Sunday, November 25, 2012

ነገረ ማርያም ብሉይ ኪዳን ክፍል አንድ 2

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
     የሴቶች ኹሉ መመኪያ  ልዑል እግዚአብሄር ሔዋንን በአርአያ በአምሳል በክብር ከአዳም እኩል አድርጎ ቢፈጥርም በሔዋን ስህተ ምክንያት ሴቶች ሁሉ የሚመኩበት ነገር አጥተው የሴትነት ክብር ተነፍጓቸው ምድረ ርስት ከመውረስ ተከልክለው ወንዶች እየተመኩባቸው ይኖሩ ነበር::ሆኖም ግን በሔዋን ምክንያት ያጡትን ክብር ዳግመኛ በቅድስት ድንግል ማርያም ተመልሶላቸዋል ከወንዶች ጋር መተካከላቸው በጉልህ ታውቋልና እመቤታችን የሴቶች ሁሉ መመኪያ ትባላለች::
     ይኸውም በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ወንዶች ሴቶችን << ሔዋን ከእኛ ወገን ከሆነ ከአዳም ብቻ ተገኘች እንጂ አዳም ከሔዋን አልተገኘም እያሉ በሴቶች ላይ እየተመኩባቸው ይኖሩ ነበር >> በዚህም ሲያዝኑ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈፀም አካላዊ ቃል ክርስቶስ ያለ አባት ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ከተወለደ በኋላ ግን ሴቶች ሁሉ ሐዘናቸው በደስታ ተለውጦ << ሔዋን ከእናንተ ወገን ከሆነ ከአዳም ብትገኝ ከኛ ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰማያዊ ንጉስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዕ ተወልዶ የለምን >> እያሉ  የሚመኩባት ሆነዋልና እመቤታችን የሴቶች እናቶቻችን እህቶቻችን ሁሉ መመኪያቸው ናት (1ኛ ቆሮ 11*12: ገላ 4*4)
     ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሴቶች በድንግል ማርያም ምክንያት ስላገኙት መተካከል በመጽሐፉ ላይ <<ከመ ኢይትመካህ በእንተ ዘአውሃ ብእሲተ ዘእንበለ ብእሲት ወለደት ድንግል ብእሴ ዘእንበለ ብእሲ ከመ በሱታፌ መንክር ይትዐወቅ ዝንቱ አሐዱ ክብርቴንተ ፍጥረት>> አዳም ያለ እናት ሔዋንን ስለአስገኘ እንዳይመካ ድንግል ያለ አባት ክርስቶስን ወለደች ድንቅ በሚሆን አንድነት ይህ አንድ ፍጥረት እኩልነት ይታወቅ ዘንድ በማለት አስረድስቷል::
    በብሉይ ኪዳን ቀድሞ ወንዶች ሴቶችን ከእናንተ ወገን በሆነች በሔዋን ስሕተት ምክንያት ከርስታችን ከገነት ወጥተናል እያሉ ምክንያት በመፍጠር ሴቶችን ምድረ ርስትን አያካፍላቸውም ነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈላቸው መልእክዩ ላይ << ከክርስቶስ ጋር እንድትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰውየለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁስ እንኪያስ የ አብርሃም ዘር እንደ ተስፋው ቃል ወሾች ናችሁ>> (ገላ 3* 28)በማለት እውነተኛውን ትምህርት በማስተማር እኩልነታቸውን አጉልቶ አስተምሯል:: ሴቶችም ይህንን ትምህርት በመረዳታቸው የሰውን ዘር ሁሉ ወደ ቀደመ ቦታችን ወደቀደመ ርስታችን ወደ ቀደም ክብራችን የመለሰ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ ወዲህ ወንዶችን << በኛ ምክንያት ከገነት ከመንግስተ ሰማያት ብትወጡ ከኛስ ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም ጌታ ተወልዶ ርስታችሁን ገነት መንግስተ ሰማያ አግኝታችኋል የለምን>> እያሉ የሚመኩናት ህነዋል ቅድስት ድንግል ማርያም የሴቶችን ዕዳ የከፈለችላቸው መመኪያቸው ናት::
     ይህንንን ልዩ ምስጢር ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ << ወሀሎ ላዕለ ትዝምደ አንስት ዕዳ ለትዘምድ ዕደው እስመ እማአዳም ወፃት ብእሲት እንበለ ብእሲት ወበእንተ ዝንቱ ወለደት ድንግል ብእሴ እንበለ ዘርዐ ብእሲ ከመ ትፈድዮ ለብእሲ ዕዳሃ ለሔዋን >> ለወንዶች የሚከፈለው ዕዳ በሴቶች ላይ ነበረ ያለ እናት ሔዋንተገኝታ ነበርና ለዚህም ድንግል ያለ ያለ ወንድ ዘር ክርስቶስን ወለደች ሔዋንን ብድራት ለወንዱ ትከፍለው ዘንድ በማለት ሲገልፀው::
     ሌላኛው ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም በሔዋን ስንፍና ምክንያት ሴቶች ያጡትን ክብር ዳግመኛ በድንግል ማርያም ምክንያት ማግኘታቸውን በስፋትና በጥልቀት ሲገልፅ (O daughters of the nation approach and learn to praise) የህዝቦች ሴቶች ልጆች ሆይ ከአባቶቻችሁ ስህተት ነፃ ያወጣችሁን ቅረቡት እርሱንም ማመስገን ተማሩ ያ ሔዋን የዘጋችውን የማይናገር አፍ አሁን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተከፈተ ለእህቶቻችን ምስጋናን ለመዘመር አሮጊቷ ሴት  ሔዋን በምላሶቻችሁ ዙሪያ የዝምታን ገመድ ቋጠረች የድንግል ልጅ እስራታችሁን ፈታ ጮሃችሁ ታመሰግኑ ትዘምሩ ዘንድ ያገባችሁ ሔዋን የዝምታን መጠምጠሚያ በአፋችሁ አኖረች ግን ድንግሊቱ የተዘጋውን የምላሳችሁን በር ከፈትች እስከ አሁኑ ወገናችሁበሔዋን ምክንያት አንሶ ነበር ከእንግዲህ ወዲህ ግን ሃሌ ሉያን ለመዘመር ተመልሷል ከእናታችሁ ከሔዋን ክፋት የተነሳ ከፍርድ በታች ነበራችሁ ከእህታችሁ ከድንግል ማርያም ልጅ የተነሳ ግን ነጻ ወጣችሁ ያለ ህፍረት ምስጋናን ለማዘእም ፊታችሁን ግለጡ በልደት ለሰው ልጆች ነጻነት የሰጣችሁን ታመሰግኑ ዘንድ በማለት ድንግል ማርያም ለሰው ልጆች ነጻነት በተለይ ለሴቶች እኩልነት ያደረገችውን ድርሻ በስፋት አስተምሯል::
    ይኸውም ሔዋን ሴቶች ሁሉ ለእግዚአብሄር ምስጋና እንዳያቀርቡ የዘጋቺውን አፍ ዳግመኛ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሄር ክብር ዝማሬ እንዲያቀርቡበት ምክንያት ሆናቸዋለችና የሴቶች ሁሉ መመኪያ ተብላለች::
    የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን:: ይቆየን   አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment