Monday, December 31, 2012

ሰማእት ቅዱስ መርቆሪዮስ

              በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
     ይትባረክ አግዚአብሔር አምላከ አባዊት እስከ ዛቲ ሰዓት አሜን
  “አንሰ ኢይክህዶ ለአግዚአብሔር አምላኪየ /እኔ ጌታዬን አልክድም/  ቅዱስ መርቆሬዎስ በንጉሱ ፊት ሳይፈራ ሳያፍር ከተናገራቸው የተወሰደ።
  “ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዓው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት ተሣሃለነ በከመ ዕበየ ሣህልከ” /ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ። ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ እንደ ይቅርታው ብዛት ይቅር ይበለን።”/ አሜን። (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁጥር ፯)
በዚህ ዕለት ማለትም ህዳር ፳፭ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፈ። አገሩ ሮም አስሌጥስ ነው። አባት እናቱ አረማውያን ነበሩ። ቅዱስ መርቆሬዎስ ከተወለደ በኋላ መልአኩ የተናገረው ቃል ሁሉ እንደተፈጸመ ሲያውቅ አባቱ ከነ ቤተሰቡ አምነው ተጠምቀዋል። የመርቆሬዎስ ስመ ጥምቀቱ “ፕሉፖዴር” ነው፤ ገብረ እግዚአብሔር ማለት ነው። በጥበብ በፈሪሀ እግዚአብሔር አድጎ አባቱ ሲሞት የአባቱን ሹመት ወረሰ።
 ንጉሱ ዳኬዎስ ይባላል። መምለኬ ጣዖት ነበር። በርበሮች በጠላትነት ተነስተውበት እንደምን ላድርግ ብሎ የምክር ቃል ሲልክበት መልአኩ በአምሳለ ወሬዛ ቀይህ በሊህ ሰይፍ ይዞ በዚህ ጠላቶችህን ድል ትነሳለህ ደስ ብሎህ በተመለስክ ጊዜ ግን ጌታህ እግዚአብሔርን አስበው ሲለው ታይቶት ነበርና አትፍራ ጌታ ጠላቶቻችንን አሳልፎ ይሰጠናል ብሎት አጽናንቶት ዘመቱ። መርቆሬዎስም ኃይል ተሰጥቶት ጠላቱን ድል ነስቶ ሲመለስ ከሃዲው ንጉስ ኡልያኖስ ወዲያው ኃይል ለሰጡን ለረዱን ለዓማልክቶቼ በዓል አድርጌአለሁና ፈጥነህ ና ብሎ ላከበት። ሄዶ ሹመት ሽልማትህ ላንተ ይሁን “አንሰ ኢይክህዶ ለአግዚአብሔር አምላኪየ /እኔ ጌታዬን አልክድም/ ላቆመው ጣኦት አልሰግድም በማለቱ የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችለውን መከራ ተቀበለ። በመጨረሻም ህዳር ፳፭ በዛሬዋ ቀን አንገቱን ቆርጠው ገደሉት ደም ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሰሰ። †††መርቆሬዎስ ከዕረፍቱም በኋላ ብዙ ተአምራትን አድርጓል፤ ፈረሱ ለሰባት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፤ በኋላም አንገቱን ቆርጠው ገድለውታል እንዴት ብሎ የሚገረም የበልአምን አህያ ይጠይቃት፤ እኛስ እስመ አልቦ ነገር ዘይሳኣኖ ለእግዚያብሔር ብለን እንመልሳለን:: ዘኁልቁ 22፡28
የቅዱስ መርቆሬዎስ ስዕልም በአዎንታ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ምስክርነት ሰጥቷል። ይህም ሊታወቅ ዛሬ በሀገራችን በምድረ ተጉለት በስሙ ከታነጸ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ደነነ ስዕሉ እያሉ ሲዘምሩ ጎንበስ ቀና ሲሉ እንደሚታይ ይነገራል።

የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስ ረድኤቱ በረከቱ አማላጅነቱ ቃል ኪዳኑ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
  እኔን የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሌንም ተሸክሞ ዕለት ዕለት ይከተለኝ…. ማቴ.፲፡፴፰-፵
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። (ዕብ ፲፪፡፩¬-፪)
ይትባረክ አምላከ አባዊነ ይቆየን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Wednesday, December 26, 2012

ሊቀ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤል

         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 ለአናንያ ወአዛርያ ወሚሳኤል /፪/
ውእቱ ያድኅነነ ወሚሳኤል ውእቱ ያድኅነነ/፪/

ትርጉም ፡- አናንያን አዛርያን ሚሳኤልን እንዳዳናቸው እኛንም ያድነን፡፡

ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም አነሣሁ” አለና አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኃይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኃይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” አለ፡፡(ዳን.10፥5-9) ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡

ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች” አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ”(ዳን.10፥13) ብሎ በተናገረው ንግግሩ በመላእክት ላይ የተሾሙ ሌሎች አለቆች እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቅዱሳን መላእክት ዘንድ ስላሉት ነገዶች ሲገልጽ “… በሰማይ ያለውን በምደር ያለውን የሚታየውንና የማይታየውን መናብርትም ቢሆኑ አጋእዝትም ቢሆኑ መኳንንትም ቢሆኑ ቀደምትም ቢሆኑ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ” (ቈላ.1፥16) በማለት ይዘረዝራቸዋል፡፡ ከዚህ ተነሥተን መላእክት በተለያዩ ዐበይት ነገዶች የተከፈሉና ለእያንዳንዱም ነገድ የራሱ የሆነ አለቃ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚህ ዐበይት የመላእክት ነገዶች መካከል አንዱ በሆነው አርባብ በሚባለው ዐቢይ ነገድ ላይ የተሾመ ሲሆን ከ100ው ነገደ መላእክት መካከል ከበታቹ የሚመራቸው ዐሥር ነገደ መላእክት አሉት፤ ከተማቸውም በሰማየ ራማ ነው፡፡
ቅዱሳን መላእክት በቅዱስ ሚካኤል ፊት አውራሪነት የሰው ልጆች ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ተዋግተው ድል ከመንሳታቸው አስቀድሞ ቅዱስ ገብርኤል፣ እንደ አምላክ ሊመለክ የወደደውን ሳጥናኤልን በመቃወም ‹‹ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ - “አይዞአችሁ ፈጣሪያችን ፈጥሮ አይጥለንምና አስክናገኘው፣ እስክናውቀው ድረስ በያለንበት እንቁም፡፡” (አክሲማሮስ ገጽ.35)በማለት መላእክትን ያረጋጋ መልአክ ነው፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ የፋርስ ባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን ሁሉ ሲያስገዛለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም አወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም የሚቃወመኝም የለም፡፡”(ኢሳ.10፥13-14) ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ ዱራ(አዱራን) በሚባል ስፍራ ላይ አቆመው፡፡ በግዛቱ በልዩ ልዩ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉትን ሹማምንቱንና ገዢዎችን ሰበሰባቸው፤ “የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሥ ናብከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፡፡ ወድቆም ለማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣል” ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን አዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ የመለከቱና የእንቢልታው እንዲህም የዘፈን ድምፅ በተሰማ ጊዜ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡

በባቢሎን አውራጃዎች ላይ የተሾሙ አናንያና(ሚሳቅ)፣ አዛርያ(ሲድራቅ) እና ሚሳኤል(አብደናጎ) ግን ንጉሥ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡ ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ነገሩት፤ ንጉሥም እጅግ ተቆጥቶ ወደ እርሱ አስጠራቸው፡፡ እርሱ ላቆመው ለወርቅ ምስል ያልሰገዱ እንደሆነ እጅና እግራቸውን ታስረው ወደ እቶን እሳቱ እንደሚጣሉ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ግን “ናብከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፣ ከሚነደውም ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን (የእግዚአብሔር ፈቃዱ በእሳት ውስጥ ሰማዕትነትን እንድንቀበል እንኳን ቢሆን) አማልክትህን አንዳናመልክ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳማንሰግድለት  እወቅ” ብለው መለሱለት፡፡ የንጉሥ ናብከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ፥ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእነ ማዕረግ ልብሳቸው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው ትእዛዝን አስተላለፈ፡፡ ትእዛዙ አስቸኳይ ነበርና እነርሱን ወደ እሳቱ የጣሏቸውም ኃያላን በእሳቱ ወላፈን ተገርፈው ሞቱ፡፡ እንዲህ ሲሆን ሳለ ግን ሠለስቱ ደቂቅ ወደ አምላካቸው “በፍጹም ልባችን እናምንሃለን፣ እንፈራሃለን፣ አታሳፍረን እንጂ ገጸ ረድኤትህንም እንፈልጋለን፡፡” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታቸውን ተቀበለ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም እስራታቸውን ፈታ፤ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅም መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ስምህም ለዘለዓለም የተመሰገነና የከበረ ነው” በማለት አመሰገኑት፡፡

ንጉሥ ናብከደነፆርም ሠለስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ከእነርሱ ጋር የሰው መልክ ያለው ነገር ግን አምላክን የሚመስል መልአክ ተመለከተ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን ፊቱን ጸፍቶ አፉን ከፍቶ “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን”(ዮሐ.11፥49) ብሎ እንዳናገረው እንዲሁ ናብከደነፆርንም “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ እንዲናገር አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅን መልክ ያለው በኋላም መልአክ ብሎ የተናገረለት ቅዱስ ገብርኤልን ነበር፡፡ እርሱ ስለመሆኑ ለነቢዩ ዳንኤል በተገለጠበት ግርማ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ናብከደነፆርም ወደ እሳቱ እቶን በመቅረብ እነዚህ ብላቴኖችን “እናንተ የልዑል አምላክ ባሮች ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው፡፡” እነርሱም ከእሳቱ ወጡ ሹማምንቱና መኳንንቱ፣ አማካሪዎችና የአገር ገዢዎች ሁሉ እሳቱ በእነዚህ ብላቴኖች ላይ አንዳች አቅም እንዳልነበረው፣ ከጠጉራቸው ቅንጣት አንዱን እንኳ እንዳላቃጠለው፣ ሰናፊናቸውም እንዳልተለወጠ፣ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ፡፡ ንጉሥ ናብከደነፆርም መልአኩን ልኮ ያዳናቸውን የእነዚህን ቅዱሳንን አምላክ አመሰገነ፡፡ በእነርሱ አምላክ ላይም የስድብን ቃል የሚናገር ሰው እንደሚገደልና ቤቱም የጉድፍ መጣያ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ፡፡ አናንያ አዛርያ ሚሳኤልም በንጉሡና በሹማምነቱ ዘንድ ሞገስ አገኙ በክብርም ከፍ ከፍ አሉ፡፡(ዳን.3 በሙሉ)

ስለዚህም ቤተ ክስርቲያን መንጎቿ የእምነትን ፍሬ ከእነዚህ ብላቴኖች ተምረው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑና የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት እንዲረዱ በታኅሣሥ 19 ቀን ይህን ዕለት ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነት በድርጊት ሊታይ የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምናለሁ የሚል ሁሉ ካመነበት ጊዜ አንስቶ ክርስቶስን መስሎ ለመኖር ሊተጋና መስሎ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ በሠለስቱ ደቂቅ የታየው እምነት በአንድ ጀምበር የተገነባ እምነት ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ በአንድ እግዚአብሔር ታምነው በቅድስና ሕይወት በመመላለስ የመጣ እምነት ነው፡፡ እነዚህ ብላቴኖች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን የድል አክሊል ተስፋ አድርገዋልና፥ አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል የነደደውን የእሳት እቶን አላስፈራቸውም፤ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት በእሳት ተቃጥለው ለመሞት እንኳ አስጨከናቸው፡፡ እንዲህም ሆነው በመገኘታቸው በእምነታቸው እግዚአብሔርን ደስ አሰኙት፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ባለሟሉን ቅዱስ ገብርኤልን በመላክ ከእሳቱ እቶን ታደጋቸው፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ እምነት ኃጢአት በነገሰበት በአሁኑዋ ዓለም በእኛ ክርስቲያኖች ላይ ሊታይ የሚገባው እምነት ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚመጣውነ መቅሰፍት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት እንደሚያጠፋልን በእግዚአብሔር ታምነን በእምነት ኃጢአትን ልንቃወመው ይገባናል፡፡ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ጸሎት ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

አቡነ ተክለሀይማኖት

            በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
   እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በፍርኩታ በምድር ጕድጓድም ተቅበዘበዙ። ዕብ.11፡33-40
ስለ አምላካቸውም ሲሉ ሁሉን ትተው፣ ሁሉን ንቀው አምላካቸውን እንደተከተሉ መጽሐፍ ቅዱሳችን ያስረዳል።
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።(ማቴ.16፡25-27
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ስለቅዱሳኑ ሲናገር፤ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው።” ይላል። መዝ. 67/68፡35
ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ፣ እንዲሁም የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው ይጠግባሉና፣ መጽናናትንም ያገኛሉና…+++ ጌታ በተራራ ስብከቱ ከተናገራቸው፣ ካስተማራቸው የሕይወት ምግብ የሆነ ቃሉ በማቴ.5፡1-ፍጻሜ
እግዚአብሔር አምላካችን ሰማዕታትን በደም፤ ቅዱሳንን በገዳም፤ ሐዋርያትን በአጽናፈ ዓለም፤ መላእክትን በአጽራርያም እንዳጸናቸው እኛ ሁላችንንም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችን በቅድስት ቤተክርስቲያን በበጎ ምግባር በጾም በጸሎትና በትሩፋት ያጽናን ስለ አባታችን ተክለሀይማኖት ታሪክ ትንሽ ልበል

      አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡

በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡

አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ «አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡» /ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫/
ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-
«እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
«ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
«የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን ፥ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
«ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
«ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡

በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ። በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡
ሰላም ለዝክረ ስምከ በጥንተ ፊደሉ መስቀል ስም ክቡር ወስም ልዑል።
ተክለሃማኖት ማቴዎስ በዓለ ቀዳማይ ወንጌል
ከመ እወድሰከ መጠነ አውሥኦተ እክል።
ማዕሠረ ልሳንየ ትፍታሕ ማርያም ድንግል።

ትርጉም ‹‹ የስምህ መነሻ ፊደል የመስቀል ምልክት ለሆነው እና ክቡር ገናና ለሆነው ስም አጠራርህ ሰላም እላለው ። የወንጌል ተቀዳሚ ስም ማቴዎስ የተባልክ ተክለሃይማኖት ሆይ እንደ ችሎታዬ አመሰግንህ ዘንድ አንደበቴ ትፈታልኝ ዘንድ ድንግል ማርያምን እማልዳለሁ።››

የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖትን ታሪክ በዘመን እየከፈልን ባጭሩ ስንመለከተው ደግሞ፡-
የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት አባት ቅዱስ ፀጋዘአብ በሸዋ ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህን ነበሩ፡፡ መጋቢት 24 ቀን አባታችን ተክለሃይማኖት ተፀነሱ በታህሣስ 24 ቀን በ1190 ዓ.ም አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከእናታቸው ከቅድስት እግዚሐሪያ እና ከአባታቸው ከቅዱስ ፀጋዘአብ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በ3ኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመሠገኑ፡፡ በተወለዱ በ40ኛው ቀን ክርስትናን በመነሳት ፍስሐ ጽዮን “የጽዮን ደስታ” ተበለው ተጠሩ፡፡ አባታችን 7 ዓመት እስከሞላቸው ድረስ ከአባታቸው ከፀጋዘአብ ዘንድ እየተማሩ አደጉ፡፡ አባታችን በ15 ዓመታቸው ዲቁናን ከጌርሎስ ዘንድ ተቀበሉ፡፡ አባታችን በ22 ዓመታቸው ከአቡነ ጌርሎስ ዘንድ ቅስናን ተቀበሉ፡፡ በከተታ አውራጃ 3 ዓመት ወንጌልን እያስተማሩ ብዙ ድንቅ ነገርን አደረጉ፡፡ አባታችን በዳዊት ፀሎት ከነቢያት ምስጋና ሌሊቱን ሙሉ ይተጉ ነበር በያንዳንዱ መዝሙርም 10፣ 10 ስግደትን ይሰግዱ ነበር፡፡ በሕዳር 24 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ወደ ላይ ነጠቃቸው (አወጣቸው) ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር 25ኛ ካህን ሆነው የሥላሴን መንበረን “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አጥነዋል፡፡ በሐይቅ 10 ዓመት በደብረዳሞ 12 ዓመት ኖረዋል፡፡ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በ1267 ዓ.ም ደብረ ሊባኖስን በአት አድርገው ኖሩ፡፡ ለ22 ዓመት ቆመው በመፀለይ የአንድ እግራቸው አገዳ ተሠበረ ደቀ መዝሙሮቻቸው በጨርቅ ጠቅልለው ቀበሩት፡፡ በአንድ እግራቸው ለ7 ዓመት በፀሎት ቆሙ በጠቅላላው ለ29 ዓመት በፀሎት ከቆሙ በኋላ በ99 ዓመት ከ10 ወር ከ10 ቀን ነሐሴ 24 ቀን 1290 ዓ.ም አረፉ አባታችን ባረፉ 54 ዓመታቸው በ1354 ዓ.ም ለአባታችን ለአቡነ እዝቅያስ ተገልጸው አጽማቸው ከደብረ አስቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ ግንቦት 12 ቀን እንዲፈልስ አድርገዋል፡፡

ህዳር 24 ቀን 25ተኛ ካህናተ ሰማይ ሆነው በሠማይ የሥላሴን መንበር ያጠኑበት
ታህሳስ 24 ቀን የአባታችን ልደት
ጥር 24 ቀን የአባታችን ስባረ አጽም
መጋቢት 24 ቀን የአባታችን ጽንሠት
ግንቦት 12 ቀን የአባታችን ፍልሰተ አጽም
ነሐሴ 24 ቀን የአባታችን እረፍት
የአባታችን ቡራኬ ይድረሰን አሜን!
“ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኩሴ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ እርስ በእርሳችሁም ተዋደዱ ትዕዛዛቱንም ጠብቁ” የሐዲስ ኪዳኑ ሙሴ የአባታችን የተክለሃይማኖት ምክር

በደብረ አሚን ከሚገኘው ገድላቸው ደግሞ ባጭሩ፡-

የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው መ ምሳሌ 10፡ 7

የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው እንዳሉ ነቢያት እኛም ነብያትን ሐዋርያትን ጻድቃንን ሰማእታትን አክብረን ብንቀበላቸው በረከተ ስጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት መሆኑንን በማሰብ ከጻድቃን መካከል አንዱ የሆኑትን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ተጋድ
ሎ በትንሹ እንመልከት::አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላሎሽ ወይም ዞረሬ ቅዱድ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ክልል ከአባታቸው ከጸጋዘአብ ከእናታቸው ከእግዟእኅረያ ታኅሣሥ 24 ተወለዱ ::በወላጅ አባታቸው በካህኑ ጸጋዘአብ ግብረ ዲቁናን ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው ቄርሎስ ከተባሉት ግብጻዊ ጳጳስ በ15 አመታቸው ዲቁናን ተቀበሉ::እንዲሁም እድሜያቸው 22 አመት ሲሆን ከላይ ስማቸው ከተገለጹት ጳጳስ የቅስናን ማዕረግ ተቀበሉ ከዚህ በኋላ ለህዝቡ ወንጌል እየሰበኩ ጣዖት አጋንንትን እያደቀቁ ህዝቡን አምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰው አባኢየሱስ ሞዓ ወደ ሚገኙበት ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ሃይቁን በእግራቸው እንደ ደረቅ መሬት በመርገጥ ወደ ደሴቱ በመግባት የምንኩስናን በመቀጠል ከአባ ኢየሱስ ሞዓ እጅም የምንኩስናን ቀሚስ የንጽህናን ምልክት ተቀብለው ለ12 ዓመታት አቡነ አረጋዊ ወዳቀኑበት ገዳም ደብረ ዳሞ በመግባት በጊዜው ከነበሩት አበምኔት ከአባ ዮሐኒ ቆብና አስኬማ ተቀብለው በገድል በቱሩፋት መንፈሳዊ ተጋድሎዋቸውን ቀጠሉ::ከዚህ ሁሉ በኋላ በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት ስምንት ጦሮችን ሁለቱን በፊት ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ ሁለቱን በግራ አስተክለው እጆቻቸውን በትምህርተ መስቀል አምሳል በመዘርጋት የክርስቶስን ህማምና ሞት ነገረ መስቀሉን በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም በጸሎት በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ ከቁመት ብዛት የተነሳ ጥር 24 ቀን የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች እግራቸው እስኪሰበር በጸሎት የቆዩባቸው አመታት 22 ናቸው ::በመአልትና በሌሊት በትጋትና በቁመት በተጋድሎ ብዛት አንዲት የእግራቸው አገዳ ስትሰበር ዕድሜያቸው 92 አመት ሆኖ ነበር::ከዚህ በኋላ ለ7 አመታት በአንድ እግራቸው ብቻ በመቆም ያለ ምግብ ሌትም ቀን ምእንቅልፍ በአይናቸው ሳይዞር እንደ ምሰሶ ጸንተው በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነት ሲለምኑ ኖረዋል ::በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ::
የአባታችን የአቡነ ተክለ ሀይማኖት ምልጃና ጸሎታቸው ረድዔትና በረከታቸው በኛ በልጆቻቸው ላይ ይደርብን አሜን!

 ምንጭ ታምረ ተክለሐይማኖት ዘደብረ አሚን

 የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Saturday, December 22, 2012

ሐዋሪያዊው ቅዱስ እንድሪያስ ሰማእትነት


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 ታኅሣሥ ፬ ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ (በዚህ ዕለት የተመሰገነ ቅዱስ እንድርያስ በሰማዕትነት አረፈ።)
  “አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር ግብረ እደ እጓለ እመሕያው”
 ቁጥሩ ከ12ቱ ሐዋርያት ነው:: የሊቀ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ነው::
እንድርያስ ማለት ጽኑዕ በኩር ማለት ነው። የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ነው።
"በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም፡- በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።" ማቴ.፬፡፲፰ እንዲል እንዲል ወንጌል
ዓለምን ዞረው ለማስተማር ዕጣ ሲያወጡ ለሐዋርያው እንድርያስ ልዳ ደረሰው። ልዳ ማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ አገር ናት። ከሰባ ሁለቱ አንዱ ፊሊሞናን አስከትሎ ሲሄድ ከቤተ ጣዖት ደረሰ። ፊሊሞና ድምጻዊ ነበር። ሊያስተምር ወደዚያች አገር ገባ፤ “አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር ግብረ እደ እጓለ እመሕያው” እያለ ሲያስተምር አህዛብ ተሰበሰቡለት። አስተምሮ አሳምኗቸዋል። ልድያ የምትባል ሴትም ከሞተች በኋላ አስነስቷል። ከዚህ በኋላ ምዕማናንን ከገቢረ ጽድቅ ወደ ገቢረ ኃጢአት እንዳይመለሱ የሚመክሩ የሚያስተምሩ መምህራንን ካህናትን ሾሞላቸዋል።መካነ ጸሎት ሰጥቷቸው ወንጌል ካልደረሰበት ለማዳረስ እስከ ሀገረ በላዕተ ሰብእ ድረስ ሄዶ አስተምሯል። ጽኑዕ መባሉ ቅሉ ስለዚህ ነው። ከላይ በስዕሉ ላይ እንደምታዩት ያረፈው በመስቀል ተሰቅሎ ነው። ብዙዎች ትምህርቱን ሰምተው ተዓምሩን አይተው አምነው ተጠምቀዋል። ነቢያተ ሐሰት ካህናተ ጣኦት ጥቅም የሚቀርባቸው ሲሆን ኃያላኑን ሰብስበው ዋጋችሁን እንሰጣችኋለን ሐዋርያው እንድርያስን አጥፋልን አሉት ሲያስተምርም አገኙት፤ ለመግደል ሄደው በዚያው አምነውም ቀርተዋል። እነዚያም ካህናት ወይ ከገንዘባችን ወይ ከሕዝባችን አልሆን ብለው ሾተል ይዘው ወጡ፤ ሐዋርያው እንድርያስ ግን ከፍ ካለ ቦታ ላይ ቆሞ እንዲህ ሲል ሰበከ። "የአህዛብ ጣኦታት የሰው እጅ ስራ ናቸው ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸቱም፤ እጅ አላቸው አይዳስሱም፤ እግር አላቸው አይሄዱም በጉሮሮአቸውም አይናገሩም የሚሰሯቸው የሚያምኑባቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሆናሉ፤ መዳን በእግዚአብሔር ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እያለ ሰበከ።” ከቃሉ ጣዕም ከአንደበቱን ቅልጥፍና ከነገሩ ማማር የተነሳ የወገባቸው ትጥቅ ተፈታ ሾተላቸውን ጣሉ፤ በጌታችን አምነው ተጠመቁ።
የሐዋርያው እና የሰማዕቱ የቅዱስ እንድርያስ ረድኤት በረከቱ ምልጃና ጸሎቱ ከሁላችን ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር።
ፀሐፊ ቤተማርያም
ዋቢ መጽሐፍት መዝገበ ታሪክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን አሜን።

Friday, December 21, 2012

ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ

           በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ዮሐንስ ማለት ፍሰሓ ወሐሴት ሠላም ርህራሄ ወሳህል ማለት ነው። ወልደ ነጎድጓድ፣ አቡቀለምሲስ፣ ነባቤ መለኮት፣ ታዖሎጎስ ይለዋል፡፡ “ቃዳሚሁ ቃል ውእቱ” ብሎ ምስጢረ ሥላሴን አምልቶ አስፍቶ ይናገራልና፡፡ ፍቁረ እግዚእ ይለዋል፡፡ “ዝኩ ካልዕ ረድዕ ዘያፈቅሮ እግዚእ ኢየሱስ” ይለዋልና፡፡ ዮሐንስ 21፡7 መውደድንስ ሁሉንም ይወዳቸው የለምን ቢሉ የርሱ የተለየ ነውና፡፡ ከቶማስም የሱ መወደድ ይበልጣል፡፡ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን ቢዳስሰው እጁ ከእሳት እንደገባ ጅማት ተኮማትሯል፡፡ እርሱን ግን በከናፍሩ ቢስመው በጭኑ ቢያስቀምጠው ምንም ምን አልሆነም ::
  ንጹህ ወድንግል ይለዋል፡፡ ጌታን ከመውደዱ የተነሳ ጌታም እናቱን እነዃት እናትህ ሲል ድንግል ማርያምን በሱ በኩል ተሰታናለች፡፡ እኛም ዛሬ ልጆቿ ነንና ደስ ይበለን ይበላችሁ የድንግል ማርያም የአስራት፣ የተስፋና የስስት ልጆች፡፡ ዮሐንስ 19፡26፡፡ ዮሐንስ ሀገሩ ገሊላ አውራጃ ሲሆን ከታላቅ ወንድሙ ከያዕቆብና ከአባቱ ከዘብድዮስ ጋር ዓሣ እያጠመደ ይኖር ነበር። እናቱ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ስትሆን ማርያም ትባላለች።

     ዮሐንስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን በሕይትም በኑሮም ጌታ ስለሚመስል (ፍቁረ እግዚእ) ይባለል። ነገረ መለኮትን በበለጠ ከሌሎች አምልቶ አስቶ በጥልቀት በማስተማሩ ነባቤ መለኮት (ታዖሎጎስ)ተሰኝቷል። ስለጌታም ባለው ቅናት ባሳየው የሀይል ሥራ በኦኔርጌስ (ወልደ ነጎድጓድም) ተብሏል። ፍጥሞ በምትባል ደሴት በራዕይ መጻእያትን በመግለጡ ባለራዕይ (በግሪክ አቡቀለምሲስ) ይባለል። በዕለተ ዓርብ በመስቀል ሥር ተገኝቶ የጌታን መከራ መስቀል በማየቱ ፊቱ በሀዘን ስለተቋጠረ ቁጽረ ገጽ (ፊቱ በሀዘነ የተቋጠረ) ስምም ተሰቶታል። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የፋሲካን እራት ያዘጋጀ አንካሳን የፈወሰ ታለቅ ሐዋርያ ነው። (ሊቃስ 22፡8) እስከ መስቀል አምላኩን ተከትሎ እመቤታችንን በአደራ የተረከበ ባለአደራ ሐዋርያ ሲሆን ከጰራቅሊጦስ በዓል በኋላ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋራ በኢየሩሳሌም በአንጾኪያ በሎዶቅያ በእስያ ከተሞች በተለይ በኤፌሶን በአሁኑ ቱርክ አስተምሯል። (ዮሐ.19፡26) በወጣትነት ዕድሜው ተጠርቶ በዕለተ ዓርብ የጌታን መከራ እያሰበ ያነባ የነበረ በፍቅር በታማኝነት እስከመጨረሻ ድረስ የጸና ከጌታ ያልተለየ ወንጌላዊ ሲሆን ወንጌልን ጨምሮ 3 መልዕክታትን የጻፈ እንዲሁም በበፍጥሞ ደሴት ራዕይ የጻፈ ታላቅ ሐዋርያ ነው።
ከወንጌላዊው፣ ከሐዋርያው፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ረድኤትና በረከት ይክፈለን አሜን። !!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን አሜን።

Thursday, December 13, 2012

አባ አጋቶን እና አባ መቃርዮስን

አባ መቃሪዮስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

 “በኢሩቤል ላይ የምትኖር  የቀለያትንም (ጥልቅ ባሕርንም) ጥልቀት የምትመለከት ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ አቤቱ ስለቅዱሳን ሁሉ ብለህ ማረን ይቅርም በለን ደግ ሰው አልቆአልና አሜን።” ይህ የቅዱሳን ሁሉ ልመና ነው።
በመስከረም  14 የሚዘከሩ ቅዱሳን አባቶች
የአባ አጋቶን እና የአባ መቃርዮስን መታሰቢያ በዓላቸዉን ትዘክራለች።
    “ቅዱሳን በመለኮታዊ ማዕጠንት የተቀጣጠሉ ዕጣን ሲሆኑ የተቀጣጠሉበትም በፈጣሪያቸው ፍቅር ነው።” (ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)
    “የቅዱሳን ሕይወት ተርታ ታሪክ ወይም ተረት አይደለም፤ ይልቁንስ እግዚአብሔርን የሚከተሉና በሥራቸው ሁሉ የእርሱ ጥበቃ ያልተለያቸው ሰዎች ታሪክ ነው።” (ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)
    ቅዱስ ማለት በግእዝ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ንዑድ፣ ክቡር፣ ልዩ መሆን ማለት ነው።
    ይህ ቃል ለእግዚአብሔር የባሕርዩ መገለጫ ነው፤ እግዚአብሔር በባሕርይው ቅዱስ ነውና። በባሕርዩ ቅዱስ የሆነውን አምላክ የሚያገለግሉ 
መላእክትንና ደጋግ ሰዎች የስሙ ቀዳሾች የክብሩ ወራሾች ናቸውና ቅዱሳን ይባላሉ። ቅዱሳን አካሄዳቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ፤ ሕጉን የጠበቁ ያስጠበቁ፣በሕጉ ከታዘዘውም በላይ በገድል በትሩፋት ጸንተው የኖሩ ናቸው። ስለ ቅዱስ ሥራቸው እግዚአብሔር በቅድስና ያከበራቸው ናቸው። ልዑል እግዚአብሔር በአራያው ፈጠረን ሲባል ቅሉ እርሱ ቅዱስ ተብሎ እኛን ቅዱሳን እርሱ ጻድቅ ተብሎ እኛን ጻድቃን እንዳሰኘን ማለታችን መሆኑ እርግጥ ነው። ስለ ቅዱሳን መናገር መመስከር ደግሞ ስለ ቀደሳቸው እግዚአብሔር መመስከር መናገር ነው።
    መቼም ያልተማረ ካልሆነ በስተቀር ቅዱሳን ፍጡራን መሆናቸውን የማያውቅ ማንም የለም፤ ከፍጡራን የሚለያቸው ግን በሃይማኖታቸው በበጎ ምግባራቸው በእግዚአብሔር ፊት ያገኙት ሞገስ ነው።
    ቅዱሳን ስንል እንደየቅድስናቸው ቅዱሳን ነብያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ጻድቃን፣ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን አበው፣ ቅዱሳን ነገስታት፣ ቅዱሳን ሊቃውንት፣ ቅዱሳን ጳጳሳት፣ ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል)፣ ቅዱሳት አንስት፣ ቅዱሳን መላእክት፣ መካናት፣ መጽሐፍት፣ ናቸው። ከነዚህ ደግሞ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በዛሬዋ ዕለት መታሰቢያቸው ከሚዘከርላቸው ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል) ውስጥ አባ አጋቶንና አባ መቃርዮስ ባጭሩ እንመልከት።

   አባ አጋቶንን ያስተማረዉና ያሳደገዉ አባ ጴሜን ነዉ፡፡ በመቀጠልም ከአባ እስክንድር ጋር በአስቄጥስ ገዳም ኖሯል፡፡ አንድ ጊዜ አንድ አባት ወደ ኣባ አጋቶን ገዳም ሄዶ …… ”ከወንድሞች ጋር መኖር እሻ ነበር እስቲ ምከረኝ አለዉ”…….አባ አጋቶንም “በኑሮህ ሁሉ የእንግዳ ሰዉ ዓይነት ልቡና ይኑርህ፣ ልክ በመጀመሪያ ያገኘሃቸዉ ቀን የምትሆነዉን ዓይነት፤ በጣምም አትቅረባቸዉ በጣምም አትራቃቸዉ…..”አለዉ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርዮስ “ይህ መቀራረብ ምን ያስከትላል?” ሲል ጠየቀዉ፡፡ አባ አጋቶንም

    “ያማ እንደ ኃይለኛ ዐዉሎ ነፋስ ያለ ነዉ ሊንሳፈፍ የሚችለዉን ሁሉ እያነሳ የዛፎችን ፍሬ ያበላሸዋል፡፡” አባ መቃርዮስም “ያለ መጠን መናገር ይህን ያህል ይጎዳል። “እንዴት ሲል ጠየቀዉ”….አባ አጋቶንም “የማይቆጣጠሩትን ምላስ ያህል መጥፎ ጾር የለም ፣እርሷ የፈተናዎች ሁሉ እናት ናት፡፡” አለዉ…. “ጠንካራ መነኩሴ ማለት ተዋጊ ነዉ ብሎ መክሮአቸዋል፡፡”

   አባ መቃርዮስ ታላቁ የተወለደዉ በ፫፻ ዓ.ም በንስጥራ አካባቢ ነዉ፡፡ በገዳመ አስቄጥስ የምንኩስና ሕይወትን ካደራጁ አበዉ አንዱ ነዉ፡፡ ከአባ እንጦንስ አባ ጳውሊ ጋር በ፫ኛ ደረጃ ላይ ያለ ታላቅ አበ መነኮሳት ከሆኑት አንዱ እሳቸው ናቸው።
    ታድያ ቅዱሳን መነኮሳት መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለምና ከተድላ ዓለም ተለይቶ ቤት ልስራ፣ ዘር ልዝራ፣ ሳይሉ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ በየዋሻው በየገደሉ፣ በየገዳማቱ ጸንተው የኖሩ ናቸው። ለዚህም ነው ቅዱ ጳውሎስ “ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።” በማለት ዕብ.፲፩፡፴፰ ላይ የተናገረው።
የሰው ልጆች ፪ (ሁለት) አማራጮች ብቻ አላቸው። ወይ አግብተው በጋብቻ ሕግ መኖር፤ አለያ መንኩሶ በምንኩስና ሕይወት ይኖራል። ከዚህ የተለየ ሕይወት የለም።
    “ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው።” ፩ቆሮ.፯፡፯
    ”ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው። ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።” (፩ቆሮ.፯፡፩-፪)
     “እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።” (፩ቆሮ.፯፡፰-፱) ብርሃነ ዓለም ቅ/ጳውሎስ ይህን ሁሉ ሲናገር የጋብቻን ቅድስናንም ሳይናገር አላለፈም “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።” ዕብ.፲፫፡፬
እሱ ባስጓዘን መንገድ እንድንጓዝ መድኃኔአለም ይርዳን አሜን።
የቅዱሳን ሁሉ በረከትና ርድኤታቸው አይለየን አሜን።

       ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡ እድሜ ለንሰሐ ዘመን ለፍሰሃ ሰጥቶኝ ይህችን ታህል ስለ አባታችን እንድመሰክር የረደኝ አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
    አመስግኛት የማልሰለች፣ ስለሷ ተናግሬ የማይደክመኝ፣ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Tuesday, December 11, 2012

s.t Phanourius

    We know nothing for certain about the background of St Phanourius, nor exactly when he lived. Tradition says that when the island of Rhodes had been conquered by Moslems, the new ruler of the island wished to rebuild the walls of the city, which had been damaged in previous wars. Several ruined buildings were near the fortress, and stone from these buildings was used to repair the walls at the end
of the fifteenth century, or the beginning of the sixteenth.

While working on the fortress, the Moslems uncovered the ruins of a beautiful church. Several icons, most of them badly damaged, were found on the floor. One icon, of St Phanourius, looked as if it had been painted that very day. The local bishop, whose name was Nilus, was called to see the icon. It said, "Saint Phanourius."

The saint is depicted as a young soldier holding a cross in his right hand. On the upper part of the cross is a lighted taper. Twelve scenes from his life are shown around the border of the icon. These scenes show him being questioned by an official, being beaten with stones by soldiers, stretched out on the ground while soldiers whip him, then having his sides raked with iron hooks. He is also shown locked up in prison, standing before the official again, being burned with candles, tied to a rack, thrown to the wild animals, and being crushed by a large rock. The remaining scenes depict him standing before idols holding burning coals in his hands, while a demon stands by lamenting his defeat by the saint, and finally, the saint stands in the midst of a fire with his arms raised in prayer.

These scenes clearly revealed that the saint was a martyr. Bishop Nilus sent representatives to the Moslem ruler, asking that he be permitted to restore the church. Permission was denied, so the bishop went to Constantinople and there he obtained a decree allowing him to rebuild the church.

At that time, there was no Orthodox bishop on the island of Crete. Since Crete was under the control of Venice, there was a Latin bishop. The Venetians refused to allow a successor to be consecrated when an Orthodox bishop died, or for new priests to be ordained, hoping that in time they would be able to convert the Orthodox population to Catholicism. Those seeking ordination were obliged to go to the island of Kythera.

It so happened that three young deacons had traveled from Crete to Kythera to be ordained to the holy priesthood. On their way back, they were captured at sea by Moslems who brought them to Rhodes to be sold as slaves. Lamenting their fate, the three new priests wept day and night.

While in Rhodes the priests heard of the miracles performed by the holy Great Martyr Phanourius. They began to pray to him with tears, asking to be freed from their captivity. Each of the three had been sold to a different master, and so remained unaware of what the others were doing.

By the mercy of God, each of the priests was allowed by his master to pray at the restored church of St Phanourius. All three arrived at the same time and prostrated themselves before the icon of the saint, asking to be delivered from the hands of the Hagarenes (Moslems, descendents of Hagar). Somewhat consoled, the priests left the church and returned to their masters.

That night St Phanourius appeared to the three masters and ordered them to set the priests free so that they could serve the Church, or he would punish them. The Moslems ignored the saint's warning, believing the vision to be the result of sorcery. The cruel masters bound the priests with chains and treated them even worse than before.

Then St Phanourius went to the priests and freed them from their shackles, promising that they would be freed the next day. Appearing once more to the Moslems, the holy martyr told them severely, "If you do not release your slaves by tomorrow, you shall witness the power of God!"

The next morning, all the inhabitants of the homes where the priests were held awoke to find themselves blind, paralyzed, and in great pain. They considered what they were to do, and so decided to send for the priests. When the three priests arrived, they asked them whether they could heal them. The priests replied, "We will pray to God. May His will be done!"

Once more St Phanourius appeared to the Hagarenes, ordering them to send to the church a document granting the priests their freedom. He told them that if they refused to do this, they would never recover their sight or health. All three masters wrote letters releasing the priests, and sent the documents to the church, where they were placed before the icon of St Phanourius.

Before the messengers returned from the church, all those who had been blind and paralyzed were healed. The priests joyfully returned to Crete, carrying with them a copy of the icon of St Phanourius. Every year they celebrated the Feast of St Phanourius with deep gratitude for their miraculous deliverance.

The saint's name sounds similar to the Greek verb "phanerono," which means "to reveal" or "to disclose." For this reason, people pray to St Phanourius to help them find lost objects. When the object is recovered, they bake a sweet bread and share it with the poor, offering prayers for the salvation of saint's mother. Her name is not known, but according to tradition, she was a sinful woman during her life. St Phanourius has promised to help those who pray for his mother in this way

Monday, December 10, 2012

ስለ ሐዋርያት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
የሐዋርያት ዝርዝር
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሐዋርያት ዝርዝር በአራት ቦታዎች ተጽፎ ይገኛል፡፡ እነዚህ ዝርዝሮች በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌሎች ሲገኙ በዮሐንስ ወንጌል ግን ዝርዝሩ አልሠፈረም፡፡ የመጨረሻው ዝርዝር የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ ላይ ነው፡፡


ማቴዎስ 10.1-4፣ ማርቆስ 3.16-19፣ ሉቃስ 6.13-16፣ የሐዋ. ሥራ 1.13-14
ጴጥሮስ ጴጥሮስ ጴጥሮስ ጴጥሮስ
እንድርያስ ያዕቆብ ወ/ዘብዴዎስ እንድርያስ ዮሐንስ
ያዕቆብ ወ/ዘብዴዎስ ዮሐንስ ያዕቆብ ወ/ዘብዴዎስ ያዕቆብ ወ/ዘብዴዎስ
ዮሐንስ እንድርያስ ዮሐንስ እንድርያስ
ፊልጶስ ፊልጶስ ፊልጶስ ፊልጶስ
በርተሎሜዎስ በርተሎሜዎስ በርተሎሜዎስ ቶማስ
ቶማስ ማቴዎስ ማቴዎስ በርተሎሜዎስ
ማቴዎስ ቶማስ ቶማስ ማቴዎስ
ያዕቆብ ወ/እልፍ. ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ. ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ. ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ.
ታዴዎስ ታዴዎስ ስምዖን ቀነናዊው ስምዖን ቀነናዊው
ስምዖን ቀነናዊው ስምዖን ቀነናዊው የያዕቆብ ይሁዳ የያዕቆብ ይሁዳ
ያስቆሮቱ ይሁዳ ያስቆሮቱ ይሁዳ ያስቆሮቱ ይሁዳ -

ይህ የሐዋርያት ዝርዝር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍትም በልዩ ልዩ ቦታ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህልም የገድለ ሐዋርያትንና የቅዳሴ ማርያምን መመልከት ይቻላል፡፡

ገድለ ሐዋርያት ቅዳሴ ማርያም
ጴጥሮስ ጴጥሮስ
እንድርያስ ያዕቆብ
ያዕቆብ ወ/ዘብዴዎስ ዮሐንስ
ዮሐንስ እንድርያስ
ፊልጶስ ፊልጶስ
በርተሎሜዎስ በርተሎሜዎስ
ማቴዎስ ቶማስ
ቶማስ ማቴዎስ
ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ. ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ.
ታዴዎስ ታዴዎስ
ስምዖን ቀነናዊው ስምዖን
ያስቆሮቱ ይሁዳ ማትያስ

