Tuesday, December 8, 2015

የቅድስት አርሴማ ተአምር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

እነሆ ተአምር ከሰማእቷ ቅድስት አርሴማ
ገዳም።
ለሌሌች አድርሱ ይህን መስክሩ.!
እናት ማዬት ስለተሳናት ልጃቸው ብለው ሱባኤ
ለመያዝ ጎንደር ጭልጋ ወረዳ ቅድስት አርሴ ማ
ገዳም ተገኝተዋል። በገዳሙ ስርአት መሰረት ሱባኤ ይዘው ለሁለት ሳምንት ገብተዋል፣
በፀሎት እና በልመና ሳያቋርጡ የዘውትር
ናፍቆታቸውን በልመና ወደ ፈጣሪ ያሳስባሉ
ሰማእቷን እርጅኝ ይህችን አንድ
ፍሬ ህፃን ብርሃን ስጫት ለኔም ረድኤትሽ ይድረሰኝ
እያሉ ሳያቋርጡ ይፀልያሉ። በዚህ ሁኔታ ሁለት ሳምንት ተቆጠረ
በስተመጨረሻም ቀነ ቀጠሮው ደረሰ እና አንድ ቀን
እማማ በሱባኤ እያሉ ሚጡዬ ከተኛችበት ባንና
ተነሳች እና በድንጋጤ
ሁሉን አተኩራ አዬቻቸው በማደሪያው ያሉትን
አብረዋት ያሉትንም ከእንቅልፏ ተነስታ አፍጥጣ አስተዋለቻቸው ሰዎቹም
ሁለት ልብ ሆኑ ማየት አትችልም ነበርና አሁን ግን
ሁሉንም እያዬች በልጅነት ግራ መጋባት እንዲህ ብላ
አሳገራሚ ነገር ነገረቻቸው።
>> አንዲት ሴት ተነሽ ተነሽ ብላ ቀሰቀሰችኝ
ሴትዬዋ ደግሞ እንደዚህች ትመስላለች ብላ በማደሪያው ቤት ያለውን የቅድስት
አርሴማ ስዕለ አድህኖ ጠቁማ አሳዬቻቸው። ማዬት
የተሳናት ህፃን ልጅ በሰማእቷ እርዳታ ማዬት
ቻለች። ይህም ብቻ አይደለም! ህፃኗ እንዲህ ብላም
ነግራቸዋለች የቀሰቀሰቻት ይች
ሴት ብዙ ጊዜ እየታዬቻት ታናግራት እንደነበርም ነግራቸዋለች!
እማማ በሱባኤ በነበሩበት ቀናት አይኗ ለማያዬው
ህፃን
ሰማእቷ በአይነ ልቦናዋ ትገለጥላት እና ትታያት
ነበር።
አይደንቃችሁም ወዳጆቼ? የእናት ልመና ቀላል አይደለም!!!
እምነታቸው የፀና ነውና ለዛውም ፊደል ሳይቆጥሩ
በልቦናቸው
ብርሃን እየተመሩ ፈቃዱን እየፈፀሙ ይኖራሉና
እግዚአብሔር
ም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈፅምላቸዋል! የእናቶች ፀሎት እና
ልመና ጠብ የምትል አይደለችም!! ያደለው
ቅዱሳንን ተማፅኖ
እንዲህ ቤቱ በተአምራት ይሞላል! ይባረካል
ይፈወሳል!
እኛስ??? … … እስካሁን ዶክተርን ልመና ካገር አገር
የምንባዝን ስንቶቻችን ነን? እኔ የሚገርመኝ ማን
ወደ ማን
ነበር መምጣት የሚገባው? ባለፀጋስ ማነው?
መድሀኒት
ያለውስ የት ነው? እግዚአብሔር ሁላችንም ወደ ልቦናችን
ይልሰን እና በእጃችን የያዝነውን እንቁ
እንድናስተውል ይርዳን።
እግዚአብሔር ይህንን የቅዱሳኑን ድንቅ እና በረከት
እንድናይ
የበቃን የተዘጋጀን እንድንሆን ይርዳን አሜን። የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን!
~Like
~Comment
~Share 

Thursday, August 27, 2015

መንፈሳዊ ተጋድሎ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: 
1.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ምን ማለት ነው?


መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት - አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ÷ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነፃ ፈቃዱ ወስኖ፥ በሙሉ ልቡናው፥ በሙሉ ኃይሉ የሚያደርገው የውስጥና የውጭ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፥ ጥረትና ትግል ነው፡፡
ሀ. ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው፡፡
ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም›› ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማያቋርጥ ጦርነት ነው፡፡ (ገላ 5፥12) ታላቁ አባት ኢዮብም ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ?›› በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿአል፡፡ ይህም ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው፡፡ ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል፡፡
ይህ ሲባል ግን ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ሥጋ በራሱ ርኵስ አይደለምና፤ ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰውን (ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው) ከፈጠረ በኋላ ‹‹ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡›› ተብሏል፡፡ (ዘፍ1፥31) ሥጋ ርኵስ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ወልድ (ቃል) ‹‹ሥጋ ሆነ›› ባልተባለ ነበር፡፡ (ዮሐ 1፥14) አዳምና ሔዋን ከኃጢአት በንጽሕና ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፣ አይተፋፈሩም ነበር›› እንዲል (ዘፍ 2፥25)  ህፃናት፣ ልጆች  ሰውነት አላቸው ነገር ግን የኃጢአት ምኞት የላቸውም፡፡
ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ ተፈጥሮአዊና ንጹህ የሆነ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣  በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም/መግራት ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን በመጠቀም ይሠራል÷ ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ ‹‹ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ፡፡ (ዘዳ 32፥15)
ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ‹‹ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ›› እንዳለ፡፡ በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ (1ኛ ቆሮ 9፥27) በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ›› እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባናል፡፡
ለ. ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር እንጂ›› እንዳለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ሰው ከሰው ጋር በመጣላት የሚያደርገው ትግል ሳይሆን ጥንተ ጠላታችን ከተባለው በእባብ ወይም በዘንዶ ከተመሰለው ዲያብሎስና ከእርሱ ጋር ካሉት ሠራዊቱና መልእክተኞቹ ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ (ኤፌ 6፥12)
ከአዳምና ከሔዋን ከልጃቸውም ከቃየን ጀምሮ ሰይጣን የሰው ልጆችን ዘወትር ይዋጋል፤ ከዘላለም የሞት ፍርድ ሥር ሊጥል ይሠራል፡፡ በዚህም ውጊያው ከነቢያት ፤ከሐዋርያት ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ብዙዎችን ጥሏል፡፡
ዛሬም በገዛ ባሕርያችን የሚገኘውን ፈቃደ ሥጋ በመጠቀም፣ የራሱን በመጨመርና የተለያዩ ፈተናዎችን በማቀናበር ይዋጋናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፡፡›› እንዳለ ጠላት ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በኃጢአትና ሞት ሊውጥ ዘወትር ይተጋል፡፡ ማንም ሰው ደግሞ ከዚህ ፈተናና ውጊያ ሊያመልጥ አይችልም፤ ስለዚህ ሐዋርያት ‹‹በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት››፣ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡›› እንዳሉን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ለብሰን ልንዋጋው ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ 5፥8-9፣ኤፌ 6፥11)
ሐ. የሚመጣውን ዓለም ደስታ ተስፋ እያደረጉ ብቻ በዚህ ዓለም ሕይወት ከደስታ ውጪ መሆን ማለት አይደለም፡፡
ደስታ በራሷ የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆነች፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጠች፤ ንጹሕ ፈርጥ ነች፡፡ (ገላ 5፥22)
እውነት ነው፤ በዚህ ዓለም ስንኖር መከራ አለብን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ እስካለ ድረስ ከጨለማው ዓለም ገዢ ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ የሚመጣ ልዩ ልዩ ፈተናና ከሥጋችንም ባሕርይ ከሚገኘው ክፉ ምኞትና ርኵሰት ሥራ እንዲሁም ከሌሎቹ የኃጢአትና የፈተና ዓይነቶች ጋር በማያቋርጥ እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል ውስጥ መኖሩ የግድ ነው፡፡ መከራና ስቃይ፣ ትግልና ጦርነት የሌለበት በዘለዓለማዊ ደስታ ብቻ የሚኖርበት ሕይወት በሚመጣው ዓለም የሚገኝ ነው፡፡
በዚህ ምድር በጉዞ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን ጨርሳ ድል ከነሱት አባላቷ ጋር አንድ እስክትሆን ድረስ መከራው፣ እንቅፋቱ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ የግድ ነው፡፡ ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፡፡›› እንዲል (ሐዋ 14፥22)
ይህ ሲባል ግን በዚህ ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከደስታ የተራቆቱ ዘወትር በኅዘንና በስቃይ ብቻ የሚኖሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሚለዩትና ዘወትር ለመለየት ጥረት የሚያደርጉት የውሸት ከሆነው ኃጢአት (ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል) ከሚገኘው ደስታ እንጂ ከእውነተኛውና ከሰማያዊው ደስታ አይደለም፡፡
መንፈሳዊ ተጋድሎ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና ረድኤት መንፈስ ቅዱስ መሪና አስተማሪ፣ የሚያነቃቃና የሚያጽናና፣ የሚያርምና የሚገሥጽ፣ የሚረዳና የሚያጸና፣ በመሆን ስለ ክርስቶስ በክርስቶስ ጸጋ የሚከናወን በመሆኑ መከራንና ስቃይን በሚያስረሳ እውነተኛ ደስታና ሰላም የተሞላ ሕይወት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ስለ ክርስቶስ በማስተማራቸው ምክንያት ገዢዎች ልብሳቸውን ገፈው በበትር እንዲመቱ አዘዙ በበትር ከመቷቸውም በኋላ በወኅኒ ቤት ጣሏቸው እነርሱ ግን ከጀርባቸው ደም እየፈሰሰ በመንፈቀ ሌሊት እንኳን እግዚአብሔርን በመዝሙር ያመሰግኑ ነበር፡፡ እውነተኛውና ሰማያዊው ደስታ በልቡናቸው ሞልቶ ነበርና፡፡ (ሐዋ 16፥22-25)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐዋርያት እንዲህ ይለናል ‹‹ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው  በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቷቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፡፡››(ሐዋ 5፥40-41)
ቅዱስ ዮሐንስ ካሲያን የተባለው አባት በተጋድሎ በግብጽ በረሃ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩት መነኰሳት ሲናገር ‹‹ እነዚህ ምድራዊ መላእክት ናቸው፤ የግብጽን በረሀዎች በደስታ ወደ ተሞላ መዝሙርና እግዚአብሔርን የማመስገኛ ገነትነት ለውጠዋልና››  ብሏል፡፡
በአጠቃላይ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ከተድላ ሥጋ፣ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ በመሸሽ ሰማያዊና እውነተኘ በሆነ ሰላምና ደስታ ውስጥ መኖር ይህንንም ለማግኘት መጋደል ማለት ነው፡፡

2.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማው ምንድነው?
ሀ. የድል አክሊል (የዘለዓለም ሕይወት) ለመቀበል
እግዚአብሔር አምላካችን ሰዎች ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ከአምላካቸው ጋር መኖር ከመረጡ ሊሰጣቸው ያዘጋጀው ከመነገርና ከመታሰብ በላይ የሆነ የዘለዓለም  ሕይወት አለ፡፡ የሰው ልጅ ሕሊናዊ ነፃ ፈቃዱ ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ በየጊዜው እየደከመና ወደ ኃጢአት እያዘነበለ መጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ከብሮ ባየ ጊዜ ከአባቶቻችን ጀምሮ ዘወትር የሚቀና ክፉ ጠላትም (ዲያብሎስ) አለን፤ ባገኘው አጋጣሚ ስንፍናችንንና ድካማችንን እየተከተለ እነዚህንም በመጠቀም ዘወትር ከአምላካችን ሊለየን እንደሚተጋም ከላይ ተመልክተናል፡፡

