትዮጵያዊው አባት አቡነ ቀውስጦስ አንዱ ናቸው፡፡ ለመሆኑ አቡነ ቀውስጦስ ማን ናቸው? ምንስ ቃል ኪዳን ተሰጣቸው? ባጭሩ እንመልከት ምልጃና በረከታቸው ይደርብን አሜን
ጻድቀ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ የተወለዱት በሸዋ ክፍለ ሀገር በወግዳና ቡልጋ ውስጥ ሲሆን አባታቸው ገላውዲዮስ እናታቸው እምጽዮን ይባላሉ፡፡ የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማት እናት እግዚአኃሪያ እና እምነጽዮን ታናሽና ታላቅ እህትማማቾች ናቸው፡፡ ገላውዴዎሰ እና እምነጽዮን እግዚአብሔር የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ለዓመታት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል ፊት ሲጸልዩና ሲለምኑ የእመቤታችንም ስዕል አፍ አውጥቶ አናገረቻቸው እንዲህም አለቻቸው፡፡ ‹‹አንድ ልጅ አስቀድማችሁ ትወልዳላችሁ የሚወለደውም እኔ በተወለድኩበት ግንቦት 1 ቀን ሲሆን እረፍቱም በእኔ የእረፍት ቀን ጥር 21 ነው፡፡ እሱም የሰማያዊ ንጉስ ጭፍራ ይሆናል፡፡ ››አለቻቸው በተገባላቸው ቃል መሰረት ግንቦት 1 ቀን ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ ተወለዱ፡፡
ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ የዚህን ዓለም ተድላ ደስታና ጣዕም ንቀው ፈለገ ሐዋርያትን ተከትለው በሸዋ፤ በከፋና፤ በጅማ ዞረው የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማስተማር ከአረማውያን ነገስታትና ባላባቶች የሚደርስባቸውን መከራና እንግልት በመታገስ በተጋድሎ ጸንተው ብዙውን ሕዝብ ከአምልኮት ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከኃጢያት ወደ ጽድቅ መልሰዋል፡፡በተለይ በሸዋ ክፍለ ሀገር ፈንታሌ ተራራ ላይ ሠረቲ ለምትባል ጠንቋይ እየተላላኩ ህዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ አራት መቶ ሰባ ሺህ ሦስት መቶ አጋንንትን እንደ ነብዩ ኤልያስ በጸሎታቸው ከሰማይ እሳት አውርደው ተራራውን ደምስሰው አጋንንቱን አቃጥለዋል፡፡ሕዝቡንም ለጣዖትና ለጠንቋይ ከመገዛት አድነውታል፡፡
ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ በብዙ ተጋድሎ ሲኖሩ በሰማዕትነት ያርፍ ዘንድ ስለ እግዚአብሔር መንግስትና ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚተጉ እንጂ የዚህን ዓለም መንግሰት ሀብትና ሥልጣን የማይሹ እውነተኛ መናኝ ነበሩና የታናሽ ወንድማቸው የአጼ ይኩኖ አምላክ ልጅ አጼ አምደጽዮን የአባቱን እቁባት በማፈግባቱ ‹‹ይህንን ልታደርግ አይገባም››ብለው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ (ማር 7፡14-29) ቢገስጹት 11 አሽከሮችን በሌሊት ልኮ ከበዮ ወደ እንሳሮ ሀገር ካስወሰዳቸው በኃላ ኮሶ አረህ ከሚባለው አፋፍ ላይ እኩለ ሌሊት በጦር ጎናቸውን አስወግቶ ደማቸውን አፈሰሰሰ፡፡ደማቸውም እስከታላቁ ወንዝ ጅማ ድረስ ሆነ፡፡የፈሰሰው ደማቸውም ቀይ ብርሃን ሲሆን የሌሊቱ ጨለማ ከጸሐይ ሰባት እጅ የሚበልጥ ብርሃን በአውራጃውቹ ሁሉ ታየ፡፡በዚህ የተነሳ እስከ ዛሬ ድረስ ሀገሩ ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡
በብዙ ተጋድሎ ከቆዩ በኃላ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሳትለይ በስቃይ ላይ ላሉም በዘመናቸው ሁሉ ስለነበራቸው ተጋድሎ ንጽህናና ምናኔ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ድንግል ማርያምና ቅዱሳኑኑ እና መልአክታኑን አስከትሎ ቃል ኪዳን ሊሰጣቸው መጣ፡፡ እንዲህም አላቸው እኔ ለአንተ ዓይን ያላውን ጆሮ ያልሰማውን መንግስተ ሰማያትን አዘጋጀውልህ በዚያም ታላቅ ወንበር ታገኛለን በዘመንህ ስላሳለፍካቸው ክርስቲያናዊ ተጋድሎህ 7 የብርሃን አክሊላትን አዘጋጀውልህ 2ቱ እንደ እነ ነብዩ ኤልያስና ነብዩ ሳሙኤል ለሆነ ንጽህናህ 2ቱ እንደ እነ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ለሆነ የወንጌል ስብከትህ 2ቱእንደ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ፊቅጦር በትዕግስት ሥለተጋደልክ አንዱ ስለ ልብ ርህራሄ ነው አላቸው፡፡
እንዲሁም ስለ እኔ ምስክርነት የሞትክባት ምድር እንደ ዳዊት ሀገር እንደ ኢየሩሳሌም ትሁንልህ ወደ እርሷ የሄደውንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቃብሬ ጎሎጎታ እንደ ሄደ እቆጥርለታለሁ፡፡ ብዙ ኃጢያት የሰራ ሰው ንሰሐ ገብቶ በዚህች ሀገር በስምህ ጥቂት ምጽዋት ቢሰጥ እኔ ኃጢያቱን እደመስስለታለሁ፡፡በጠበልህም ቢጠመቅ በደሉን አጠፋለታለሁ፡፡ደምህ በምድሪቷ ፈሷልና፡፡
በእረፍት ዕለትህ ለቤተክርስቲያን ለቅዱስ ቁርባን ስንዴ ወይንና ዕጣን ያቀረበ ኃጢያት የሰራ ቢሆን ንሰሐ ቢገባ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንደተቀበለ ንጹህ ሰው አደርገዋለው፡፡ ለስምህ መታሰቢያ በታነጸው ቤተ መቅደስ በንጹህና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበል ሰው ራሱን ቤተሰቡን እና ባልጀሮቹን ያድናል፡፡
ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ ይህንን ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ አረገ፡፡ቅዱሳን መልአክትም ነፍሳቸውን ከሥጋቸው በክብር ለዩ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በሰማይ መካከል ሆና ነፍሳቸውን በፈገግታ ተቀበለች ፡፡
የእረፍታቸውም እለት እመቤታችን ባረፈችበት ጥር 21 ቀን በመሆኑ እመቤታችንም መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ በልጄ በረከት እባርካቸዋለሁ ብላ ቃል ኪዳን ገባችላቸው፡፡ ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ ባረፉበት ዕለትም ብዙዎች ከደዌአቸው በረከትና ፈውስ አግኝተዋል፡፡ አሁንም ድረስ ደማቸው በፈሰሰበትና አጽማቸው ባረፈበት ቦታ ብዙ ምዕመናን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስ እያገኙበት ነው፡፡የጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ በዓል ግንቦት 1 ቀን የተወለዱበት ጥር 21 ቀን ያረፉበትና ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን በማዘከር በታላቅ ድምቀት በገዳሙ ይከበራሉ፡፡
ገዳመ ቀውስጦስ የሚገኘው ከአዲስ አባባ በስተሰሜን 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሲሆን ወደ ደብረ ሊባኖስ በሚወስደው መንገድ ሙከጡሪ ከተማ ሲደርሱ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ሚቴና በዩ በሚባለው አካባቢ ልዩ ስሙ መገንጠያ ከሚባል ቦታ ነው ውይም ወደ ጅሩ አርሴማ ቅድስት ሲሄዱ ወርደው ከአቡነ ቀውስጦስ ተባርከው መሄድ ይችላሉ ፡፡መንገዱ እዚያው ገዳሙ ድረስ መኪና የሚያስገባ በመሆኑ ምዕመናን ቦታው ድረስ በመሄድ ከጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ በረከት ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እገልጻለን፡፡የጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ ረድኤትና በረከት ጸሎት ዘወትር አይለየን አሜን ፡፡ አባት ሆይ በረከትህን እናገኝ ዘንድ ባርከን!!!
ምንጭ፡-ገድለ አቡነ ቀውስጦስ

ጸሀፊ ገዛኸኝ ፈንታሁን