ከ12 ሐዋርያት መካከል ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ ያዕቆብ፣ እንድርያስ፣ ቶማስ፣ ማቴዎስ፣ ስምዖን ቀነናዊ፣ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ፣ በርተሎሜዎስና ፊልጶስ በአራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ዝርዝሮችና በሁለቱ አዋልድ መጻሕፍት ላይ ስማቸው ሳይለወጥ የሚገኝ ሲሆን ያስቆሮቱ ይሁዳ ደግሞ ታንቆ በመሞቱ የተነሣ በሐዋርያት ሥራ ላይ ስሙ ባይጠቀስም በሦስቱ ወንጌላውያን መጻሕፍትና በገድለ ሐዋርያት ላይ ተጽፎአል፡፡
• ሐዋርያው ማትያስ የተተካው በዚሁ ሐዋርያ ምትክ ነው፡፡ በቅዳሴ ማርያም ላይም አባሕርያቆስ ስሙን ጠቅሶት ይገኛል፡፡
• ታዴዎስ ከአራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ዝርዝሮች በሁለቱ እና በሁለቱ አዋልድ መጻሕፍት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የያዕቆብ ይሁዳ (ከአስቆሮቱ ይሁዳ ለመለየት) ደግሞ በቀሩት ሁለቱ ማለትም በሉቃስ ወንጌልና በሐዋርያት ሥራ ላይ ተመዝግቦአል፡፡
• ማቴዎስና ማርቆስ እንዲሁም ገድለ ሐዋርያትና ቅዳሴ ማርያም ታዴዎስ በሚለው ስሙ ሲጠሩት ወንጌላዊው ሉቃስ ግን በሁለቱም መጻሕፍቱ (በወንጌሉና በየሐዋርያት ሥራ) ‹የያዕቆብ ይሁዳ፣ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ›፣ በማለት ይጠቅሰዋል፡፡

በእሥራኤላውያን ዘንድ ከአንድ በላይ ስም የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ሕዝብ ጋር በመኖራቸውና የብዙ ቋንቋ ማለትም የግሪክ፣ የዕብራይስጥ፣ የአራማይክ፣ የሮማይስጥ ወዘተ. ተናጋሪዎች በመሆናቸው በልዩ ልዩ ቋንቋ ብዙ ስሞች አሏቸው፡፡
ለምሳሌ
• ጴጥሮስ (ላቲን) ፤ ስምዖን (ዕብራይስጥ) ፤ ኬፋ (አራማይክ)
• ቶማስ (ዕብራ) ፤ ዲዲሞስ (በግሪክ መንታ ማለት ነው፡፡
• ማቴዎስ - ሌዊ
• ማርቆስ - (ሮማይስጥ)፣ ዮሐንስ (ዕብራ)
• ሳውል (ዕብራ)፣ ጳውሎስ (ግሪክ)

በልዩ ልዩ ስም ተጠርተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ታዴዎስም ‹ልብድዮስ-የያዕቆብ ይሁዳ› ተብሎ በሦስት ስም ተጠርቷል፡፡
የሐዋርያት ክብር በቤተ ክርስቲያን
ቅዱሳን ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን ቀዳማውያን አበው፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሠው፣ ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ፣ በመሆናቸው በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ልዩ ክብር አላቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ መንገድ ታከብራቸዋለች፡፡
ሀ. ትምህርታቸውን ሳታዛባ በመጠበቅ፡- በዙዎች በልዩ ልዩ ዘመን ከእውነተኛው ትምህርተ ሐዋርየት አፈንግጠዋል፡፡ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በሲሞን መሠርይ መሥራችነት ከተነሱት ግኖስቲኮች ጀምሮ በኋላ ዘመን እስከፈለቁት አርዮሳውያን፣ መቅዶንዮሳውያን፣ ሰባልዮሳውያን፣ ንስጥሮሳውያን፣ መሐመዳውያንና ሉተራውያን ድረስ ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያቆየችላቸውን ትምህርተ ሐዋርያት፣ ትውፊት ሐዋርያትን ትተው በገዛ ፍልስፍናቸውና ምኞታቸው ፈቃድ ሲመሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን የሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት ጠብቃ እስከዛሬ ኑራለች፡፡
ለ. ገድላቸውን በመመስከር፡- አበው ሐዋርያት የክርስትና ኑሮ ፋና ወጊዎች በመሆናቸው ከከሀድያን፣ ከመናፍቃን፣ ከአረማውያን፣ ከትዕቢተኛ መኳንንትና መሳፍንት፣ ከዚህ ዓለም የዲያብሎስ አሽከላ ጋር ተጋድለው በደማቸው ቀለም በአጥንታቸው ብዕር ነው - ክርስትናን የጻፉት፡፡ ጽፈውም ብቻ ሳይሆን ኑረው ቀምሰው አሳይተውናል፡፡ ‹እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ እዩም› እንዳለ ልበ አምላክ ዳዊት በሹክሹክታ የተማሩትን በጩኸት፣ በጨለማ የተማሩትን በብርሃን፣ በቤት የተማሩትን በሰገነት ገልጠውታል፡፡ በዚህ ጊዜም ጨለማ የሰፈነበት ዓለም የወንጌልን ብርሃን መቀበል ተስኖት ፍዳ መከራ አብዝቶባቸዋል፡፡ ይህ ያደረጉት ተጋድሎ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በገድላቸው፣ ወዘተ ይገኛል፡፡ ጽፎ መረከብ ማስተማርም ብቻ ሳይሆን በእግራቸው የተተኩ አበውም መንገዳቸውን ተከትለውታል፡፡
ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ተጋድሎ ለትውልድ ሁሉ ትመሰክረዋለች፡፡ ልጆቿ አሠረ ፍኖታቸውን እንዲከተሉ ታስተምራቸዋለች፡፡ ልጆቿም ‹የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፡፡ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእሥራትና በወኅኒ ተፈተኑ፡፡ በመጋዝ ተሠነጠቁ፡፡ በሠይፍ ተገድለው ሞቱ፡፡ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፡፡ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ፡፡› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ዕብራ. 11.38፡፡
ስለ ወንጌል ክብር፣ ስለ ርትዕት ሃይማኖት የተሠው፣ የቤተ ክርስቲያን መዓዛ የሆኑ ሐዋርያትን ገድል በተግባር ያውሉታል፡፡
ሐ. በዓላቸውን በማክበር፡- ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ሐዋርያት የሰማዕትነታቸውን (ከቅዱስ ዮሐንስ በቀር፣ እርሱ ግን ሳይሞት ወደ ብሔረሕያዋን ስለተወሰደ የተወለደበት ይከበራል፡፡ ዮሐ. 21.22፡፡) በዓል ታከብራለች፡፡ የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረ ነውና፡፡
ይህ የሐዋርያት በዓል ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ጀምሮ ይከበር ነበር፡፡ የሰርምኔሱ ሊቀ ጳጳስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያት በሰማዕትነት ያረፉበት በዓል በጥንታውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ይከበር እንደነበር በ2ኛው መ/ክ/ዘመን ላይ ዘግቦ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሐዋርያት በዓል በድምቀት በቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሠረት የቅዱሳን ሐዋርያት በዓል የሚከበርበት ዕለት እንደሚከተለው ነው፡፡
1. ዮሐንስ ወንጌላዊ መስከረም 4 (ልደቱ)
2. ሐዋርያው ማቴዎስ ጥቅምት 12
3. ሐዋርያው ፊልጶስ ኅዳር 18
4. ሐዋርያው እንድርያው ታኅሳስ 4
5. ሐዋርያው ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ የካቲት 10
6. ሐዋርያው ማትያስ መጋቢት 8
7. ሐዋርያው ያዕቆብ ወ/ዘብዴዎስ ሚያዝያ 17
8. ሐዋርያው በርተሎሜዎስ መስከረም 1
9. ሐዋርያው ስምዖንን ቀነናዊ/ናትናኤል ግንቦት 15
10. ሐዋርያው ቶማስ ግንቦት 26
11. ሐዋርያው ታዴዎስ ሐምሌ 2
12. ሐዋርያው ጴጥሮስ ሐምሌ 5
 ሐዋርያው ጳውሎስ ሐምሌ 5

መ. በስማቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በመሰየም:-አስቀድሞ እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል ‹ሰንበቴን ስለሚጠብቁ፣ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ፣ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላል፡- በቤቴና በቅጥር ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ› ኢሳ. 56.4 ብሎ ለቅዱሳን ልጆቹ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ታቦት ተቀርፆላቸው በስማቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ይከበራሉ፡፡
ሠ. በስማቸው በመጠራት፡- ቅዱሳን ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን መሠረት የክርስትና ፈር ቀዳጅ ናቸውና ዘወትር ሊታሰቡ ይገባል፡፡ በመሆኑም በክርስቲያኖች ዘንድ ክርስትና ከተነሱበት ዕለት ጀምሮ በስማቸው መጠራት ባህላችን ነው፡፡
ረ. ሥዕላቸውን በማክበር ፡- ከጥንቱ የካታኮምብ (ግበበምድር) ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ የቅዱሳን ሐዋርያት ሥዕል ለሥርዓተ አምልኮ (ለጸሎት፣ ለምልጃና ለምሥጋና) መጠቀም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ የሐዋርያት ሥዕል በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ይገኛል፡፡ ምእመናንም አስቀድመው የልብሳቸውን ዘርፍ እየነኩ በጥላቸው ላይ እየተኙ ይፈወሱ እንደነበሩት ሁሉ የሐዋ. 5.15፣ 19.11 ዛሬም ሥዕላቸውን እየዳሰሱ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ያገኙበታል፡፡
ሰ. በአማላጅነታቸው በመታመን ፡- የቅዱሳን አማላጅነት በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርትና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተለያዩ ቦታዎች ተገልጦ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የቅዱሳን ሐዋርያት አማላጅነትም ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ጀምሮ የታወቀ የታመነም ነው፡፡ በሮማ መንግሥት ጨካኝነት የተነሣ በግበበምድር ለመኖር የተገደዱት ጥንታውያን ክርስቲያኖች፣ በግበበ ምድሩ ግድግዳ ላይ በጻፉት ጸሎታቸው፤ ‹ጳውሎስና ጴጥሮስ ሆይ ድል እናገኝ ዘንድ ጸልዩልን› ብለው የተናገሩት ተገኝቷል። 
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡

ስለ ቅዱሳን

    ቅዱስ፡-  ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥ ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ ማለት ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል። ቅዱስ ማነው? ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥ ማዕከለ ዓለም ፥ ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው የለም፡፡ ነቢዩ አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ። ኢሳ ፵ ፥ ፳፭ ፡፡ ፩ ስሙ ቅዱስ ነው የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። «ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና» እንዲል ይህ ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው ፥ በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነድዳቸው ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም «አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ አርትተውታል። የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ ፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም ጠንቋዩን በርያሱስን በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት ፈውሷታል። የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ። ፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤ የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ ፥ አምላክ ፥ ንጉሥ ነው ፤ ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥ ሕያው ፥ ኃያል ፥ ረቂቅ ፥ መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው ፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ ፥ ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና አባት ነው። ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ፤ » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫። እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት የታደጋቸውን እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥ ድንቅንም የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤ » እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ ፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ ፮፥፱-፲፩ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Sunday, December 9, 2012

ሰማእት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ(እመ እሙዝ)

                 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን::
    ወር በገባ በ29 በቤተክርስቲያናችን ታስበው ከሚውሉት እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳን ከገባላቸውን ከሰጣቸው እናቶች ኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ /እመ እሙዝ/ ትገኛለች ታዲያ ፍቅርተ ክርስቶስ /እመ እሙዝ/ ማን ናት? ምን ቃል ኪዳን ተሰጣት? እናም ደረገችውን ተጋድሎ በጥቂቱ እንመልከት
ጻድቃን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፡፡ ማቴ. 10፡40-42
በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቂት ወረዳ ጥባ ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ ምዑዝ ኪዳነ
ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት ገዳም ትገኛለች፡፡ ይህች ገዳም ከአዲስ አበባ በደሴ ወደ ጎንደር በሚወስደው መንገድ 665 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ገራገር/ ፍላቂት/ ከምትባለው ከተማ በመውረዱ በእግር 2፡30 /ሁለት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ / እንድተጓዙ ከ370 ዓመት ባለይ ያስቆጠረቸውን እመ ምዑዝ ኪዳነምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶ በአንድ ቀን የሠራቻትና ለጌታ በአራቱም አቅጣጫ የሰገደችውን ታላቅና ድንቅ ቤተመቅደስ ያገኛሉ ፡፡ የዚህች ታላቅ ገዳም መሰራች ኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ፃድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ያገኛሉ፡፡ የዚህች ታላቅ ገዳም መስራች ኢትጵያዊት ሰማዕትና ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በደቡብ ጎንደር ደራ ፎገራ አንበሳሜ ወረዳ ልዩ ስሙ አቡነ ሐራ ገዳም አዋሳኝ ከተታ ማርያም ተብሎ በሚጠራ ቦታ በሚያዚያ 4 /አራት/ቀን ተፀንሳ ታህሳስ 29 / ሃያ ዘጠኝ/ ቀን በጌታ ልደት ተወለደች፡፡ አባቷ ላባ እናትዋ ወንጌላዊት የተባሉ እግዚዘብሔርን የሚወዱ ትዕዛዙን የሚከብሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ መሀን ሆነው ልጅ ባመውለዳቸው እያዘኑ ተግተው ወደ እግዚአብሔር በመፀለያቸው ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የመሰለች የልጅ እናት በፀሎተዋ ለሀገር ለወገን የምትበቃ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚይም 80/ሰሚኒያ ቀን / ሲሆናት ለልጅነት ጥምቀት ወደ ቤተ መቅደስ በወሰዷት ጊዜ ከጥምቀት በኋላ ስጋ አምላክ ስትቀበል /ስትቆርብ/ ሕይወት የሆነውን ቅዱስ ስጋህን ክቡር ደምህን የሰጠኸኝ አምላኬ ክብር ምስጋና ይግባህ ብላ አመስግናለች፡፡ ስመ ክርስትናዋ ማርያም ፀዳለ ሲሆን የአለም ስሟ ሙዚት ነው፡፡ ፍቅርተ ክርስቶስ የምንኩስና /የቆብ/ ስሟ ነው፡፡
እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አባ ዳንኤል ከሚባል አባት መፅሐፍን እየተማረች ካደገች በኋላ ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ እናትና አባቷ ሊድሯት በመፈለጋቸው ዘርዓ ክርስቶስ ለሚባል ከደጋግ ሰዎች ወገን ለሆነ ሰው አጋቧት ፡፡ ማታ እንደ ሙሽሮች ደምብ ወደ ጫጉላ ቤት ሲገቡ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ቅደሱ ዘርዓ ክርስቶን ወንድሜ ሆይ እኔ የእናት አባቴን ፍቃድ ለመፈፀም ነው እንጂ ስጋዊ ሙሽራ መሆን አልፈልግም ፡፡ ፍላጎቴ የእግአብሔት ሙሽራ መሆን ነው በማለት ብታማክረው ቅዱስ ዘርዓ ክርስቶስም ፀጋ እግዚአብሔት የበዛለት ሰው ነበርና እኔም እናት አባቴን ላክበር ፈቃዳቸውን ለመፈፀም ነው እንጂ የስጋ ፈቃድ የለኝም በማለት ከተነጋገሩ በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ ለቤተሰቦቻቸውን ለአገሬው እንደ ባልና ሚስት ግን በንፅህና ለ40/ አርባ አመት / ሁለቱም በድንግልና ኖረዋል፡፡ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቢግራቸውም ሁለቱም ይህስ አይሆንም ብለው ለ40 /አርባ ቀን / በጾም ፀሎት በትጋት ጸልየዋል፡፡ መልአኩ ተገልጦ ይህ የእግዚአብሔ ፈቃድ ነው ሁለታችሁም ድንግልናችሁ አይፍስም ብሎ ነግሮአቸዋል፡፡ ከዚያም ወንድ ልጅ ወልደዋል ህፃኑ በተወለደ በ7/ሰባት/ ዓመቱ በቅዱስ ሚካኤል እቅፍ ገነትን ለ7 /ሰባት/ ቀናት ከጎበኛ በኋላ ወደ ምድር ሲመልሰው በእናት አባቴ አምላክ ይዤሃለሁ ወደዚች ወደ ከፋች ከረፋች ዓለም አትመልሰኝ ብሎ ቢለምነው ቅዱስ ሚካኤልም ከአምላክ ጠይቆ በብሔረ ህያዋን የህፃናት አለቃ ተብሎ እንዲቀመጥ አድርጎታ ፡፡ ስሙም ዳግማዊ ቂርቆስ ተብሏል፡፡

ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶና ቅዱስ ዘርዓ ክርስቶስም ልጅ ከወለዱ በኋላ እንደ ቀደሞው በቅድስና በንፀህና ፀንተው ኑረዋል፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው ንጉስ አፄ ሱስንዮስ ሃይማኖቱን ለውጦ ሁለት ባህርይ የሚሉ ካቶሊኮችን በመቀበሉ ክርስቲያኖችን እየገደለ ነው የሚል ወሬ ሰምተው ወደ ንጉ በመሄድ ሳይፈሩ ስለ ተዋህዶ ሃማኖታቸው በንጉ ፊት መስክረዋል፡፡ ንሱም በጣም የበዛ መከራን አድርሶባቸዋል፡፡ መከራ በበዛ ቁጥር እነርሱም እየፀኑ ተከታዮቻቸውንና የንጉሰን ሠራዎቶች ሳይቀር እያሳመኑ ቢያስቸግት በሰማዕትነት ከተቀበሉት ውስጥ የማሕበር ስለሴው ጻድቁ አምደ ስላሴ የጎረጎሪ ማርያም አባ መርአዊ የመሲ ኪዳነ ምህረቷ እመ ወተት እና ከ60 , 0000 /ስልሳ ሺህ / ባይ ክርሰቲኖች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ቅዱስ ዘርዓ ክርስቶስም ልጅ ከወለዱ በኃላ እንደ ቀድሞው በቅድስና በንጽህና ጸንተው ኑረዋል፡፡በዘመናቸው በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው ንጉስ አጼ ሱስንዮስ ሃይማትን ለውጡ ሁለት ባህሪይ የሚሉ ካቶሊኮችን በመቀበሉ ክርስቲያኖችን እየሀደለ ነው የሚል ወሬ ሰምተው ወደ ንጉስ በመሄድ ሳይፈሩ ስለ ተዋሕዶ ሀይማታቸው በንጉስ ፊት መስክረዋል፡፡ንጉሱም በጣም የበዛ መከራ አድርሶባቸዋል፡፡ መከራ በበዛ ቁጥር እነርሱም እየጸኑ ተከታዮቻቸውንና የንጉሱን ሰራዊቶች እያሳመኑ ቢያስቸግሩ በሰማዕትነት አንገታቸውን አስቆርቷቸዋል፡፡አንገታቸውም ሲቆረጥ ከሁለቱም ደም ውሃ ወተት ፈሷዋል፡፡በዚያን ዘመን ከእነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ጋር ሰማዕትነት ከተቀበሉት ውስጥ የማህበረ ስላሴው ጻድቁ አምደ ስላሴ የጎረጉር ማርያም አባ መርአዊ የመሲ ኪዳነ ምህረት እመ ወተት እና ከ60 ሺ በላይ ክርስቲያኖች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንገቷ ከተቆረጠና ሰማእትነት ከተቀበለች በኋላ ወደ ምድር መልሶ አንገቷን ከቀሪው የሰውነተዋ ክፍል ጋር አዋህዶ ከአንቅልፍ አንደሚነቃ ሰው ቀስቅሶ አስነስቷቷል፡፡ ከዚያም አቡነማርቆስ ስርዓተ ምንኩስናን በመቀበል ዋልድባ ገዳም ለ4 /አራት/ ዓመት አገልግላለች፡፡ ከዚም ከ500 /አምስት መቶ/ የሚበልጡ ተከታዮችዋን መነኮሳትን አስከትላ በሰሜን ወሎ ቆቦ ወረዳ ወደምትገኘውና በፃድቁ በአባ ጉባ ተመስርታ ጠፍታ ወደ ነበረችው ራማ ኪደና ምህረት አንድነት ገዳም በመሄድ ገዳሟን አቅንታ የወንድ የሴት ብላ ስርዐዓት ሰርታ ገዳሟን አስተካክላ 500/አምስት መቶ የሚሆኑ አገልጋች መነኮሳትን አኑራ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ጀምራለች፡፡በመንገዷም ላይ በላኤተ-ሰብ / ሰውን የሚበሉ / ወደ ሚኖሩበት አካባቢ በመድረስ እነርሱም እርሷንና 60/ ስልሳ/ የሚሆኑ አገልጋዮችዋን በጉጠት በማውጣት አራት /4/ ወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ዘግተውባቸዋል፡፡ ከአራት ወር በኋዋላም በዓል አድገው ለመብላት ከቤት ቢያወጧቸው መልካቸው እንደ ፀሐይ የሚያበራ ቢሀንባቸው አንቺ ሴት ምንድን ናችሁ ብለው ጠይቀዋታል፡፡ እርሷም ክርሰቲያን መሆናቸውናና እነሱ የስላሴ ሕንፃ የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንዴለባቸው ብትመክቸው ምን አንብላ ብለዋታል ፡፡ እርሷም ከራማ ኪዳነ ምህረት ስትነሳ የእህል ዘርን በአገከልጋዮቿ አሲዛ ነበርና ስንዴው በአንድ ቀን ዘርታ በቅሎ ታጭዶ ደርቆ ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡/ ደርሷል/ ፡፡ እርሷ ቀምሳ ብታቀምሳቸው እንደማር እንደ ወተት የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም እንደዚህ እያደረጉ እየሰሩ እንዲበሉ አስተምራ አስጠምቃ ከ6/ስድስት/ የሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናትን አስተክላላቸዋለች ፡፡ ከዚያም የተወሰኑ አገልጋዮችን አስቀምጣላቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ለ7 ዓመታት በአየሩሳሌም ከኖረች በኋላ የአመቤታችን በዓል ለማክበር ወደ ግብፅ በመሄድ ላይ ሳለች በመንገድ አንድ ቤተክርስቲየን ውስጥ ገብታ ስትፀልይ እመቤታችን በስዕሏ ላይ ተገልጣ ቦታዋ በኢትዮጵያ መሆኑን ነግራ እጇን ዘርግታ ወደ ኢትዮጵያ ሂጂ ብላ ከነገረቻት በኋላ በብርሃን አምድና በቅዱስ ሚካኤል እየተመራች አሁን ወደ ምትታወቅበትና የእግዚአብሔት ድንቅ ሥራ ወደ ተገለፀበት እመ ምዑዝ ኪዳነ ምህረት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ደርሳለች፡፡ በቦታው ስትደርስ የቦታው ልምላሜ የሚያስደስት ነበርና ይህች ቦታ ምንታምር ብላለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን ደረስ ምንታምር በመባል ይጠራል፡፡ ምንታምር ላይ ከአገልጋዮቿ ጋር በመሆን አርፋ ሳለ ከኢየሩሳሌም መርቶ ያመጣት የብርሃን አምድ በዚያ ቦታ ላይ በስፋት ረቦ / ከምድር እስከ ሰማ ተተክሎ/ ብታየው መልአኩም ቦታሽ ይሄ ነው ብሎ ቢነግራት በዚያው ተቀምጣለች፡፡ የቦታው ባለአባት ይህን ቦታ ልቀቂ ቢሎ ቢጠይቃት እግዚአብሔር የሰጠኝ ቦታዬ ነው ብላዋለች፡፡ እርሱም ለክስ ወደ ጎንደር በመሄድ ንጉስ አፄ ሱስንዮስ አርፈው አፄ ፋሲል ነግሰው ነበርና እሳቸውን ፍርድ ቢጠይቃቸው በዝና ያውቋት ነበርና ቤተክርሰቲያን ካልተሰራ ትልቀቅልህ ከተሠራ ግን ሌላ ቦታ ይሰጥሃል የሚል ፍርድ አስፈርዶ ሲመልስ ቅዱስ ሚካኤል ቀድሞ ቶሎ ቤተክርሲቲያን ስሪ እንዲህ የሚል ፍርድ ተፈርዷል ብሎ ነግሯት ‹‹ ታህሳስ 14 ቀን ከነግህ ፀሎት በኋላ በሰንሰልና በስሚዛ ግድግዳዋን በአይጥ ሀረግ ማገር አድርጋ የግድግዳ ቤተ መቅደስ በዕለተ አርብ በአንድ ቀን ሰርታ ታህሳስ 16 ቀን እሁድ ታቦተ ኪዳነ ምህረትን አስገብታ ቅዳሴ አስቀድሳለች ›› ቅዳሴውም ከተፈፀመ በኋላ ጌታቸውን ከቅዱስ መንበሩ ላይ እንዳለ ሆኖ ከእናቱ ከእመቤታችን ጋራ ታያቸው፡፡ ከመንበሩ ወርዶም ይህን ቦታ በባረከው ጊዜ የስሚዛው ቤተመቅደስ በአራቱም አቅጣጫ ለፈጣሪው ሰገደ፡፡ የመሬት መናወጥም ሆነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ልታጠፋን መጣህን ቤተክርሰቲያኔንስ ልታፈርሳት ነው ; ብላ ብትጠይቀው ይህ የሰንሰል ቤተመቅደስሽ ዳግም እስከምመጣ ድረስ ሳፈርስ ሳይታደስ ፀንቶ ይኖራል፣ በውስጡም እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ የክሀድያንና ፣ መናፍቃን እግር አይገባበትም፣ በውስጧ ቁርባንን የተቀበሉ ሁለ ኃጢያታቸው ይሰረይላቸዋል፣ ዘወትር ምህረቴ በረከቴ ከእነርሱ ጋር ይኖራል በማለት ተናግሮ ተሰወራቸው፡፡

ከዚያም በኋላ መነኮሳትና መነኮሳይያት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የትሩፋት ዜናዋን ሰምተው ከየአቅጣጫው ተሰበሰቡ፡፡ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም በአምላክ ሀይል ተጋድሎአቸውን ይፈፅሙ ዘንድ ታስተምራቸው ፣ ትመክራቸው፣ በተግባርም እያሳየቻቸው ለብዙ ዘመናት ከኖሩ በኋላ በገዳሙ ላይ የአጋንንት ፆር እንዳይነሳ ወንዶቹን ለብቻ ሴቶቹን ለብቻ አደረገች፡፡ ዘወትርም እንዳይተያዩ የእግዚአብሔት መልዐክ በቅድስተ ፍቅርተ ክርሰቶስ ፀሎት ይጠብቃቸው ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከዚህ ኃላፊ ዓለም መለየቷ በቀረበ ጊዜ ሁለት መላዕክት ወደ እርሷ መጥተው በብርሃን ሰረገላ ጭነው ወደ ደብረ ነባት ይኸውም ወደ ብሔረ- ህያዋ ወስደው በዚያ ቅዱስ ቁርባንን አቀብለው ወደ ቦታዎ መለሷት፡፡ መልዐኩም ከጻማ ከድካም ከመታረዝ ከረሐብ ከጥም ከመትጋት ከእንባ በሌሊትና በቀን ከመጮህ ከዚህ ዓለም የምትለይበት ጊዜ እነሆ ደረሰ አላት፡፡
የካቲት 27 ቀንም ወደ ምስራቅ እጇን ዘርግታ ቆማ ስትጸልይ በቤተክርስቲያ ውስጥ ከደስታ ብርሀን ጋር ያማረ ሽታ መላ ጌታችን ከአዕላፋት መልአክትና ቅዱሳን ጋር ወደ እርሷ መጣ፡፡ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ሰገደች፡፡ ተንበረከከች እጅግም አለቀሰች፡፡ ከወደቀችበት ቦታ አንስቶ ‹‹ ላጠፋሽ አልመጣሁም ወዳጄ ላከብርሽ ነው እንጂ›› አላት፡፡የዘለአለም መንግስት አዘጋጅቼልሻለሁ እና ደስ ይበልሽ ፡፡ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ቃል ኪዳን እንዲገባላት ተማጸነችው ጌታችንም ‹‹ሁሉም እንደ ቃልሽ ይሁንልሽ በስምሽ ስሜ ተጨምሯልና ለቤተክርስቲያንሽ መባ የሰጠ፣ የተላከ ፣የተቀበረ፣ ቤተ መቅደስሽ መጥቶ የተሳለመ ፣ እስከ 12 ትውልድ የምህረት ቃል ኪዳን ሰጠሁሽ በረከቴም በቤቱና በልጆቹ በገንዘቡም ላይ ይደር የገድልሽ መጽሐፍ ባለበት አጋንንት ሰይጣናት አይቀርቡም በአዝመራ ስምሽን በጠሩት ጊዜ የለመለመ ይሁን በጸሎትሽ የተማጸነ ሁሉ ባለጤና ይሁን ስምሽን በእውነት የሚጠራ የከበረ ነው፡፡ ያለመጠራጠር በቀናች ሐይማኖት የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ ያጻፈ ያነበበ የተረጎመ በሐይማኖት የሰማ እስከ ቀዝቃዛ ውሃ ድረስ የሰጠ ኃጢያቱ ይሰረይለታል፡፤ስለድካምሽ ስለትሩፋትሽ 7 አክሊሎችን እና ይህን ሁሉ ቃል ኪዳን ሰጠሁሽ ፡፡ ላልምረው ቦታሽን አላስረግጠውም›› ብሏት ወደ ሰማይ አረገ፡፡
በማግስቱ ትንሽ ህመም ታመመች ደናግል መነኮሳትን ጠርታ የእረፍት ቀኗ መድረሱን ነገረቻቸው ከመካከላቸው አንዷን ለገዳሙ አስተዳዳሪነት መርጣ በፍቅር ስም ተሰናበተቻቸው፡፡የዳዊት መዝሙርንም ስትጸል የካቲት 29 ቀን እሁድ አጥቢያ ጠዋት በጌታ በዓል አንቀላፋች ነፍሷ ከስጋዋ ተለየች፡፡ ጌታችንም ከእናቱ ጋር ከቅዱሳኑ ጋር መጥቶ ነፍሷን ተቀብሎ ወደ ዘለዓለም ገነት ወሰዳት፡፡ ቅዱሳንም ከመላእክት ጋር እልል እያሉ እያመሰገኑ ወደ ዘለዓለም ቦታ ገነት አስገቧት፡፡ ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ መቃብር ላይ 40 ቀናት ብርሃን ሲበራበት ታይቷል፡፡

