Wednesday, December 26, 2012

ሊቀ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤል

         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
 ለአናንያ ወአዛርያ ወሚሳኤል /፪/
ውእቱ ያድኅነነ ወሚሳኤል ውእቱ ያድኅነነ/፪/

ትርጉም ፡- አናንያን አዛርያን ሚሳኤልን እንዳዳናቸው እኛንም ያድነን፡፡

ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም አነሣሁ” አለና አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኃይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኃይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” አለ፡፡(ዳን.10፥5-9) ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡

ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች” አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ”(ዳን.10፥13) ብሎ በተናገረው ንግግሩ በመላእክት ላይ የተሾሙ ሌሎች አለቆች እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቅዱሳን መላእክት ዘንድ ስላሉት ነገዶች ሲገልጽ “… በሰማይ ያለውን በምደር ያለውን የሚታየውንና የማይታየውን መናብርትም ቢሆኑ አጋእዝትም ቢሆኑ መኳንንትም ቢሆኑ ቀደምትም ቢሆኑ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ” (ቈላ.1፥16) በማለት ይዘረዝራቸዋል፡፡ ከዚህ ተነሥተን መላእክት በተለያዩ ዐበይት ነገዶች የተከፈሉና ለእያንዳንዱም ነገድ የራሱ የሆነ አለቃ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚህ ዐበይት የመላእክት ነገዶች መካከል አንዱ በሆነው አርባብ በሚባለው ዐቢይ ነገድ ላይ የተሾመ ሲሆን ከ100ው ነገደ መላእክት መካከል ከበታቹ የሚመራቸው ዐሥር ነገደ መላእክት አሉት፤ ከተማቸውም በሰማየ ራማ ነው፡፡
ቅዱሳን መላእክት በቅዱስ ሚካኤል ፊት አውራሪነት የሰው ልጆች ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ተዋግተው ድል ከመንሳታቸው አስቀድሞ ቅዱስ ገብርኤል፣ እንደ አምላክ ሊመለክ የወደደውን ሳጥናኤልን በመቃወም ‹‹ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ - “አይዞአችሁ ፈጣሪያችን ፈጥሮ አይጥለንምና አስክናገኘው፣ እስክናውቀው ድረስ በያለንበት እንቁም፡፡” (አክሲማሮስ ገጽ.35)በማለት መላእክትን ያረጋጋ መልአክ ነው፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ የፋርስ ባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን ሁሉ ሲያስገዛለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም አወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም የሚቃወመኝም የለም፡፡”(ኢሳ.10፥13-14) ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ ዱራ(አዱራን) በሚባል ስፍራ ላይ አቆመው፡፡ በግዛቱ በልዩ ልዩ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉትን ሹማምንቱንና ገዢዎችን ሰበሰባቸው፤ “የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሥ ናብከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፡፡ ወድቆም ለማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣል” ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን አዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ የመለከቱና የእንቢልታው እንዲህም የዘፈን ድምፅ በተሰማ ጊዜ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡

በባቢሎን አውራጃዎች ላይ የተሾሙ አናንያና(ሚሳቅ)፣ አዛርያ(ሲድራቅ) እና ሚሳኤል(አብደናጎ) ግን ንጉሥ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡ ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ነገሩት፤ ንጉሥም እጅግ ተቆጥቶ ወደ እርሱ አስጠራቸው፡፡ እርሱ ላቆመው ለወርቅ ምስል ያልሰገዱ እንደሆነ እጅና እግራቸውን ታስረው ወደ እቶን እሳቱ እንደሚጣሉ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ግን “ናብከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፣ ከሚነደውም ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን (የእግዚአብሔር ፈቃዱ በእሳት ውስጥ ሰማዕትነትን እንድንቀበል እንኳን ቢሆን) አማልክትህን አንዳናመልክ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳማንሰግድለት  እወቅ” ብለው መለሱለት፡፡ የንጉሥ ናብከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ፥ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእነ ማዕረግ ልብሳቸው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው ትእዛዝን አስተላለፈ፡፡ ትእዛዙ አስቸኳይ ነበርና እነርሱን ወደ እሳቱ የጣሏቸውም ኃያላን በእሳቱ ወላፈን ተገርፈው ሞቱ፡፡ እንዲህ ሲሆን ሳለ ግን ሠለስቱ ደቂቅ ወደ አምላካቸው “በፍጹም ልባችን እናምንሃለን፣ እንፈራሃለን፣ አታሳፍረን እንጂ ገጸ ረድኤትህንም እንፈልጋለን፡፡” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታቸውን ተቀበለ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም እስራታቸውን ፈታ፤ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅም መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ስምህም ለዘለዓለም የተመሰገነና የከበረ ነው” በማለት አመሰገኑት፡፡

