Monday, December 31, 2012

ሰማእት ቅዱስ መርቆሪዮስ

              በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
     ይትባረክ አግዚአብሔር አምላከ አባዊት እስከ ዛቲ ሰዓት አሜን
  “አንሰ ኢይክህዶ ለአግዚአብሔር አምላኪየ /እኔ ጌታዬን አልክድም/  ቅዱስ መርቆሬዎስ በንጉሱ ፊት ሳይፈራ ሳያፍር ከተናገራቸው የተወሰደ።
  “ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዓው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት ተሣሃለነ በከመ ዕበየ ሣህልከ” /ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ። ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ እንደ ይቅርታው ብዛት ይቅር ይበለን።”/ አሜን። (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁጥር ፯)
በዚህ ዕለት ማለትም ህዳር ፳፭ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፈ። አገሩ ሮም አስሌጥስ ነው። አባት እናቱ አረማውያን ነበሩ። ቅዱስ መርቆሬዎስ ከተወለደ በኋላ መልአኩ የተናገረው ቃል ሁሉ እንደተፈጸመ ሲያውቅ አባቱ ከነ ቤተሰቡ አምነው ተጠምቀዋል። የመርቆሬዎስ ስመ ጥምቀቱ “ፕሉፖዴር” ነው፤ ገብረ እግዚአብሔር ማለት ነው። በጥበብ በፈሪሀ እግዚአብሔር አድጎ አባቱ ሲሞት የአባቱን ሹመት ወረሰ።
 ንጉሱ ዳኬዎስ ይባላል። መምለኬ ጣዖት ነበር። በርበሮች በጠላትነት ተነስተውበት እንደምን ላድርግ ብሎ የምክር ቃል ሲልክበት መልአኩ በአምሳለ ወሬዛ ቀይህ በሊህ ሰይፍ ይዞ በዚህ ጠላቶችህን ድል ትነሳለህ ደስ ብሎህ በተመለስክ ጊዜ ግን ጌታህ እግዚአብሔርን አስበው ሲለው ታይቶት ነበርና አትፍራ ጌታ ጠላቶቻችንን አሳልፎ ይሰጠናል ብሎት አጽናንቶት ዘመቱ። መርቆሬዎስም ኃይል ተሰጥቶት ጠላቱን ድል ነስቶ ሲመለስ ከሃዲው ንጉስ ኡልያኖስ ወዲያው ኃይል ለሰጡን ለረዱን ለዓማልክቶቼ በዓል አድርጌአለሁና ፈጥነህ ና ብሎ ላከበት። ሄዶ ሹመት ሽልማትህ ላንተ ይሁን “አንሰ ኢይክህዶ ለአግዚአብሔር አምላኪየ /እኔ ጌታዬን አልክድም/ ላቆመው ጣኦት አልሰግድም በማለቱ የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችለውን መከራ ተቀበለ። በመጨረሻም ህዳር ፳፭ በዛሬዋ ቀን አንገቱን ቆርጠው ገደሉት ደም ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሰሰ። †††መርቆሬዎስ ከዕረፍቱም በኋላ ብዙ ተአምራትን አድርጓል፤ ፈረሱ ለሰባት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፤ በኋላም አንገቱን ቆርጠው ገድለውታል እንዴት ብሎ የሚገረም የበልአምን አህያ ይጠይቃት፤ እኛስ እስመ አልቦ ነገር ዘይሳኣኖ ለእግዚያብሔር ብለን እንመልሳለን:: ዘኁልቁ 22፡28
የቅዱስ መርቆሬዎስ ስዕልም በአዎንታ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ምስክርነት ሰጥቷል። ይህም ሊታወቅ ዛሬ በሀገራችን በምድረ ተጉለት በስሙ ከታነጸ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ደነነ ስዕሉ እያሉ ሲዘምሩ ጎንበስ ቀና ሲሉ እንደሚታይ ይነገራል።

የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስ ረድኤቱ በረከቱ አማላጅነቱ ቃል ኪዳኑ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
  እኔን የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሌንም ተሸክሞ ዕለት ዕለት ይከተለኝ…. ማቴ.፲፡፴፰-፵
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። (ዕብ ፲፪፡፩¬-፪)
ይትባረክ አምላከ አባዊነ ይቆየን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

No comments:

Post a Comment