Sunday, February 3, 2013

አቡነ መበዓ ጽዮን


         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር፣ ውሉደ ብርሃን፣ በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን የተሰኛችሁ የኀያሉ የልዑል እግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ልጆች፣ የቅዱሳን ሁሉ በለሟሎች፣ በእግዚአብሔርና እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን ስም ሰላም እያልኳችሁ  ነው::
 “እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡“ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ †♥† መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው። በአባታቸው ስም ሀብተ ጽዮንም ብሎ ይጠራቸዋል። እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው። አባታቸው ንቡረ ዕድ ሀብተ ጽዮን እናታቸው ሂሩት ይባላሉ። ደገኛ ጻድቅ ሲሆኑ ከታወቁበት ግብራቸው በሳምንት ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። ጌታ ሐሞት እንዳጠጡት ያንን እያሰቡ። አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚ፣ ቡናና ትርንጎ አፈርቷል፤ ጻድቁ ሌላ አስደናቂ ታሪክ አላቸው አርብ አርብ ሲዖል እየገቡ እልፍ እልፍ ነፍሳትን ያወጡ፤ በገበያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ካስተማሩ በኋላ ይመግቡ ነበር። በየወሩ የመድኃኔ ዓለም በዓል እየዘከሩ የወጣ የወረደውን ሁሉ የገበያውንም ሰው ሁሉ ያበሉ ይመግቡ ነበር። ዛሬም ሲዖል እየገቡ ያወጣሉ። “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?”ዮሐ.3፡12 እንዳለ ጌታ ዛሬም ይህንን የሚጠራጠሩ ብዙዎች አሉ። እኛ ግን በዚህ እናምናለን እንታመናለን። በጥቅምት 27 ብዙ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ቀንም ነው። አባታችን በጥቅምት 27 ቀንም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። አባታችንን አንድ ገበያ የሚያህል ሰው ይከተላቸው ነበር። የአባታችን አባ መባ ጽዮን በራሳቸው ገዳም ማጢቆስ በተባለ ገዳም አፅማቸው ይገኛል። በትግራይ ሽሬ አሎጊንም የሚባል ትልቅ ገዳም አላቸው። የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድኃኔ ዓለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው። እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በዓብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች። ጌታችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ክብሩ ከጻድቁ አቡነ መበዓ ጽዮንና ከአባ ጽጌ ድንግል በረከት ረድኤትን ያድለን አሜን።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያውያን ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ፣ መጽሐፈ ስ/ሳር፣ ነገረ ቅዱሳን ፪
        ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
      በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
አዘጋጅ ቤተ ማርያም

No comments:

Post a Comment