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቂት ወረዳ ጥባ ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ ምዑዝ ኪዳነ ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት ገዳምም በዓላቶቿ የሚከበሩት ታህሳስ 16 የቅዳሴ ቤቷ እንዲሁም የካቲት 29 ቀን በዓለ እረፍቷ ይከበራል፡፡
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡
ምንጭ፡- ገድለ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ
ጸሀፊ ገዛሀኝ ፈንታሁን

Saturday, December 8, 2012

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ


        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
     ስለ እመቤታችን፣ ስለሐዋርያት፣ ስለነገስታት፣ ስለጻድቃን፣ ስለሰማዕታት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት በአጠቃላይ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እንወቅ፣ እንመርምር፣ እንጠይቅ፣እንማማር ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ እዝነ ልቦናችንን ይክፈትልን፤ ያዲስ ኪዳን ኪሩብ የጸጋ መፍሰሻ ምልዕተ ክብር ምልዕተ ውዳሴ የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጢር ትግለጥልን አሜን!!!
 ቅዱሳን ጻድቃን መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለምና ከተድላ ዓለም ተለይቶ ቤት ልስራ ዘር ልዝራ ሳይሉ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ ጸንተው የኖሩ ናቸው።
  አኗኗራቸው ድምጸ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ግርማ ሌሊቱን ሳይሳቀቁ ደዋ ጥሰው፣ ደንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው ነው። ይህን ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።” በማለት በዕብ.11፡37-38 የገለጸው።

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ (፩ሺ፪፻፩ ዓ.ም/1201 ዓ.ም/
 ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የቅዱስ ላሊበላ ወንድም ልጅ ሲሆን አባቱ ሐርቤይ እናቱ መርኬዛ ይባላሉ። በግብረ መንፈስ ቅዱስ ታህሳስ ፫ ማክሰኞ ዕለት ተወለዱ። “ቅዱስ ነዓኩቶ ለአብ ሲወለድ እናቱ ምጥ ይኋት ካህናት ቅዳሴውን ገብተው ሳለ ዲያቆኑ ነአኩቶ ሲል ስለተወለደ ስሙ ነዓኩቶ ለአብ ተባለ።” እንደ ዮሐንስ በድንግልና የኖረ የመንፈስ ቅዱስ መንኮራኩር ሠረገላ ተሰጥቶት እንደፈለገ እየሄደ የሚንቀሳቀስ የበቃ ጻድቅ ነበር።
ቅድስ ነአኩቶ ለአብ የጌታን መከራ እያሰበ በቁመቱ ልክ ጉድጓድ አስቆፍሮ በዙርያው ጦር አስበጅቶ ጦሩ እንዲወጋው አርብ አርብ ዕለት ደሙ እየፈሰሰ እልፈ እልፍ እየሰገደ ፵ (40) ዓመት ኖረ።
በአንድ ቀን ጌታችን በአካል በቤተ መቅደስ ተገልጾለት ወዳጄ ልጄ ነዓኩቶ ለአብ ሆይ የዚህች የቅጣት ዓለም ጊዜ በቃህ እኔ ለሰው ልጆች ስል ደሜን ያፈሰስኩት መከራውን የተቀበልኩት አንድ ቀን ነው። አንተ ግን ፵ (40) ዓመት ሙሉ ደምህን እንባህን እያፈሰስክ አትዘን ባንተ ቤተ መቅደስ ተገኝተው በአንተ አማላጅነት አምነው የተማጸኑትን፣ ቦታህን ሳይረግጥ፣ ዝክርህን ሳይዘክር ዝናህን ሰምቶ ያሰበህን እንኳ እምርልሃለሁ። አንተም እስከ ዐለተ ምጽአት ተሰውረህ ስለ ሰው ልጅ ሃጢአት ኑር ብሎታል። በተጨማሪም እስከ እለተ ምጽአት በዚህ ቦታ ለሚመጡ ሕሙማን ስትፈውስ ቆይ ብሎታል። ዛሬም ከጣራው ፀበሉ ይንጠባጠባል፤ በጋ ከክረምት አይደርቅም። እንደውውም ክረምት ይቀንሳል በጋ ይጨምራል። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ያሳነጻት አሸተን ማርያም የተባለች ቤተ መቅደስ አለች። አሸተን የተባለችበት ምክንያትም ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አንጿት ሲያበቃ ማዕጠንት ሲያጥን ብዙ ቅዱሳን ቤተ መቅደስ ገብተው ጥቅጥቅ ብለው ቁመው ሲመለከት እናንተ ደግሞ እንዴት መጣችሁ ብሎ ቢጠይቃቸው ማዕጠንቱን አሽተን መጣን ስላሉ ዛሬም ስሟ አሽተን ማርያም ትባላለች። ይህችን ቤተ ክርስቲያን በ ፩ሺ፪፻፲፩ /1211 ዓ.ም አነፃት።
የላሊበላምን ልጅ ይትባረክን አሳድጎ መንግስቱን ለእርሱ አውርሶ በሞት ፈንታ ከሥጋው ታህሳስ ፫ /3/ ቀን እንደ ሄኖክ ተሰውሯል።ወደ ፊት በሕይወት ይመጣል፤ የተሰወረውም በተወለደ በ፸ /70/ ዓመቱ ነው። በስሙ 3 ቤተክርስቲያን ተሰርቶአል። በዚህ ጻድቅ ገድል ለ፳፩ / ለ21/ ቀናት የታሸ በአማላጅነቱ ያመነ እድሜው እንደሚረዝም ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።
“ጻድቅ በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ እውነት እላችኋለሁ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።" ማቴ. ፲፡፵¬-፵፪ (10፥40¬-42)
 ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

አባ ሊቃኖስ


             በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
  ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ አባ ሊቃኖስ ዘእምተሰዓቱ ቅዱሳን /በዚህ ዕለት ከ9 ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ሊቃኖስ አረፉ።
  “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (“የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
“እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” ሐዋ.፬፡፳ (4፡20)
የቅዱሳን ሕይወት ተርታ ታሪክ ወይም ተረት አይደለም ይልቁንስ እግዚአብሔርን የሚከተሉና በሥራቸው ሁሉም የእርሱ ጥበቃ ያልተለያቸው ሰዎች ታሪክ ነው። (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)
  ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አክሱም ከቆዩ በኋላ ለስብከት በዮሓ ክፍላቸው ሲሰማሩ አቡነ ጰንጠሌዎንና አቡነ ሊቃኖስ ርቀው እንዳይሄዱ ሕዝቡ ስለተማጸናቸው ከከተማ ሳይርቁ አምስት ምዕራፍ ርቀት ገዳማቸውን መሠረቱ። አቡነ ሊቃኖስ ከአክሱም በስተ ሰሜን ከሚገኙ ደብረ ቆናጽል ከሚባለው ኮረብታ መቀመጫውን አድርገው የከተማውን ሕዝብ እያስተማሩ ለ፳፩ ዓመታት ቆይተዋል።
የአባታችን ገዳም ደብረ ቆናጽል በመባል ይታወቃል። “ደብረ ቆናጽል” ማለት “የቀበሮ ታራራ” ማለት ነው። ደብረ ቆናጽል በተፈጥሮ ልምላሜ የማይለየው ቦታ ሶሆን ተራራማ ሆኖ ዙርያው ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነው። የአክሱም አከባቢው ክርስቲያኖች ንዋያተ ቅዱሳቱን የሚጠብቅላቸና ጽላተ ሙሴን የሚያጥንላቸው መነኩሴ የሚመርጡት ከዚህ ከአባ ሊቃኖስ ደብረ ቆናጽል ገዳም ነው። የአክሱም ሕዝብ ይህን የተመረጠውን መነኩሴ ንዋያተ ቅዱሳት ጠባቂ፣ አጣኝ ብቻ ሳይሆን ከጳጳስ በበለጠ አባትነቱን ይቀበሉታል።
በዚህ አኳኋን እስከ ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም ድረስ ተጠብቆ የኖረውን ገዳም ፋሽስት ኢጣልያን ሀገራችንን በግፍ ሲወር ይህን ገዳም እጅግ አጎሳቆለው። ቤተ ክርስቲያኑን ማደርያቸውና የጦር መሣርያ ተሸካሜዎች የአጋሰሶች ማጎሪያ አደረጉት። ገዳሙ ከፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ ጀምሮ ጠፍ ወይም ምድረ በዳ ሆኖ ሲኖር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥቂት መነኮሳት በቦታው መቀመጥ ጀምረዋል።
ይህን ገዳም የመሠረቱት ከተሰዐቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ሊቃኖስ ለአክሱም ሲታይ ቅርብ በሆነ ቦታ ስለተቀመጠ ከአጼ ካሌብና ከአጼ ገ/መስቀል ጋር ለማገናኘት ዕድል ስለነበራቸው ለሐዋርያዊ ተግባራች እገዛ አድርጎላቸዋል። በዚህ መሠረት ደግሞ ከፅርዕ፣ ከሱርስ ቋንቋዎች መጽሐፈ ሐዲሳትን በከፊል ወደ ግእዝ እንደተረጎሙ ይነገራል። ይህን ሁሉ ተጋድሎ ካደረጉ በኋላ በክብር  ኅዳር ፳፰ አርፈዋል። የአባታችን ረድኤትና በረከት አይለየን።
የጻድቃን መሥዋዕታቸው የዐይናቸው እንባ ነው። (ማር ይስሐቅ) የቅዱሳን ሁሉ በረከታቸው ልመናቸው ሁላችንንም ታበርታን አሜን።

ዋቢ መጽሐፍት

ነገረ ቅዱሳን ፪ በማኀበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል፣ መዝገበ ታሪክ ፩፣፪፣ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ በአቡነ ጎርጎርዮስ

የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ( የገሊላ ባሕር ፫ ስያሜዎች አሉት፡- (፩) የገሊላ ባሕር (በገሊላ አውራጃ ስለሚገኝ)፣ በዙሪያው ባሉ ጌንሴሬጥና ጥብርያዶስ በሚባሉ ከተሞች ስም ደግሞ (፪) ባሕረ ጌንሴሬጥ እና (፫) ባሕረ ጥብርያዶስ ይባላል) ባለች ቤተሳይዳ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው የአባቱ ስም ዮና ሲሆን ትውልዱም ከነገደ ሮቤል ነው። እናቱ ደግሞ ከነገደ ስምዖን ወገን የሆነች ነበረች። በመሆኑም እንደ ኦሪት ሥርዐት ስም ሲያወጡለት በእናቱ ነገድ ስም ስምዖን ብለውታል። አባቱ ዮና የያዕቆብና የዮሐንስ አባት ከሆነው ከዘብ
ዴዎስ ጋር የሥራ ባልንጀራ ሲሆን የሁለቱም ሥራቸው ዓሣ እያጠመዱ መሸጥ ነበር። እድሜው ፭ ዓመት ሲሆን ኦሪትን እየተማረ እንዲያድግ በአቅራቢያቸው ወዳለ ወደ ቅፍርናሆም ምኩራብ ሰደዱት። ቅዱስ ጴጥሮስ በቅፍርናሆም እየተማረ ካደገ በኋላ በዚያው ቤት ሠርቶ ኮንኮርድያ (ጴርጴቱዋ) የምትባል ሚስት አግብቶ እንደ አባቱ ዓሣ እያጠመደ በመሸጥ መኖር ጀመረ።

ለቅዱስ ጴጥሮስ እንድርያስ የተባለ ወንድም ነበረው። ሥራውም ልክ እንደ ወንድሙ ዓሣ ማጥመድ ነበር። ነገር ግን ይህ እንድርያስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም፤ እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እያለ ስለ ክርስቶስ ሲመሰክር ሰምተው ክርስቶስን ከተከተሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሐዋርያት አንዱ ነው (፪ኛው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ነው) /ዮሐ. ፩: ፴፭ - ፵/።

