Monday, November 19, 2012

ሰማእት መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
  “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ!!!!” ማቴ. ፲፬፡፰ /14፡8/
  በዚህ ዕለት “የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።” መዝ.115/116፡15 እንዲል ወንጌል መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገቱ የተሰየፈበት ዕለት መታሰቢያ ክብረ በዓል ነው።
“እኔም ለዚህ ነገር አዋጅ ነጋሪና ሐዋርያ በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ ለመሆን ተሾምሁ፤ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም።” ፩ጢሞ.፪፡፯/1ጢሞ.2፡7/
  እንዲል ወንጌል ሐዋርያው ሰማዕት መጥመቀ መለኮት ቅዱስ
ዮሐንስ ንጉሱን ሳይፈራ ከአምላኩ የሕይወትን አክሊል ከሰጪው እግዚአብሔር ሊቀበል እውነትን ሰበከ፤ እውነትን አስተማረ። እንዲህም ሲልም ጨኸ፤ “በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ።” ማቴ.፫፡፩-፬ /ማቴ.3፡1-4/ /ማር.፩፡፩-፮ /ማር.1፡1-6/ ዮሐ.፩፡፳፫ /1፡23/
“ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።” ዮሐ.፩፡፳፫ /1፡23/
  ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን። የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። ወጥታም ለእናትዋ። ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች። ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። ማር.፮፤፲፯-፳፱ /6፡17-29/ ማቴ.፲፬፡፩-፲፫ /ማቴ.14፡1-13/
  “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” ራዕይ ፪፡፲ /2፡10/ እንዲል ወንጌል አንገቱ ለ15 ዓመታት ክንፍ አውጥታ አስተምራ ሚያዝያ 15 አርፋለች። ክብሩ እንደምን ነው ቢሉ ጌታውን ለማጥመቅ በመብቃቱ ጌታም #አማን እብለክሙ ኢተንስአ እምትውልደ አንስት ዘየዐብዩ ለዮሐንስ# ትርጉሙም “እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም” ማለት ነው። (ማቴ.11፡11) ብሎ ጌታ መስክሮለታል። በተስፋ ያመነው በቃልኪዳኑ የተማጸነውን እስከ ፶ (50) ትውልድ ሊምርለት ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።
"ኪዳንየ ተካየድኩ ምስለ ሕሩያንየ"  (መዝ.88/89፡3) 
  “ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። ማቴ.፭፡፲፩-፲፪/5፡11-12/ ከቅዱስ ዮሐንስ ረድኤትና በረከቱን ይክፈለን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

No comments:

Post a Comment