Thursday, August 27, 2015

መንፈሳዊ ተጋድሎ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: 
1.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ምን ማለት ነው?


መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት - አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ÷ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነፃ ፈቃዱ ወስኖ፥ በሙሉ ልቡናው፥ በሙሉ ኃይሉ የሚያደርገው የውስጥና የውጭ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፥ ጥረትና ትግል ነው፡፡
ሀ. ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው፡፡
ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም›› ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማያቋርጥ ጦርነት ነው፡፡ (ገላ 5፥12) ታላቁ አባት ኢዮብም ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ?›› በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿአል፡፡ ይህም ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው፡፡ ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል፡፡
ይህ ሲባል ግን ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ሥጋ በራሱ ርኵስ አይደለምና፤ ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰውን (ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው) ከፈጠረ በኋላ ‹‹ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡›› ተብሏል፡፡ (ዘፍ1፥31) ሥጋ ርኵስ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ወልድ (ቃል) ‹‹ሥጋ ሆነ›› ባልተባለ ነበር፡፡ (ዮሐ 1፥14) አዳምና ሔዋን ከኃጢአት በንጽሕና ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፣ አይተፋፈሩም ነበር›› እንዲል (ዘፍ 2፥25)  ህፃናት፣ ልጆች  ሰውነት አላቸው ነገር ግን የኃጢአት ምኞት የላቸውም፡፡
ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ ተፈጥሮአዊና ንጹህ የሆነ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣  በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም/መግራት ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን በመጠቀም ይሠራል÷ ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ ‹‹ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ፡፡ (ዘዳ 32፥15)
ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ‹‹ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ›› እንዳለ፡፡ በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ (1ኛ ቆሮ 9፥27) በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ›› እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባናል፡፡
ለ. ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር እንጂ›› እንዳለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ሰው ከሰው ጋር በመጣላት የሚያደርገው ትግል ሳይሆን ጥንተ ጠላታችን ከተባለው በእባብ ወይም በዘንዶ ከተመሰለው ዲያብሎስና ከእርሱ ጋር ካሉት ሠራዊቱና መልእክተኞቹ ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ (ኤፌ 6፥12)
ከአዳምና ከሔዋን ከልጃቸውም ከቃየን ጀምሮ ሰይጣን የሰው ልጆችን ዘወትር ይዋጋል፤ ከዘላለም የሞት ፍርድ ሥር ሊጥል ይሠራል፡፡ በዚህም ውጊያው ከነቢያት ፤ከሐዋርያት ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ብዙዎችን ጥሏል፡፡
