Monday, November 24, 2014

አባ ሕርያቆስ

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አባ ሕርያቆስ በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይመልሳልና ብለው ግብረ ገብም ከሆነ ይሾም ብለዋል፡ በጸሎቱ ይጠብቃል..

''ሕርያቆስ ማለት'' :- ህሩይ ማለት ነው ፡ ለሹመት መርጠውታልና: አንድም ረቂቅ ማለት ነው ምሥጢረ ሥላሴን ይናገራልና ፡ ከሊቃውንትስ ምሥጢረ ሥላሴን የማይናገር የለም ብሎ ከሁሉ ይልቅ እሱ አምልቶ አስፍቶ አጉልቶ ይናገራልና አንድም ፀሐይ ማለት ነው፡ አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ ብሎ ጽፏልና : አንድም ብርሃን ማለት ነው፡ የምዕመናንን ልቦና በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና ፡ ዘአብርሃ መንበረ ማርቆስ በብርሃን እንዲል ፡አንድም ንብ ማለት ነው፡ ንብ የማይቀምሰው አበባ የለም እሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለም፡ይህም እንደምን ነው ቢሉ፡ ሐዋርያት የተማረ ግብረ ገብ ይሾም ብለው ሥራት ሰርተዋል፡ይህስ አይደለም ሁለቱን አስተባብሮ የያዘ አይገኝም ብሎ የተማረ ከሆነ ይሾም ብለዋል::በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይመልሳልና
ብለው ግብረ ገብም ከሆነ ይሾም ብለዋል፡በጸሎቱ ይጠብቃል: በትሩፋቱ ያጸድቃል:ትምህርቱን ውሎ አድሮ ያደርገዋልና ብለው ሾሙት ፡ይህም አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ግብረ ገብ ነው ፡ ቢማርም ለጸሎት ለቅዳሴ ያህል ነበር፡በብህንሳ በ10000  መነኮሳት በ10000 መነኮሳይያት ተሹሟል በብዙም መሾም ልማድ ነው፡፡

አባ ሆርና አባ ኤስድሮስ በ1000 አባ አሞን በ3000 አባ ጳኩሚስ በ6000 አባ ሰራብዮን በ10000 ተሾሙ:ይህችም ብህንሳ ቅድመ ትሰይም አርጋድያ ወድህረ መኑፍ ይላል: ብዙ ግዜ ስመ ተፋልሶ አግኝቷታል :በፊት አርጋድያ ኋላም መኑፍ ተብላለች ዛሬም ብህንሳ ትባላለች:ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ናት:እንደ ዘጌ እንደ ቆራጣ እንደ ቀንጠፋሜእርሱም ግብረ ገብ ነውና ሥራት ቢያጸናባቸው ይጣሉታል:ያልተማረ ነውና ይንቁታል:ከመጠምጠም መማር ይቅደም እንዲሉ ከመሾም መማር አይቀድምምን እያሉ; እሱ ግን ወእቀውም ዮም በትህትና ወበፍቅር ብሎ እንዲያመጣው: እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር እና በትህትና ጸንቶ ያስተምራቸው ነበር::


ከዕለታት ባንዳቸው በምን ምክንያት እንሻረው አሉ:ቀድሰህ አቁርበን ብለን በዚህ ምክንያት እንሻረው ብለው መክረው ቀድሰህ አቁርበን አሉት: የሱ ግን ተምኔቱ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤቴ ምስጋና እንደ ባህር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግበው እንደመጠጥ ጠጥቼው እንደ ልብስ ለብሼው እያለ ይመኝ ነበር፡ ቅዳሴ ገብቶ ሥርዓቱን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግር የማንን እናውጣለት እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ የለመኗትን የማትነሳ የነገሯትን የማትረሳ እመቤታችን ገልጻለት ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ብሎ ወይእዜኒ ንሰብሐ እስኪል ድረስ ሰተት አድርጎ ተናግሮታል:የሚንቁት የሚጠሉት ይህ የነገሩትን ቀለም እንኳን አከናውኖ መናገር የማይችል ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እደርሳለው ብሎ አገኝ አጣውን የቆጥ የባጡን ይቀባጥራል: ብለው አደነቁበት የሚወዱት የሚያከብሩት ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲ ያለ ምሥጢር ከእሩቅ ብዕሲ ይገኛልን ብለው አደነቁለት፡ ወዲያው የሚወዱት የሚያከብሩት ጽፈን ደጉሰን አንይዘውምን አሉ፡ የሚንቁት የሚጠሉት ደግሞ ማን ተናገረው ብለን እንይዘዋለን አሉ እንደ ልማዱ አድርገን አንይዘውም አሉ:: ለሃገራቸው እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደሆነ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል: ከእሳት ደህና የወጣ እንደሆነ ከውሃ ይጥሉታል ከውሃ የወጣ እንደሆነ ከህሙም ላይ ይጥሉታል ድውይ የፈወሰ እንደሆነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል፡፡


ይህንንም ቅዳሴ ማርያም ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ላይ ጣሉት ከእሳት ደህና ወጣ፡ ከውሃ ጣሉት ከውሃ ደህና ወጣ፡፡ ከህሙምላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ: ይልቁንም ሙት አስነስቷል፡፡ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ጽፈው ደጉሰው ይዘውታል:በጥራዝም 14ኛአድርገው ጠርዘውታል: ከ14ቱ ቅዳሴም ተአምራት ያልተደረገበት የለም፡ የቀደሰበት ምን ቀን ነው ቢሉ፡ ከእመቤታችን ከ 33ቱ በዓላት ባንዱ ቀን ነው፡ አንድ ባህታዊ ከባለሟልነት የተነሳ ከ33ቱ በዓላት ማንን ትወጃለሽ ብሎ እመቤታችንን ጠየቃት:ኪዳነምህረትን ልደታን አስተርአዮን ፍልሰታን አለችው፡ ከሊህ ከ4ቱስ ማንን ትወጃለሽ ቢላት ከጠባብ ወደ ሰፊ: ከጨለማ ወደ ብርሃን: የወጣውበት ነውና ልደቴን እወዳለው አለችው፡ ቀድሞ እነ ሳልወለድ እናትና አባቴን መባችሁን አንቀበልም ብለው አዝነው ተክዘው ነበር፡ የነሱ ሃዘን ሃዘኔ ነውና እኔን ከወለዱ በኋላ መባቸውን ተቀብለዋቸው ደስ ብሎዋቸዋል: የነሱ ደስታ ደስታዬ ነውና እንዳለችው የልደታ እለት ነው የቀደሰው::እሱስ ማንን ሊቀድስ ኖሯል ቢሉ ከቅዳሴ ሐዋርያት ሌላ አያቅም ነበርና ቅዳሴ ሐዋርያትን፡ ይህስ አይደለም ለእመቤታችን ቅዳሴ ሐዋርያት ምኗ ነው: ምን ቢቸግር ተበድሮ ጋሬዳ እንዲሉ ቅዳሴ እግዚእን ሊቀድስ ነበር ስሟን ባያነሳ እምድንግል ተወሊዶ ከመ ፈቃድከ ይፈጽም ብሎ በምሥጢር ያነሳታል::


ከባህር ወዲህስ ማን አምጥቶልናል ቢሉ ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ መደባይ ታብር በሚባል ቦታ ይኖር ነበር እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን ከሶርያ አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ በደመና ጠቅሳ ያሬድ ካለበት አድርሳ አንተ ውዳሴዬን አንተ ቅዳሴዬ ንነግራችሁት በዜማ ያድርስ ብላቸው እነሱም ነግረውት በዜማ አድርሶታል፡፡ ከዚሁ አያይዞ 13ቱንም ቅዳሴ በዜማ ደርሷል: ይህም ሊታወቅ ሥረይ በቅዳሴ ማርያም ይበዛል::ከተከዜስ ወዲህ ማን አምጥቶልናል ቢሉ ሳሙኤል ትውልደ ጌዴዎን ዘገበዘ አክሱም ይለዋል እሱ አምጥቶልናል እሱም ይሄን እየደገመ ሲሄድ ክንድ ከስንዝር ከመሬት መጥቆ ይሄድ ነበር: ከዕለታትም በአንዳቸው ውሃውን ቢባርከው ህብስት ሆኖለት ተመግቦ ምዕመናንን መግቧቸዋል፡፡ እመቤታችንም የፍቅር ምልክት ሁለት ንዋያት ሰታዋለች ነጭ እጣን እና እንቁ ነው፡፡ ከዛም አያይዛ ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ ጋራ አንድ አድርጎ የሚደግመውን ሰው አንተ ከገባህበት ውሳጤ መንጦላዕት አገባዋለው:ብላ ተስፋውን ነግራዋለች:: ይህውም ሊታወቅ ዛሬ በዋልድባ ያጠና በቃሉ: ያላጠና በመጽሃፍ ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል የለም:ይህም ተስፋ ውዳሴዋን ከቅዳሴዋ ጋር አንድ አድርጎ ለምደግም ሰው ሁሉ ነው:እንጂለሱ ብቻ አይደለም:አንድ ባህታዊ ከምስጋናሽ ሁሉ ማንን ትወጃለሽ ብሎ ቢጠይቃት ልጄ ዳዊትን አቡነ ዘበሰማያትን ቢደግሙለት እንዲወድ እኔም ውዳሴዬን ቅዳሴዬን ቢደግሙልኝ ወዳለሁ ብላዋለች ::
አባ ሕርያቆስ ተሹሞ ሳለ ብዙ ድርሳንን ደርሷል ብዙ ተግሳጽ ጽፏል ከብዙውም አንዱ ይህ ቅዳሴ ማርያም ነው እረፍቱ በጥቅምት 2 ነው::
አኮቴተ ቁርባን ዘእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደርሰ በመንፈስ ቅዱስ አባሕርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሃገረ ብህንሳ ጸሎታ ወበረከታ የሃሉ ምስለ ኩሎሙ ህዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም አሜን፡፡
ኃጥያታችንን ከሚያስተሰርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን አሜን !!!!!: ምንጭ ፡- ቅዳሴ ማርያም አንድምታ

Monday, November 3, 2014

አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)


            በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
*እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል!
*ቅዱሱ አባታችን:- "ቡላ-የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን::
*ዳግመኛም "አቢብ-የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን::
+እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን::
*አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
*ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ!
*ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ!
*የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን::
+" ልደት "+
=>አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ::
+በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ: ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"
+" ጥምቀት "+
=>ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በሁዋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኩዋን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ 'አጥምቀው' አለችው::
+ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ: እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::
+" ሰማዕትነት "+
=>የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገውት ድንገት ሕዳር 7 ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ::
+በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ 18 ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል::
+" ገዳማዊ ሕይወት "+
=>ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በሁዋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ::
+ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው::
+" ተጋድሎ "+
=>አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል: ፊቱን በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል: ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል::
+በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር::
+የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነሕና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን" አለው::
"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ:
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ:
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል::
+" ዕረፍት "+
=>አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ10 ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::
+ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ 'አምላከ አቢብ ማረኝ' ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::
+" ታላቁ አባ ዕብሎይ "+
=>ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው:: ብዙ መጻሕፍት 'ርዕሰ ገዳማውያን' ይሉታል:: የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ በመሆኑ በዕለተ ዕረፍቱ (የካቲት 3 ቀን) እንመለከተዋለንና የዚያ ሰው ይበለን::
+" ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት "+
=>ከሁሉ አስቀደሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ (አድናቆት): ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::
+ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘ) ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ እንኩዋን የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ-የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: (መዝ. 78:3)
+እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና 300 አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::
+በወቅቱ የክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር::
በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::
+ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር::
+እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::
+ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ ወደ ሃገረ ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ::
+በፍጻሜውም መኮንኑ ቅዱስ ዮልዮስን ከቤተሰቡና ከ1,500 ያህል ተከታዮቹ ጋር: 2ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል::
=>አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን::
=>ጥቅምት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
2.አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
4.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
5.ቅዱሳን አሞኒና ሙስያ (የታላቁ ዕብሎ ወላጆች)
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
6.ታላቁ አባ ቢጻርዮን
=>+"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ:: መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል:: +"+ (ማቴ. 16:24)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
  
writing by dn yordanos abay

Sunday, October 5, 2014

(ዘመነ ጽጌ) ነገረ ማርያም


     "ልጄን ከግብፅ ጠራሁት" (ት.ሆሴዕ 11፥1 )
አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ አንዘ ትጎይዩ ምስሌሁ እም ሃገር በመዋእለ ሄሮድስ ርጉም።
አዘክሪ ድንግል አንብአ መሪረ ዘውኅዘ እማእይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ።
አዘክሪ ድንግል ረሃበ ወጽምአ ምንዳቤ ወሃዘነ ወኩሎ አጸባ ዘበጽሃኪ ምስሌሁ።
ትርጉም፡- ድንግል ሆይ፤ ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን ከርሱ ጋራ ከሃገር ወደ ሃገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋራ መሰደዱን አሳስቢ።
ድንግል ሆይ፤ ከአይኖችሽ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር አንባ አሳስቢ።
«ድንግል ሆይ ረሃቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ›› (ቅዳሴ ማርያም)
ጽጌ የሚለው ቃል የግዕዝ ሲሆን አበባ የሚል የአማርኛ ትርጉም አለው። ከመስከረም 26 ጀምሮ እስከ ሕዳር 6 ቀን ድረስ ያለው ወቅት “ወርሃ ጽጌ” የሚባል ሲሆን ስያሜው በአገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የክረምቱ ጨለማ ተገፎ ብርሃን የሚፈነጥቅበት፤ አበቦች ለዓይን ማራኪ የሆነውን ንጉስ ሰሎሞን እንኳን በክብሩና በጥበቡ ሊለብሰው ያልተቻለውን በእደ ሰብእ ያልተዘጋጀውን ውብ የሆነ ልብሳቸውን ተጎናጽፈው የሚመለከታቸውን ሁሉ ትኩረት የሚስቡበት፤ ለአፍንጫ ተስማሚ የሆነውን ጥዑም መዓዛቸውንም እንካችሁ ብለው ያለስስት የሚቸሩበት፤ አእዋፍ ዝማሬያቸውን ከወትሮው በላቀ ሁናቴ የሚያንቆረቁሩበት፤ ንቦች ከአበባ አበባ እየዘለሉ ጣፋጭ ማርን የሚያዘጋጁበት፤ ሁሉ አምሮ፤ ሁሉ ደምቆ፤ አዲስ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ፤ ይህን ጊዜ ወርሃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ፣ በመባል ይታወቃል፡፡
በወንጌል እንዲህ የሚል መልእክት እናገኛለን
“አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም።” ሉቃ 12፥27
አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ዕፅ በልተው የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደሉ፡፡ ከፈጣሪያቸው ጋር ራሳቸውን ለማስተካከል /አምላክ ለመሆን/ በማሰብና በመመኘታቸው ይቅርታ የማይገባውን ዓመጽ ፈፀሙ፡፡
በዚህም ምክንያት «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ» /ዘፍ. 2:18 / ተብሎ አስቀድሞ በተነገራቸው ሕግ መሠረትም:-
* ለሔዋን «በፀነሰሽ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛዋለሁ፣ በጭንቅ ትወልጃለሽ፣
* ለአዳም ደግም ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፣ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች. . . »/ዘፍ.3.15-19/ ተብለው ተረገሙ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣሉ፤ ከገነት ተባረሩ፤ የሞት ሞት ተፈረደባቸው፤ ሞት ሰለጠነባቸው፡፡አዳምና ሔዋን በበደሉት በደል ምክንያት ከገነት ከተሰደዱ በኋላ ከእግዚአብሔር የተለዩና የተዋረዱ ሆኑ። የሚወልዷቸው ልጆችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር የተለዩና የተዋረዱ የተረገሙ ስለነበር በተለያየ መልኩ መከራዎች ሁሉ የሚደርሱባቸው ሆኑ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቸርና ሩህሩህ አምላክ ስለሆነ የፈጠረውን ፍጥረት የማይንቅ፤ ስቃይን የሚመለከት ቸር አምላክ ነውና የአዳም ስቃይ ስላሳዘነው ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀለት፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነውና ወደ ቀደመ ክብሩ እንደሚመልሰው ቃል ኪዳን ገባለት። የዘመኑ ፍጻሜ /የቀጠሮው ቀን/ በደረሰ ጊዜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የእግዚአብሔር ቃል /ወልድ/ መጣ፤ ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፡፡ በዚያን ጊዜ ዮሴፍ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።
ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ምድራዊ ንግስናውን የሚነጥቀው መስሎት ደነገጠ፥ ተጨነቀ፤ ተጠበበ። ንጉስ ሄሮድስም አንድ ዘዴ አፈለቀ እሱም ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ከተረዳ በኋላ፥ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ላከ። እንዲህም ብሎ የሽንገላ ቃል ተናገራቸው። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ ብሎ አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ሰብአ ሰገልም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውንቀጠሉ። ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻአቀረቡለት፡፡የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡
«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለውይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡» /ማቴ. 2 13 14/
ታዲያ ይህ ሽሽት፤ ይህ የስደት ወቅት ዘመነ ጽጌ በመባል ይታወቃል። ዮሴፍም በህልሙ ከመልአኩ እንደተነገረው አህያውንና ስንቁን፤ እመቤታችንን እስከ ልጇ፤ ሰሎሜንም ጭምር ይዞ ጉዞውን ከእስራኤል ወደ ግብጽ ሐገር ሸሸ። መንገዳቸውን በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ፤ የሲናን በረሃ አቋርጠው ወደ ግብጽ ሐገር ሄዱ። በዚያን ሰዓት ውርጩ፤ ብርዱ፤ ርሃቡ፤ እንግልቱ በዝቶባቸው ነበር፤ ጉዞውም አስጨናቂ ነበር፤ ምግባቸውን ግን ከሰማይ መና እየወረደላቸው ይመገቡ ነበር። በዚህ ወቅት ደግሞ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር የደረሰባት እንግልት፤ ስቃይ፤ ርሃብ፤ ጥሙን ሁሉ የሚታሰብበት እለት ነው።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
writing by betemariam

Wednesday, September 24, 2014

እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን

      
           በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
‹‹ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ›› 1ኛ ቆሮ 1፤23
ይህን ኃይለ ቃል ቅዱስ ጳውሎስ ተናግሮታል፡፡ የቀድሞ ስሙና ምግባሩ ሳውልና አሳዳጅ ማለት ነው፡፡
ሳውሎ ገማልያ ከተባለ ከኦሪት ሕግ አዋቂ ጠንቅቆ የተማረ ስለ ኦሪት ሕግና ስርአት አብዝቶ የሚጨነቅ ነበር፡፡በዚህ ምክንያት የክርስቲያኖች መብዛት የክርስቶስ አምላክነት በብዙ ቦታ ሲሰበክ እጅግ አብዝቶ ይጠላ ነበር፡፡በተለይ በክርስቶስ የሚያምኑትን ወንዶችንም ሴቶችንም ሕጻናትንም ጭምር ወደ ወህኒ ቤት ለማስገባት ይጣደፍ ነበር፡፡ ሳውል ይህን ሁሉ የሚያደርገው እግዚአብሔርን ያስደሰትኩ እየመሰለው ነበር፡፡ከእለታት በአንድ ቀን በደማስቆ የክርስቲያኖችን መብዛትና ሰው ሁሉ በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ማመኑ እጅግ ስላስጨነቀው ክርስቲያኖችን የሚያስርበትና የሚደበድብበት ፈቃድ ከሊቀ ካህናት አገኜ፡፡ ይህን ፈቃድ ይዞ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ በፍጥነት እየተጓዘ ሳለ ‹‹ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ ›› የሚለውን ቃል ከሰማይ ሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ ጉልበቱ ልቡናው ተናወጸበት፡፡ እንዲህም ብሎ መለሰለት ‹‹ ጌታ ሆይ እኔ የማሳድድህ አንተ ማን ነህ ›› አለው ፡፡ የሐዋ ርያት ስራ 9
በዚህ ጊዜ ‹‹ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ ›› በማለት ጌታችን መለሰለት፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባወነ ከማን ጋር መሄድ እንዳለበት ጌታችን ለሳውል ነገረው ፡፡ ሳውል ሃሳቡና ዓላመው ከትፋት ወደ መልካምነት ተመለሰ፡፡ ሳውልም በክርስቶስ ቸርነትና ምሕረት እየተደነቀ ወደ ሐናንያ ሄደ፡፡ ሰዎቹም እየመሩት ሐናንያ ዘንድ አደረሱት፡፡ ሀናን አስቀድሞ ጌታ በራእይ ነግሮት ነበርና ሐናንያም ሳውልን ተቀበለውና አጠመቀው አስተማረውም፡፡ ሳውልም በረታ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ ፡፡ ሳውል ስሙ ተቀየረ ጳውሎስ ተባለ ብርሃን ማለት ነውና፡፤ምግባሩም የክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል ቀን ና ሌት መስበክና ማስተማር ሆነ፡፡ ልቡ በክርስቶስ ፍቅር ተነደፈ ፡፡ አሁን የእግዚአብሔር ፍቅር ገባው ፡፡ ስለገባው ስለ ክርስቶስ አምላክነት አዳኝነት እየሰበከና እያስተማረ መልካም ተጋድሎውን ያከናውን ጀመር፡፡እንዲሁም በስሙ መከራን ለመቀበል ራሱን አዘጋጀ፡፡ ስለ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስያን አብዝቶ ይጨነቅ ነበር ፡፡ ይህ ድንቅ በሆነ አጠራር የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን በመስበኩ ለእንግልት ለእስራት ተዳረገ፡፡አስራ አራት መልእክታቱን ሁሉ በወህኒ ቤት እያለ የላካቸው ናቸው፡፡ ስለ ጌታችን ከተናገረው አንዱን እስኪ እንመልከት፡፡
‹‹ እኛግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ››
‹‹ የግሪክ ሰዎች ጥበብን አይሁዶች ምልክትን ይሻሉ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ›› በማለት ክርስቲያኖች ማንን መመልከትና ወደ የት ፊታቸውን ማዞር እንደሚገባቸው አስረዳ፡፡ ቅዱሳን ከዓለም ምናምንቴ የራቁ ስለሆነ ስሙን እየጠሩና በስሙ እያስተማሩ የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሰበኩ መከራን ተቀበሉ፡፡
ለመሆኑ የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ ምንምን እናስባለን
ሀ - መከራውን እንሰብካለን
ለ -ድንግል ማርያምን እንሰብካለን
ሐ -ቅዱሳንን እንሰብካልን
መ -እንደምንፈተን እናውቃለን ፈተና እንደሚኖርብን እንሰብካለን ፡፡
ሀ መከራውን እንሰብካለን ፡- ክርስቲያን በስሙ ብቻ አምኖ አይቀመ ጥም ጌታችንና አምላካችን ፈጣሪያችን ስለ እኛ ሲል የተቀበለውን መከራውን እያሰብን እንኖራለን፡፡ እንሰብካለንም፡፡ ጌታ በፈቃዱ የእኛን ስጋ ለብሶ መከራን ተቀብሎ ከባርነት ነጻ አውጥቶ ወደ ዘላለማዊ ደስታ ወዳለብት ድንቅና ግሩም ቦታ ወስዶናል፡፡ ይህ የተከፈለልን ዋጋ እጅግ ግሩምና ድንቅ ነው ፡፡ እርሱ አምላካችን ስለ እኛ ሲል መከራን ተቀበለ፡፡ ‹‹ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን ›› ት/ ኢሳ 53፤4 ነቢዩ እንደተናገረው ጌታችን በቁስሉ ፈወሰን በህማሙ እኛ ዳን ስለዚህ ሁልጊዜ መከራውን እንሰብካለን፡፡ ዮሐ 19፤1 ማቴ 27፤57
በእለተ አርብ በፈቃዱ የተቀበለውን መከራ አራቱ ወንጌላዊያን ዘግበውታል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን በሚያመሰግንበት ምስጋነው እንዲህ ብሎ ተናግሯል ‹‹ እስመ በፈቃዱ ወበስምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጻእ ወ አዳኅነነ ፣በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጣና አዳነን ›› ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ ፡፡በማለት በፈቃዱ ዓለምን እንዳዳነ ይነግረናል፡፡ ቅዱሳን የተሰቀለውን ክርስቶስን ሲሰብኩ መከራውንም ጭምር ይሰብካሉና እኛም ክርስቲያኖች መከራውን እንሰብካልን፡፡
ለ -ድንግል ማርያምን እንሰብካለን ፡- የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውንና ተስፋችን እመቤታችንን እንሰብካለን፡፡ ጌተ ሰው ሆነ ስንል ከማን ከእመቤታችን ጌታ ስጋና ደም ሕይወት ነው ስንል ከእመቤታችን የነሳው ነው ስለምንል የእመቤታችንን ክብር ቅድስና የአምላክ እናት መሆኗን አማላጃችን መሆኗን እንሰብካለን፡፡ እመቤታችንን ካልሰበክንማ ክርስትናችን ከንቱ ነው ፡፡ ዋጋም አያሰጥም፡፡ እም አምላክ ወላዲተ አምላክ የአዳም ተስፋ የሔዋን መድኃኒት የመእመናን አለኝታ የመላእክት እህት የሁላችን መጽናኛ መሆኗን እንሰብካልን፡፡ ድንግል ማርያምን ካልሰበክን ምን ተስፋ አለን ወደማንስ እናጋጥጣለን፡፡
ሉቃስ 1፡45 ፣ ዮሐ 2፤ 1 ፣ መዝ 131፤ 1
ሐ- ቅዱሳንን እንሰብካለን ፡- ቅዱሳን ስለ ጌታችን ብዙ መከራን ስለተቀበሉ ለእኛም የመልካም ነገር ሁሉ አርአያ ስለሆኑን ስማቸውን እየጠራን እንሰብካለን፡፡ ዝክራቸውንም እዘከርን እንኖራለን፡፡ ጥቅሙን እኛ ስልምናውቀው ስለ ቅዱሳን አብዝተን እናስተምራለን፡፡ ቅዱሳን የገታችንን ቅዱስ ወንጌልን ስላስተማሩ ና ስለ ሰበኩ ለእኛም ስላስተረፉልን እንሰብካለን፡፡ እብ 13፤7 ‹‹ ዋኖቻችሁን አስቡ ›› ተብለናልና ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምኑንም ሳያውቁትና ሳይረዱት ከመሬት ተነስተው የከበሩትን ቅዱሳንን ሲያቃልሉ አያፍሩም፡፡ ምክንያቱም ምሥጢሩን ሰይጣን ስለሚሸሽጋቸው፡፡ እኛግን እግዚአብሔር ያከበራቸውን የመረጣቸውን እናከብራልን እንስበካለን፡፡ የተሰቀለውን ክርስቶስን የምንሰብክ ነንና፡፡
መ - ሌላው የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ ፈተና እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ዓለም ለክርስቲያኖች ብዙ አይነት መሰናክል አዘጋጅታለች፡፡ ክርስቲያን በመሆናችን ክርስቶስን በማምለካችን ልዩልዩ ፈተና ይመጣብናል፡፡ ፈተና እንደሚመጣ አውቀንና ተረድተን ልንኖር ግድ ይለናል፡፡ምክንያቱም የተሰቀለውን ክርስቶስን የምንሰብክ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና፡፡ ለዚህ ነው ውዳሴና አምልኩ ለስሙ ይሁንና አምላካችን ና ፈጣሪያችን እንዲህ ብሎ የነገረን፡፡ ‹‹ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል ›› ማቴ 24፤13
ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የ ተሰቀለውን ክርስቶስን የምንሰብክ ነንና ለፈተና ተዘጋጅተን እንዲንኖር ያስፈልጋል፡፡ የሐዋ ስራ 21፤13
ማቴ 8፤23
የቅድስት ሥላሴ ቸርነት
የእመቤታችን አማላጅነት
የአባ ጊዮርጊስ ዘ ጋስጫ ቃል ኪዳን
እንዲሁም የቅዱሳን ሁሉ በረከታቸውና ቃል ኪዳናቸው ከሁላችን ጋር ይሁን አሚን

Saturday, August 2, 2014

አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ

 


          =>ኢትዮዽያዊው ጻድቅ የተወለዱት በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሸዋ (መርሃ ቤቴ) ነው:: ወላጆቻቸው ዘካርያስና ሶፍያ እግዚአብሔርን የሚፈሩ: እመ ብርሃንን የሚወዱና ለነዳያን የሚራሩ ነ...በሩ::

+ደጉ ዘካርያስ መስፍን ሲሆን እርሱ በሌለበት የሸዋ ገዢ ሊያገባት በመሞከሩ ቅዱስ ገብርኤል ቀስፎታል:: ሕዝቡ ገዢነቱን ለዘካርያስ ሰጥተውታል:: ከቆይታ በሁዋላም ድንግል ማርያም የተባረከ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን "ዮሐንስ" አሉት:: በሒደት ግን ዘዮሐንስ (የዮሐንስ) ተብሏል::

+ቅዱሱ ዘዮሐንስ እስከ 7 ዓመቱ ድረስ በእናቱ እቅፍ ቆይቶ ወደ ትምሕርት ገብቷል:: ጸጋ እግዚአብሔር ጠርቶታልና በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አደን ይወድ ነበርና ሊያድን ሲወጣ 'ብርሕት ደመና' ድንገት ነጥቃ ከኢትዮዽያ (ሽዋ) ወደ ኢየሩሳሌም (ጐልጐታ) አደረሰችው::

+ደስ ብሎት ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ደመናዋ ወደ ሃገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በሁዋላም ከሰማይ ነቢዩ ኤልያስና መጥምቁ ወርደው ባረኩትና "ክፍልህ ከእኛ ጋር እንዲሆን መንን" አሉት::

+ዘዮሐንስ ወላቹንና ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ (ዲቁና ነበረውና) 25 ዓመት ሞላው:: ያን ጊዜ ወላጆቹ "እንዳርህ" ቢሉት "የለም! አይሆንም" አላቸው:: አርጅተው ነበርናስ ለእነርሱ ዕረፍት ጸለየ:: ፈጣሪም ሰምቶታልና 2ቱም በክብር ተከታትለው ዐረፉ::

+ሕዝቡ በወላጆቹ ፈንታ "እንሹምሕ" ቢሉት "እንቢ" ብሎ ወርቁን: ብሩን: ርስቱን: ቤቱን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ:: ጊዜው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባረፉ በ50 ዓመት አካባቢ ሲሆን አባ ሕዝቅያስ አበ ምኔት ነበሩ:: (ከዚህ በሁዋላ አንቱ እያልን እንቀጥል)

+አባ ዘዮሐንስ ለ7 ዓመታት ገዳሙን ረድተው መነኮሱ:: እንደ ልማዱ ደመና ነጥቆ ወስዷቸው ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ዻዻሳት ቅስና ተቀብለዋልና በደብረ ሊባኖስ ለ25 ዓመታት አገለገሉ:: ቤተ መቅደሱን በመዓልት 7 ጊዜ በሌሊት 7 ጊዜ ያጥኑ: እልፍ እልፍ ይሰግዱ: ተግተው ይጸልዩ: ይታዘዙም ነበር::

+ከዚያም በፈጣሪ ትዕዛዝ በትግራይና በሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ወንጌልን ሰብከዋል:: እድሜአቸው 70 በሆነ ጊዜ ወደ ጌታ መቃብር (ጐልጐታ) ሔደው ተሳልመው በእርሱ (በጌታ) ትዕዛዝ ወደ ደራ (ጣና ዳር) ተመለሱ::

+በአካባቢውም ገብርኤልና መስቀል ክብራ የሚባሉ ደጋግ ባለ ትዳሮች ነበሩና በእንግድነት ከቤታቸው አደሩ:: ቤቱ በቅጽበት በበረከት ሞላ:: እነርሱም የጻድቁን አምላክ አመሰገኑ::

+ቀጥሎም በመስቀል ክብራ መሪነት ጻድቁ ዘዮሐንስ ወደ ክብራን ገብርኤል ደሴት ገቡ:: (በነገራችን ላይ ደሴቱ ክብራን የተባለ መስቀል ክብራ በምትሰኘው ደግ ሴት ስም ነው:: እርሷና ባሏ ገብርኤል የተቀደሱ ሰዎች ነበሩና)

+ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ ወደ ደሴቶቹ (ክብራንና እንጦንስ ኢየሱስ) እንደ ገቡ ደሴቶቹ በግማሹ የስውራን ቤት: እኩሉ ደግሞ የጣዖት (ዘንዶ) አምላኪዎች መኖሪያ ነበር:: ጻድቁ ክብራን ገብርኤልንና እንጦንስ ኢየሱስን የመሠረቱት በ1315 ዓ/ም አካባቢ በዐፄ ዓምደ ፅዮን ዘመን ነው:: በአካባቢው ዘንዶ ይመለክ ነበርና ያንን በጸሎታቸው አጥፍተው ሕዝቡን አጥምቀዋል::

+በዚያም ገዳሙን የወንድና የሴት ብለው ከፈሉ:: የወንዶች ክብራን ሲሆን ሴት አይገባበትም:: አበ ምኔቱም ራሳቸው ጻድቁ ነበሩ:: የሴቶች እንጦንስ ኢየሱስ ከካህናት በቀር ወንድ አይገባበትም:: እመ ምኔቷም እናታችን ቅድስት ክብራ (መስቀል ክብራ) ሆነች::

+ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ በክብራን ለ35 ዓመታት ተጋድለዋል:: ለጸሎት ከመቆማቸው ብዛት እግራቸው አብጦ: ቆሳስሎ ነበር:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ይገለጽላቸው: ያነጋግራቸውም

ነበር::

+እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርተው: ለወንጌል እንደሚገባ ኑረው: በተወለዱ በ105 ዓመታቸው  ዐርፈዋል:: ጌታችንም በስማቸው ለተማጸነና ገዳማቸውን ለሳመ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ልደታቸው ደግሞ ሕዳር 13 ቀን ይከበራል:: ገዳማቸው (ክብራን ገብርኤልና እንጦንስ ኢየሱስ) ድንቅ ነውና እንድታዩት ተጋብዛቹሃል::

Thursday, February 6, 2014

ቅዱሳን ጻድቃን አባቶች እና የሰማእታትን ክብር


         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 ‘’ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ’’ ሮሜ 13፡7
ቅዱሳን ጻድቃን አባቶች እና የሰማእታትን ክብርመስጠት እንዳለብን አጭር መልዕክት ቃል ኪዳን ማለት በሁለት ወገኖች መካካል የሚደረግ ስምምነት፤ማሐላ፤ኑዛዜ ማለት ነው፡፡በዚህ ቃል መሰረት እግዚአብሔር ከፍቅሩ ብዛት የተነሳ በህይወት ዘመናቸው ሁሉ ራሳቸውን ለእርሱ አሳልፈው የሰጡትን መስቀሉን ተሸክመው ለኖሩ እና ካገለገሉ ቅዱሳን ጋር የማይሻር፤ የማይለወጥለ፤ የማይረሳ፤የማያረጅ ህያውና ዘለዓለማዊ የሆነ ቃል ኪዳን እንደገባላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ህሩያንየ - ከመረጥኩት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ››መዝ 88፡3 እግዚአብሔር አምላክ ከወደደው ጋር ቃል ኪዳን እንደሚያደርግ የማይለወጥ መሆኑንንም አረጋግጦ ሲናገር ‹‹ኪዳኔን አላረክስም ከከንፈሬ የወጣውን አልወጥም››በማለት በግልጽ ይነግረናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሰጠው ቃል ኪዳን ሞት ሊገድበው አይችልም፡፡ ብዙ ጊዜ ቅዱሳን በአጸደ ሥጋ ያማልዳሉ ብለን ስንናገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ሆነን አይደለም፡፡ሲጀመር አንድ ነዋሪ ወይም ዜጋ ዜግነታዊ መብቱ የሚጠበቅለት ግዴታውን መወጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡እንደዚሁ አንድ ሰው በቅዱሳን ምልጃ መጠቀም የሚችለው በቅዱሳኑ አማላጅነት ማመን ሲችል ብቻ ነው፡፡ነገር ግን ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆቿ እንዳይጠፉ ዜጋ ለሆነውም ላልሆነውም የቅዱሳኑን አማላጅነት ዘወትር ትሰብካለች ፡፡
ቅዱሳን ከእረፍተ ሞታቸው በኋላ እንደቀደመው በአጸደ ስጋ እያሉ ሲያደርጉ እንደነበረው የመጾም ፤የመስገድ ፤ ልዬ ልዬ መከራዎችን መቀበል ባይኖርባቸውም አስቀድመው ባደረጉት ተጋድሎ በተሰጣቸውን የማማለድ ጸጋ አምነው ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች እንደሚድኑበት እንዲህ ተብሎ ነው የተጻው ቆላ 2፡5 ‹‹በስጋ ምንም እንኳ ብርቅ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ ›› ሐዋሪያው በስጋ ምንም እንኳን ቢለይ በመንፈስ ከእነርሱ የማይረቀው ለምንድነው የሚለውን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ይህም የሚያስረዳን ቅዱሳን ከእረፍታቸው በኋላ ከእኛ የማይርቁ መሆኑን ነው የሚያሳየን፡፡ አንዲህም ተብሎ ተጽፏል ‹‹ኤልሳዕ ሞቶ ቀበሩትም ከሞዓብም አደጋ ጣዬች በየዓመቱ ወደ ሀገሩ ይገቡ ነበር፡፡ ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዬች አዬ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ ››2 ነገስት 13፡20 ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም እንደማይባል እርገጠኛ ነኝ፡፡እንደው ስንፍና ይዞአቸው ካልሆነ፡፡
ሌላው በቅዱሳን ስም ዝክር እያሉ መደገስ መብላት ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ይወዳሉ በምክንያት ነው የሚበሉት ይላሉ እንዲህ ተብሎ ነው በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን የጻድቃን ስም ለሚጠሩ በማይታበይና በማያልፈው ህያው ቃሉ እንዲህ ይላል ‹‹ነቢይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብዩን ዋጋ ይወስዳል ፤ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኃለው ዋጋው አይጠፋበትም›› ማቴ 10፡41-42
ታናናሾቹ የተባሉት ይኸውም በስጋዊ ኑሮአቸው የሌላውን እጅ ጠብቀው ለሚኖሩ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በስጋዊ ኑሮ በልጽገው ለሚገኙት ሁሉ የሚሰጠው ነገር ቢያጣ እንኳ በነቢያና በጻድቃን ስም ‹‹ ስለ አምላከ ጻድቃን አምላከ ነቢያት›› ብሎ የጻድቅን ወይም የነብይን ስም ከክርስቶስ ጋር አስተባብሮ ጠርቶ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ ቢሰጥ ዋጋው እንደማይጠፋበት መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው፡፡የዚህንም ዋጋ ታላቅነት ሲናገር የነብዩን የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል በማለት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ዋጋው ተገልጸል፡፡
የቅዱሳን ስም በመጥራት የሚደረገው መንፈሳዊ ስራ ጊዜያዊና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ ሳይሆን የማይቋረጥ መሆኑን ክቡር ዳዊት በመዝ 111/112፡6 የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል: በማለት ዘላለማዊ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ እንዲሁም የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ምሳ 10፡17
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምጽዋት፣ዝክር እና ሌሎችንም ስራዎች በቅዱሳን ስም የምታደርገው ክርስቶስ ለወዳጆቹ የገባውን ቃል ኪዳን ይዛና እግዚአብሔር ያዘዘውን የወደደው መሆኑን አውቃ ነው፡፡ስለ አምላከ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ ስለ አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፤ስለ አምላከ ሰማእት ቅድስት አርሴማ ….. እያለች ስማቸውን ከአምላካችን ስም ጋር አስተባብራ የምትጠራው ከባለቤቱ ተምራ ነው፡፡ ቅዱሳን ራሳቸው የእግዚአብሔርን ስም የሚጠሩት በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ስም በማንሳት ነበር፡፡ ኤልያስ ፈጣሪውን ሲጠራ የአብርሃም የይሳቅ የያዕቆብ አምላክ ሆይ እያለ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረና ፡፡ኤልሳዕ ደግሞ የኤልያስ አምላክ እያለ ይጠራ ነበር፡፡
እንዲህ እንደ ኤልያስ በዘመናቸው ከእነርሱ በፊት የነበሩ ቅዱሳንን የሚከብሩ እነርሱ ደግሞ በተተኪው ትውልድ በመልካም ስማቸው ይዘከራሉ፡፡ መታሰቢያቸውም በኢሳ 56፣4-7 “እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚለኝንም ነገር ለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና፡- በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣችኃለሁ የማይጠፋ የዘለዓለም ስም እሰጣችኃለሁ አለ “ የማይጠፋ ስም “ /ይሰመርበት/ ምልጃ የእግዚአብሔር ትዕዛዝና ፈቃድ ነውን? አዎ አንዳንድ ሰዎች ራሳችን በቀጥታ እንጸልያለን እንጂ አማላጅ መፈለግ መንገድ ማብዛት ነው ይላሉ ይህ ድፍረት ነው:: መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ዘፍ 20፡1-7 መመልከት እንችላለን አቤሜሌክን አብርሃም እንዲጸልይለት ራሱ እግዚአብሔር እንደነገረው እንመለከታለን፡፡እንዲሁም ኢዮ 42፡7-9 ባሪያዬ ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል ያለው እግዚአብሔር ነው እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ በእኛ የማታረቅን አኖረ፡፡እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን 2ኛ ቆሮ 5፡19-20 ታዲያ መናፍቃን ይህ ሁሉ ማስረጃ እያለ ለምን ይክዳሉ ከተባለ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው በመጨረሻው ዘመን እንደገዛ ምኞታቸውና አሳባቸው ለክህደት እንዲመቻቸው አድርገው መጽሐፍትን የሚያጣምሙ ክፉዎች እንደሚመጡና እንደሚያስቱ ብዙዎችም ከዚህ የተነሳ ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ እናንተ ግን ልጆቼ ሆይ አስቀድማችሁ እወቁ ተብሏል፡፡በመሆኑም ‹‹አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ ››2ኛ ዜና መዋ 13፡12 አዎ አትዋጉ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ያስተማረን እግዚአብሔር ነውና አላውቅም አስተምሩን ሌላ ነገር ነው ቅዱሳንን መስደብ መዝለፍ ግን ሐጢያት ነው፡፡ምክንያቱም በቅዱሳን አማላጅነት እንኳን ባያምኑ መጽሐፍ ቅዱስ እናትና አባትህን አክብር ይላል እናም ቅዱሳን እናቶቻችን ቅዱሳን አባቶቻችንን ልናከብር ይገባል፡፡እርግጠኛ ነኝ ማናችንም ወላጅ እናታችንን ወይም ወላጅ አባታችንን አንድ ሰው ከመሬት ተነስቶ ቢሰድብብን ወይም ቢመታብን ዝም እንል ይሆን? ቅዱሳን እናቶቻችን ቅዱሳን አባቶቻችንን ከዚህም በላይ ናቸውና አይ አላከብርም የሚል ካለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል “ እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደተወለዱ አዕምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ሆነው በማያውቁት ነገር/ባልገባቸው/ እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ የአመጻቸውን ደመወዝም ይቀበላሉ“ 2 ጴጥ 2፣12 እኛ ግን ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በ 2 ጢሞ 3፣17 ላይ እንደገለጸው ከልጅነት ጀምሮ በተማርነው ትምህርት ጸንተን ስንገኝ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ እንሆናለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የማያውቁ ይቃወማሉ ይህ ግን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጽሐፍትንና የእግዚአብሔርን ሀይል አታውቁምና ትስታላችሁ ማቴ 5፡22-29 ብሎ እናውቃለን እያሉ ይስቱ የነበሩትን ሰዶቃውያኑን ከገሰጻቸው ተግሳፅ ተካፋዮች የእነርሱን እርሾ ተቀብለው ይስታሉ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም የጌታችንን ትምህርት አስተማረች እንጂ የስድብ ቃልን አላስተማረችም፡፡ ይሁ 1፣8-10 “እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ስጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ስልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፡፡የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ስጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ “ ግን ግን አንድ ጥያቄ ላንሳ ? አለም ለበሽታዎች ቀን እየሰየመች በዓል ብላ ታከብራለች ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን አብነት አድርገው ቃን ኪዳኑን የፈጸሙ ቅዱሳን እንደምን አይከበሩ፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ይቆየን
አቅራቢ ገዛኸኝ ፋንታሁን ዘአርሴማ