ሽልማት፣ አክሊል የሚሰጠው ደግሞ ማሸነፍ ለሚችል ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ሰነፍና ቸልተኛ ሰው ግን ሊሸለም አይገባውም አንድ ሰው ጎበዝ ወይም ሰነፍ መሆኑ የሚታወቀው ደግሞ በፊቱ ያጋጠመውን ውድድር ወይም ፈተናና መከራ ማሸነፍና ማለፍ ሲችል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማ በገዛ ባሕርያችን ያለን መጥፎ የኃጢአት ዝንባሌና ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያመጣብንን ፈተናና ሽንገላ ከእግዚአብሔር ርዳታና ቸርነት ጋር ሕሊናን በማንቃት፣ ራስን በመግዛትና ጠንክሮ በመጋደል አምላካችን ያዘጋጀልንን የድል አክሊል የዘላለም ሕይወትን መቀበል ነው፡፡ ‹‹ የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል›› አንዲል (1ኛ ጢሞ 6፥12) ሐዋርያቅ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ መከራዎችን አልፎ ገድሉን በድል አድራጊነት ሲፈጽም ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል ( 2ኛ ጢሞ 4፥7-8)
ለ. ለመንፈሳዊ እድገት
ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለፍሬ የሚበቃው የድል አክሊልን መቀዳጀት የምንችለው የማያቋርጥ (የማይቆም) መንፈሳዊ ዕድገት ሲኖረን ነው፡፡ በጥምቀት ያገኘነው አዲሱ ሕይወታችን ዘወትር ማደግ ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በዛፍ ተክል ይመሰላል፡፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ፍሬ እስከሚያፈራለት ጊዜ ድረስ ያለው ድካም ቀላል አይደለም፡፡ የዛፉ ችግኝ እንዲያበቅል፣ እንዲለመልም፣ አንዲያብብና እንዲያፈራ አትክልተኛው ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ በየጊዜው ውሃ ማጠጣት፣ ማረምና መኰትኰት፣ ፀረ ዕፅዋትና ፀረ ሕይወት የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን አድጎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ዕለተ ዕለት ጠንክረን በትዕግሥት መሥራት በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናት ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ተጋድሎም ዓላማው መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያቀጭጩ  ከጸጋ እግዚአብሔርም የሚያራቁቱ ኃጢአትና የዲያብሎስ ፈተናን በመቃወም መንፈሳዊ ምግቦችንም በመመገብ አዲሱ ሕይወታችንን ማሳደግ ነው፡፡
                                                                                                 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቅዱስ ሰራባሞን የኒቅዩስ ሊቀ ጳጳስ - ሕይወቱና ተጋድሎው

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 
ቤተ ክርስቲያን በዓላውያን ነገሥታት አሰቃቂ ስደት በደረሰባት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕት ዓመታት ውስጥ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አንዱ የሆነውና ለዛሬው የተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የምንመለከተው ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞን ዘኒቅዩስ ነው። አባቱ አብርሃም ይባላል፤ አያቱ የቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ አጎት ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። ሲወለድ ወላጆቹ “ስምዖን” ብለው ስም አወጡለት፤ “ሰራባሞን” የጵጵስና ስሙ ነው። የዐረብኛ እና የግዕዝ መጻሕፍት “ሰራባሞን” ሲሉት፣ የቅብጥና እንግሊዝኛ ምንጮች ደግሞ “ሰራፓሞን” ብለው ይጠሩታል።

በተወለደበት በኢየሩሳሌም ሳለ ክርስቲያን መሆን አጥብቆ ይፈልግ ነበር። እመቤታችን በራእይ ተገልጻ ወገኖቹ አይሁድ እንዳይገድሉት ወደ ግብፅ ሄዶ እንዲጠመቅና አገልግሎቱንም በዚያ እንዲፈጽም ስለነገረችው ቤተሰቦቹን ጥሎ መነነ። ግብፅ ሲደርስ እመቤታችን የእስክንድርያ 16ኛ ፓትርያርክ የነበረውን አቡነ ቴዎናስን (282-300) ባዘዘችው መሠረት አስተምሮ አጠመቀው። የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜያት፣ የነቢያትንና ሐዋርያትን መጻሕፍት ተማረ፣ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳን እና የበልኪሮስን ድርሳናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠና።

ከዚያም ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ በሆነ እልሐብጡን በተባለ በአባ ሳዊሮስ ገዳም ውስጥ መነኮሰ። ከዘመናት በኋላ በተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ዘመን (300-311) የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፍ በእርሱ ምትክ የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መራ፤ ከገድሉ እንደምናነበው ወደ ተመደበበት ሀገረ ስብከት ሲገባ የተደረገለት አቀባበል የደመቀ ከመሆኑ የተነሣ ጌታ በሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ታጅቦ ሲገባ እንደተደረገለት የሚመስል ነበረ። በቅዱስ ሰራባሞን አገልግሎት በኒቅዮስና በአጎራባች ከተሞች የነበሩ ጣዖታት ተሰባብረው ወድቀዋል፤ በእጁ በርካታ ገቢረ ተአምራት ተደርገዋል፤ በመስቀሉ አጋንንትን አባሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ስለ ወንጌል ብዙ መከራን ተቀብሏል፤ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ብዙ ዘለፋ ደርሶበታል። አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና ሚሊጦስ በእርሱ ዘመን የነበሩ መናፍቃን ናቸው። የአርዮስ ዋና ክህደት “ወልድ (ክርስቶስ) ፍጡር ነው” የሚል ሲሆን ሚሊጦስ ደግሞ “ከማርያም የተወለደው ክርስቶስ በምትሐት ነው እንጂ በእውነት አይደለም” የሚል ነበር። ሰባልዮስ “እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው” ብሎ የሚያስተምር ሲሆን፤ ሰራባሞን ሁሉንም ተከራክሮ ረቷቸዋል።

