Wednesday, September 24, 2014

እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን

      
           በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
‹‹ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ›› 1ኛ ቆሮ 1፤23
ይህን ኃይለ ቃል ቅዱስ ጳውሎስ ተናግሮታል፡፡ የቀድሞ ስሙና ምግባሩ ሳውልና አሳዳጅ ማለት ነው፡፡
ሳውሎ ገማልያ ከተባለ ከኦሪት ሕግ አዋቂ ጠንቅቆ የተማረ ስለ ኦሪት ሕግና ስርአት አብዝቶ የሚጨነቅ ነበር፡፡በዚህ ምክንያት የክርስቲያኖች መብዛት የክርስቶስ አምላክነት በብዙ ቦታ ሲሰበክ እጅግ አብዝቶ ይጠላ ነበር፡፡በተለይ በክርስቶስ የሚያምኑትን ወንዶችንም ሴቶችንም ሕጻናትንም ጭምር ወደ ወህኒ ቤት ለማስገባት ይጣደፍ ነበር፡፡ ሳውል ይህን ሁሉ የሚያደርገው እግዚአብሔርን ያስደሰትኩ እየመሰለው ነበር፡፡ከእለታት በአንድ ቀን በደማስቆ የክርስቲያኖችን መብዛትና ሰው ሁሉ በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ማመኑ እጅግ ስላስጨነቀው ክርስቲያኖችን የሚያስርበትና የሚደበድብበት ፈቃድ ከሊቀ ካህናት አገኜ፡፡ ይህን ፈቃድ ይዞ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ በፍጥነት እየተጓዘ ሳለ ‹‹ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ ›› የሚለውን ቃል ከሰማይ ሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ ጉልበቱ ልቡናው ተናወጸበት፡፡ እንዲህም ብሎ መለሰለት ‹‹ ጌታ ሆይ እኔ የማሳድድህ አንተ ማን ነህ ›› አለው ፡፡ የሐዋ ርያት ስራ 9
በዚህ ጊዜ ‹‹ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ ›› በማለት ጌታችን መለሰለት፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባወነ ከማን ጋር መሄድ እንዳለበት ጌታችን ለሳውል ነገረው ፡፡ ሳውል ሃሳቡና ዓላመው ከትፋት ወደ መልካምነት ተመለሰ፡፡ ሳውልም በክርስቶስ ቸርነትና ምሕረት እየተደነቀ ወደ ሐናንያ ሄደ፡፡ ሰዎቹም እየመሩት ሐናንያ ዘንድ አደረሱት፡፡ ሀናን አስቀድሞ ጌታ በራእይ ነግሮት ነበርና ሐናንያም ሳውልን ተቀበለውና አጠመቀው አስተማረውም፡፡ ሳውልም በረታ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ ፡፡ ሳውል ስሙ ተቀየረ ጳውሎስ ተባለ ብርሃን ማለት ነውና፡፤ምግባሩም የክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል ቀን ና ሌት መስበክና ማስተማር ሆነ፡፡ ልቡ በክርስቶስ ፍቅር ተነደፈ ፡፡ አሁን የእግዚአብሔር ፍቅር ገባው ፡፡ ስለገባው ስለ ክርስቶስ አምላክነት አዳኝነት እየሰበከና እያስተማረ መልካም ተጋድሎውን ያከናውን ጀመር፡፡እንዲሁም በስሙ መከራን ለመቀበል ራሱን አዘጋጀ፡፡ ስለ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስያን አብዝቶ ይጨነቅ ነበር ፡፡ ይህ ድንቅ በሆነ አጠራር የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን በመስበኩ ለእንግልት ለእስራት ተዳረገ፡፡አስራ አራት መልእክታቱን ሁሉ በወህኒ ቤት እያለ የላካቸው ናቸው፡፡ ስለ ጌታችን ከተናገረው አንዱን እስኪ እንመልከት፡፡
‹‹ እኛግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ››
‹‹ የግሪክ ሰዎች ጥበብን አይሁዶች ምልክትን ይሻሉ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ›› በማለት ክርስቲያኖች ማንን መመልከትና ወደ የት ፊታቸውን ማዞር እንደሚገባቸው አስረዳ፡፡ ቅዱሳን ከዓለም ምናምንቴ የራቁ ስለሆነ ስሙን እየጠሩና በስሙ እያስተማሩ የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሰበኩ መከራን ተቀበሉ፡፡
ለመሆኑ የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ ምንምን እናስባለን
ሀ - መከራውን እንሰብካለን
ለ -ድንግል ማርያምን እንሰብካለን
ሐ -ቅዱሳንን እንሰብካልን
መ -እንደምንፈተን እናውቃለን ፈተና እንደሚኖርብን እንሰብካለን ፡፡
