Saturday, March 16, 2013

ሰማእት ማርታ


                                                                                        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ሞቤድ ፋርሶች ሶርያን በተቆጣጠሩበት በ4ተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የዞሮአስትራኒዚም እምነት ተከታይና ፈራጅ ዳኛ ነው፡፡ ማርታ ደግሞ እርሱ በዳኝነት በተሰየመባት ከተማ ትኖር የነበረች በጥንታዊያን የሶርያ ክርስቲያኖች ዘንድ “የቃል ኪዳን ልጆች” ተብለው ከሚጠሩት ወገን ነበረች፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለእርሱዋም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰማዕትነት የምትቀበልበት ጊዜው ደርሶ ኖሮ ይህ የከተማዋ ዳኛ ወደ እርሱ አስጠርቶ እንዲህ ብሎ አስጠቅቆ ተናገራት፡-
 “አንቺ ሴት እኔ የምልሽን ብቻ ልብ ብለሽ አድምጪ፤ ምኞትሽን ተከትለሽ እኔ የምልሽን ከመፈጸም እንዳትዘገዪ ተጠንቀቂ፡፡ በእምነትሽ ትኖሪ ዘንድ አልከለክልሽም፤ እምነትሽን በተመለከተ እንደ ፈቃድሽ ማድረግ ትችያለሽ፡፡  ነገር ግን እኔ የማዝሽን ብቻ ፈጽሚ፤ እኔ የምልሽን የፈጸምሽ እንደሆነ ከሞት ቅጣት ትድኛለሽ፡፡ ማርታ ሆይ ይህ “ቃል ኪዳን” የምትይውን የማይረባ ነገርሽን ትተሽ ገና ወጣትና መልከ መልካም ሴት ነሽና ባል ፈልገሽ አግቢ፤ ሴቶች ልጆችንና ወንዶች ልጆችን ወልደሽ ኑሪ” ብሎ አዘዛት፡፡

ጥበብን የተሞላች ማርታም እንዲህ ብላ መለሰችለት “አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ከታጨች በኋላ አንድ ሰው መጥቶ እጮኛዋን ገድሎ የታጨችይቱን ድንግል ሊነጥቅ ወይም ከእጮኛዋ ውጪ ይህቺ ሴት ሌላ ወንድ ልታገባ ሕጉ ይፈቅዳልን? ብላ ጠየቀችው፡፡ ሞቤድም  “አ…ይ በፍጹም!” ብሎ ይመልሳል፡፡ ራሱዋን ለክርስቶስ ያጨች ማርታም “እንዴት ታዲያ አንተ እጮኛዬ ያልሆነውን እንዳገባ ታዘኛለህ፤ እኔ ለአንድ ሰው የታጨው ድንግል ነኝና” አለችው፡፡ ሞቤድም በመገረም “በእርግጥ አንቺ እጮኛ አለሽን? ብሎ ይጠይቃታል፡፡ ክብርት ማርታም “እኔ ለእውነት የታጨው ድንግል ነኝ” ብላ ትመልስለታለች፡፡ እርሱም መልሶ “ለማን?” ብሎ  ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም “እርሱን ታውቀው ዘንድ አንተ የሚገባህ አይደለህም” ብላ ትመልስለታለች፤ “እሺ የት ነው ያለው?” ብሎ መልሶ ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም “ለንግድ እሩቅ ሀገር ሄዷል፤ ነገር ግን የመመለሳሻው ቀን ስለተቃረበ በቅርቡ ይመጣል፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡ ሞቤድም በመልሱዋ በመደነቅ “ስሙ ማን ይባላል? አላት፡፡ እርሱዋም “ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይባላል ብላ መለሰችለት፡፡
ይህን ሁሉ ስትናገር ግን ሞቤድ ስለክርስቶስ እየነገረችው እንደሆነ አላስተዋለም ነበር፡፡ “የት ሀገር ነው ለንግድ የሄደው የሀገሪቱ ከተማስ ማን ትባላለች? ብሎ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ እርሷም “ሀገሩ በሰማያት ነው፤ እርሱ ያለባትም ከተማ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ትባላለች” አለችው፡፡ በዚህን ጊዜ ዞሮአስትራናዊው ሞቤድ ስለጌታችን ስለመድኃኒታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ እየነገረችው እንደሆነ ተረድቶ ልቡ በቁጣ ነደደ፡፡ በቁጣም ገንፍሎ በዙሪያው ላሉት መሰሎቹ “አስቀድሜም እነዚህ ሰዎች ግትሮች ናቸው ብያችሁ ነበር ለእነዚህ ተለሳልሶ መናገር ስንፍና ነው፡፡”ብሎ ከደነፋ በኋላ ወደ እርሱዋ ተመልሶ “አንቺን ከራስሽ እስከ እግር ጥፍርሽ ድረስ በሰይፍ ቆራርጬ ከገደልኩሽ በኋላ ያኔ እጮኛሽ መጥቶ ከትቢያና ከቆሻሻ ውስጥ ፈልጎሽ በማግኘት ያገባሽ እንደሆነ እናያለን” ብሎ ዝቶ ተናገራት፡፡ ማርታም በድፍረት “በእርግጥም እርሱ በታላቅ ክብር ይመጣል፡፡ ለእርሱ የታጩትን ከትቢያ ለይቶ ያስነሣቸዋል፡፡ በሰማያዊ ጠልም ንጹሐን ያደርጋቸዋል፤ የደስታንም ዘይት ይቀባቸዋል፤ የሰርግ ቤቱ ወደሆነችው በሰው እጅ ወዳልተሠራች ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም አስገባቸዋል”ብላ መለሰችለት፡፡ እርሱም አሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ሰውነቱዋን ሁሉ በሰይፍ ቆራርጠው እንዲገድሉዋት ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡ እነርሱም እንደታዘዙት ፈጸሙባት፡፡ እርሱዋም ሰማዕትነት በዚህ ጨካኝ ዳኛ ተቀብላ በሰማያት ወደ ተሰበሰቡት በኩራት ማኅበር ገባች፡፡ እነሆ አሁን በነፍሱዋ የሚወዳትን አምላኩዋን እያመለከች ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከአእላፋት መላእክት፤ ከቅዱሳን ነፍሳት ሁሉ ጋር በፍጹም ደስታና ደኅንነት ትኖራለች፡፡”
ጥያቄው ግን እኛስ ለክርስቶስ የታጨን ደናግላን አይደለንምን? የሚለው ነው፡፡ ጥንቱን መጠመቃችን እንደ አምስቱ ደናግላን መብራታችንን ከዘይታችን ጋር ይዘን ማለትም መልካም ሥራን ከፍቅር ጋር፣ ንጽሕናን ከምጽዋት ጋር አስተባብረን በመያዝ የጌታችንን መምጣት በትጋት እንጠባበቅ ዘንድ አይደለምን?
ቅዱስ ጳውሎስ በትዳር የተሳሰሩ ባልና ሚስት በራሳቸው አካል ላይ ሥልጣን እንደሌላቸው ገልጦ ጽፎልናል፡፡(1ቆሮ.7፡4) በዚህ ምሳሌ እኛም ለክርስቶስ ታጭተናል፡፡(2ቆሮ.11፡2) ስለዚህም ይህ ሐዋርያ “ሥጋ ግን ለጌታ ነው …. ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? ብሎ ተናገረ፡፡ በመሆኑም የኃጢአት ፈቃድ ከውስጣችን መንጭቶ ሊያሳድፈን ሲነሣ ይህ አካል እኮ የኔ አይደለም፤ የብርቱው ንጉሥ የክርስቶስን አካል ነው ብለን የኀጢአትን ፈቃድ ልንቃወም ይገባናል፡፡ በዝሙት ሊያረክሰን የመጣውን ሰውንም ልክ እንደ ማርታ አካላችን የክርስቶስ እንጂ የእኛ እንዳልሆነ ገልጠን እንነገረውና እንደአመጠጡ እንመልሰው፡፡ በእግጥም በዋጋ ተገዝተናልና የእኛ አይደለንም፤ ስለዚህ በሥጋችን እግዚአብሔርን እናክብረው፡፡ (1ቆሮ.6፡13-20)ሁል ጊዜም ለአእምሮአችን ሰውነታችን የእኛ እንዳልሆነ የንጉሥ እልፍኝና የመንፈሱ ቤተ መቅደስ እንደሆነ እንገረው፡፡ ለልጆቻችንም ሰውነታችውን ከኃጢአት እንዲጠብቁ “ሰውነታችሁ የእናንተ እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ ተጠምቃችሁ በሁሉ ሥፍራ ለሚገኘው ለክርስቶስ ሆናችኋልና ጌታ በእናንተ ላይ እንዳይቆጣ ራሳችሁን ከነውር ሁሉ ንጹሐን አድርጉ” ብለን እንምከራቸው፡፡ ሰውነትን የሚያረክሱ ኃጢአቶች ምን ምን እንደሆኑ ገልጠን እናስረዳቸው፡፡
ጌታ ሆይ! ይህን ልዩ የሆነ ክብር ያጎናጸፍከን ላንተ ክብር ይሁን፤ ነገር ግን እኛ በደምህ ዋጅተህ፣ ከጎንህ በፈሰሰው ውኃ አንጽተህ የራስህ ያደረግኸውን ይህን ሥጋችንን በመተላለፋችን አሳደፍነው፡፡ ጌታ ሆይ! ለዚህ መተላለፋችን ይቅር በለን፤ በንስሐ አንጻን፣ ቀድሰንም፤ ዳግም ወደዚህ ታላቅ በደል እንዳንገባ ማስተዋልን አድለን፤ እኛም ስላንተ ያለን መረዳት ታላቅ እንዲሆንልን እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን!!! 

Saturday, March 9, 2013

ጦማችንና ምጽዋታችን ምን ይምሰል (በቅዱስ ኤፍሬም)


                         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ለቅዱስ ኤፍሬምና ለሌሎችም የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ጦም፣ ጸሎት እንዲሁም ምጽዋት ለነፍስ እንደ ብርሃን ናቸው፡፡ ዐይን ያለ ብርሃን ድጋፍ እንደማታይ እንዲሁ ነፍስም ያለእነዚህ ድጋፍ መንፈሳዊውን ዓለም መረዳት አትችልም፡፡ ጌታችንም “እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!”(ማቴ.6፡22)በማለት ብርሃን ያላቸው እነዚህን ነው፡፡ እነዚህን በአግባቡና ከከንቱ ውዳሴ ተጠብቀን የፈጸመናቸው ከሆነ መንፈሳዊ ማስተዋላችን እጅግ የጠለቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ከሰው ክብርን በመሻት የፈጸምናቸው ከሆነ እነዚሁ ራሳቸው መልሰው ያጠፉናል፡፡
እነዚህ በአግባቡ ካልተገለገልንባቸው በኃጢአትችን ላይ ኃጢአትን እንድንጨምር ያደርጉናል፡፡ ስለዚህ በእኛ ያለው ብርሃን (ጦም፣ጸሎት፤ እንዲሁም ምጽዋት) በከንቱ ውዳሴና በሌሎችም ኃጢአት ጨለማ ከሆነ በፊት ከፈጸምናቸው ኃጢአት ጋር ተደምረው እኛን ወደ ጥልቁ ጨለማ ይጥሉናል፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችን “ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ” ማለቱ፡፡ ይህን ድንቅ የሆነ አስተምህሮ እንድታስተውሉትና እኔ በትርጉሙ እንደተደነቅሁ በእናንተም ትደነቁ ዘንድ ቅዱስ ኤፍሬም ወንጌላትን ከተረጎመበት መጽሐፉ ያገኘሁትን ትርጓሜ እነሆ ብያችኋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መጽሐፉን ገዝቶ በመላክ የተባበረኝን ወንደሜን ሙሉጌታ ሙላቱን ከልቤ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡   
ጌታችን ጦማችን ምን መምሰል እንዳለበት ሲያስተምር “እንደ ጦመኛ እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡(ማቴ.6፡18)