ዛሬም በገዛ ባሕርያችን የሚገኘውን ፈቃደ ሥጋ በመጠቀም፣ የራሱን በመጨመርና የተለያዩ ፈተናዎችን በማቀናበር ይዋጋናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፡፡›› እንዳለ ጠላት ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በኃጢአትና ሞት ሊውጥ ዘወትር ይተጋል፡፡ ማንም ሰው ደግሞ ከዚህ ፈተናና ውጊያ ሊያመልጥ አይችልም፤ ስለዚህ ሐዋርያት ‹‹በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት››፣ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡›› እንዳሉን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ለብሰን ልንዋጋው ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ 5፥8-9፣ኤፌ 6፥11)
ሐ. የሚመጣውን ዓለም ደስታ ተስፋ እያደረጉ ብቻ በዚህ ዓለም ሕይወት ከደስታ ውጪ መሆን ማለት አይደለም፡፡
ደስታ በራሷ የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆነች፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጠች፤ ንጹሕ ፈርጥ ነች፡፡ (ገላ 5፥22)
እውነት ነው፤ በዚህ ዓለም ስንኖር መከራ አለብን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ እስካለ ድረስ ከጨለማው ዓለም ገዢ ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ የሚመጣ ልዩ ልዩ ፈተናና ከሥጋችንም ባሕርይ ከሚገኘው ክፉ ምኞትና ርኵሰት ሥራ እንዲሁም ከሌሎቹ የኃጢአትና የፈተና ዓይነቶች ጋር በማያቋርጥ እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል ውስጥ መኖሩ የግድ ነው፡፡ መከራና ስቃይ፣ ትግልና ጦርነት የሌለበት በዘለዓለማዊ ደስታ ብቻ የሚኖርበት ሕይወት በሚመጣው ዓለም የሚገኝ ነው፡፡
በዚህ ምድር በጉዞ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን ጨርሳ ድል ከነሱት አባላቷ ጋር አንድ እስክትሆን ድረስ መከራው፣ እንቅፋቱ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ የግድ ነው፡፡ ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፡፡›› እንዲል (ሐዋ 14፥22)
ይህ ሲባል ግን በዚህ ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከደስታ የተራቆቱ ዘወትር በኅዘንና በስቃይ ብቻ የሚኖሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሚለዩትና ዘወትር ለመለየት ጥረት የሚያደርጉት የውሸት ከሆነው ኃጢአት (ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል) ከሚገኘው ደስታ እንጂ ከእውነተኛውና ከሰማያዊው ደስታ አይደለም፡፡
መንፈሳዊ ተጋድሎ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና ረድኤት መንፈስ ቅዱስ መሪና አስተማሪ፣ የሚያነቃቃና የሚያጽናና፣ የሚያርምና የሚገሥጽ፣ የሚረዳና የሚያጸና፣ በመሆን ስለ ክርስቶስ በክርስቶስ ጸጋ የሚከናወን በመሆኑ መከራንና ስቃይን በሚያስረሳ እውነተኛ ደስታና ሰላም የተሞላ ሕይወት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ስለ ክርስቶስ በማስተማራቸው ምክንያት ገዢዎች ልብሳቸውን ገፈው በበትር እንዲመቱ አዘዙ በበትር ከመቷቸውም በኋላ በወኅኒ ቤት ጣሏቸው እነርሱ ግን ከጀርባቸው ደም እየፈሰሰ በመንፈቀ ሌሊት እንኳን እግዚአብሔርን በመዝሙር ያመሰግኑ ነበር፡፡ እውነተኛውና ሰማያዊው ደስታ በልቡናቸው ሞልቶ ነበርና፡፡ (ሐዋ 16፥22-25)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐዋርያት እንዲህ ይለናል ‹‹ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው  በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቷቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፡፡››(ሐዋ 5፥40-41)
ቅዱስ ዮሐንስ ካሲያን የተባለው አባት በተጋድሎ በግብጽ በረሃ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩት መነኰሳት ሲናገር ‹‹ እነዚህ ምድራዊ መላእክት ናቸው፤ የግብጽን በረሀዎች በደስታ ወደ ተሞላ መዝሙርና እግዚአብሔርን የማመስገኛ ገነትነት ለውጠዋልና››  ብሏል፡፡
በአጠቃላይ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ከተድላ ሥጋ፣ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ በመሸሽ ሰማያዊና እውነተኘ በሆነ ሰላምና ደስታ ውስጥ መኖር ይህንንም ለማግኘት መጋደል ማለት ነው፡፡