በዚህ የተነሣ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። አርዮስና ሚሊጦስ የሚያስተምረውን ባለመቀበላቸው በክፋታቸው ጸንተው ብዙዎችን እያሳቱ፣ በትዕቢታቸውም ልባቸውን እያኮሩ ቢያገኛቸው በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ የአርዮስና ሚሊጦስን አንገታቸውን በመሐረብ ይዞ “እናንተ አባታችሁን ዲያብሎስን በክህደት የምትመስሉ እስከ መቼ ድረስ ነው በዚህ ክህደታችሁ ሰውን የምታጠፉ?” ብሎ ገስጿቸዋል (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 130-137)። አርዮስ ከክሕደቱ የማይመለስ ከሆነ አንጀቱ ተበጣጥሶ እንደሚሞት፣ ሚሊጦስም ካልተመለሰ ሥጋውን በቁሙ ዕፄያት እንደሚበሉት ትንቢት ተናግሮባቸዋል። እምቢ በማለታቸው በሁለቱም ላይ ይኸው ተፈጽሞባቸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅልጥያኖስ (284-305) የሚያፈርሳትን ቤተ ክርስቲያን ሰረባሞን ሲሰራ፣ ጣዖት የሚያመልኩትንም ሰዎች በክርስቶስ ስም ሲያሳምናቸው ንጉሡ እና መኳንንቱ ስጋት ጨመረባቸው። ሰራባሞን እንዲታሰር እና ስለ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳያስተምር በእስክንድርያው ገዢ አውጣኪያኖስ፡ ኮሞስ፡ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ሰራባሞን ግን ከአቋሙ አልተናወጸም። ስለዚህ እስር ቤቱን አንዴ በታሕታይ ግብጽ አንዴ ደግሞ በላዕላይ ግብጽ በበረሃው ሁሉ በማፈራረቅ አሰቃዩት። እርሱ ግን ስቃዩንና ዛቻውን ከምንም ሳይቆጥር በእስር ቤት ውስጥም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳምኗል። የላዕላይ ግብፅ ገዢ የነበረው አርያኖስ (ከከሐዲው አርዮስ የተለየ እና የሀገረ እንጽና ገዢ የነበረ) ብዙ ካሠቃየው በኋላ በኒቅዩስ ከተማ ወደብ አቅራቢያ አንገቱን እንዲቆርጡት ትዕዛዝ ሰጠ። የሚጓዙበት መርከብ ግን አልንቀሳቀስም አለ። ቅዱስ ሰራባሞንን ከመርከቡ ሲያወርዱት በሰላም ሄዱ። በዚህ ሁኔታ እያለ እንኳን ወንጌልን መስበክና ትንቢት መናገርን አልተወም።

ይህ በእርሱ ላይ የሞት ውሳኔ የሰጠበት አርያኖስ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስን ክዶ ክርስቲያን እንደሚሆን በመጨረሻም ሰማዕትነትን ተቀብሎ እንደሚሞት፣ እንዲሁም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት እንደሚሞትና “ተፍጻሜተ ሰማዕት” እንደሚሆን እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፥ “ወበከመ፡ ጴጥሮስ፡ ቀዳማየ፡ እምሐዋርያት፡ ከማሁ፡ አንተኒ፡ ትከውን፡ ተፍጻሜተ፡ ሰማዕት። ናሁ፡ አቅደምኩ፡ ነጊሮተከ፡ ዘይከውን፡ በጊዜሁ።” (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 158)። እንደ ትንቢቱም ሁሉም ተፈጽሟል። በመጨረሻም ከሀገረ ስብከቱ ኒቅዩስ በስተደቡብ በምትገኘው ቦታ ወስደው ኅዳር 28 ቀን (በቅብጥ አቆጣጠር ሐቱር 28 ቀን) አንገቱን በሰይፍ ቀሉት።

ደቀመዛሙርቱ አስከሬኑን በመንገድ ላይ እንዳልባሌ ነገር ተጥሎ ሲያዩት በመረረ ሐዘን ተውጠው እያለቀሱ “እረኛችን ሆይ ለማን ታስጠብቀናለህ? አባታችን ሆይ እንግዲህ ማን ይሰበስበናል? አውሬ ከቦናል፣ በወንጌል ኮትኩተህ ያሳደግከው ተክልህን ከእንግዲህ ማን ይንከባከበው?” እያሉ መሪር እንባን ያነቡ ነበር። ከብዙ ለቅሶ በኋላ አስከሬኑን ወስደው በኒቅዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር አሳረፉት (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል166)።

ከገድሉ እንደምናነበው ሰራባሞን ባደረገው ተጋድሎና በጽንአቱ በርካታ የክብር ስሞችና ቅጽሎች ተሠጥተውታል። ዋና ዋናዎቹም፥ “ብፁዕ ወቅዱስ ሰማዕት”፣ “ለባሴ መንፈስ”፣ “ለባሴ፡ አምላክ”፣ “ዓምደ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ሐረገ ወይን”፣ “ሐዲስ ዳንኤል”፣ “ላዕከ መንፈስ ቅዱስ”፣ “ሙሴ ሐዲስ”፣ “ጳውሎስ ዳግመ”፣ “ዮሐንስ ሐዲስ”፣ “መስተጋድል ዐቢይ” የሚሉት ናቸው።

በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በስሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ታንጸዋል፣ ገድል ተጽፎለታል፣ በስንክሳርም ይዘከራል። ገድሉ እና የሰማዕትነቱ ዜና በቅብጥ እና ዐረብኛ ቋንቋ የተጻፈና የተተረጎመ ሲሆን ሁሉም ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አልተገኘም። የቅብጡ ቅጂ በHyvernat, (ገጽ. 304-31) የታተመ ሲሆን የዐረብኛው ደግሞ (Kairo 27 በሚል ዝርዝር) በKraf (1934:12) ካታሎግ ተሠርቶለታል። በቅርቡ ደግሞ Youssef (2013: 263-280) የሚባል ተመራማሪ “ሰራባሞንን የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን ምንባባት” ብሎ ጥናታዊ ጽሑፍ አውጥቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያነ የቅዱስ ሰራባሞን ዜና ሕይወት እና ተጋድሎ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን እምብዛም ጎልቶ የሚታወቅ ባይሆንም በሕዳር 28 ስንክሳር ይታወሳል። ከዚህም በላይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገድሉ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1408-1497) ተተርጉሞ ይገኛል። ይህም ገድል አሁን ከሚገኙት የቅብጥና ዐረብኛ ቅጂዎች ይልቅ የተሟላ እና ይዘቱም ሰፊ ነው። ይህ ገድል በ1970ዎቹ ውስጥ (EMML 6533) በሚል መለያ ማይክሮ ፊልም ተነስቷል።