ሀ መከራውን እንሰብካለን ፡- ክርስቲያን በስሙ ብቻ አምኖ አይቀመ ጥም ጌታችንና አምላካችን ፈጣሪያችን ስለ እኛ ሲል የተቀበለውን መከራውን እያሰብን እንኖራለን፡፡ እንሰብካለንም፡፡ ጌታ በፈቃዱ የእኛን ስጋ ለብሶ መከራን ተቀብሎ ከባርነት ነጻ አውጥቶ ወደ ዘላለማዊ ደስታ ወዳለብት ድንቅና ግሩም ቦታ ወስዶናል፡፡ ይህ የተከፈለልን ዋጋ እጅግ ግሩምና ድንቅ ነው ፡፡ እርሱ አምላካችን ስለ እኛ ሲል መከራን ተቀበለ፡፡ ‹‹ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን ›› ት/ ኢሳ 53፤4 ነቢዩ እንደተናገረው ጌታችን በቁስሉ ፈወሰን በህማሙ እኛ ዳን ስለዚህ ሁልጊዜ መከራውን እንሰብካለን፡፡ ዮሐ 19፤1 ማቴ 27፤57
በእለተ አርብ በፈቃዱ የተቀበለውን መከራ አራቱ ወንጌላዊያን ዘግበውታል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን በሚያመሰግንበት ምስጋነው እንዲህ ብሎ ተናግሯል ‹‹ እስመ በፈቃዱ ወበስምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጻእ ወ አዳኅነነ ፣በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጣና አዳነን ›› ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ ፡፡በማለት በፈቃዱ ዓለምን እንዳዳነ ይነግረናል፡፡ ቅዱሳን የተሰቀለውን ክርስቶስን ሲሰብኩ መከራውንም ጭምር ይሰብካሉና እኛም ክርስቲያኖች መከራውን እንሰብካልን፡፡
ለ -ድንግል ማርያምን እንሰብካለን ፡- የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውንና ተስፋችን እመቤታችንን እንሰብካለን፡፡ ጌተ ሰው ሆነ ስንል ከማን ከእመቤታችን ጌታ ስጋና ደም ሕይወት ነው ስንል ከእመቤታችን የነሳው ነው ስለምንል የእመቤታችንን ክብር ቅድስና የአምላክ እናት መሆኗን አማላጃችን መሆኗን እንሰብካለን፡፡ እመቤታችንን ካልሰበክንማ ክርስትናችን ከንቱ ነው ፡፡ ዋጋም አያሰጥም፡፡ እም አምላክ ወላዲተ አምላክ የአዳም ተስፋ የሔዋን መድኃኒት የመእመናን አለኝታ የመላእክት እህት የሁላችን መጽናኛ መሆኗን እንሰብካልን፡፡ ድንግል ማርያምን ካልሰበክን ምን ተስፋ አለን ወደማንስ እናጋጥጣለን፡፡
ሉቃስ 1፡45 ፣ ዮሐ 2፤ 1 ፣ መዝ 131፤ 1
ሐ- ቅዱሳንን እንሰብካለን ፡- ቅዱሳን ስለ ጌታችን ብዙ መከራን ስለተቀበሉ ለእኛም የመልካም ነገር ሁሉ አርአያ ስለሆኑን ስማቸውን እየጠራን እንሰብካለን፡፡ ዝክራቸውንም እዘከርን እንኖራለን፡፡ ጥቅሙን እኛ ስልምናውቀው ስለ ቅዱሳን አብዝተን እናስተምራለን፡፡ ቅዱሳን የገታችንን ቅዱስ ወንጌልን ስላስተማሩ ና ስለ ሰበኩ ለእኛም ስላስተረፉልን እንሰብካለን፡፡ እብ 13፤7 ‹‹ ዋኖቻችሁን አስቡ ›› ተብለናልና ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምኑንም ሳያውቁትና ሳይረዱት ከመሬት ተነስተው የከበሩትን ቅዱሳንን ሲያቃልሉ አያፍሩም፡፡ ምክንያቱም ምሥጢሩን ሰይጣን ስለሚሸሽጋቸው፡፡ እኛግን እግዚአብሔር ያከበራቸውን የመረጣቸውን እናከብራልን እንስበካለን፡፡ የተሰቀለውን ክርስቶስን የምንሰብክ ነንና፡፡
መ - ሌላው የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ ፈተና እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ዓለም ለክርስቲያኖች ብዙ አይነት መሰናክል አዘጋጅታለች፡፡ ክርስቲያን በመሆናችን ክርስቶስን በማምለካችን ልዩልዩ ፈተና ይመጣብናል፡፡ ፈተና እንደሚመጣ አውቀንና ተረድተን ልንኖር ግድ ይለናል፡፡ምክንያቱም የተሰቀለውን ክርስቶስን የምንሰብክ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና፡፡ ለዚህ ነው ውዳሴና አምልኩ ለስሙ ይሁንና አምላካችን ና ፈጣሪያችን እንዲህ ብሎ የነገረን፡፡ ‹‹ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል ›› ማቴ 24፤13
ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የ ተሰቀለውን ክርስቶስን የምንሰብክ ነንና ለፈተና ተዘጋጅተን እንዲንኖር ያስፈልጋል፡፡ የሐዋ ስራ 21፤13
ማቴ 8፤23
የቅድስት ሥላሴ ቸርነት
የእመቤታችን አማላጅነት
የአባ ጊዮርጊስ ዘ ጋስጫ ቃል ኪዳን
እንዲሁም የቅዱሳን ሁሉ በረከታቸውና ቃል ኪዳናቸው ከሁላችን ጋር ይሁን አሚን