Monday, November 19, 2012

ስላሴ



                      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ሥላሴ የሚለው ሠለሰ ሦስት አደረገ ከሚለው የግዕዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን ሶስት ሦስትነት ማለት ሲሆን በያዘው ምስጢር ግን አንድም ሦስትም ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ሦስትነታቸው በስም በአካል በግብር አንድነታቸው በባሕሪይ በሕልውና በመለኮት በሥልጣን በፈቃድ ነው፡፡
፩. የስም ሦስትነት፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ነው፡፡ ማቴ28፡19
፪. የአካል ሦስትነት፡- ለአብ
ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ለወልድ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ለመንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ አለው መዝ 33፡15 መዝ118፡ 73 ኢሳ 66፡1 ዘፍ 18፡1-4 ማቴ 3፡16
፫. የግብር ሶስትነት፡- የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ የወልድ ግብሩ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው፡፡ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺም ስላልን የሚበላለጡ አይደሉም አንድ ናቸው እንጂ፡፡ ዮሐ 10፡30 ምስጋና ይገባል አንድም ሦስትም ለሆኑ ለቅድስት ሥላሴ።
ለህታዌክሙ፡- አብ፡ወልድ፡መንፈስ፡ቅዱስ፡ሆይ፡ የፍጥረት ሁሉ ስነ ባህርይ ፈጥሮ በበላይነት ለሚገዛ መለኮታዊ ሥነ አእምሮ ሰላምታ ይገባል፡፡
ሥሉስ ቅዱስ ሆይ፡- በተመኘሁ ጊዜ የክብር ሦስትነታችሁን ለማግኘት ተመራምሮ አንድነትን ከሦስትነት ሳይቀላቅል የመለኮት አንድነት በዘላለማዊት ሕልውና አምናለሁ፡፡
ለዝክረ ስመክሙ፡- አብ፡ወልድ፡መንፈስ፡ቅዱስ፡ሆይ፡- ከሦስትነት ዝቅ ወይም ከፍ ለማይል የስም አጠራራችሁ ሰላምታ ይገባል፡፡
ሥሉስ ቅዱስ ሆይ፡- በሦስትነት ጸንቶ ለሚኖር የባህርይ አምላክነታችሁ መለኮታዊ እጅ ከተከለው፡ ተክለ ጽድቅ ፍሬያችሁከወይን ዘለላ ቸርነታችሁ ትመግቡኝ ዘንድ ደጅ እጠናለሁ እኔ አገልጋያችሁ (ከመልከአ ሥላሴ የተወሰደ)

የዓለም ገዢ ሥሉስ ቅዱስ ሆይ፡-
በወዳጃችሁ በአርሃም እንደገባችሁ ከእናንተ ዘንድ የሚሰጠውን ሰማዕትነት በአክሊል እቀዳጅ ዘንድ ተድላ ደስታ ካለበት ገነት አግቡኝ፡፡ ሃጢአቴን በይቅርታ ቃል ደምስሳችሁነፍሴን ከሚቃወሟት አጋንንት አድኗት፡፡
አብ፡ወልድ፡መንፈስ፡ቅዱስ፡ሆይ፡- በእውነት ስማችሁን እጠራ ዘንድ ከወደኩበት አንሱኝ ከሩቅ ጥቀሱኝ ከቀትር ጋኔን ከድንገተኛ መጋኛ ትጠብቁኝ ዘንድ እማጸናለሁ፡፡
አብ፡ወልድ፡መንፈስ፡ቅዱስ፡ሆይ፡-የምስጋና፡ፍሬ፡እንዳፈራና፤ከአንደበቴም፡የጸሎት፡እሸት፡አበረክትላችሁ፡ዘንድ፡በልቡናዬ፡እርሻ፡ላይ፡መልካሙን፡ፍሬ፡ትዘሩ፡ዘንድ፡እማፀናለው፡፡ (ሰይፈ ሥላሴ ዘዘወትር)

“ወንድሞቻችን እኛስ እንዲህ እናምናለን ያልተወለደ እግዚአብሔር አብ በተለየ አካሉ አንድ ነው፤የተወለደ እግዚአብሔር ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስም በተለየ አካሉ አንድ ነው፡፡ በወደደው የሚያድር የአብ የወልድ እስትንፋስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ አንድ ነው፡፡አብ አልተወለደም ዓለም ሁሉ ሳይፈጠር ወልድን የወለደ ነው እንጂ ወልድም ዓለም ሁሉ ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ ተወለደ፤መንፈስ ቅዱስም ዓለም ሁሉ ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ ሠረጸ፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘአትናቲዎስ ገጽ ፶፭፡፡)
“ሰናቋርጥ የሦስቱን ምስጋና አንድነት እንናገራለን ፍጹም አሸናፊ አንድ አምላክ እግዚአብሔር አብ፤ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ የምትመሰገነው ምስጋናህ በሰማይ በምድር ምሉ ነው፡፡ ( ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ገጽ ፩፻፲፪ ፡፡)
“አብ በአካሉ በገጹ በመልኩ ያለ ነውና ወልድም እንዲሁ በአካሉ በገጹ በመልኩ ያለ ነውና መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ በአካሉ በገጹ በመልኩ ያለ ነውና እንደሰውም አይወሰኑም አምላክነት ያለው አካላት ናቸውና፡፡ በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ ብሎ ይህን ሃይማኖት የማያምን አንዲህ እኛ እንደወሰንነው አድርጎ ሃይማኖቱን የማይጽፍ ቢኖር ሐዋርያት ያስተማሯት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታወግዘዋለች” ( ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ገጽ ፹፩ ፦ም.፳፮ ፡፡)


በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት። አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና። ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ አላት። አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። እነርሱም። ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም። በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው።
እርሱም። የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች። ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች። ሣራም ስለ ፈራች። አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም። አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት። ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ። እግዚአብሔርም አለ። እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው። እግዚአብሔርም አለ። የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ። ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር። አብርሃምም ቀረበ አለም። በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን? እግዚአብሔርም። በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ አለ። አብርሃምም መለሰ አለም። እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም አለ። ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ። ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ? እርሱም። ለአርባው ስል አላደርገውም አለ። እርሱም። ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም አለ። ደግሞም። እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም አለ። እርሱም። እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ። እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ። (ዘፍ.፲፰፡፩-፴፫) 18፡1¬-33
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡ ሌሊትና ቀን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና ሳይሰለቹ የሚጠብቁን ሊቀነ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሩፋኤል ቅዱስ ዑራኤል ቅዱስ ራጉኤል ቅዱስ ፋኑኤል እልፍ አእላፋት የሆኑ ጠባቂ መላእክት ሳመሰግን በደስታ ነው፡፡
በጸሎታቸው ያልተለዩኝን ጻድቃን አባቶቼን አቡነ ተክለሃይማኖትን አቡነ ገብረምንፈስ ቅዱስን አቡነ ሀብተማርያምን አቡነ አረጋዊን አቡነ ኪሮስንና ሌሎች ቅዱሳን አባቶቼን እንዲሁም እናቶቼን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራን ቅድስት አርሴማን ብዙ ያልጠቀስኳቸው ቅዱሳንን ለማመስገን ቃላት የለኝም፡፡
በሰማዕትነታቸው የጥንካሬ ምሳሌ የሆኑልኝ በጸሎታቸው የረዱኝን ቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቅዱስ እስጢፋኖን መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስንና ሌሎችን ቅዱሳን ሰማዕታትን ሁሉ በእጅጉ አመሰግናለሁ ለዘላለሙ አሜን፡፡
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

No comments:

Post a Comment