ንጉሥ ናብከደነፆርም ሠለስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ከእነርሱ ጋር የሰው መልክ ያለው ነገር ግን አምላክን የሚመስል መልአክ ተመለከተ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን ፊቱን ጸፍቶ አፉን ከፍቶ “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን”(ዮሐ.11፥49) ብሎ እንዳናገረው እንዲሁ ናብከደነፆርንም “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ እንዲናገር አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅን መልክ ያለው በኋላም መልአክ ብሎ የተናገረለት ቅዱስ ገብርኤልን ነበር፡፡ እርሱ ስለመሆኑ ለነቢዩ ዳንኤል በተገለጠበት ግርማ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ናብከደነፆርም ወደ እሳቱ እቶን በመቅረብ እነዚህ ብላቴኖችን “እናንተ የልዑል አምላክ ባሮች ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው፡፡” እነርሱም ከእሳቱ ወጡ ሹማምንቱና መኳንንቱ፣ አማካሪዎችና የአገር ገዢዎች ሁሉ እሳቱ በእነዚህ ብላቴኖች ላይ አንዳች አቅም እንዳልነበረው፣ ከጠጉራቸው ቅንጣት አንዱን እንኳ እንዳላቃጠለው፣ ሰናፊናቸውም እንዳልተለወጠ፣ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ፡፡ ንጉሥ ናብከደነፆርም መልአኩን ልኮ ያዳናቸውን የእነዚህን ቅዱሳንን አምላክ አመሰገነ፡፡ በእነርሱ አምላክ ላይም የስድብን ቃል የሚናገር ሰው እንደሚገደልና ቤቱም የጉድፍ መጣያ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ፡፡ አናንያ አዛርያ ሚሳኤልም በንጉሡና በሹማምነቱ ዘንድ ሞገስ አገኙ በክብርም ከፍ ከፍ አሉ፡፡(ዳን.3 በሙሉ)

ስለዚህም ቤተ ክስርቲያን መንጎቿ የእምነትን ፍሬ ከእነዚህ ብላቴኖች ተምረው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑና የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት እንዲረዱ በታኅሣሥ 19 ቀን ይህን ዕለት ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነት በድርጊት ሊታይ የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምናለሁ የሚል ሁሉ ካመነበት ጊዜ አንስቶ ክርስቶስን መስሎ ለመኖር ሊተጋና መስሎ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ በሠለስቱ ደቂቅ የታየው እምነት በአንድ ጀምበር የተገነባ እምነት ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ በአንድ እግዚአብሔር ታምነው በቅድስና ሕይወት በመመላለስ የመጣ እምነት ነው፡፡ እነዚህ ብላቴኖች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን የድል አክሊል ተስፋ አድርገዋልና፥ አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል የነደደውን የእሳት እቶን አላስፈራቸውም፤ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት በእሳት ተቃጥለው ለመሞት እንኳ አስጨከናቸው፡፡ እንዲህም ሆነው በመገኘታቸው በእምነታቸው እግዚአብሔርን ደስ አሰኙት፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ባለሟሉን ቅዱስ ገብርኤልን በመላክ ከእሳቱ እቶን ታደጋቸው፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ እምነት ኃጢአት በነገሰበት በአሁኑዋ ዓለም በእኛ ክርስቲያኖች ላይ ሊታይ የሚገባው እምነት ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚመጣውነ መቅሰፍት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት እንደሚያጠፋልን በእግዚአብሔር ታምነን በእምነት ኃጢአትን ልንቃወመው ይገባናል፡፡ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ጸሎት ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment