Thursday, February 12, 2015

ታላቁ አባት ቅዱስ ዻውሊ

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
=>አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ:: "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ::
+"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል::
*በእርግጥም ከአንተ 20 ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ
*በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ
*ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኩዋ የማትመጥነው
*በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት
*ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው" ብሎት ተሠወረው::
+ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ:: እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ:: በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)::
*በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው:: ለ80 ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል:: ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ: ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ (ማለትም ሽቻለሁና ላግኝ: ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ)" ሲል አሰምቶ ተናገረ::
+ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው:: መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ:: ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት::
+ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ዻውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር: ይመስገን" ሲል ፈጣሪውን ባረከ:: ቅዱስ ዻውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኩዋን ደህና መጣህ" አለው:: 2ቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ::
+" ቅዱስ ዻውሊ ማን ነው? "+
=>ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት:: ለምሳሌ:-
*የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ
*የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
*የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን እና
*የመጀመሪያውን ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ዻውሊን ማንሳት እንችላለን::
+ቅዱስ ዻውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ: በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው:: ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ:: ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ዼጥሮስን ወልደዋል:: 2ቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው:: ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም::
+ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ዼጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለዻውሎስ (ዻውሊ) መስጠቱ ነበር:: ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ::
+ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ዻውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው:: በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ:: በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል" ሲል ነገረው::
+በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ዻውሊ ሐሳብ ተለወጠ:: ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ:: በመቃብር ሥፍራ ለ3 ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው::
+በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት:: እየጾመ ይጸልይ: ይሰግድ ገባ:: ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት: ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለ80 ዓመታት ኖረ:: (አንዳንድ ምንጮች ግን ለ90 ዓመታት ይላሉ) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በሁዋላ ነው::
+ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የ2 ቀናት ቆይታም ቅዱስ ዻውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል:: በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል::
+ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል:: 80 ዓመት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች::
<< ጻድቅ: ቡሩክ: ቀዳሚው ገዳማዊ: መላእትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ዻውሊ ክብር ይገባል >>
+"+ ገዳማዊ ሕይወት +"+
=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::
+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::
+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::
+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::
+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::
+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::
+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::
=>አምላክ በበረከታቸው ይባርከን::
=>የካቲት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ኁሉ አባት)
2.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ-ግብፅ)
3.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት ጠበቃ)
4.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
5.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ
=>+"+ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: +"+ (ዕብ. 11:35-38)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
writing by dn yordanos abay

No comments:

Post a Comment