ቅዱስ ጴጥሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር የተዋወቀው በወንድሙ በእንድርያስ ግብዣ ነው። እንድርያስ ከመምህሩ ከመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ሰምቶ ክርስቶስን ከተከተለ በኋላ ወዲያውኑ ለወንድሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ “በትርጓሜው ክርስቶስ የሚሉት መሲሕን አገኘነው” በማለት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወስዶታል። ጌታም ቅዱስ ጴጥሮስን ባየው ጊዜ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ (ጴጥሮስ) ትባላለህ” አለው /ዮሐ. ፩ : ፵፪ - ፵፫/። ይህም ወደ ፊት እርሱን እንደሚከተለውና “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ ሲመሰክር ስሙን ቀይሮ “አንተ ዐለት (ጴጥሮስ) ነህ …” እንሚለው ትንቢት ሲነግረው ነው /ማቴ. ፲፮ : ፲፫ - ፳/።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ እየተዘዋወረ ሲያስተምር አንድ ቀን ጠዋት በጌንሴሬጥ ባሕር ወደብ ብዙ ሰዎች ቃሉን ለመስማት ተሰበሰቡ። ጌታችን በወደቡ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ሲደክሙ ያደሩ ዓሣ አጥማጆችን አገኘ። ከነዚህም መካከል ቅዱስ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ እንዲሁም ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ። ጌታችንም ቃሉን ለመስማት የተሰበሰበውን ሕዝብ ብዛት አይቶ ከሕዝቡ ጋር ፊት ለፊት እየተያየ ለማስተማር እንዲመቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ታንኳ ገብቶ በታንኳው ላይ ሆኖ ማስተማር ጀመረ። ትምህርቱን ሲጨርስ ቅዱስ ጴጥሮስን “መረብህን ጣልና ዓሣ ያዝ” አለው። ሌሊቱን ሙሉ ሲደክሙ አድረው ምንም አይነት ዓሣ አላገኙም ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ “መምህር ሆይ! ሌሊቱን ሁሉ ስንደክም አድረን ምንም አላገኘንም፤ ነገር ግን እንደቃልህ መረቡን ወደ ባሕር እንጥላለን” በማለት ሳይጠራጠር መረቡን ወደ ባሕር ጣለ። በዚህ ጊዜ መጎተት እስኪያቅታቸውና እስኪደነቁ ድረስ ጌታችን ብዙ ዓሦች ወደ መረቡ እንዲገቡ አደረገ። ቅዱስ ጴጥሮስ የተደረገውን ተአምር አይቶ ከጌታችን እግር ሥር ሰገደና እንዲህ አለ፡- “እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና አቤቱ ከኔ ፈቀቅ በል” /ሉቃ. ፭ : ፰/። አባቶች ይህንን ሲተረጉሙ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን የተናገረው “ባሕርንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት የሚያውቅ የእኔንማ ኀጠአት እንዴት መርምሮ ይፈርድብኝ ይሆን?!” ብሎ በመፍራትና ስለራሱ ኀጢአት በማሰብ “ካንተ ጋር መኖር የማይገባኝ ኀጥእ ነኝ” በማለት ስለፍጹም ትሕትና ነው ይላሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ጴጥሮስን ፍርሃትና ድንጋጤ አይቶ፡- “ስምዖን ሆይ አትፍራ! ከእንግዲህ ወዲህ ዓሣ ሳይሆን ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” ብሎ ሁለቱንም “ተከተሉኝ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ሁሉን ትተው ተከተሉት /ሉቃ. ፭ : ፩ - ፲፩/። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቱን፣ ትዳሩን፣ ሥራውን፣ ዘመዶቹን በአጠቃላይ የዚህን ዓለም ኮተት በሙሉ እርግፍ አድርጎ ትቶ ሙሉ ጊዜውን ከጌታ ጋር በማድረግ መደበኛ ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ለዚህም ማስረጃው በሌላ ቦታ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን “ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” ሲል መጠየቁና ጌታም “የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት በ፲፪ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በ፲፪ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስትን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” ብሎ መመለሱ ነው /ማቴ. ፲፱ : ፳፯ - ፳፱/።

ጌታችን እንደ ልማዱ በገሊላ ባሕር ዳር ባሉ መንደሮችና ከተሞች እየገባ ሲያስተምር አንድ ቀን በቤተ ሳይዳ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን ከበሽታዋ ፈወሰለት። ይህንንም ሲያደግለት የቅዱስ ጴጥሮስ እምነት ይበልጥ ጸና፤ ልቡንም ደስ አሰኘው።

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ከተከተለ ጊዜ ጀምሮ ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ የጌታችንን ትምህርት በሚገባ ተከታትሏል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ጌታ በሚያስተምራቸው ወቅት በጥያቄና መልስ ፈጣንና ንቁ ተሳትፎም ነበረው። ጌታችን ሐዋርያትን ጥያቄ ሲጠይቃቸው ብዙ ጊዜ ፈጥኖ ይመልሳል፤ እርሱም ያልገባውን ነገር ለመረዳትና የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ በተደጋጋሚ ለጌታችን ጥያቄ ያቀርብ ነበር። ጌታም በበኩሉ የተለያዩ ትዕዛዛትን ሲያዘው እንመለከታለን። ለአብነትም የተወሰኑትን ብንመለከት፡-

1. ጌታችን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አበርክቶ አምስት ሺህ ሕዝብ ሲያጠግብ አይተው ሕዝቡ ይህንንስ እናንግሠው ብንራብ ያበላናል፣ ብንታመም ይፈውሰናል፣ ብንሞት ያሥነሣናል በሚል ሥጋዊ አስተሳሰብ ሊያነግሡት ፈለጉ። ጌታችንም ይህን ሐሳባቸውን አውቆ የመጣበት ዓላማ ይህ አይደለምና ደቀ መዛሙርቱ ቀድመውት በጀልባ ተሻግረው እንዲሄዱ አድርጎ እርሱ ብቻውን ወደ ተራራ ወጥቶ መጸለይ ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱ እንደታዘዙት በመርከብ ሲሄዱ ብርቱ ነፋስ ተነሥቶ አናወጣቸው። ባራተኛው ሰዓተ ሌሊት ጌታችን በባሕሩ ላይ በእግሩ ተከተላቸውና አጠገባቸው ደረሰ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የማዕበሉ ብርታት ከጨለማው ጋር ተዳምሮ እጅግ በተጨነቁበት ጊዜ ወደ እነርሱ የሚመጣው “ምትሐት ነው” ብለው እጅግ ተረበሹ። በዚህ ጊዜ ጌታችን “አይዟችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ” ብሎ ማንነቱን ነገራቸው። ድምፁን ሰምተው ከተረጋጉ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አንተስ ከሆንህ በባሕሩ ላይ በእግሬ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ብሎ ጠየቀው። ጌታም “ና” አለው። ቅዱስ ጴጥሮስ ከመርከቡ ወረዶ መጓዝ እንደጀመረ ገና በመንፈስ ቅዱስ አልታደሰም ነበርና የማዕበሉን መበርታት እይቶ ስለፈራ መስጠም ጀመረ፤ ወደ ጌታም “አድነኝ” ሲል ጮኸ። ጌታም እጁን ዘርግቶ ወደ መርከቡ ካወጣው በኋላ “ከእኔ ጋር ሆነህ እንዴት ትጠራጠራለህ” በሚል ገሰጸው /ማቴ. ፲፬ ፥ ፳፭ - ፴፬/።

2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተማረ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ሲደርስ ሐዋርያትን በጥበብ ስለራሱ ማንነት ለማስረዳት ሲል በተዘዋዋሪ ሌሎች ሰዎች ምን እንደሚሉት ሐዋርያትን ጠየቃቸው። ሐዋርያትም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፣ አንዳንዱ ኤልያስ ነው፥ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” ሲሉ መለሱለት። ጌታችንም “ለመሆኑ እናንተስ ምን ትሉኛላችሁ” ብሎ ስለ እርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ጠየቃቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ሲል መሰከረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የእኔ ትክክለኛ ማንነት ሌሎች(አይሁድ) እንዳሉት ሳይሆን ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው (እንደተናገረው) ነው” በማለት ቅዱስ ጴጥሮስን እጅግ አድርጎ አመስግኖታል:- “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ አንተ ብፁዕ ነህ፤ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም” /ማቴ. ፲፮ ፥ ፲፫ - ፲፱/። ቅዱስ ጴጥሮስ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ከመሰከረ በኋላ ጌታችን ስሙን ቀይሮለታል። ስምዖን ይባል የነበረው “ዐለት” ተባለ (በዕብራይጥ ኬፋ፣ በጽርዕ(ግሪክ) ጴጥሮስ፣ በግዕዝ ኰኵሕ በአማርኛ ዐለት ማለት ነው)። ጌታ በዚህች ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኑን እንደሚሠራትም ተናግሯል። ይህም ማለት ቤተክርስቲያን የምትመሠረተው በቅዱስ ጴጥሮስ ሃይማኖት ማለትም በክርስቶስ ማንነት ላይ ባለ ትክክለኛ እምነት ነው ማለት ነው። እርሱም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ” መሆኑን ጠንቅቆ ማመን ነው። ሁሉም ሐዋርያት ከጌታ ጋር በነበራቸው የተማሪነት ቆይታ ከተረዷቸው ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማዎች) አንዱ ይህ ነው። ጌታም “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ የጠየቃቸውና ቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛውን መልስ ሲመልስ ማመስገኑ ይህንን ሊያስተምራቸው ስለወደደ ነው። ፫፻ (ሠለስቱ ምዕት) በኒቅያ ጉባኤ እምነታቸውን ሲመሰክሩ ካስቀመጡት ጸሎተ ሃይማኖት በፊት ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ የእምነት አገላለጽ የጥንት ክርስቲያኖች ይህን እየመሰከሩ ይጠመቁ ነበር (በመንገድ ሲሄዱም ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም መልሶ፣ እነሆ ውኃ መጠመቅን ምን ይከለክለኛል አለው። ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ይገባሃል አለው። ጃንደረባውም መልሶ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እኔ አምናለሁ” አለው . . . አጠመቀውም” እንዲል /ሐዋ. ፰፥ ፳፮ - ፍጻሜ/ )።

3. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነቱን በደብረ ታቦር ተራራ ከገለጠላቸው ሦስት ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስ አንዱ ነው። “ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ለብቻቸው ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው /ማቴ. ፲፯ ፥ ፩ - ፫/። ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችንን ጌትነት ከተመለከተ በኋላ ከደስታው ብዛት የተነሣ ጌታችንን እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር፤ “አቤቱ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ ሦስት ቤቶችን በዚህ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ” /ማቴ. ፲፯ ፥ ፩ - ፯/። ሙሴና ኤልያስ በደብረ ታቦር ከጌታችን ጋራ መታየታቸው ለቅዱስ ጴጥሮስ እምነቱን የሚያረጋግጥለትና የሚያጸናለት ነገር ነው። “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል” ብሎ በጠየቀ ጊዜ “ኤልያስ ነው ወይም ከነብያት አንዱ (ሙሴ) ነው” ብለውት ነበርና የሙሴና ኤልያስ ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ መታየት ጌታችን ሙሴ ወይም ኤልያስ አለመሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም ለቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ የመሰከረውን አብ ደግሞ በደመና ሆኖ “የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ማለቱ የቅዱስ ጴጥሮስን ምስክርነት የሚያረጋግጥ ነው።

4. ጌታችንና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ የቤተ መቅደስ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ቅዱስ ጴጥሮስን “መምህራችሁ ለቤተ መቅደስ ግብር ይገብራል ወይስ አይገብርም” የሚል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። “ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጥተው መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር አይገብርምን? አሉት። እርሱም መልሶ አዎን (ይገብራል) አለ” እንዲል /ማቴ. ፲፯ ፥ ፳፬ - ፳፭/። ቅዱስ ጴጥሮስ ግብር ተቀባዮች በጠየቁት ጊዜ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የመሰከረውንና ልጅ ደግሞ ከግብር ነጻ መሆኑን ባለማገናዘብ “አዎን ይገብራል” አላቸው። ጌታችንም “አዎን” ማለቱን አውቆ እርሱ ከግብር ነጻ መሆኑን በነገሥታት ልጆች ምሳሌ ካስረዳው በኋላ ነገር ግን እነርሱን ላለማሰናከል በተአምራት ከዓሣ ሆድ ገንዘብ አስገኝቶ ለሁለታቸውም እንዲሰጥ አዘዘው። “ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ አስቀድሞ ስምዖን ሆይ፥ ምን ትላለህ? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች? አለው። ጴጥሮስም፦ ከሌሎች ነው አለ፤ ጌታችን ኢየሱስም አለው፤ እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው። ነገር ግን እንዳያጉረመርሙ፥ ወደ ባሕር ሂድና መረብ ጣል፥ በመጀመሪያም የያዝከውን ዓሣ ወስደህ አፉን ክፈት፤ በውስጡም ሰጣጢራ ታገኛለህ፤ ይከውም አራት ድሪም ነው፤ እርሱንም ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለው” እንዲል “ማቴ. ፲፯ ፥፳፭ ፍጻሜ/። እንዳያጉረመርሙ (እንዳናሰናክላቸው) ማለቱ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ለቤተመቅደስ ግብር ሳይገብር ቀርቶ ቢሆን ኖሮ አምላክነት ብቻ እንጂ ሰውነት የለውም ባሉ ነበርና ነው።

5. ቅዱስ ጴጥሮስ ትዳሩን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን፣ ዘመዶቹን በአጠቃላይ ይህን ዓለም እርግፍ አድርጎ ትቶ ጌታችንን በመከተሉ ምን እንደሚያገኝ ጌታችንን በአንድ ወቅት ጠይቆት ነበር። “ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ መልሶ፥ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን አለው” እንዲል። ጌታችንም ሐዋርያት በጠቅላላ በፍጹም ልባቸው ዓለም በቃኝ ብለው እርሱን በመከተላቸው የሚያገኙትን ዋጋ ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፡- “እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በ፲፪ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በ፲፪ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስትን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” /ማቴ. ፲፱ : ፳፯ - ፳፱/።

6. መዝገበ ትሕትና የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ትሕትናን ሊያስተምራቸው ዝቅ ብሎ እግራቸውን ማጠብ በጀመረ ጊዜ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲደርስ ለጌታው ካለው አክብሮትና ፍቅር የተነሣ እንዲሁም እርሱ አምላክ ሲሆን ዝቅ ብሎ የእነርሱን እግር በማጠቡ እጅግ ተደንቆ “በፍጹም አታጥበኝም” አለ። ጌታችን ኢየሱስም “እኔ የምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፥ ኋላ ግን ታስተውለዋለህ” ቢለውም አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ በጌታውና በአምላኩ እግሩን መታጠብ እጅግ ስለደነቀውና ስለከበደው “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም” አለው። በዚህ ጊዜ ፈጽሞ እንቢ ማለቱን ባየ ጊዜ “እውነት እውነት እልሃለሁ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም” ብሎ መለሰለት። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁሉን ትቶ የተከተለውን ጌታ ከማጣት የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ ስለሚያውቅ “አቤቱ፥ እንኪያስ የምታጥበኝ እጆቼንና ራሴንም እንጂ እግሮቼን ብቻ አይደለም አለው። ጌታችን ኢየሱስም፦ ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤ እናንተማ ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው።” /ዮሐ. ፲፫ ፥ ፩ - ፲፩/።

7. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በካህናት አለቆችና በአይሁድ ሽማግሌዎች ተላልፎ የሚሰጥበትና መከራ የሚቀበልበት ሰዓት ሲደርስ ይህንን መራራ እውነት ለደቀ መዛሙርቱ ሲነገራቸው እጅግ ተረብሸው ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ በመጨረሻው ሰዓት ሁሉም ደቀ መዛሙርት እንደሚክዱት በነገራቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “ሌሎች ቢክዱህ እንኳን እኔ በፍጹም አልክድህም” አለው። ጌታችን እርሱ ባወቀ ዶሮ ሳየጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ቢለውም እርሱ “በፍጹም” አለ። ነገር ግን አይሁድ ጌታችንን ይዘው መከራ ሲያጸኑበት አይቶ እርሱን ያገኘ ያገኘኛል ብሎ “አንተ ከእርሱ ወገን ነህ” ሲሉት “በፍጹም አይደለሁም” እያለ መማል ጀመረ። ወዲያው ዶሮ ሲጮክ ጌታ የተናገረውን ቃል አስታውሶ በዚያችው ቃል “አላበጀሁም” በማለት በፍጹም ጸጸት ማንባት ጀመረ(ንስሓ ገባ) /ማቴ. ፳፮ ፥ ፳፱ - ፍጻሜ/።

ቅዱስ ጴጥሮስ ለጌታችን ካለው ፍቅርና ቀረቤታ ታሪኩ በቅዱስ ወንጌል በስፋት ተገልጿል፤ ሁሉንም ዘርዝሮ መጥቀስ ባይቻልም። ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን በእውነት ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን መቃብሩን በማየት ያረጋገጠ፣ ጌታችን ግልገሎቼን ጠቦቶቼንና በጎቼን ጠብቅ ብሎ እንደሾመው እርሱም ልክ እንደጌታው ለበጎቹ መልካም እረኛ በመሆን የታመነ፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ታድሶ በአንድ ጊዜ ሦስት ሺህ ነፍሳትን አሳምኖ ያጠመቀ፣ ብዙ ተአምራትን በጌታችን ኃይል ያደረገ፣ የሐናንያንና የሰጲራን ድብቅ ሥራ በመንፈስ የመረመረ፣ በሰማርያ በኢዮጴና በልዳ ዞሮ ወንጌልን ያስተማረ፣ በመጨሻም በሮማ ወንጌልን ሲሰብክ በአደባባይ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ፍጹም ጌታውን የመሰለ ታላቅ ሐዋርያ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ እየተዘዋወረ ሲያስተምር በወንጌል የወለዳቸውን ክርስቲያኖች ከልዩ ልዩ ፈተናዎች ለማጽናት ሲል ሁለት መልእክታትን ጽፏል። የመጀመሪያ መልእክቱን የጻፈው አይሁድ ለሚያሳድዷቸውና መከራ ለጸኑባቸው ከእስጢፋኖስ ሰማዕትነት በኋላ በስደት ለተበተኑ ክርስቲያኖች ነው። ሁለተኛውን መልእክቱን የጻፈበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የሮማ ግዛት መሪ የነበረው ኔሮን ቄሣር ክርስቲያኖች ሁሉ እየተያዙ እንዲፈረድባቸው አዋጅ ነግሮ ነበርና በዚሁ ምክንያት ለተጨነቁ በእስያ ላሉ ክርስቲያኖች ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሐሰተኞች መምህራን ተነሥተው በሐሰተኛ ትምህርታቸው ስላስጨነቋቸው ለማጽናት ጽፎላቸዋል።

በታናሽ እስያ እየዞረ በቃልም በመጣፍም ካስተማረና አማንያንን በመከራ እንዲጸኑ ካደረገ በኋላ በስተመጨረሻ ወደ ሮሜ ገብቶ ያስተምር ጀመረ። በዚህ ጊዜ ኔሮን ቄሣር አስይዞ አሳሰረውና በስቅላት እንዲቀጣ ተፈረደበት። ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት መፈረዱን በሰማ ጊዜ ጌታችን፡- “በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል” ያለውን ቃል /ዮሐ.21፡18/ ትዝ አለውና “አላውቀውም ብዬ መካዴን ሳያስብብኝ በዚህ ፍጹም ይቅርታ ያደርግልኛል” በማለት እጅግ ደስ አለው፡፡ የሚሰቀልበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከግዞት ቤት አውጥተው ሲወስዱት፡- “ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ እኩል እንዳልሆን ራሴን ወደ ታች ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ” ብሎ ለመነ፡፡ እነርሱም እንደለመነው አድርገው ሰቅለው ገደሉት፡፡ የተሰቀለውም ሐምሌ አምስት ነው፡፡ ይህን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡


በአጠቃላይ የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት ታሪክ በአጭሩ ከላይ የቀረበው ነው፡፡ ከዚህ ቅዱስ አባት ሕይወት ብዙ የምንማረው አለ፡፡ አንድ ጊዜ ባጠፋው ጥፋት ሁል ጊዜ እየተጸጸተ የጌታውን ይቅር ባይነት ተስፋ ሳይቆርጥ በመረረ አንብዓ ንስሐው ይቅርታን ስላገኘ ለዘመኑ ተነሳሕያን (ንስሐ ለሚገቡ) ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት መተላለፉን የቀረችለት፣ ኃጢአቱ የተከደነችለት፣ በደሉን የማይቆጠርለት ሰው ምስጉን ነው እንዳለ /መዝ.31፡1-2/ እስከ ሞት ድረስ ፍቅሩን በመግለጽ ሰማዕትነትን በሮማ አደባባይ እስከተሰቀለበት ድረስ የአይሁድን ዱላ ፈርቶ በቀላሉ አላውቀውም ብሎ ለካደው አምላክ በቆራጥነትና በታማኝነት ቁልቁል እስከ መሰቀል የደረሰ ታላቅ ሐዋርያ ነው፡፡
ጸሀፊ ቤተ ማርያም
ጸሎቱና በረከቱ በእኛ በሕዝበ ክርስቲያን ላይ አድሮ ይኑር አሜን፡፡

Thursday, December 6, 2012

ክብረ መላዕክት (በአጭሩ)

በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ አሜን!
የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ‹‹ክብር›› የሚለውን ኃይለ ቃል ሲተረጉም ‹‹ጌትነትንና፣ ከፍተኝነትንና ብርሃንነትን፣ ዋጋንና ጥቅምን አጠቃሎ ይዟል›› ይለናል፡፡
ክብር እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክትን በተመለከተ ግን ‹‹ከፍተኛነትን፣ ብርሃንነትን፣ ዋጋና ጥቅምን አጠቃሎ ይዟል›› የሚለው ሐረግ በቀጥታ ይመለከተታቸዋል፡፡
- ክብራቸው- የእግዚአብሔር ሠራዊት በመሆናቸው፡፡
- ከፍታቸው- ሰማያውያን መሆናቸው፡፡
- ብርሃንነታቸው- በሥነ - ተፈጥሮአቸው፡፡
- ዋጋና ጥቅማቸው- በአገልግሎታቸው ይታወቃል፡፡
ክብራቸው
የክብር ምንጭ እግዚአብሔር ሲሆን መላእክቱ ደግሞ የክብሩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ መላእክቱ ሲገለጡ የእግዚአብሔር ክብር እንደሚታይ መጽሐፍ ቅዱስ ያስነብበናል፡፡
‹‹እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፣ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ›› (ሉቃ. 2÷9) እንዲል፡፡ ‹‹አክባሪ ከአከበረ፣ ንጉሥ ካስገበረ›› እንዲሉ የአክባሪው ጌታ ክብር በላያቸው ሲያርፍ ቅዱሳን መላእክትን እንደሚገባ መጠን ያላከበረ የእግዚአብሔር ክብር ያልገባው ነው፡፡
ከፍታቸው
የቅዱሳን መላእክት ከፍታቸው እግዚአብሔር፣ መኖሪያቸውም በከፍታ (በሰማይ) በመሆኑ ከፍ ከፍ ያሉ ናቸው፡፡
ብርሃንነታቸው
የመላእክት ብርሃናዊነት ብሩህ አእምሮ፣ ብሩህ ተፈጥሮ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ቅዱሳን መላእክት በተገለጡበት ሥፍራ ጨለማ፣ እነርሱ በገለጡበት ልቦና ድንቁርና የለም፡፡
ለበለዓም የቀና መንገድ፣ ለዕዝራ የዕውቀት ጽዋ፣ ለዳንኤል የጥበብ ፍቺ፣ ለቆርኖሌዎስ የመዳን ሚጥስር ጉዞ፣ ለአባታችን ለኃብተ ማርያም የመጻሕፍት ትርጉም….. የሆነላቸው በመላእክት ብርሃናዊ አጋዥነት ነው (ዘኁ. 22÷35 ትን. ዳን. 9÷21 ሐዋ. 1÷3 ገድለ አቡነ ኃብተማርያም)፡፡
ዋጋና ጥቅማቸው
ዋጋና ጥቅማቸው አገልግሎታቸው ነው፡፡ ዋና አገልግሎታቸው እግዚአብሔርን ማመስገን ነው (ኢሳ. 6÷1-3 ራዕ. 5÷11)፡፡ ምሥጋናቸው እረፍታቸው፣ እረፍታቸው ምሥጋናቸው በመሆኑ ሲያመሰግኑት ‹‹ቀንና ሌሊት አያርፉም (አያቋርጡም)›› (ራዕ. 4÷8)፡፡
ቀጥሎ ያለው አገልግሎታቸው ‹‹መዳንን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው መላክ ›› ነው (ዕብ. 1÷14)፡፡ ከአዳም ውድቀት በፊት የመላእክት አገልግሎት ምሥጋና ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የቆመውን ሲያበረቱ፣ የወደቀውን ሲያነሱ፣ ንስሐ በገባውም ሲደሰቱ ከሰው ልጆች ጋር ልዩ ፍቅር፣ ፍጹም ሕብረት አላቸው (ትን. ዳን. 1÷11 መዝ. 9÷12 ሉቃ. 15÷1)፡፡
የተሟላ መልእክተኛ አድርሶ ተመላሽ ብቻ ሳይሆን አድርሶ መላሽ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት በአገልግሎት የተሟሉ በመሆናቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመልእክት፣ ለእርዳታ የሚላኩ ብቻ ያይደሉ የእኛንም ጸሎት፣ ስእለት፣ እንደሚያሳርጉ የማኑሄ መስዋእት እና የዮሐንስ ራዕይ መስክረውታል (መሳ. 13÷2ዐ፤ ራዕ. 8÷4)፡፡
ሌላው አገልግሎታቸው ደግሞ ጸሎትና ምልጃ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ ላይ የመላእክት ጸሎት እና እርዳታ ያለውን ጉልህ ድርሻ ወለል አድርጎ ያሳየናል፡፡ ጌታ የመላእክትን የምስጋናቸውን ብቻ ሳይሆን የልመናቸውን ድምጽ ይወዳል፡፡ ይህንንም በጥልቀት ለመረዳት የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጽሑፋትን ማንበብ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ትንቢተ ዳንኤል ስለ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹በዚያ ዘመን ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል›› ይለናል (ትን. ዳን. 12÷1)፡፡ መቆም፡ - ጸሎት፣ ልመና በመሆኑ ‹‹ስለሕዝብህ ልጆች›› የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ በወንጌል እንደተጻፈ የሐዋርያት ሕይወት እንዲዝል፣ እንደ ስንዴም እንዲበጠር ሰይጣን ለክፋቱ ጌታን ከለመነ እንደመገበሪያ ስንዴ እንድንነጻ ደግሞ ለደግነታቸው መላእክት እንዴት አይለምኑም? ይለምናሉ፣ ይጸልያሉ እንጂ!
የእውነት መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ›› ብሏል፡፡ (ሉቃ. 1÷19)፡፡ ቅዱስ ገብርኤልን ያህል መልአክ ቆሞ ካልማለደ ዛሬ የገብርኤልን ጸሎት ማን ይተማመን ነበር? መቆም መጸለይ ነው፡፡ ጸሎትም የመላእክት ሥራ (አገልግሎት) ነው፡፡ እንኳን መልአክ ነጋዴ በአቅሙ ‹‹ያለ ሥራ መቆም ክልክል ነው›› ይላል፡፡
በዮሐንስ ራዕይ ተጽፎ እንደምናነበው ሰባቱ ታላላቅ (ሊቃነ) መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ (ይጸልያሉ) (ራዕ. 8÷1)፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መቆማቸው የአገልግሎታቸው አንዱ ክፍል ነው፡፡
ሥልጣናቸው
ሹመት ኃላፊነት ሲሆን ሥልጣን ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ኃይል ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት ‹‹አለቅነት›› ወይም ‹‹ሥልጣን›› እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡም በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም›› ይላል (2 ጴጥ. 2÷11)፡፡
መላእክት የስድብን ፍርድ ቢመልሱ ዛሬ ተሳዳቢ አይኖርም ነበር፡፡ የእነርሱ ሥልጣን ግን ከቁጣ ትዕግስትን፣ ከፍርድ ምህረትን፣ ከግደል ይቅር በልን፣ ከአጥፋ መልስን ያስቀድማል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹የስድብን ፍርድ አያመጡም›› የተባለው፡፡ ደፋሮቹና ኩሩዎቹ ግን መላእክቱ ፍርድን ሳያመጡባቸው እራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስ በመቀጠል ‹‹በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፣ የአመጻቸውንም ደመወዝ ይቀበላሉ›› ብሏል (. 12)፡፡ በመላእክት ጸሎት የማይድን አመጽ፣ የማይሰበር ኩራት ምንኛ ከባድ ነው?
የቅዱስ ሚካኤል ሥልጣን
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤል ፊት ስለላከው መልአኩ ስለ ቅዱስ ሚካኤል እንዲህ መስክሯል፡፡
‹‹በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ፣ ወደ አዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፣ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኀጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት›› (ዘጸ. 23÷2-21)፡፡ ይቅር ማለት ወይም አለማለት የእግዚአብሔር ገንዘብ ሲሆን ጌታ ራሱ‹‹በፊቱ ተጠንቀቁ፣ ቃሉን አድምጡ፣ ኃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት›› እያለ ለመልአኩ የሰጠውን ሥልጣን አከበረ፡፡ አክባሪው በአከበረው፣ ሿሚ ሥልጣን በሰጠው ይተማመናል፡፡ ለምን? የሚል ቢኖር ግን እግዚአብሔር በሥራው ስህተት የለውምና ይግባኝ አይጠየቅም!
የቅዱስ ገብርኤል ሥልጣን
ልጅ አጥቶ እድሜው የገፋው ካህኑ ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ ይነግረው ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮለት ነበር፡፡ ካህኑ ግን በመጠራጠሩ ቅዱስ ገብርኤል የሚቀጥለውን እንደተናገረ እናነባለን፣ ‹‹እንድናገርህም፣ ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር››፡፡ ይህ ቃል መልአኩ የተላከው ለብስራት ዓላማ ብቻ እንደነበር ያሳምነናል፡፡ መልአኩ ግን በመቀጠል እንዲህ አለ ‹‹እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፣ መናገርም አትችልም›› (ሉቃ. 1÷19-20)፡፡ መልአኩ የተላከው ለብሥራት ሲሆን ‹‹ቃሌን›› አላመንህም ብሎ አንደበቱን የዘጋው በሥልጣኑ አይደለምን? ነው ወይስ አንደበቱን የሚዘጋበትን ፈቃድ ለማግኘት ወደ ላከው ጌታ ይመለስ? ሥልጣን ኃይል ነው!
ቅዱሳን መላእክት በተሰጣቸው ሥልጣን በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚፈጽሟቸው አዎንታዊ ድርጊቶች ብዙዎች ናቸው፡፡
አዘጋጅ መቅረዝ ዘተዋህዶ በመምህር ቃለአብ ካሳዬ
 የቅዱሳን መላእክቱ ጥበቃ፣ ጸሎትና ምልጃ አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!