2.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማው ምንድነው?
ሀ. የድል አክሊል (የዘለዓለም ሕይወት) ለመቀበል
እግዚአብሔር አምላካችን ሰዎች ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ከአምላካቸው ጋር መኖር ከመረጡ ሊሰጣቸው ያዘጋጀው ከመነገርና ከመታሰብ በላይ የሆነ የዘለዓለም  ሕይወት አለ፡፡ የሰው ልጅ ሕሊናዊ ነፃ ፈቃዱ ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ በየጊዜው እየደከመና ወደ ኃጢአት እያዘነበለ መጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ከብሮ ባየ ጊዜ ከአባቶቻችን ጀምሮ ዘወትር የሚቀና ክፉ ጠላትም (ዲያብሎስ) አለን፤ ባገኘው አጋጣሚ ስንፍናችንንና ድካማችንን እየተከተለ እነዚህንም በመጠቀም ዘወትር ከአምላካችን ሊለየን እንደሚተጋም ከላይ ተመልክተናል፡፡

ሽልማት፣ አክሊል የሚሰጠው ደግሞ ማሸነፍ ለሚችል ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ሰነፍና ቸልተኛ ሰው ግን ሊሸለም አይገባውም አንድ ሰው ጎበዝ ወይም ሰነፍ መሆኑ የሚታወቀው ደግሞ በፊቱ ያጋጠመውን ውድድር ወይም ፈተናና መከራ ማሸነፍና ማለፍ ሲችል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማ በገዛ ባሕርያችን ያለን መጥፎ የኃጢአት ዝንባሌና ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያመጣብንን ፈተናና ሽንገላ ከእግዚአብሔር ርዳታና ቸርነት ጋር ሕሊናን በማንቃት፣ ራስን በመግዛትና ጠንክሮ በመጋደል አምላካችን ያዘጋጀልንን የድል አክሊል የዘላለም ሕይወትን መቀበል ነው፡፡ ‹‹ የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል›› አንዲል (1ኛ ጢሞ 6፥12) ሐዋርያቅ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ መከራዎችን አልፎ ገድሉን በድል አድራጊነት ሲፈጽም ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል ( 2ኛ ጢሞ 4፥7-8)
ለ. ለመንፈሳዊ እድገት
ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለፍሬ የሚበቃው የድል አክሊልን መቀዳጀት የምንችለው የማያቋርጥ (የማይቆም) መንፈሳዊ ዕድገት ሲኖረን ነው፡፡ በጥምቀት ያገኘነው አዲሱ ሕይወታችን ዘወትር ማደግ ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በዛፍ ተክል ይመሰላል፡፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ፍሬ እስከሚያፈራለት ጊዜ ድረስ ያለው ድካም ቀላል አይደለም፡፡ የዛፉ ችግኝ እንዲያበቅል፣ እንዲለመልም፣ አንዲያብብና እንዲያፈራ አትክልተኛው ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ በየጊዜው ውሃ ማጠጣት፣ ማረምና መኰትኰት፣ ፀረ ዕፅዋትና ፀረ ሕይወት የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን አድጎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ዕለተ ዕለት ጠንክረን በትዕግሥት መሥራት በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናት ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ተጋድሎም ዓላማው መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያቀጭጩ  ከጸጋ እግዚአብሔርም የሚያራቁቱ ኃጢአትና የዲያብሎስ ፈተናን በመቃወም መንፈሳዊ ምግቦችንም በመመገብ አዲሱ ሕይወታችንን ማሳደግ ነው፡፡
                                                                                                 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቅዱስ ሰራባሞን የኒቅዩስ ሊቀ ጳጳስ - ሕይወቱና ተጋድሎው

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 
ቤተ ክርስቲያን በዓላውያን ነገሥታት አሰቃቂ ስደት በደረሰባት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕት ዓመታት ውስጥ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አንዱ የሆነውና ለዛሬው የተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የምንመለከተው ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞን ዘኒቅዩስ ነው። አባቱ አብርሃም ይባላል፤ አያቱ የቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ አጎት ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። ሲወለድ ወላጆቹ “ስምዖን” ብለው ስም አወጡለት፤ “ሰራባሞን” የጵጵስና ስሙ ነው። የዐረብኛ እና የግዕዝ መጻሕፍት “ሰራባሞን” ሲሉት፣ የቅብጥና እንግሊዝኛ ምንጮች ደግሞ “ሰራፓሞን” ብለው ይጠሩታል።

በተወለደበት በኢየሩሳሌም ሳለ ክርስቲያን መሆን አጥብቆ ይፈልግ ነበር። እመቤታችን በራእይ ተገልጻ ወገኖቹ አይሁድ እንዳይገድሉት ወደ ግብፅ ሄዶ እንዲጠመቅና አገልግሎቱንም በዚያ እንዲፈጽም ስለነገረችው ቤተሰቦቹን ጥሎ መነነ። ግብፅ ሲደርስ እመቤታችን የእስክንድርያ 16ኛ ፓትርያርክ የነበረውን አቡነ ቴዎናስን (282-300) ባዘዘችው መሠረት አስተምሮ አጠመቀው። የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜያት፣ የነቢያትንና ሐዋርያትን መጻሕፍት ተማረ፣ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳን እና የበልኪሮስን ድርሳናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠና።