የመጀመሪያውና ሁለተኛውን ትርጉም ጌታችን በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ የመጀመሪያው ስትጦሙ ከሰው ዘንድ ክብርንና ምስጋናን እናገኛለን ብላችሁ የምትጦሙ ከሆነ ከአምላክ ዘንድ አንዳች ዋጋ አታገኙም ሲለን ነው፤ ሁለተኛው ትርጉሙ ደግሞ በማይታየው እግዚአብሔር ፊት ጦምን የሚጦም ሰው በስውር የሚያየው አምላኩ በግልጥ ይከፍለዋል ሲለን ነው፡፡ ስለዚህ “አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡ 
እንዲህም ስለሆነ እግዚአብሔር ቃል ይህን ደግ ስጦታውን ትቀበል ዘንድ ጋብዞሃል፡፡ አእምሮህን በእግዚአብሔርዊ እውቀት የቀባኸውና ነፍስህን በንስሐ ውኃ ከኃጢአት ሁሉ ያጠራሃት ከሆነ እግዚአብሔር ለቅዱሳኖቹ ያዘጋጃትን ዐይን ያላያትን ጆሮም ያልሰማትን በረከት ይሰጥሃል፡፡ ስለዚህም በሰውነትህ ሕዋሳቶች ሁሉ ይህን እንደ መመሪያ ተቀበለህ ከነፍስህ ኃጢአትን አስወግድ፡፡ ራስህንም የቅድስናን ዘይት ቀባት፤ እንዲህ በማድረግህ የመሲሕው ክርስቶስ ወዳጅ ትባላለህ፡፡ አስከትሎም ጌታችን፡-
“እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል”(ማቴ.6፡22)አለን፡፡ እንዲህ ሲል ለአንተ ልክ እንደ ዐይኖችህ ብርሃን በሆኑት ጦምህና ምጽዋትህ ከበደልክ፤ በኃጢአትህ ምክንያት ያገኘህ ድንቁርናና አለማስተዋል እጥፍ ይሆንብሃል ሲለን ነው፡፡ ከሰው ምስጋናን ሽተህ የምትጦም ከሆነና የሰው ፊት አይተህ የምታደላ ከሆነ ለነፍስ ዐይን እንደ ብርሃን በሆኑት በጦምህና በምጽዋትህ በበደልከው በደል ምክንያት ከመጀመሪያው ኃጢአትህ ጋር ተደምሮ ቅጣትህን እጥፍ ድርብ ያደርግብሃል፡፡ ሴሰኝነትና እግዚአብሔርን መሳደብ ለከንቱ ውዳሴ ብለን በምንጦመው ጦምና በአድሎ በምንፈጽመው ምጽዋት ምክንያት በእኛ ላይ የሚሰለጥኑብን ኃጢአቶች ናቸው፡፡
 ጦምህና ምጽዋትህ ሁለት ዋጋ አላቸው፡፡ ከሰው ክብርን ሽተህ የምትጦም ከሆነ ኃጢአት በአንተ ላይ እንድትበረታ ደንቁርናህም እጅግ ጽኑ እንዲሆን እወቅ፡፡ ነገር ግን እጆችህን ለተቸገረ ሰው የምትዘረጋ ሕሊናህን ግን ወደ አምላክ የምታነሣ ከሆነ፣ እንዲሁም ስትጦም ጦምህን በእግዚአብሔር ፊት ያደረግህ እንደሆነ ከፈጣሪህ ዘንድ መልካምን ዋጋ ትቀበላለህ፡፡ ይህ ኃይለ ቃል “ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና፡፡”(ማቴ.6፡21) ብሎ ጌታችን ካስተማረው ትምህርት ጋር አንድ  ዓይነት ትርጉም ያለው ነው፡፡
ጦምና ምጽዋታችን በከንቱ ፈቃዳችን ምክንያት ለኃጢአት አሳልፎ እንዳይሰጠንና በደላችንንም እጥፍ ድርብ እንዳያደርግብን አምላካችን ይህን ማስተዋል ዘወትር ይሰጠን ዘንድ በዚህ የጦም ወር እንለምነው፡፡ ለወደደንና  በእኛ ጥቂት ድካም ዘለዓለማዊ ዋጋን ለሚሰጠን ለእርሱ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም  ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

