Monday, December 10, 2012

ስለ ቅዱሳን

    ቅዱስ፡-  ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥ ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ ማለት ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል። ቅዱስ ማነው? ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥ ማዕከለ ዓለም ፥ ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው የለም፡፡ ነቢዩ አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ። ኢሳ ፵ ፥ ፳፭ ፡፡ ፩ ስሙ ቅዱስ ነው የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። «ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና» እንዲል ይህ ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው ፥ በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነድዳቸው ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም «አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ አርትተውታል። የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ ፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም ጠንቋዩን በርያሱስን በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት ፈውሷታል። የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ። ፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤ የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ ፥ አምላክ ፥ ንጉሥ ነው ፤ ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥ ሕያው ፥ ኃያል ፥ ረቂቅ ፥ መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው ፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ ፥ ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና አባት ነው። ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ፤ » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫። እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት የታደጋቸውን እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥ ድንቅንም የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤ » እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ ፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ ፮፥፱-፲፩ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

No comments:

Post a Comment