ከዚያም ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ በሆነ እልሐብጡን በተባለ በአባ ሳዊሮስ ገዳም ውስጥ መነኮሰ። ከዘመናት በኋላ በተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ዘመን (300-311) የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፍ በእርሱ ምትክ የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መራ፤ ከገድሉ እንደምናነበው ወደ ተመደበበት ሀገረ ስብከት ሲገባ የተደረገለት አቀባበል የደመቀ ከመሆኑ የተነሣ ጌታ በሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ታጅቦ ሲገባ እንደተደረገለት የሚመስል ነበረ። በቅዱስ ሰራባሞን አገልግሎት በኒቅዮስና በአጎራባች ከተሞች የነበሩ ጣዖታት ተሰባብረው ወድቀዋል፤ በእጁ በርካታ ገቢረ ተአምራት ተደርገዋል፤ በመስቀሉ አጋንንትን አባሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ስለ ወንጌል ብዙ መከራን ተቀብሏል፤ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ብዙ ዘለፋ ደርሶበታል። አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና ሚሊጦስ በእርሱ ዘመን የነበሩ መናፍቃን ናቸው። የአርዮስ ዋና ክህደት “ወልድ (ክርስቶስ) ፍጡር ነው” የሚል ሲሆን ሚሊጦስ ደግሞ “ከማርያም የተወለደው ክርስቶስ በምትሐት ነው እንጂ በእውነት አይደለም” የሚል ነበር። ሰባልዮስ “እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው” ብሎ የሚያስተምር ሲሆን፤ ሰራባሞን ሁሉንም ተከራክሮ ረቷቸዋል።

በዚህ የተነሣ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። አርዮስና ሚሊጦስ የሚያስተምረውን ባለመቀበላቸው በክፋታቸው ጸንተው ብዙዎችን እያሳቱ፣ በትዕቢታቸውም ልባቸውን እያኮሩ ቢያገኛቸው በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ የአርዮስና ሚሊጦስን አንገታቸውን በመሐረብ ይዞ “እናንተ አባታችሁን ዲያብሎስን በክህደት የምትመስሉ እስከ መቼ ድረስ ነው በዚህ ክህደታችሁ ሰውን የምታጠፉ?” ብሎ ገስጿቸዋል (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 130-137)። አርዮስ ከክሕደቱ የማይመለስ ከሆነ አንጀቱ ተበጣጥሶ እንደሚሞት፣ ሚሊጦስም ካልተመለሰ ሥጋውን በቁሙ ዕፄያት እንደሚበሉት ትንቢት ተናግሮባቸዋል። እምቢ በማለታቸው በሁለቱም ላይ ይኸው ተፈጽሞባቸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅልጥያኖስ (284-305) የሚያፈርሳትን ቤተ ክርስቲያን ሰረባሞን ሲሰራ፣ ጣዖት የሚያመልኩትንም ሰዎች በክርስቶስ ስም ሲያሳምናቸው ንጉሡ እና መኳንንቱ ስጋት ጨመረባቸው። ሰራባሞን እንዲታሰር እና ስለ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳያስተምር በእስክንድርያው ገዢ አውጣኪያኖስ፡ ኮሞስ፡ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ሰራባሞን ግን ከአቋሙ አልተናወጸም። ስለዚህ እስር ቤቱን አንዴ በታሕታይ ግብጽ አንዴ ደግሞ በላዕላይ ግብጽ በበረሃው ሁሉ በማፈራረቅ አሰቃዩት። እርሱ ግን ስቃዩንና ዛቻውን ከምንም ሳይቆጥር በእስር ቤት ውስጥም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳምኗል። የላዕላይ ግብፅ ገዢ የነበረው አርያኖስ (ከከሐዲው አርዮስ የተለየ እና የሀገረ እንጽና ገዢ የነበረ) ብዙ ካሠቃየው በኋላ በኒቅዩስ ከተማ ወደብ አቅራቢያ አንገቱን እንዲቆርጡት ትዕዛዝ ሰጠ። የሚጓዙበት መርከብ ግን አልንቀሳቀስም አለ። ቅዱስ ሰራባሞንን ከመርከቡ ሲያወርዱት በሰላም ሄዱ። በዚህ ሁኔታ እያለ እንኳን ወንጌልን መስበክና ትንቢት መናገርን አልተወም።

ይህ በእርሱ ላይ የሞት ውሳኔ የሰጠበት አርያኖስ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስን ክዶ ክርስቲያን እንደሚሆን በመጨረሻም ሰማዕትነትን ተቀብሎ እንደሚሞት፣ እንዲሁም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት እንደሚሞትና “ተፍጻሜተ ሰማዕት” እንደሚሆን እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፥ “ወበከመ፡ ጴጥሮስ፡ ቀዳማየ፡ እምሐዋርያት፡ ከማሁ፡ አንተኒ፡ ትከውን፡ ተፍጻሜተ፡ ሰማዕት። ናሁ፡ አቅደምኩ፡ ነጊሮተከ፡ ዘይከውን፡ በጊዜሁ።” (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 158)። እንደ ትንቢቱም ሁሉም ተፈጽሟል። በመጨረሻም ከሀገረ ስብከቱ ኒቅዩስ በስተደቡብ በምትገኘው ቦታ ወስደው ኅዳር 28 ቀን (በቅብጥ አቆጣጠር ሐቱር 28 ቀን) አንገቱን በሰይፍ ቀሉት።

ደቀመዛሙርቱ አስከሬኑን በመንገድ ላይ እንዳልባሌ ነገር ተጥሎ ሲያዩት በመረረ ሐዘን ተውጠው እያለቀሱ “እረኛችን ሆይ ለማን ታስጠብቀናለህ? አባታችን ሆይ እንግዲህ ማን ይሰበስበናል? አውሬ ከቦናል፣ በወንጌል ኮትኩተህ ያሳደግከው ተክልህን ከእንግዲህ ማን ይንከባከበው?” እያሉ መሪር እንባን ያነቡ ነበር። ከብዙ ለቅሶ በኋላ አስከሬኑን ወስደው በኒቅዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር አሳረፉት (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል166)።

ከገድሉ እንደምናነበው ሰራባሞን ባደረገው ተጋድሎና በጽንአቱ በርካታ የክብር ስሞችና ቅጽሎች ተሠጥተውታል። ዋና ዋናዎቹም፥ “ብፁዕ ወቅዱስ ሰማዕት”፣ “ለባሴ መንፈስ”፣ “ለባሴ፡ አምላክ”፣ “ዓምደ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ሐረገ ወይን”፣ “ሐዲስ ዳንኤል”፣ “ላዕከ መንፈስ ቅዱስ”፣ “ሙሴ ሐዲስ”፣ “ጳውሎስ ዳግመ”፣ “ዮሐንስ ሐዲስ”፣ “መስተጋድል ዐቢይ” የሚሉት ናቸው።

በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በስሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ታንጸዋል፣ ገድል ተጽፎለታል፣ በስንክሳርም ይዘከራል። ገድሉ እና የሰማዕትነቱ ዜና በቅብጥ እና ዐረብኛ ቋንቋ የተጻፈና የተተረጎመ ሲሆን ሁሉም ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አልተገኘም። የቅብጡ ቅጂ በHyvernat, (ገጽ. 304-31) የታተመ ሲሆን የዐረብኛው ደግሞ (Kairo 27 በሚል ዝርዝር) በKraf (1934:12) ካታሎግ ተሠርቶለታል። በቅርቡ ደግሞ Youssef (2013: 263-280) የሚባል ተመራማሪ “ሰራባሞንን የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን ምንባባት” ብሎ ጥናታዊ ጽሑፍ አውጥቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያነ የቅዱስ ሰራባሞን ዜና ሕይወት እና ተጋድሎ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን እምብዛም ጎልቶ የሚታወቅ ባይሆንም በሕዳር 28 ስንክሳር ይታወሳል። ከዚህም በላይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገድሉ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1408-1497) ተተርጉሞ ይገኛል። ይህም ገድል አሁን ከሚገኙት የቅብጥና ዐረብኛ ቅጂዎች ይልቅ የተሟላ እና ይዘቱም ሰፊ ነው። ይህ ገድል በ1970ዎቹ ውስጥ (EMML 6533) በሚል መለያ ማይክሮ ፊልም ተነስቷል።

ብራናው አጠቃላይ 168 ቅጠል ያለው ሲሆን ከመጀመሪያ እስከ 118 ድረስ የሐዋርያው ጳውሎስ ገድል፣ ከቅጠል 119-167 ድረስ ደግሞ የሰማዕቱ ሰራባሞንን ገድል ይዟል። የሰራባሞን ገድሉ አራት ክፍሎችን ይዟል፤ እነዚህም፥ 1) ድርሳን (ከቅጠል 119-131)፣ 2) ገድል (ከቅጠል135-142)፣ 3) ተአምር (ከቅጠል 132-149)፣ 4) ስምዕ (ከቅጠል 150-167) የሚሉ ናቸው። ይህም ስለ ሰራባሞን የሚጠናውን ጥናት ይበልጥ የተሟላ የሚያደርግና በተለይ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ለዜና አበው እና ለነገረ ቅዱሳን የጥናት መስክ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ከስንክሳሩና ከገድሉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሰራባሞን የተዘጋጁ ልዩ ልዩ አርኬዎች (Chaîne ቁ. 48 እና Wein፣ Athiop. 19 [በN.Rhodokanakis አማካይነት ካታሎግ የተሠራላቸው])፣ እንዲሁም ሁለት የተለያዩ መልክአት (Chaîne ቁ. 158 እና 325) ተዘጋጅተዋል። በኢትዮጵያው የገድል ቅጅ ላይ እስካሁን የተደረገ ጥናት የለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ መነሻ ጥናት አድርጎ ገድሉንም እየተረጎመ ይገኛል።

ይህን ጽሑፍ የምንደመድመው በቪየና የሚገኘው ብራና (Vienna ms f.62v-63r) ስለ ቅዱስ ሰራባሞን ከሚያመሰግነው አርኬ ውስጥ አንዱን በማንበብ ይሆናል፤
ለከ፡ ስነ፡ ሰረባሞን፡ ዘኤፍራታ፤
ነጺሮሙ፡ ጥቀ፡ ለሕሊናሁ፡ ጥብዓታ፤
ከመ፡ ይከውን፡ ሰማዕት፡ ውስተ፡ ዓውደ፡ ግሩም፡ ሐተታ፤
ገደፈ፡ አብ፡ እጓሎ፡ ወእም፡ ወለታ፤
ወሐማትኒ፡ ሐደገት፡ መርዓታ።
የሰማዕቱ ሰራባሞን በረከት ይድረሰን!!!
ስምዓት
  • መጽሐፈ ስንክሳር - በግዕዝና በአማርኛ (ከመስከረም እስከ የካቲት)፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1994 ዓ.ም.
  • ገድለ ጳውሎስ ወሰራባሞን - (EMML 6533)- ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝ፣ በ15ኛው መ/ክ/ዘ/ የተጻፈ ብራና (እስካሁን አልታተመም)።
  • Amsalu Tefera, 2013, “Gädlä Särabamon: the case of the Ethiopic version”, a paper read on a workshop titled “EMML@40: The Life and Legacy of the Ethiopian manuscript microfilm Library” organized by Hill Museum & Manuscript Library, Saint John’s University, Collegeville, MN, USA, July 25-26, 2013.
  • Budge, Wallis, 1928, The Book of the Saints of the Ethiopian Church: a translation of the Ethiopic Synaxarium መጽሐፈ፡ ስንክሳር፡ made from the manuscripts Oriental 660 and 661 in the British Museum, vol. I, Cambridge at the University Press.
  • Chaîne, M., 1912, “Catalogue des manuscrits Ethiopiens de la collection Antoine d’Abbadie”, Paris.
  • Chaîne, M., 1913, “Répertoire de salam et Melke’e contenus dans les manuscrits éthiopiens des bibliotheques d’Europe” in Revue de L’Orient Chrétien, , deuxieme Serie, Tome viii, no. 2
  • Colin, G. 1988, “Le Synaxaire Éthiopien mois de Ḫedār” in Patrologia Orientalis, Tome 44, fascicule3, no. 99)
  • Coptic Synaxarium, reading on Hatour 28, – retrieved online -http://popekirillos.net/EN/books/COPTSYNX.pdf, accessed on May 14, 2012.
  • Hayvernat, Henry, Les Actes des martyrs del’Égypte, retrieved online from http://www.archive.org.detailes/lesactesdesmarty01hyve - accessed on November 6, 2012.
  • Kraf, George, 1934, Catalogue de manuscrits Arabes Chrétiens conserves au Caire, studi e testi 63, Città del Vaticano Biblioteca Apostolica Vaticana
  • Rhodokanakis, N. 1906, Die Äthiopischen Handscriften der K. K. Hofbibliothek zu Wein, Wein Athiop. 19.
  • Youssef, 2013, “Liturgical Texts Relating to Sarapamon of Nikiu”, Peeters Online Journal, pp. 263-280.
  • ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
    የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