Sunday, March 3, 2013

መልዐኩ ቅዱስ ሩፋኤል



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
“እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና።” ዕብ.፲፫፡፩
ሩፋኤል ማለት ፈታሄ መሕፀን ማለት ነው። ሣልሳይ ሊቀ መላእክት ነው። ለሄኖክ ወልደ ያሬድ 6 ዓመት በእግረ ገነት ወድቆ ሳለ ህበዓቱን ክሡታቱን አሳይቶታል። መ/ሄኖክ 8፡5
ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡ ቤቱንም በበረከት ሞልቶታል።
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች። ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡
የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ‹አባባ የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? ሀገሩን አላውቀውም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያን ‹አብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግ› አለው፡፡
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው ‹የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን ያህል እሰጥሃለሁ› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ‹እሺ ካንተ ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁና› አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም አዛርያስ ይባላል አለው፡፡ ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹አንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝ› ብሎ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡ እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው ፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡

ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚያገለግል ለመረዳት ‹ይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ‹ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል እነግርልሃለሁ› አለው፡፡
ጦብያም ‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ አድናን ‹ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል› አላት ከዚያም ጋር አያይዞ ‹ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነሱም ‹ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን› አሉት፡፡ ‹ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት ‹እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ› አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል ‹የወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ ‹መልአከ ከብካብ› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የ14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡
የ14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያን ‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡
ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2 ፡፡
ጦቢት ከእህሉ ከፍሎ ለተራበ የሚያበላ ከልብሱ ለተራቆተ ሰው የሚያለብስ እግዚአብሔርን ዘወትር የሚያመሰግን ለወገኖቹ የሚራራ አሥራት በኩራት የሚያወጣ ሰው ነበር፡፡ በመሆኑም በሥራው ሁሉ እንዲረዳው በችግሩ ጊዜ እንዲያጸናው ቅዱስ ሩፋኤል ተልኮለታል፡፡ እኛም በሕይወታችን የጐደለብንን ነገር እንዲሞላልን ጐዳናችንን እንዲያስተካክልልን ከክፉ ጋኔን እንዲጠብቀን አምላክ ቅዱስ ሩፋኤል ተለመነን ቅዱስ ሩፋኤልንም አማልደን ማለትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጳጉሜ የዘመን መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ዕለተ ምጽአትም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንሸጋገርባት ስለሆነች ከወዲሁ የቅዱስ ሩፋኤልን የመታሰቢያ በዓሉን ስናከብር በአማላጅነቱ ከቅዱሳን ኅብረት እንዲደምረን በንስሐ ታጥበን ደጅ ልንጠና ይገባል፡፡
የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ምልጃው፣ ጥበቃውና ቃልኪዳኑ ይደረግልን በረከቱ ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
ልመናው ከእኛ ከሀገራችንም ከኢትዮጵያ ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር።
“ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐና እስከ ዛቲ ሰዓት”
ወስብሔት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን ይቆየን።
አዘጋጅ ቤተማርያም