ብራናው አጠቃላይ 168 ቅጠል ያለው ሲሆን ከመጀመሪያ እስከ 118 ድረስ የሐዋርያው ጳውሎስ ገድል፣ ከቅጠል 119-167 ድረስ ደግሞ የሰማዕቱ ሰራባሞንን ገድል ይዟል። የሰራባሞን ገድሉ አራት ክፍሎችን ይዟል፤ እነዚህም፥ 1) ድርሳን (ከቅጠል 119-131)፣ 2) ገድል (ከቅጠል135-142)፣ 3) ተአምር (ከቅጠል 132-149)፣ 4) ስምዕ (ከቅጠል 150-167) የሚሉ ናቸው። ይህም ስለ ሰራባሞን የሚጠናውን ጥናት ይበልጥ የተሟላ የሚያደርግና በተለይ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ለዜና አበው እና ለነገረ ቅዱሳን የጥናት መስክ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ከስንክሳሩና ከገድሉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሰራባሞን የተዘጋጁ ልዩ ልዩ አርኬዎች (Chaîne ቁ. 48 እና Wein፣ Athiop. 19 [በN.Rhodokanakis አማካይነት ካታሎግ የተሠራላቸው])፣ እንዲሁም ሁለት የተለያዩ መልክአት (Chaîne ቁ. 158 እና 325) ተዘጋጅተዋል። በኢትዮጵያው የገድል ቅጅ ላይ እስካሁን የተደረገ ጥናት የለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ መነሻ ጥናት አድርጎ ገድሉንም እየተረጎመ ይገኛል።

ይህን ጽሑፍ የምንደመድመው በቪየና የሚገኘው ብራና (Vienna ms f.62v-63r) ስለ ቅዱስ ሰራባሞን ከሚያመሰግነው አርኬ ውስጥ አንዱን በማንበብ ይሆናል፤
ለከ፡ ስነ፡ ሰረባሞን፡ ዘኤፍራታ፤
ነጺሮሙ፡ ጥቀ፡ ለሕሊናሁ፡ ጥብዓታ፤
ከመ፡ ይከውን፡ ሰማዕት፡ ውስተ፡ ዓውደ፡ ግሩም፡ ሐተታ፤
ገደፈ፡ አብ፡ እጓሎ፡ ወእም፡ ወለታ፤
ወሐማትኒ፡ ሐደገት፡ መርዓታ።
የሰማዕቱ ሰራባሞን በረከት ይድረሰን!!!
ስምዓት
  • መጽሐፈ ስንክሳር - በግዕዝና በአማርኛ (ከመስከረም እስከ የካቲት)፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1994 ዓ.ም.
  • ገድለ ጳውሎስ ወሰራባሞን - (EMML 6533)- ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝ፣ በ15ኛው መ/ክ/ዘ/ የተጻፈ ብራና (እስካሁን አልታተመም)።
  • Amsalu Tefera, 2013, “Gädlä Särabamon: the case of the Ethiopic version”, a paper read on a workshop titled “EMML@40: The Life and Legacy of the Ethiopian manuscript microfilm Library” organized by Hill Museum & Manuscript Library, Saint John’s University, Collegeville, MN, USA, July 25-26, 2013.
  • Budge, Wallis, 1928, The Book of the Saints of the Ethiopian Church: a translation of the Ethiopic Synaxarium መጽሐፈ፡ ስንክሳር፡ made from the manuscripts Oriental 660 and 661 in the British Museum, vol. I, Cambridge at the University Press.
  • Chaîne, M., 1912, “Catalogue des manuscrits Ethiopiens de la collection Antoine d’Abbadie”, Paris.
  • Chaîne, M., 1913, “Répertoire de salam et Melke’e contenus dans les manuscrits éthiopiens des bibliotheques d’Europe” in Revue de L’Orient Chrétien, , deuxieme Serie, Tome viii, no. 2
  • Colin, G. 1988, “Le Synaxaire Éthiopien mois de Ḫedār” in Patrologia Orientalis, Tome 44, fascicule3, no. 99)
  • Coptic Synaxarium, reading on Hatour 28, – retrieved online -http://popekirillos.net/EN/books/COPTSYNX.pdf, accessed on May 14, 2012.
  • Hayvernat, Henry, Les Actes des martyrs del’Égypte, retrieved online from http://www.archive.org.detailes/lesactesdesmarty01hyve - accessed on November 6, 2012.
  • Kraf, George, 1934, Catalogue de manuscrits Arabes Chrétiens conserves au Caire, studi e testi 63, Città del Vaticano Biblioteca Apostolica Vaticana
  • Rhodokanakis, N. 1906, Die Äthiopischen Handscriften der K. K. Hofbibliothek zu Wein, Wein Athiop. 19.
  • Youssef, 2013, “Liturgical Texts Relating to Sarapamon of Nikiu”, Peeters Online Journal, pp. 263-280.
  • ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
    የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ

Tuesday, May 26, 2015

አቡነ ዓብየ እግዚእ

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
  ዕረፍቱ ለአቡነ ዓብየ እግዚእ
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ከአባታቸው ያፈቅረነ እግዚእ እና ከእናታቸው ከጽርሐ ቅዱሳን በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት በትግራይ ሀገረ ስብከት: በሀገረ ሰላም ወረዳ ልዩ ስሙ መረታ አሪያ በሚባል ቦታ ተወለዱ። ዕድሚያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ገና በ7 ዓመታቸው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ ምናኔ ገብተው አባ ዘርዓሚካኤል ከተባሉ አባት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎችንም መንፈሳዊ ትምህርቶች ተማሩ።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ለመጀመሪያ ጊዜ ሱባኤ የያዙት አገፋት በሚባል ቦታ ነው። ጸሎታቸውን (ሱባኤያቸውን) ከጨረሱ በኋላ ከዚህ አገፋት ከሚባል ቦታ ወደ ደብረ ዓባይ ገዳም በዝሆን ተጭነው ሄደዋል። እዛም ከቅዱሳን በረከት ተቀብለው እንደገና ወደ ዋልድባ ገዳም በመሄድ በምናኔና በጸሎት ቅዱሳንን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ቦታቸው ዋልድባ እንዳልሆነ ጌታ በራእይ ገለጸላቸው። እሳቸው ግን ቦታውን በጣም ስለወደዱ ከዚህ አልሄድም አሉ። እግዚአብሔር አምላክ ቅዱሳኑንን እንዳያዝኑበት ይጠነቀቃልና ዮናስን ቀስ አድርጎ እንዳስረዳው አባታችንን ደግሞ በተኙበት ጊዜ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ለበረከትም እንዲሆን የተኙባት ቦታ ቀርድደው ከነ አፈሩ አንስተው አሁን ገዳማቸው ባለበት ቦታ በመረታ አኖሩዋቸው።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ወደ ኢየሩሳሌም በደመና ሰረገላ ተጭነው፣ በመሄድ የጌታን መቃብርና ጎልጎታን በመሳለም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ከአቡነ እንጦንስና ከአቡነ መቃርስ መቃብር አፈራቸውን ለበረከት ይዘው በመምጣት በገዳሙ በትነውታል።
ንዕማን ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር ወደ አገሩ እንደወሰደ፣ እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ከተቀበሩበት መቃብር ከሮም፣ ከደብረ ምጥማቅ ከእመቤታችን ገዳም፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ መቃብር፣ ከአክሱም ጽዮንና ከሌሎችም ቅዱሳን መካናት፣ አፈራቸውን ያዙ።
መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል "ገዳምህ ይዘኸው ብትሄድ ለሰውና ለእንስሳ መድኃኒት ይሆንልሃል። ገዳምህ ልዩ ስሙ ተንስሐ በተባለ ቦታ ነው" ብሎ በራእይ ስለነገራቸው ህዳር 20 ቀን በብርሃን ሰረገላ ተጭነው የተቀደሰውን አፈር በትነውታል።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ ልዩ ልዩ ተአምራት በእግዚአብሔር ኃይል አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል
   1- የጻድቁ አባታችንን የተቀደሰው አፈር ይዘው ሲመጡ መምጣጣታቸውን ያወቁ ተንስሐ በሚባል ገዳም የተቀበሩ ቅዱሳን አባቶች፣ ልክ እንደ አልዓዛር ከመቃብራቸው በመነሳት ጻድቁ አባታችንን ተቀብለዋቸዋል። ጻድቁ አባታችን ዓብየ እግዚእም በብርሃን ሰረገላ ወርደው ባርከዋቸዋል።
    2- አጼ ገብረመስቀልና የመንፈስ ቅዱስ ጓደኛቸው አቡነ ብእሴ እግዚእ የተባሉት አብረው እያሉ ሁለት ሰዎች ሞተው ወደ ቀብር ሲወስዷቸው በስውር በእግዚአብሔር ስም ጸልየው ከሞት አስነስተዋቸዋል። ይህ ተአምር የተደረገው በአክሱም ጽዮን ውስጥ ነው። ይህንን የአቡነ ዓብየ እግዚእ ቅድስና የገለጹት አቡነ ብእሴ እግዚእ ናቸው።
    3- በተጨማሪም ኤልያስ በመጎናጸፊያው ዮርዳኖስን ወንዝ መትቶ ከኤልሳዕ ጋር በደረቅ እንደተሻገሩ እና ሙሴ የኤርትራን ባህር ከፍሎ እስራኤላውያንን እንዳሳለፋቸው ሁሉ ጻድቁ በነበሩበት ወቅት የተከዜን ወንዝ ሞልቶ ብዙ ነጋድያንና አረማውያን ተጨንቀው እያሉ የተከዜን ወንዝ በመባረክ ውሃዉን አቁመው እንዲሻገሩ አድርገዋል።
(ነገ ካልዕ 1:7-10፣ ዘዳ 14:10-30)
ይህንን ድንቅ ተአምር የተመለከቱ ከ 900 በላይ የሚሆኑ እስላሞች: የእግዚአብሔርን ቸርነትና የጻድቁን ድንቅ ሥራ በማድነቅ ወደ አባታችን ዓብየ እግዚእ በመቅረብ ተጠምቀው ወደ ክርስትና እምነት ተመልሰዋል።
ጻድቁ አባታችን አቡነ ዓብየ እግዚእ ኢልክን በተባለ ከመቀሌ 10 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ሱባኤ ይዘው ይጸልዩ ነበር። በዚህ ስፍራም በስማቸው በፈለቀው ጠበል ብዙ የካንሰር (የነቀርሳ) በሽታ ታማሚዎች እየዳኑ ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ መድኃኒት ታጥቶለት በዚህ ደዌ ለሚማቅቁት በሽተኞች የዚህ ቅዱስ ጻድቅ ጠበል በእምነት መጥተው ለሚጠመቁት ሁሉ ፍቱን መድኃኒት ስለሆነ ወጥተው በመጠመቅ ከበሽታቸው እንዲፈወሱ እግረ መንገዳችንን ሳንጠቁም አናልፍም።
ጻድቁ አባታችን አቡነ ዓብየ እግዚእ ከማረፋቸው በፊት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ የተገለጹበት ቦታ ከምርፋቁ በላይ ባለው ተራራ ላይ ይገኛል።
ቅድስት ሥላሴ የገቡላቸው ቃል ኪዳንም -- በስምህ የዘከረ፣ የመጸወተ፣ ገድልህን የሰማ፣ ቤተ ክርስቲያንህን ያሳነጸ፣ በዚህ ቦታ መጥቶ የጸለየውንና የቆረበውን እስከ 30 ትውልድ እምርልሃለሁ ብሏቸዋል። የተሰቀልኩባት፣ የተቀበርኩባት የቀራንዮ፣ የእናቴ የማርያም እንዲሁም የቅዱሳኑን መቃብር አፈር በዚህ ቦታ ስለበተንከው ቦታው እንደ ኢየሩሳሌም ይሁንልህ ብሎአቸዋል።
ጻድቁ አቡነ ዓብየ እግዚእ በጾምና በጸሎት፣ በትምህርት እንዲሁም የክርስቶስን ወንጌል በማስፋፋት፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽ ሃይማኖታዊ ገድላቸውንና ሩጫቸውን ከፈጸሙ በኋላ በ 190 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም መንግሥተ ሰማያት ተሸጋግረዋል።
የጻድቁ መቃብር ያለው በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ ውስጥ ነው። ግንቦት 19 ቀን በገዳሙና በስማቸው በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በታላቅ መንፈሳዊ አከባበር ይከበራል።
    የጻድቁ በረከት በጸሎትና ረድኤት ካንዣበበው መከራ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን አሜን !!!

Friday, March 13, 2015

አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2





    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን
  1. አርባ መአልትና አርባ ሌሊት
  2. ጾም የሚሉት ናቸው፡፡

በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/

“ወላምድኅረ ተፈጸመ ለአዳም ፵ መዋዕል በምድር ኀበ ተፈጥረ አባዕናሁ ውስተ ገነተ ኤዶም ኩፋ.9፥12 ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደገነት አስገባነው፡፡ ሔዋንንም በሁለት አርባ ማለትም በሰማኒያ ቀኑዋ ወደገነት አስገቧት ኩፋ.4፥12

በተጨማሪም አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔር ካፈረሰ በኋላ ዲያብሎስ በአቋራጭ መጥቶ አስወጣው እንጂ ሱባኤ የገባው ለአርባ ቀናት ነበር፡፡ ይህን አርባ ቀን የሰው ልጆች ከስህተት በኋላ በቀንም ሆነ በዓመት ለጾም፣ ለሱባኤ፣ ከዚያ አልፎ ለመቅጫነት አግልሏል፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው የሰው ልጅ በንፍር ውኃ የተቀጣው አርባ መአልትና ሌሊት ነበር፡፡ “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናም አዘንማለሁና የፈጠርሁትንም ፍጥረት በምድር ላይ አጠፋለሁና ዘፍ.7፥12 “የሰማይ መስኮቶች ተከፈቱ ዝናቡም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ” ዘፍ.7፥12

በዚህ ዐይነት አርባ ቀን እግዚአብሔር ሰውን እንደቀጣበት እናያለን፡፡ መቅጣት ብቻ ሳይሆን በዚህ የአርባ መአልትና የአርባ ሌሊት ዝናም ምድርን ከበዛባት ርኲሰት አጥቧታል፡፡ ምክንያቱም የጥምቀት ምሳሌ ነውና፡፡ ማየ አይህ /የጥፋት ውኃ/ የጥምቀት ምሳሌ ለመሆኑ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡” 2ጴጥ.3፥20ና21

አሁንም ከዚሁ ሳንርቅ የመርከቧ መስኮቶች የተከፈቱት በአርባ ቀን መሆኑን ይገልጻል፡፡ “ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ” ዘፍ.8፥6 መርከቧ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት ያደረጉት ጉዞ አርባ ዓመት እንደፈጀ ተጽፏል፡፡ ይህም መንገድ ደግሞ የአርባ ቀን መንገድ ነበር በእግዚአብሔር ቁጣ ወደ አርባ ዓመታት ተለወጠ እንጂ፡፡ “በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ ዓመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ” ዕብ.3፥7-19 ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎታል፡፡

እስራኤል አርባ ዘመን መና ከደመና እየወረደላቸው ተመግበዋል፣ ውኃ ከአለት እየፈለቀላቸው ጠጥተዋል፡፡ ሲያምጹም ተቀጥተዋል፡፡ ሙሴ ወንድሞቹን እስራኤልን ለመጎብኘት የመጣው በአርባ ዓመት ነበር “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ የሥራቸውን መከራ ተመለከተ” ዘፀ.3፥11 ሐዋ.7፥23 የተሰደደውም በዚሁ እድሜው ነው፡፡ በምድያም በግ በመጠበቅ አርባ ዘመን ኖሯል እንደገና እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዲያወጣ እግዚአብሔር የላከው በአርባ ዘመን ነበር፡፡ “አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ ታየው፡፡ ዘፀ.3፥30

ይህም ብቻ አይደለም ሙሴ ለዚህ አገልግሎት በተመረጠበት ጊዜ በሲና ተራራ አርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል “ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ቆየ” ዘፀ.24፥19 ዝም ብሎ ሥራ ፈትቶ አይደለም የቆየው እየሠራ ነው ሥራውም ጾም ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው በዚያም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበር አልበላም አልጠጣም” ዘፀ.34፥27 እየጾመ ነበር ማለት ነው በዚህ ጾሙ ሙሴ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች ተቀብሎበታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከንቱ ሳይሆን ዋጋ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ የኤልያስ ጉዞ አርባ ቀን አርባ ሌሊት እንደነበረ ተጽፏል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና የምትሔድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው ተነሥቶም በላ ጠጣ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሔደ” 1ነገ.19፥4-8

ሕዝቅኤል አርባ ቀን ጾሞ 600 ሙታን አስነሥቷል፡፡ እዝራ ሱቱኤል አርባ ቀን ጾሞ የጠፋ መጻሕፍትን መልሷል አብረው የነበሩ አምስት ሰዎች ቀን ቀን ይጽፋሉ ማታ ማታ ጥቂት እህል ውኃ ይቀምሱ ነበር እዝ.ሱቱ.13፥23-25 ጌታችን በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል ሉቃ.2፥22 ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2 በተነሣ በአርባኛው ቀን ወደሰማይ አረገ ሐዋ.11፥10 ሰው በተጸነሰ በአርባ ቀኑ ተስዕሎተ መልክዕ ይፈጸምለታል፡፡ “በአርባ ቀን ትሾመዋለህ” እንዲል ቅዱስ አትናቴዎስ ወንድ በተወለደ በአርባ ቀኑ ሴትም በ80 ሁለት አርባ ክርስትና ይነሣል፡፡ ሰው በአረፈ በአርባ ቀኑ ጸሎተ ፍትሐት ይደርስለታል፡፡ ሰው በአርባ ቀን ጸሎት ተክሊል ይደርስለታል ፍት.ነገ. እን.24 ገጽ 322

አርባ ቀን ይህን ያህል ምስጢር ያለው ቀኑ ነው ጌታችን ለምን? አርባ ቀን ጾመ ስንል ከላይ ያየናቸው አበው ነቢያት ብዙውን ጊዜ የጾሙት አርባ ቀን ነው፡፡ ቢቀንስ አጎደለ ከፍ ቢያደርግ አበዛ ብለው አይሁድ የነቢያትን ሕግ አፈረሰ በማለት ትምህርቱ አንቀበልም ባሉ ነበርና ይህን ምክንያት ለመንሳት አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ፡፡ እስራአል 40 ዓመት ተጉዘው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ እናንተም 40 ቀን ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የጥፋት ውኃ በምድር አርባ ቀንና ሌሊት ዘነመ ምድር ነጻች ሰው አርባ ቀንና ሌሊት ቢጾም ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል ሲለን ነው፡፡ ጾም ለርስት ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃ ከኀጢአት የሚያነጻ እንደሆነ ሊያስተምረን በኦሪት በተጾመው ቁጥር ጾሞ ሥርዓትን ሰጠቶናል፡፡

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17

መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡

መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስፈጽመን
                                                                                                          በመ/ር ምሥጢረሥላሴ ማናየ

ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል


   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
 ቀውስጦስ ዘመሐግል ፥ ኢትዮጵያዊ አባቱ ገላውዲዎስ(ዘርዓ ኢየሱስ)
እናቱ እብነ ጽዮን ይባላሉ። በግንቦት 1 ቀን ተወለደ ሲወለደም ይኩኖ አምላክ ተባለ
ሀገሩ ሽዋ መሐግል ይባላል። ሲጠራም ቀውስጦስ ዘመሐግል ተብሎ ይጠራል።
ይህ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት እግዚእ አርያና እብነ ጽዮን ታላቅና ታናሸ ናችው።
ይህ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሙአቸው ከ12 ንብረ ዕድ ወስጥ አንዱ ሲሆን ደብረ ሊባኖስንም የሚያጥንበትም ወር በመጋቢት ወር ነበር።
ቁጥሩም ሲሾምኛ12 ነው ሕዝቡ አጥብቆ የሚወደውና የሚያከበረው አባት ነበር።
ይህንን ጻድቅ አመደ ጽዮን የተባለው ሰው በ11አሽከሮች አስይዞ አብዮ ከተባለው ቦታ ወደ አንሳሮ
አሰወሰደወና ከዚያም ወደ አርሲ ፈነታሌ ተራራ ጫካ ሄዶ 47 ሺህ 300አጋንነትን ከሰማይ እሳታ አውርዶ አቃጥሎአቸዋል በጸሎቱ።ይህ ጻድቅ ልደቱ ከእመቤታችን  ልደት እረፍቱ  ከእመቤታችን እረፍት ጋር ሲሆን እረፍቱም በጥር 21 ቀን ነው።    የጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ በረከት ይደርብን!!!!!

Thursday, February 12, 2015

ታላቁ አባት ቅዱስ ዻውሊ

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
=>አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ:: "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ::
+"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል::
*በእርግጥም ከአንተ 20 ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ
*በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ
*ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኩዋ የማትመጥነው
*በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት
*ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው" ብሎት ተሠወረው::
+ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ:: እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ:: በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)::
*በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው:: ለ80 ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል:: ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ: ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ (ማለትም ሽቻለሁና ላግኝ: ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ)" ሲል አሰምቶ ተናገረ::
+ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው:: መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ:: ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት::
+ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ዻውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር: ይመስገን" ሲል ፈጣሪውን ባረከ:: ቅዱስ ዻውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኩዋን ደህና መጣህ" አለው:: 2ቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ::
+" ቅዱስ ዻውሊ ማን ነው? "+
=>ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት:: ለምሳሌ:-
*የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ
*የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
*የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን እና
*የመጀመሪያውን ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ዻውሊን ማንሳት እንችላለን::
+ቅዱስ ዻውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ: በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው:: ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ:: ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ዼጥሮስን ወልደዋል:: 2ቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው:: ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም::
+ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ዼጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለዻውሎስ (ዻውሊ) መስጠቱ ነበር:: ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ::
+ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ዻውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው:: በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ:: በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል" ሲል ነገረው::
+በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ዻውሊ ሐሳብ ተለወጠ:: ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ:: በመቃብር ሥፍራ ለ3 ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው::
+በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት:: እየጾመ ይጸልይ: ይሰግድ ገባ:: ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት: ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለ80 ዓመታት ኖረ:: (አንዳንድ ምንጮች ግን ለ90 ዓመታት ይላሉ) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በሁዋላ ነው::
+ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የ2 ቀናት ቆይታም ቅዱስ ዻውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል:: በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል::
+ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል:: 80 ዓመት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች::
<< ጻድቅ: ቡሩክ: ቀዳሚው ገዳማዊ: መላእትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ዻውሊ ክብር ይገባል >>
+"+ ገዳማዊ ሕይወት +"+
=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::
+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::
+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::
+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::
+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::
+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::
+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::
=>አምላክ በበረከታቸው ይባርከን::
=>የካቲት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ኁሉ አባት)
2.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ-ግብፅ)
3.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት ጠበቃ)
4.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
5.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ
=>+"+ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: +"+ (ዕብ. 11:35-38)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
writing by dn yordanos abay